“የኢትዮ-ኤርትራ ችግር መፍትሄ፣ ድንበር ማስመር ሳይሆን ድንበር ማፍረስ ነው”
"የኢትዮ-ኤርትራ ችግር መፍትሄ፣ ድንበር ማስመር ሳይሆን ድንበር ማፍረስ ነው"
——————————–
ኤርትራዊው ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ እንዲህ ተጠየቀ;
አዲስ አድማስ ጋዜጣ : የኤርትራ ህዝብ አሁን ያሉበትን የነፃነት ሁኔታ ከቀድሞው ጋር ሲያስተያዩት ምን ትርጉም ይሰጥዎታል?
ተከስተ ነጋሽ: እኔ እኮ በመጀመሪያም ኤርትራውያኖች ከማን ነው የሚገነጠሉት የሚል አቋም ነው ያለኝ። ማነው ከማን የሚገነጠለው? የደቡብ ወይም የኦሮሞ ህዝቦች እንገነጠላለን ቢሉ ኖሮ ምክንያት ነበራቸው፡፡ የኤርትራ የነፃነት ጥያቄ በተነሳበት ወቅት ኤርትራውያኑና ከላይ የጠቀስኳቸው ህዝቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ያገኙትን እድል (Comparative advantage) ስናይ፣ ኤርትራውያኑ በጣም ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ (በጣሊያን፣ በእንግሊዝ፣ በፌዴሬሽኑ ዘመን) በ1960ዎቹ የአዲስ አበባ ሀብታሞቹ እነሱ ነበሩ። በትምህርት መስክ ሃያ አምስት በመቶ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ኤርትራውያን ነበሩ። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችንም ካየሽ 25 በመቶ የሚሆኑት ኤርትራውያን ነበሩ፡፡ ከተማረው ሰላሳ አምስት በመቶው ክፍል ኤርትራውያን ነበሩ፡፡