ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በአሜሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝት ያደርጋሉ

His Holiness Abune Mathias

  • ለ10 ዓመታት (ከ፲፱፻፸፬ – ፲፱፹፬ ዓ.ም.) በስደት ለ15 ዓመታት (፲፱፹፬- ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.)  በሐዋርያዊ አገልግሎት ቆይተውበታል፡፡
  • በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ በኒውዮርክ ከተመሠረተውና የጃማይካ ተወላጆች ከሚገኙበት የኒውዮርክ ቅድስ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ቀጥሎ የመጀመሪያውን የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በዋሽንግተን ዲሲ (መካነ ሕይወት መድኃኔዓለም) አቋቁመዋል፡፡
  • ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያን መዋቅርንና የሁለተኛ ሲኖዶስ ምሥረታን በመቃወም የእናት ቤተ ክርስቲያን እንቅሰቃሴመርተዋል፡፡
  • የትኛውም አካል ባላሰበበት ዘመን ስለ ዕርቀ ሰላም አሳስበዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስንና ሌሎች በስደት የሚገኙ አባቶችን በአትላንታ ጆርጅያ በአካል አግኝተው ከተወያዩ በኋላ ለኢትዮጵያው ቅ/ሲኖዶስ መልእክት በመላክ ዕርቀ ሰላም እንዲጀመር መሠረት ጥለዋል፡፡
  • ቃለ ዐዋዲው ለሰሜን አሜሪካ ሀ/ስብከት እንዲስማማ ኾኖ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመው በቅዱስነታቸው የሰሜን አሜሪካ ቆይታ ዘመን ነው፡፡
  • ‹‹ተዐቀቡኬ እምሐሳውያን ነብያት›› በሚል ርእስ በዋሽንግተን ዲሲ በተዘጋጀው ከፍተኛ ጉባኤ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ሤራ ቤተ ክርስቲያንን እያወካት መኾኑን በመግለጽ ካህናትና ምእመናን በብርቱ እንዲቋቋሙት አጠንክረው አስተምረዋል፤ በእመቤታችን ቅድስና ላይ የስሕተት ትምህርት ለማስተማር የሞከሩ ካህናትን በመምከር ከስሕተታቸው አልመለስ ያሉትን አውግዘው በመለየት ሃይማኖታዊ ቅንዐታቸውን በተግባር ገልጸዋል፡፡
  • ‹‹የተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን መረከብ አንፈልግም፤ ታሪካዊ አንድነታችንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያናችን መጠበቅ አለበት›› በሚል የተነሣሣውን የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች እንቅሰቃሴ በማጠናከር የሰንበት ት/ቤቶች እንዲስፋፉ አድርገዋል፡፡ በሀ/ስብከቱ ማኅበረ ቅዱሳን በእናት ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሥር የሚያበረክተው አገልግሎት እንዲጠናከር የማይቋርጥ ምክርና አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡