የፓርላማ ተመራጩ ሊቀ አእላፍ በላይ መኰንን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው ተሾሙ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕግ አገልግሎት መምሪያ ዋና አማካሪ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው ተሾሙ፡፡
በዛሬው ዕለት የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው የተሾሙት ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ÷ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ከ፲፱፻፺፫ – ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. ሦስት ዓመታት ውስጥ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በመኾን አብረዋቸው ሠርተዋል፡፡
በመንበረ ፓትርያርኩ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ፣ በቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት፣ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በከፍተኛ የአስተዳደር ሓላፊነት/ዲንነት በመሥራት በርካታ ተሞክሮዎች እንዳሏቸው የተገለጸው ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ፣ በትምህርት ዝግጅታቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡
በዚኹ ሞያቸው የማማከርና የፍ/ቤት ክርክር ጉዳዮች በሚከናወንበት በመንበረ ፓትርያርኩ የሕግ አገልግሎት መምሪያ እየሠሩ ያሉት ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ፣ በሪፍት ቫሊ ኮሌጅም በማታው መርሐ ግብር እንደሚያስተምሩ ተገልጦአል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በንግድ አስተዳደር የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን (ኤም.ቢ.ኤ) በተልእኮ በመከታተል ላይ እንዳሉ ተዘግቧል፡፡ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የሠለጠኑበትና ሥራ የጀመሩበት ሞያ ነርሲንግ እንደነበርም ታውቋል፡፡ ተሿሚው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግን በመወከል የፓርላማ ተመራጭ ናቸው፡፡
