የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሽግግር ዘመኑን አፈጻጸም ይገመግማል
- ግምገማውን ተከትሎ የዋና ሥራ አስኪያጅ ሹመትና መዋቅራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ በተለያዩ የመቀስቀሻ አጀንዳዎች አሉባልታ ሲነዙ፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያንን ለአድማ ሲቀስቀሱ በቆዩ ሓላፊዎች ላይ የሚወሰዱ ርምጃዎች ይጠበቃሉ፡፡
- ለዋ/ሥ/አስኪያጅ ሹመት÷ በጎጠኝነትና በጥቅመኝነት የማግባባት እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው፤ ወደ ረዳት ሊቀ ጳጳሱ እና ወደ ፓትርያርኩ የጳጳስና የባለሥልጣን አማላጅ የላኩ፣ የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ የተጠመዱም አሉ፤ ከብር 6.7 ሚልዮን በላይ በኾነ የገቢ ጉድለት ከሓላፊነታቸው የተወገዱትና በዘረጉት አስከፊ የሙሰኞች ሰንሰለት መዋቅራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚጥሩት የቀድሞው የሀ/ስብከቱ ዋ/ሥ/አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ አንዱ መኾናቸው እየተነገረ ነው፡፡
- በግምገማው ሀ/ስብከቱ÷ ከአሉባልተኞች ተጽዕኖና በባለጉዳዮች ከመጨናነቅ እፎይታ አግኝቶ በዕቅድና ጥናት ላይ የተመሠረቱ የልማት ተግባራትን ክንውን ማስተባበር፣ ቅ/ሲኖዶስ የአፈጻጸም አቅጣጫ የሰጠበት የለውጥ አመራር መዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር የብዙኀኑን ግንዛቤ አግኝቶና ዳብሮ በሥራ ላይ እንዲውል የውይይት መድረኰችን ማመቻቸት ትኩረት እንደሚሰጣቸው ተመልክቷል፡፡
- የደብረ ሊባኖስ ገዳም ይዞታ በማስደፈር በዙሪያው ከተማ/ከተሜነት እንዲስፋፋ በማድረጋቸውና ሥርዐተ ማኅበሩን በመጣሳቸው በማኅበረ መነኰሳቱ የተባረሩት ጸባቴ አባ ኃይለ መስቀል ውቤ የታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም ሊቀ ሊቃውንት ሊኾኑ ነው፡፡ በከፋ ሙሰኝነታቸው ከሚታወቁት የአ/አ ደብረ ምሕረት ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጸሐፊና ሒሳብ ሹም ጋራ የምእመኑ የማያባራ ተቃውሞ የሚሰማባቸው የደብሩ አስተዳዳሪ፣ አባ ኃይለ መስቀል ውቤን ተክተው የገዳሙ ጸባቴ ይኾናሉ – ተጠያቂነት የሌለበት፣ ዘራፊዎችን የሚያበረታታ ዝውውር!!
