የምእመናን ቆጠራና ምዝገባ በአህጉረ ስብከት ሓላፊነት ይካሄዳል: የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ መግለጫ
- ቅ/ሲኖዶስ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት እውነታውንና ትክክለኛውን የሚገልጽ ጽሑፍ እንዲዘጋጅ መመሪያ ሰጠ
- የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት ለምልአተ ጉባኤው ስብሰባ የሰጠው ሽፋን ‹‹የጉርሻ ያህል ነው›› በሚል ተነቀፈ
- ‹‹ጉባኤው አገር አቀፍ ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፍም ነው፤ የምንሰጠው ትምህርት ነው፤ የምንወድቀው የምንነሣው ስለ ሀገር ጉዳይ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን በዐይን የሚታይ በእጅ የሚጨበጥ ታሪክ ነው ያስረከበችው፤ በምን ምክንያት ነው ቀለል የሚለው›› /ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ/
- ‹‹ከባለሥልጣናት[ከመንግሥት] የምናገኛቸውን መልእክቶች እናስተላልፋለን፤ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ እናቶች በሆስፒታል እንዲወልዱ ደጋግማችኹ አስተላልፉን ብለው ነግረውን በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ሺሕ ሕዝብ በተሰበሰበበትና በየአጋጣሚው እናስተላልፋለን፤ እኛም እዚህ ስለ አገር ጉዳይ እንነጋገራለን፤ የምንነጋገረው ግን የሚተላለፈው የጉርሻ ያህል ነው፤ ለሕዝቡ እንዲተላለፍ እንጂ የሚዲያ ሱሰኛ ኾነን አይደለም፤ የሚነገረው ነገር ለሕዝቡ በአግባቡ ቢተላለፍ መልካም ነው›› /ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ቆጠራና ምዝገባ በእያንዳንዱ አህጉረ ስብከት ሓላፊነት እንደሚካሄድ ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡
‹‹ቤተ ክርስቲያን በሥሯ ያሉ ምእመኖቿን ቆጥራ መመዝገብ እንድትችል›› የሚካሄደው ይኸው ታላቅ አገራዊ ክንዋኔ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በሚያዘጋጀው ቅጽ አማካይነት እንደሚከናወን ነው ቅዱስ ሲኖዶሱ የገለጸው፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ስለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት ሁሉም ሰው መጻፍ ሲገባው እውነት ያልኾነውን፣ በማስመሰል የሚነገረውንና የሚጻፈውን ማስተካከል እንደሚገባ ቅዱስ ሲኖዶሱ አሳስቧል፡፡
በመኾኑም እውነተኛውንና ትክክለኛውን አስተካክሎ ለሕዝብ፣ ለትውልደ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል መነሻ ይኾን ዘንድ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የኮሚቴ አባልነት ተጠንቶ የቀረበውን ጽሑፍ ምልአተ ጉባኤው በንባብ ሰምቶ ጉዳዩ ወደ ሊቃውንት ጉባኤ እንዲቀርብ ትእዛዝ መስጠቱን ቅ/ሲኖዶሱ አስታውቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ ሊቃውንት ጉባኤው ስለ ኢትዮጵያ ታሪካዊነትና ጥንታዊነት አብራርቶ፣ አስፍቶና አምልቶ ለግንቦት፣ ፳፻፮ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርብ ተወስኗል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በመክፈቻ ሥርዐተ ጸሎት የጀመረውንና ለዐሥር ቀናት ያህል ሲያካሂድ የቆየውን የመጀመሪያ ዓመታዊ የምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብስባ ዛሬ፣ ጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በጸሎት አጠናቋል፡፡
ምልአተ ጉባኤው መደበኛ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ባወጣው ባለ28 ነጥብ መግለጫ የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች አካትቷል፡-
