በዩጋንዳ የህዳር ሚካዔልን የንግስ በዓል ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን….

በውጪ ሐገር በስደት ላይ በሚገኘው ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመራው የካምፓላ መካነሰላም መድሃንያለም ቤተክርስትያን በዩጋንዳ የህዳር ሚካዔልን የንግስ በዓል ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ አንዳከበሩት በስፍራው የነበረው የፔን ዘ ኢትዮጵያ ዘጋቢ ገለፀ።
ከለሊቱ አስራአንድ ሠዓት ጀምሮ በማህሌት የጀመረው ክብረ በዓል በደብሩ መሪጌታ ይህይስ ዓለሙ ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል።<ውእቱ ሚካዔል መልዓከ ኃይለ ልዑል።ውእቱ ልዑለ መንበር ይስአለነ……>
በዕለቱ ቅዳሤ በርካታ ምዕመናን የታደሙ ሲሆን ከማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አስራ ስምንት ከቁጥር አስራአምስት እስከ ሃያ አንድ በቆሞስ አባ ኃይለማርያም ተነቧል። ስርዓተ ቁርባን ከተከናወነ በኋላም በቆሞስ አባ አብዩ የዕለቱን በዓል በማስመልከት ኦሪት ዘፀአት ምዕራፍ አስራ አራት ከቁጥር አስራ ዘጠኝ ጀምሮ ያለውን ቃል በተመለከተ የወንጌል ማዕድ ቀርቧል።
የቅዳሤ ስርዓቱ እንዳበቃም ታቦተ ህጉ በካህናትና ምዕመናን ታጅቦ በክብርና በምስጋና ዜማ ታጅቦ በአውደ ምህረቱ ላይ መሪጌታ ይህይስ <አንተኑ ሚካዔል መና ዘአወረድከ።ወአንተኑ ለእስራዔል መና ዘአወረድከ።>በያሬዳዊ ዜማ ወረብ አቅርቧል።
የደብሩ አስተዳዳሪ ቀሲስ ፀሐይ ደስታ በበዓሉ ፍፃሜ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እግዚአብሔር አምላክ እስራዔላዊያንን ከግብፅ የባርነት ቀንበር ነፃ የወጡበትን ዕለት በመዘከር ይህንን ታላቅ በዓል ቤተክርስትያን በድምቀት እንደምታከብረውና በዓሉ የስደተኞች በዓል ሊባል እንደሚችል ጠቁመው ስደተኞች ሁላችን እግዚአብሔር አምላክ እስራዔላዊያንን ከግብፅ የፈርዖን አገዛዝ እንዳዳናቸው ሁሉ እኛንም ለሐገራችን ያብቃን ሲሉ ቃለ ምዕዳን ሰጥተዎል።
በመጨረሻም የአምልኮ ነፃነት በተረጋገጠባት ዩጋንዳ ኤርትራዊያንና ኢትዮጵያዊያን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች የፖለቲካ ድንበር ሣያግዳቸው በአንድ ደብር ፈጣሪያቸውን ሲያመሠግኑ የዚህ ዜና ዘጋቢ ተመልክቷል።
Pen Ethiopian