የመንግሥትን የአክራሪነት ፍረጃ ተከትሎ የቤተ ክህነቱን ተቋማዊ ለውጥ የሚቃወሙ ጥቅመኞች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የሚሰነዝሩት ውንጀላ ተጠናክሯል፤ ማኅበሩ ክሥ ለመመሥረት እየተዘጋጀ ነው

Aba sawiros

  • ከጉጂ ቦረናና ሊበን ዞኖች ሀገረ ስብከትና ሌሎች አብያተ ክርስቲያን በዘረፉት ገንዘብ ‹‹ሺበሺ›› በሚለው አስከፊ የሙስና ስያሜ የሚታወቁትና በነፍስ ግድያ ወንጀሎች የሚጠረጠሩት አቡነ ሳዊሮስ የሚያስተባብሯቸው የግብር አምሳሎቻቸው፣ መልአ ገነት አባ አፈ ወርቅ ዮሐንስ እና መልአከ ገነት አባ ዮናስ ታደሰ ዋነኛ ተጠያቂዎች ይኾናሉ ተብሏል፡፡
  • ማኅበረ ቅዱሳንን ‹‹የዐፄ ምኒልክ ሥርዐት እንዲመለስና የዐፄ ምኒልክ ባንዴራ እንዲሰቀል የሚፈልጉ ናቸው›› ብለው በመንግሥታዊ ስብሰባ ላይ በይፋ በመክሰስ ርምጃ እንዲወስድበት የጠየቁት የወሊሶ ሀ/ስብከት ሥ/አስኪያጅ መልአከ ገነት አባ አፈ ወርቅ፣ በመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ‹‹አጥቢያዎች ፐርሰንት እንዳይከፍሉ ሕዝቡን ይከፋፍልብናል፤ ወጣቶችን ያደራጅብናል›› በሚል በቅ/ሲኖዶስ እንዲታገድ ጠይቀዋል፡፡
  • የደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀገረ ስብከትን በሊቀ ጳጳስነት ይኹን በሥራ አስኪያጅነት ለመምራት ችሎታውም ሥነ ምግባሩም እንደሌላቸው ተቃውሞ የቀረበባቸው አቡነ ሳዊሮስ እና መልአከ ገነት አባ አፈ ወርቅ ዮሐንስ ለ፴፪ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ባቀረቡት ‹ሪፖርት›፣ የአስተዳደራቸውን ብልሹነት የተቃወሟቸውን አገልጋዮችና ምእመናን ‹‹ሥራ ዐጦች እና ተራ ዱርዮዎች›› በማለት ዘልፈዋል፡፡
  • በቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በተገበረው የሽግግር መዋቅርና ለቀጣይ የለውጥ አመራር ባካሄደው የመዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር የአሠራር ጥናት የማኅበረ ቅዱሳን ሞያተኞች ግንባር ቀደም ተሳትፎ በማድረጋቸው ሕገ ወጥ ጥቅማቸው የሚነካባቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳደር ሓላፊዎች የመንግሥትን የአክራሪነት ውንጀላ አመካኝተው ማኅበሩን ለማሸማቀቅ በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ ነው፤ ፴፪ውን የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቅሰቀሳ መድረክነት እየተጠቀሙ ነው፡፡
  • ከኀምሳው አህጉረ ስብከት የሚበዙት ማኅበረ ቅዱሳን በተቋማዊ ለውጥ አመራር፣ በቅዱሳት መካናትና አብነት ት/ቤቶች ድጋፍና ክብካቤ፣ በስብከተ ወንጌል መስፋፋትና መጠናከር ያደረገውን አስተዋፅኦ በሪፖርታቸው በማካተት እየገለጹ ባለበት ኹኔታ፣ እንደ መልአከ ገነት አባ ዮሐንስ አፈ ወርቅና መሰሎቻቸው የሚያቀርቡት የውንጀላ ሪፖርት ለአንዳንድ ጥቅመኛ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳደር ሓላፊዎች የቅስቀሳ መሣርያነት መዋሉ የአጠቃላይ ጉባኤውን ተሳታፊዎች እያስቆጣ ነው፤ የስብሰባ አመራሩም እያጠያየቀ ነው፡፡