ስንቱን አጣን!
ከፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም
እንደ ኢትዮጵያ ባለ ኋላቀር አገር አገር ውስጥ መሠልጠን ብዙ ችግር አለበት፤ እኔ ራሴ በኮምፒዩተር መጻፍ ከጀመርሁ ሠላሳ ዓመት ሊሆነኝ ነው፤ ታዲያ መብራት ጠፋና የምሠራው ባጣ የቆዩ ወረቀቶችን ሳገላብጥ አንድ እአአ በዲሴምበር 26 1965 ከዱሮ ተማሪዬ የተጻፈልኝን ደብዳቤ አገኘሁ፤ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በነበረ ከአንድ በጣም ጎበዝ ወጣት የተላከልኝ ነበረ፤ ከተመረቀ በኋላ በአንድ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ ለጥቂት ዓመታት ሠርቶ ትምህርቱን ለመቀጠል ወደ አሜሪካ ሄዶ በሎዝ አንጄለስ አካባቢ ከሚገኝ ትምህርት ቤት ገብቶ ነበር፤ ደብዳቤውን የጻፈልኝ ከዚያ ነው፤ ደብዳቤው ሰባት ገጾች አሉት፤ ከሰባቱ ገጾች አምስቱ ስለኢትዮጵያ ያለውን ስጋት የሚገልጽ ነው፤ በሎዝ አንጀለስ አካባቢ ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት በሚያደርግበት ጊዜ ሁሉ ብዙዎቹ የሚያሳዩት የመንደረኛነት ስሜት እያበሳጨው የተማሩት ሰዎች በእንደዚህ ያለ ማኅበረሰባዊ ኋላቀርነት ውስጥ ሆነው ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እንዴት መራመድ ትችላለች? እያለ ይሰጋ ነበር።