“ከህወሓት የባስክ ትሆናለህ” አሉኝ

Abraha Desta
November 19
"ከህወሓት የባስክ ትሆናለህ" አሉኝ
———————————–

"ጨቋኝ ስርዓት አልፈልግም" ብዬ በፃፍኩት ላይ አንድ የፌስቡክ ወዳጄ "አንተ ራስህ ስልጣን ብትይዝ ከህወሓት የባስክ አምባገነን ትሆናለህ" አለኝ።

እኔም እላለሁ፣

ከህወሓት የተሻልኩ እንደምሆን እርግጠኛ አይደለሁም (ራሴ ለግዜው እንደ ፓርቲ ልቁጠር)። ስለ አንድ ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ። እኔ ሰለማዊ ታጋይ ነኝ። ስልጣን የምይዘው በህዝባዊ ምርጫ እንጂ በጠመንጃ አይደለም። የምወዳደረው በሐሳብ እንጂ በሃይል አይደለም።

ስለዚህ ስልጣን ስይዝ የራሴ ወታደር፣ ፖሊስ፣ ዳኛ ወዘተ ይዤ አልመጣም። ስልጣን የምይዘው በሕገመንግስት መሰረት እስከሆነ ድረስ በኔና በወታደሮቹ ያለ ግንኙት ሕገመንግስታዊ ይሆናል። ስለዚህ ወታደሮቹ እንደፈለኩ የግሌ የስልጣን ጥም ለማርካት አላዝዛቸውም። ዳኞችም ነፃ ይሆናሉ።

ስለዚህ እኔ ስልጣን ከያዝኩ በኃላ ከህወሓት ካልተሻልኩ በህዝብ ምርጫ እንደወጣሁ ሁሉ በሚቀጥለው በህዝብ ምርጫ ከስልጣን እወርዳለሁ። ከስልጣን ላለመውረድ ምንም ዓቅም የለኝም፤ ምክንያቱም በምርጫ ስልጣን የያዘ አካል የግሉ ወታደርና ፖሊስ የለውም። የስልጣን መሰረቴ የህዝብ ድምፅ ከሆነ በስልጣን ለመቆየት ስል ህዝብን አልጨቁንም። ከጨቆንኩ ደግሞ ህዝቡ ያወርደኛል።

የኢህአዴግ መንግስት ሰለማዊ ትግልን አጨልሞብኝ በትጥቅ ትግል ስልጣን ከያዝኩ ግን አምባገነን የመሆን ዕድል አለኝ። ምክንያቱም የስልጣን ምንጬ ጠመንጃ እንጂ ህዝብ አይደለም። ለህዝብ ታማኝና አገልጋይ የምሆንበት ዕድል ይጠባል። ስለዚህ በምርጫ ስልጣን የያዘ መንግስት ቢያበላሽ እንኳ በምርጫ ይወርዳል። አሁን የቸገረን በጠመንጃ የመጣ መንግስት ነው።

ዓላማችን ስልጣን መያዝ ብቻ ሳይሆን ስልጣን በጠመንጃ ከመያዝ በምርጫ የምያዝበት ስርዓት መገንባት ጭምር ነው።

(ስልጣን የመያዝ ዕቅድም ፍላጎትም የለኝም። የኔ ፍላጎት በነፃነት የፈለኩትን ማድረግ ነው። እኔ የሌሎችን መብት ሳልዳፈር የፈለኩትን የማድረግ ነፃነት እንዲኖረኝ የህዝብ መንግስት ወይ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አለበት። ስልጣን መያዝ ነፃነትን ይገድባል)።

It is so!!!