፴፪ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ተጀመረ
- የቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ በፍርድ ቤቶች ያለው ተቀባይነት ማነስ ያስከተለው ችግር፣ ልዩ እምነት ያላቸው አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሱት ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ተጽዕኖ፣ ወደ ዐረብ አገሮች እየሔዱ እምነታቸውን ወደ እስልምና የሚለውጡ ኦርቶዶክሳውያን ቁጥር መበራከትና ከእኒህም የካህናት ሚስቶች መኖራቸው፤ የአብነት ት/ቤቶች ህልውና ቀጣይነትና በተለይም የመጻሕፍተ ሊቃውንት ጉባኤያት በብዛት መታጠፍ፤ የመንፈሳዊ ኮሌጆች አስተዳደር፣ የደቀ መዛሙርቱ ምልመላና ምደባ፤ በአገልጋዮች እጥረት የአብያተ ክርስቲያን መዘጋትና ባልታወቁ ሰዎች የመቃጠል፣ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች(ዐደባባዮች፣ መካነ መቃበር፣ የልማት ቦታዎች) መደፈርና ወደ ግል የማዞር ችግር ጉባኤውን እያወያየ ነው
- ‹‹የቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ሀብቶች ምእመናን ናቸው፡፡ ብዙ ገቢ ማፍራታችን እሰየኹ ሊባል የሚገባው ቢኾንም ምእመናንን በማብዛት በኩል የተሠራው ሥራ አመርቂ አይደለም፤ የሰበካ ጉባኤያት ዋናው ትኩረት ከገንዘብ ይልቅ በገንዘብ ባለቤቶች ምእመናን ላይ መኾን ይኖርበታል፡፡›› /የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ/
- አህጉረ ስብከት በ፳፻፭ ዓ.ም. ከገቢያቸው ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ፈሰስ ያደረጉት 35 በመቶ ከ89 ሚልዮን ብር በላይ ደርሷል፤ ከ፳፻፬ ዓ.ም. ፈሰስ ያሳየው ጭማሪ 27‚000‚000 ያህል ብቻ ነው፡፡ የፈሰሱ መጨመር አጠቃላይ የገቢ ዕድገትን ቢያሳይም የመንበረ ፓትርያርኩ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ትክክለኛነቱን የሚያረጋግጥበት ስምሪትና በጀት የለውም፡፡
- ‹‹በደቡብ ሱዳን አምስት ያህል አብያተ ክርስቲያን ተተክለው አገልግሎት እየሰጡ ከጋምቤላ ሀ/ስብከት ጋራ እየተዳደሩ ነው›› በሚል የቀረበው ፍጹም ሐሰት ኾኖ መገኘቱ የአህጉረ ስብከቱ ሪፖርት በጥንቃቄ መታየት እንደሚገባው ያመላከተ ኾኗል፡፡
- ፴፪ኛው አጠቃላይ ጉባኤ በተሰብሳቢዎች አቀባበል፣ በአዳራሽ ዝግጅትና መስተንግዶ፣ በጉባኤ ሰነዶች አደረጃጀት መሻሻል ታይቶበታል፤ ይኹንና ለአንገብጋቢ ጉዳዮች ትኩረትና ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ ከመወያየት ይልቅ ሪፖርቶችን ለማዳመጥ የተመደበው ሰዓት የዓመታዊ ስብሰባውን አብዛኛውን ጊዜ የሚወስድ መኾኑ ይታያል፡፡
- ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያዎችና ድርጅቶች ሓላፊዎች፣ ከኀምሳ በላይ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ የካህናት፣ ምእመናን፣ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና የስብከተ ወንጌል ተወካዮች፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አድባራት አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት በአጠቃላይ ከ900 በላይ ተሰብሳቢዎች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
የዜናው ዝርዝር ይቀጥላል