የጣዖታት መፈራረስና ጦስ ጥምቡሳቸው

ተሻለ መንግሥቱ

ለረጂም ጊዜ ሥልጣን ላይ መቆዬት ከጣዖትነት ተለይቶ አይታይም፡፡ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1933 እስከ 1945 የአሜሪካን ፕሬዚደንት የነበሩት ፍራንክሊን ዴ. ሩዝቬልት እስከዚያን ዘመን ድረስ በልማድ ብቻ ሲከበር የነበረውን የሁለት ዙር የሥልጣን ዘመን በጡጫ ሳይሆን በምርጫ አልፈው በአሜሪካን ሀገር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሦስተኛ ዙር ሥልጣን በመያዛቸው ክፍተት ያሳዬው ሕገ መንግሥቱ ተሻሽሎ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ማንም ሰው ከሁለት ዙር በላይ ሊመረጥ እንዳይችል ተገድቧል፡፡ እንዲያ የተደረገው ሥልጣን በአዳዲስ ሰዎች እየተያዘ የአዳዲስ ሰዎች አእምሮ አዳዲስ ነገር እያፈለቀ ሀገሪቱ የጥቂት አምባገነን ዜጎች መፈንጪያ እንዳትሆን ነው፡፡ ሕዝብ ከፋም ለማም አዳዲስ መሪዎችን የማየት ጉጉትና ፍካጎት አለው፡፡ አመራሩ ላይ አንድ ፊት ብቻ እየታዬ ትውልዶች ሊፈራረቁ አይገባም፡፡ ለውጥን መሻት፣ የሚበጀውን ከማይበጀው መርጦ ለሹመት ካልፈለገም ለሽረት ማብቃት የሕዝብ የማይገሰስ መብት ሊሆን ሲገባ ብዙዎች የአፍሪካና በተለምዶ ሦስተኛው ዓለም በመባል የሚታወቁ ሀገራት መሪዎች ከዚህ ሥልጣንን እንደመዥገር ሙጭጭ አድርጎ የመያዝ ጠባይ ሊላቀቁ አልቻሉም፡፡ ተፈጥሮኣቸውም በአካል ሰው ይምሰሉ እንጂ በባሕርይ መዥገርና አልቅት ናቸው – ምንም ጥርጥር በሌለው ሁኔታ፡፡

አንድ ሰው የያዘውን ሥልጣን ለባለወርተራ መለቀቅ እንደሚኖርበት ካልተረዳና የሀገሪቱን ጦር እንደግል ሎሌው አድርጎ ያሻውን ማድረግ ከቻለ ለሕዝብ የማሰቡንና ለሀገር ዕድገት የመቆርቆሩን ነገር ከራሱ ብልጽግናና የሥልጣን ዕድሜ መራዘም እጅግ ያነሰ ክብደት ነው የሚሰጠው፡፡ እናም ‹በዚህን ዓመት በሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ደግሜ ላልመረጥ እችላለሁ፤ ይህን ዙር ስጨርስ የመጨረሻው የሥልጣን ዘመኔ ያበቃል፤ ፓርላማየን አስጸድቄ ከእስካሁኖቹ ተመራጮች በተሻለ ለመንግሥቴና ለሕዝቤ በሀገሬ የታሪክ መዝገብ የሚሠፍር አንዳች የተለዬ ሥራ ማከናወን ይጠበቅብኛል፤…› የሚል መሪ ሊገኝ የሚችለው ሥልጣን ከአንድ ሰው ዕጅ ወጥታ የሕዝብ ስትሆን ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ በጋዳፊ ሰሞኑን እያየነው እንዳለነው በእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ዓይነት እንስሳዊ ፍልስፍና መሪውን የሚያንገጫግጭ ሁኔታ በተፈጠረ ቁጥር ተያይዞ ገደል መግባት ከሆነ ነገሩ ሁልጊዜ ከዜሮ የመጀመር ዕጣ የሀገሪቱና የሕዝቡ መርገምት እንደሆነ ይቀራል ማለት ነው፡፡

አንድ ሰው ሥልጣን ላይ ለብዙ ዘመናት ተጎልቶ ከከረመ ያ ሰው በሥልጣን ስካርና በሀብት ብዛት እነዚህንም ተከትሎ በሚከሰት ዕብሪትና የማን አብኝነት ትምክህት አእምሮው ይደነብሻል፡፡ የብዙዎች ነገሥታትንና በጉልበት ሥልጣን የያዙ ፕሬዚደንቶችን ሁኔታ ስናይ እውነታው ከዚህ ከምንለው የተለዬ አይደለም፡፡ ከቅርብ የዓለማችን ታሪክ፣ ከዛፍ ቁመት በላይ የማትበርር አይሮፕላን ለልጄ ሥሩልኝ ብሏል የተባለውን የዩጋንዳውን ‹መሪ› ኢድ አሚንን ይዘን ስብሰባ ላይ የሲጋራ ትርኳሽና መተርኮሻን ጨምሮ በዕጁ የሚገኝ ማናቸውንም ነገር በመወርወር ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን ሳይቀር እንደቤቱ ተላላኪ በመቁጠር የሚማታውን የኛውን መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን አክለን፣ በመስቀል አደባባይ ባልተዘጋ ሜጋፎን ‹ጭቃ ሕዝብ› ብለው ምዕመናንን በመሳደብ የራሳቸውን ጭቃነት በገሃድ የገለጡትን የሃይማኖት አባትና በተግባሩም በአንደበቱም ለሕዝብ ያለውን ንቀትና ዕብሪት ዘወትር ካለማሰለስ በኩራት የሚገልጠውን አቶ መለስን ጨምረን የእነዚህን አምባገነኖች ትክለ ሰውነት ብናጤን ብዙና ብዙ መናገር እንችላለን፤ መናገሩ ብቻውን ፋይዳቢስ ሆኖ መቅረቱ ከፋ እንጂ፡፡

በሥልጣን ወንበር ላይ ተዘፍዝፎ ብዙ ዘመን የሚቆይ ሰው ወደጣዖትነት የሚሸጋገር መሆኑ የሚያስተባብሉት እውነታ አይደለም፡፡ አምባገነን – ማንኛውም የፖለቲካም ይሁን የሀብት አምባገነን – ራሱን እንደ አንድ ተራ የሕዝብ አካል ከመቁጠር አልፎ የሕዝብ ፈጣሪ የሆነ ያህል ይሰማዋል፡፡ ወደዚያ የአምልኮት ደረጃ እንዲደርስ ግን ብዙ ግብኣቶች አሉ፡፡ በተወሰነ ደረጃ የሕዝቡ የራሱ አስተዋፅዖ ቀላል አይደለም፡፡ በአንድ ወይ በሌላ መልክ ያ ሰውዬ ይካብ ይካብና ተቀምጠው የሰቀሉት ቆሞ ማውረድ የማይቻልበት አደገኛ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የመንግሥቱን ታሪክ በቀላሉ ማስታውስ እንችላለን፡፡ ሊገላገሉት ፈልገው የላኩትን ተመልሶ እንዴት እንደፈጃቸውና እንዳስፈጃቸው እናስታውሳለን፡፡ ቀላልና ግልብ ይዘት ያላቸው አእምሮዎች ወደሥልጣን ማማ ሲሰቀሉ የሚያመጡት ዳፋ በቀላሉ የሚገመት እንዳልሆነ አሁንና ሰሞኑን ከሊቢያ ሁኔታ ጭምር ብዙና ብዙ እያየን ነው፡፡ እጅግ አብዛኛው የሊቢያ ሕዝብ ‹በቃኸን! አጉራህ ጠናን› እያለው እሱ ራሱ በአማጽያኑና በተራዳኢያቸው ኔቶ ዱላ ወገብ ዛላው ተሸመድምዶ ቅታው የውኃ ሽታ ሆኖ ባለበት ሁኔታ ሕዝቡን ‹ባላችሁ መሣሪያ እነዚህን ዐይጦች ከትሪፖሊና ከመላዋ ሊቢያ አጽዱ› ሲል መስማታችን አምባገነኖች በርግጥም የሚሉትንና የሚያደርጉትን በጭራሽ የማያውቁ፣ በነሲብም የሚንቀሳቀሱና የዐይጥን ያህል እንኳን አንጎል የሌላቸው መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡ በመሠረቱ አንድ ሥሩ በጣም ታች ድረስ ወርዶ የተተከለ ዛፍ ሲነቀል ስንትና ስንት አካባቢያዊ ጥፋት እንደሚያደርስ ከልምድ እናውቃለን፡፡ መጥፎን ዛፍ ሥር ሳይሰድ በእንጭጭነቱ ወይ በለጋነቱ መንቀል ሲገባ በይደር ካቆዩት ዳፋው ብዙ ነው፡፡ ዛፉ ከጠነነ በኋላ፣ ሥሮቹን ውስጥ ለውስጥ የትና የት ድረስ ከሰደደ በኋላ እንንቀልህ ቢሉት ዙሪያ ገባው ይመነጋገላል፡፡ ነገሩ በዕንቁላሌ በቀጣሽኝ ዓይነት ነው፡፡ የ42 ዓመቱ አፄ ጋዳፊም ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረው እንግዲህ በብፅኣቱ ሳይሆን ለረጂም ዘመን ሥልጣን ላይ ተቀምጦ የጣዖት ያህል በሕዝቡ ሥነ ልቦናዊና አጠቃላይ ኑባሬ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ቀላል ባለመሆኑ ነው፡፡ እንጂ ሰውዬው የለየለት ዕብድ መሆኑንማ ከንግግሩም ሆነ ከአድራጎቱ ጥንትም ሆነ አሁን በበቂ ሁኔታ መረዳት ይቻላል፡፡ ጋዳፊ ጨዋና ጥሩ ሰው የሚባለው በዚያው ግም ለግም ተያይዘህ አዝግም በሚባልለቱ በአፍሪካ ኅብረት ይሁን ድርጅት ውስጥ ነው፡፡ ዱሮም እኮ ቢሆን ቂጥኛም ከውርዴ – ከቢጤው – ጋር ይጫወታል ነው እሚባለው፡፡ እነሱም ደናቁርት ናቸው፡፡ ይሄ ኅብረት ተብዬውም በመልክ ሳይሆን በባሕርይ የፉንጋዎች ጥርቅም ነው፡፡ ለሽርሽርና ለውሎ አበል የሚመጣበት ባዶ ቀፎ፡፡

ጣዖት ካለ አምላኪም አለ፡፡ ዓለማችን ቡራቡሬ ናት፤ ክፉኛ የተዠነጓጎረች ዥንጉርጉር፡፡ አፄ ምኒሊክ በደገኛ ምግባራቸው እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በሕዝብ ዘንድ መማያ ነበሩ፡፡ አፄ ኃይለሥላሤም ከእምዬ ምኒሊክ ደረጃ ባይቀራረብም ለብዙዎች የጣዖት ያህል ነበሩ፡፡ እንዲያውም እሳቸው ከወረዱ ሀገር ትፈርሳለችና ትወድማለች ብቻ ሳይሆን ‹ፀሐይ ብርሃኗን ትነሳለች፤ ምድር ትናወጣለች፤ ዓለም ትጠፋለች› ብለው በየዋህነትና አገዛዙ ለዘመናት ባሳደረባቸው ጫና የተነሳ የሚያምኑ ነበሩ፡፡ እርግጥ ነው እምነታቸው ያን ያህል በተጋነነ መልኩም ባይሆን ከዚያን ወዲህ ከደረሰብን ያልጠበቅነው ችግር አኳያ ሟርታቸው በተወሰነ ደረጃ ውኃ የሚያነሳ ሃቅነት እንዳለው ለነፍሳችን ያደርን ምራቅ የዋጥን ዜጎች በተለይ አሁን አሁን አፋችንን ሞልተን ልንመሠክር እንደፍራለን፡፡ ከእርሳቸው በኋላ ማርና ወተት ይዘንባል ብለን በየዋህነት የጠበቅን ዜጎች ፅድቁ ቀርቶብን በቅጡም ልንኮነን አልቻልንም፡፡ ብዙ ተገደልን፤ ታሠርን፤ ተሰደድን፤ ተንገላታን፤ በርሃብና በኑሮ ውድነት ተጠበስን፤ የሚያስብልን መንግሥትና ዕንባችንን የሚያብስ ደግ ሰው አጣን፤ ተዋረድን፤ በዘርና በጎሣ ተከፋፈልን፤ የጋራ መለያ ባንዴራና ብሔራዊ መዝሙር ሳይቀር አጣን፤ በአጭሩ ያልሆነው የለም ማለት ይቀላል፡፡

ይህ ሁሉ የሆነውና እዬሆነ ያለው በሀገራችን መሠረት ያለው ሕዝባዊ የሥልጣን ሽግግር ባለመኖሩ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ሥልጣን አያያዝ ‹ሠርክ አዲስ› እንደሆነ አለ፡፡ አንዱ ይመጣል የኋለኛውን እየናደና እያንጓጠጠ በአዲስ ርዕዮተ ዓለምና ፍልስፍና ሁሉን ነገር ‹ሀ› ብሎ በኢዲስ መልክ ይጀምራል፡፡ ሌላኛው ይመጣል የነበረውን እያንቋሸሸና እየረገመ ከባዶው ሊጀምር ይኳትናል፡፡ ሁሉም እየተነሣ ያለፈውን መኮነን እንጂ ካለፈው ጥቂት ነገርን እንኳን በምሥጋናና በአክብሮት ተቀብሎ እንደእርሾም ያን ይዞ አይጀምርም፡፡ ያለፈን ካላወገዙ ሥልጣን የሚረጋላቸው አይመስላቸውም፡፡ መረገም ነው፡፡ ሁሉም ታዲያ ባዶና የመርግምት ውጤቶች እንደሆኑ ዕድሜያቸውን ጨርሰው ወደማይቀሩበት ይጓዛሉ፡፡ ችግሩ ሁሉም የገምቢው ሳይሆን የአፍራሹ ኃይል ወገኖች በመሆናቸው የጣዖት አምላኪዎቻቸው በሚያደርጉላቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ በሀገርና በሕዘብ ላይ የሚያደርሱት የዞረ ድምር ከግምት በላይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ አካሄድ በቶሎ ካልተወገደ መቼም ቢሆን ሀገር ሳይኖረን በገዛ ሀገራችንም እንደመፃተኛ እንደተቆጠርን በገዛ ቀያችን ግዞተኛ ሆነን እንቀራለን፡፡ ይህን አስጠሊታ ሀገራዊ ምስል ለማሰወገድ ደግሞ በተለይ ከወጣቱ ብዙ ይጠበቃል፡፡ ዘመኑ የሥልጣኔ መሆኑን ተገንዝቦ ከፋፋዮች ያበጁለትን የመለያያ ሥልት ንቆ በአዲስ ሀገራዊ ስሜትና መርህ ወጣቱ ከተንቀሳቀስ ሀገሩን ከአጭበርባሪዎች መንጋጋ ፈልቅቆ ለማውጣትና የነጻነቱ ባለቤት ለመሆን እስካሁን በዋዛና ፈዛዛ በከንቱ ካሳለፍነው ዘመን አንጻር ብዙ ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ ነጻነቱን እንደተነጠቀ ዘላለሙን የሚኖረው ከፋፋዮች በቀየሱለት መንገድ ከተጓዘ ብቻ ነው፡፡ ያ ደግሞ ቢያንስ ለሃያ ዓመታት ስለታዬ ማንን እንደጠቀመ በግልጽ ታውቋል፡፡ እናም ወጣቱ ላይ ያለው የኃላፊነት ሸክም ከሁሉም ይበልጣልና የሀገሩ መፃኢ ዕድል ያገባኛል የሚል ዜጋ ሁሉ ከጎኑ ተሰልፎ በመተባበር፣ በመካከሉ የገነባቸው ከፋፋይ አጥሮች ካሉ እነዚያን በአስቸኳይ ነቃቅሎ በመጣል በሚጠቅመው የጋራ ኅብረት ተሠልፎ ሀገሩን ከወሮበሎች ተጨማሪ ጥፋት ሊታደጋት ይገባል፡፡ ይህን ሲያደርግ ደግሞ አሁን በሊቢያ እያየነው እንዳለነው እንዳይሆን ከነሱም ሆነ ከሌሎች ገምቢ ትምህርት በመቅሰም በተቻለ መጠን ትልቅ መስዋዕትነትን በማያስከፍል መልክ የትግል ስልትን መቄስ ተገቢ ነው፡፡ የስሙኒ ዶሮ የብር ገመድ ይዛ ጫካ እንዳትገባ መጠንቀቅ ብልህነት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በሌለን አቅም ያን ያህል ብዙ ወጪ ማውጣት ይከብደናል፡፡ የአንዲት ሀገር ለጆች በተለያዩ ጎራዎች ተሠልፈን መተላለቅም ከእንግዲህ ዕርም ሊሆንብን ይገባል፡፡ ከሌሎች መማር አለብን፡፡ ያበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት ሊጫወት አይጠበቅበትምና የቁርጡ ቀን ሲመጣ እነአቶ መለስም ከነጋዳፊ በመማር ሕዝብ ሳያልቅና ሳይተላለቅ በጊዜ አዋጭ መፍትሔ ሊሰጡ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቀኑ የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መምጣቱ በጭራሽ አይቀርም፡፡ ከእንግዲህ ጦሩም በሕዝብ ላይ መተኮስ ሊሰለቸው ይገባል፡፡ መግደል እኮ የጭካኔ ተግባር እንጂ ሊኮሩበት የሚገባ ብርቅዬና ለፅድቅ የሚያበቃ ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ ፖሊስንና ደኅንነትን ጨምሮ በተለይ የጸጥታው ተቋምና ወታደሩ የወጡበትን ሕዝብ በጥይት እንዳይቆሉ በማይም ቃሌ ገዝቻለሁ፤ አደራ! የበሉበትን ወጪት መስበርም ወንጀልነቱ ቀደም ሲል በተደጋጋሚ እንደታዘብነው በመንግሥት ቢሸፈንም ኃጢያትነቱ ግን በሰማይ ይጠብቃል፡፡ ደሞዛቸውን የሚከፍለው መለስ ሳይሆን ይህ ሕዝብ መሆኑን ማጤን ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብስ አንዴውኑ በቁሙ ሞቷልና ከአሁን በኋላ የሚፈራው ነገር አይኖርም፡፡ የሚፈልገው እንደምንም ጎትጉቶ በማንቃት ወደተቃውሞው አምባ ማውጣት ብቻ ነው፡፡ እየሞተ ከመኖር ይልቅ እየኖረ መሞትን የሚመርጥበት ጊዜ መምጣቱ ስለማይቀር ያኔ ጠበንጃዎች ሁሉ ትናጋቸው እንዲዘጋ የሕዝብ ወገን ከሆነ የጦርና የጸጥታ ኃይል ብዙ ይጠበቃል፡፡ ለማንኛውም እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ ከዳግም መከራም ይሠውረን፡፡ ልባቸው ለተደፈነ መከፈትን፣ ዕውቀትን ለተራቡ የግንዛቤ አድማስ መስፋትን፣ ቂም በቀል ላረገዙ አስተዋይነትን፣ በመርዘኝነት ለተለከፉ ማርከሻ መድሐኒትን አንድዬ አብዝቶ ይስጥልን፡፡

([email protected])