ከኦነግና ሌሎች የዘር ድርጅቶች ጋር መነጋገርና መተባበር ለምን ያስፈልጋል?
ከጌታቸው በጋሻው
አርሊንግተን፣ ቨርጂኒያ ውስጥ፣ July 10, 2011 በተደረገው ስብሰባ ላይ ኦነግን አስመልክቶ ባደረግኩት ንግግር ዙሪያ ምስጋናና ማበረታቻ ብቻ ሳይሆኑ ከተራ ስድቦች አንስቶ እስከ መሰረታዊ ብሄራዊና አገራዊ የደህንነት ጥያቄዎች ድረስ ቀርበውልኛል። ይህ ንግግሬ ይህን ያህል ሰዎችን ለማነጋገር በመቻሉና የዘር ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ውስጥ የሚኖራቸውን ሚናና ቦታ ግልጥልጥ ባለ መልኩ እንድንነጋገርበት ውይይት በማጫሩ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል፣ የንግግሬም ዋና ዓላማ ይኽው ነበርና። አሁንም፣ ይህንኑ ውይይት በጥልቀት ለማስቀጠልና በንግግሬ ውስጥ ያልተገለጹ ቁምነገሮችን ይበልጥ ለማብራራት ይህንን ጽሁፍ አቀርባለሁ።
ስድቡን መተዳደሪያቸው ላደረጉት ልተወውና በውይይቱና በትችቱ ውስጥ ቅንነትንና ተቆርቋሪነትን የሚያሳዩ ሀሳቦቻቸውን በአደባባይና በግል ላቀረቡልኝ ታላላቅና የማከብራቸው ውድ ኢትዮጵያዊያን ግልጽና ቀጥተኛ የሆኑ መልሶችና ውይይት ይገባቸዋል ብዬ አምናለሁ። ይህንንም በማድረግ የሀሳቦችን ጥራት ለማግኘት እንችላለን፣ አገራችንን ገጥሞ ያለውን የመገነጣጠል አደጋ በውል እንገንዘባለን፣ ምናልባትም በተረጋጋ በተከባበረና በበለጸገ የሀሳብ ልውውጥ የአደጋውን ማፈኛ ብልሀትም አብረን እንፈጥራለን። ስለዚህ፣ ዋና ዋና የሆኑትን የውይይቱን ነጥቦች አጠር አጠር አድርጌ በክፍል በክፍሉ እየለየሁ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ። ረዘመ ብለው የሚከፉ ካሉም አረፍ አረፍ እያሉ አንብበው ሊጨርሱት ይችላሉ እላለሁ።
ምኞትንና እውነታን እንለይ
ብዙ ጊዜ በምናደርጋቸው ውይይቶች ውስጥ መሰረታዊ ችግሮች ሆነው የማገኛቸው ነገሮች በስሜታዊ ክርክሮችና በጭብጥ ሁኔታዎች መሀል ያሉ ልዩነቶች የሚፈጥሯቸው አለመግባባቶች ናቸው። የኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄን ስናነሳ ብዙ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ። በሁሉም አገሮችና ኅብረተሰቦች ውስጥ እንደሚደረጉት፣ እኛም ተወልደን እስክናድግ ድረስ፣ ቤተሰቦቻንና ትምህርት ቤቶቻን ሲያስጠኑንና ሲያስጨብጡን የነበሩት አገራዊ ጉዳዮች ስለኢትዮጵያ አስደናቂ የታሪክ ቅርስና ባለቤትነት፣ትልቅነትና ገናናነት፣ ድንበሯን አስከባሪና ለነጻነቷ ሟችነት፣ በራስ መተማመንና ብሄራዊ ኩራት እና ብዙ የአንድን ሰው ብሄራዊ ስሜትና ምንነት ሊያዳብሩና ሊያጥነክሩ የሚችሉ የታሪክ ትውስታዎችና ትዝታዎች ናቸው። ይህ ደግሞ በራሱ ምንም ክፋት የሌለበት ኅብረተሰባዊ መግለጫ ነው። ዛሬ ላለን የኢትዮጵያዊነት ስሜትና ታማኝነት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላል የሚገመት አይሆንም።
በአንጻሩ ደግሞ፣ ይህ ስሜታዊ የአገር ፍቅር በቅጡ ካልተያዘና የአገሪቱን ጉዳዮች በሙሉ በስሜታዊነት ብቻ እየተመለከትን በተጨባጭነት በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ነባራዊ እውነታዎችን በውል እንዳንገነዘብ የሚያደርገን ከሆን በውስጡ ብዙ ችግሮችን ያረገዘ ነው ለማለት ይቻላል። አገርን መውደድና ለሁለንተናዊ እድገቷና ደህንነቷ ማሰብና መቆርቆር አንድ ነገር ነው። ችግሮችን ደግሞ በይዞታቸው ለመረዳትና ለማገናዘብ አለመቻል ሌላ ነገር ነው።
ለምሳሌ፣ ዛሬ ያለንን የዘር ችግሮች ሳስብ፣ እንደኔ ስሜታዊ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ፣ በአገራችን ውስጥ አንዳች የዘር ፖለቲካ አይኖርም ነበር፣ አንድም የዘር ድርጅት አይፈጠርም ነበር፣ በምንም መልኩ የዘር ክልሎች አይመሰረቱም ነበር፣ ሁሉም በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ኮርቶና ተመክቶ የፈለገበት የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ማንም ሳይጠይቀው፣ ማንም ሳያስገድደው፣ በነፃነት ለመኖር ይችል ነበር። ነገር ግን፤የአገራችን እውነታ እኔ እንድምፈልገውና እንደምመኘው ሆኖ አልተገኘም። ሦስት ምሳሌዎች ብቻ ላቅርብ።
አንደኛ፣ የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን ብቻ በመውሰድ፣ በ1961ዓመተ ምኅረት፣ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር፣ የዛሬ 50 አመት ማለት ነው፣አቶ እድሪስ አወተ በኤርትራ በረሃ ውስጥ የመጀመሪያዋን የመገንጠል (እነርሱ የነጻነት ይሏታል) ጥይት ከተኮሱባት ዕለት ወዲህ የዘር ፖለቲካው፣ የዘር ድርጅቱ፣ የዘር ጥላቻው እየከፋ ሄደ እንጂ አልበረደም። ሀቁ እንደሚከተለው ነው።
- ኤርትራ ተገነጠለች፣ የዓለም መንግስታት ድርጅት አንድ ነጻ አባል አገር ሆነች (እኔ አሁንም ተስፋ አልቆረጥኩም፣ ኤርትራን እስከዛሬ ድረስ እንደሌላ አገርና መንግስት ቆጥሬ አላውቅም2)።
- የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር (ወያኔ፣ የዘር ድርጅት) የኢትዮጵያን መንግስት ያዘ፣ ኢትዮጵያን በዘጠኝ የዘር ክልሎች ሸነሸነ፣ በፈለገው ጊዜ ሊበትናት አንቀጽ 39ን ህገ-መንግስቱ ውስጥ ደነገገ።
- ወያኔ የሚጠቀምባቸውን ብዙ ጥገኛ (ተለጣፊ) የዘር ድርጅቶች በመላ አገሪቱ ውስጥ ፈለፈለ።
- ከወያኔ ቁጥጥር ውጭ ደግሞ ቀደም ብለው የተደራጁና የታጠቁ የዘር ድርጅቶች (እንደ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር – ኦነግ- እና ኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር – ኦብነግ- ያሉ ድርጅቶች) ተበራከቱ።
- ኢትዮጵያዊንትን ተቀብለውና አምነው ዛሬ በህብረት ፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉትን አባል ድርጅቶችን እንኳን ብንቆጥር (በአገር ውስጥ መድረክን፣ በውጭ ደግሞ ኢኃዴህን) አብዛኞቹ የዘር ድርጅቶች ናቸው።
ሁለተኛ፣ በኢትዮጵያዊነት የተደራጁና ዛሬ “የአንድነት ኃይሎች” ነን የሚሉት በእውነት ከተመረመሩ በቦታውም ላይ የሚገኙ አይመስለኝም። እስቲ ከእነኝህ “የአንድነት ኃይሎች” ነን ከሚሉት ድርጅቶች ውስጥ ሚዛን በሚደፋ መልኩ የኢትዮጵያን ሕዝብ ድጋፍና ክብር ያለው አንድ ድርጅት ለናሙና እናቅርብ። አንድም እንደማይገኝ በሙሉ እምነት ለመናገር የምችል ይመስለኛል። ይህም ሁኔታ አሁን በተያዘው መልኩ ከቀጠለ ደግሞ ወደፊትም በረጅም ጊዜ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ድርጅት ለመምጣት መቻሉን በጣም እጠራጠራለሁ። እነኝህ “የአንድነት ኃይሎች” ነን የሚሉት ድርጅቶች ተባብረው በጋራ ለመታገልና ለዘር ድርጅቶች አማራጭና ተፎካካሪ ሆነው ለመቅረብ አለመቻላቸው ቀርቶ፣ እያንዳንዳቸው እንኳን በራሳቸው ውስጥ ድርጅታዊ ውህደታቸውን ጠብቀው ለመቆዬት ያልቻሉና የተከፋፈሉ ደካማ ቡድኖች ወይም ስብስቦች ናቸው። አባላቶቻቸውም ተራ በተራ እየተውአቸው ሲወጡ እነዚህ ድርጅቶች ለትግሉ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የሰው ሀይል ክፉኛ እያመነመኑ መሆናቸውንም የሚገነዘቡት አይመስለኝም፣ ወይም ግድ ያላቸው ሆኖ አይታየኝም።
ሦስተኛ፣ ኢትዮጵያ ወዳጅ ጎረቤትና ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ የላትም። ከሰሜን በኩል፣ በተጭበረበረ መንገድ ነጻነቷን ከኢትዮጵያ ያወጀችው ኤርትራ ኢትዮጵያን በዘላለማዊ ቀውስ ውስጥ ለመጨመር አርፋ የምትተኛ አይደለችም። በምዕራብ በኩል፣ ሱዳን ኢትዮጵያን አዳክማና አፈራርሳ ብዙ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ጥቅሞችን ለማግኘት ሁሌም የምትጥር የዘወትር ጠላት ናት። በምስራቅ በኩል ደግሞ፣ ሶማሊያ አንድ ሦስተኛውን የኢትዮጵያን ምድር እስከ አዋሽ ድረስ ለመውሰድና ታላቋን ሱማሌ ለመመስረት ሌት ተቀን ከማጥቃት የማትቦዝን የሁልጊዜ ደመኛ ናት። ምናልባት እንደሁኔታው፣ በደቡብ ብቻ፣ ኬኒያ ኢትዮጵያን ለመጉዳት የማትፈልግ፣ ነገር ግን የክፉ ቀን ወዳጅ ልትሆን የማትችል ለስላሳ ጎረቤት ናት። ይህ ሁሉ የአደጋ ምንጮች አጎራባች በሆኑት አገሮች ክልል ብቻ ሲታይ ነው። አጠቃላይ የአካባቢውን ሁኔታ ከወሰድን ደግሞ አገራችን በአስፈሪ የእሳት ረመጥ ውስጥ መገኘቷን ለመገንዘብ አያዳግትም። የግብፅንና የመካከለኛ ምስራቅ አረባዊያን መንግስታት ጥቅምና ጠላትነት ከኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነትና የሕዝቧ ውህደት ጋር ፍጹም ተጻራሪነት አላቸው።
ሲጠቃለል፣ ምንም እንኳን በአገር ተቆርቋርነትና በቅን አሳቢነት በርካታ ኢትዮጵያኖች የአገሪቱ ግዛታዊ አንድነትና የሕዝቧ በስምም መኖር የሁልጊዜ ፍላጎታቸውና ምኞታቸው ቢሆንም፣ በውስጥና በውጭ ያሉት ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታዎች ለኢትዮጵያ የሚያመቹ እንዳልሆኑ በውል መረዳት ይጠበቅባቸዋል። በወያኔና በተለያዩ የዘር ድርጅቶች በኩል የተቃጡት የመገነጣጠል አደጋዎች በየጊዜው እየስፉ ሲሄዱ፣ ኢትዮጵያን ሊከላከል የሚችል እውነተኛ የአንድነት ኃይል አሁን በእርግጠኝነት ጠንክሮ አልተደራጀም፣ በቦታው ላይ አይገኝም። በአንጻሩ፣ አንዳንድ “የአንድነት ኃይሎች” ነን የሚሉ ቡድኖች በሚተፏቸው የቂምና የጥላቻ ፖለቲካና ትንኮሳ የባሰ የመገነጣጠል አደጋን በአገሪቱ ላይ እንዲያንዣብብ እያደረጉ መሆናቸውን ማጤን ያስፈልጋል።
ዛሬ የኢትዮጵያ መኖር አለመኖር ጉዳይ የወያኔ ውሳኔ ነው
ለጊዜው ለሚያገኘው ጥቅማ ጥቅሞች እራሱን ከወያኔ ተቃዋሚነት ወደ ደጋፊነት ከለወጠ አንድ ሰው ጋር በአንድ ማኅበራዊ የመዝናኛ ጊዜ ላይ ተገናኝተን ለምን እንደሚደገፋቸው ስንጠይቀው ከሰጠን መልሶች ውስጥ አንዱ አዕምሮዬ ውስጥ ተቀርጾ ቀርቷል። “ደርግን ጥለው ሲገቡ ኢትዮጵያን የመበተን ችሎታና አማራጭ ነበራቸው፣ ግን አላደረጉትም፣ አልፈለጉትም” አለ። “ስለዚህ” አለ አከታትሎ “ዛሬ ከምን ጊዜውም በበለጠ ደረጃ የኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት ተረጋግጧል” ብሎ ነገረን። ወያኔም በየዕለቱ የሚነገረን ይህንኑ ነው፣ “እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ ትወድማለች!” እያለ። ይህ ወንድማችን በአንድ በኩል በጣም ትክክል ነው። በዚያን ወቅት፣ ዛሬም ቢሆን፣ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንደ አገርና መንግስት እንዳትኖር ለማድረግ ይችላሉ። ልብ እንበል፣ ኢትዮጵያ ሁነኛ ጠባቂና ተከራካሪ የላትም። ወያኔ ግን ሞኝ አይደለም፣ ባዶ ቤት ያገኘ አንድ ዘራፊ ሌባ ቤቱን ከነንብረቱ ለምን ያፈርሳል ወይም ለምን ጥሎ ይሄዳል እውስጡ ያለውን ነገር በሙሉ አውጥቶ እስኪጨርስ ድረስ? ወንድማችን ሆን ብሎ የሳተው ይህንን ነው። ወያኔ ደርግን ጥሎ ሲገባ፣ ያገኛት ኢትዮጵያ ባለቤት ያልነበራት ድንግል አገር ከነሙሉ ንብረቷና ሀብቷ ነው። ተሻሚና ተፎካካሪ እስካልገጠመው ድረስ፣ ወያኔ እየገደለም፣ እያሰረም፣ እያባረረም ኢትዮጵያን ዛሬ ባለቺው መልኳ እየገዛትና እየቦጠቦጣት ይኖራል። በወያኔ ስር ያለው የኢትዮጵያ አንድነት ይህ ነው።
እንግዲህ፣ ይህ የኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄ ሌላ መልክ የሚኖረውና የሚያሳስበው ወያኔ በዚህ በያዘው መንገድ ለመግዛት ሲያቅተው ብቻ ነው። ለዚያ ለወንድማችን ስንመልስለት እኛ ያልነው፣ “አይ ወንድማችን፣ የኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት ከመሰረቱ የተናጋውና በእርግጠኝነት አደጋ ላይ የወደቀው ወያኔ ስልጣን ከያዘና በህገ መንግስት ደንግጎ፣ አገሪቱን በዘጠኝ የዘር ክልሎች ከፋፍሎና የኢትዮጵያዊነትን ብሄራዊ ስሜት አደብዝዞ፣ ሳይቻለው ሲቀር በትኖ ለመጥፋት የተዘጋጀ ዕለት ነበር” ነው። ይህ ወንድማችን፣ ለዚህ ለኛ ክርክር መልስ ለመስጠት አልፈለገም፣ የጥቅም ጉዳይ ሆኖበት ነው እንጂ እውነት መሆኑን ከልቡ ስለሚያውቀው።
ይህ ከወንድማችን ጋር የነበረን ክርክር በሁላችንም መሀል በየዕለቱ የሚካሄድ ነው። ወያኔ ዝም ብሎ አንድ ቀን ጠዋት ከመሬት ተነስቶ እንደ ጨዋታ ኢትዮጵያን አይበትንም። ወያኔ ጥቅሙን ያውቃል። እርግጥ ነው ኢትዮጵያን አይወድም ወያኔ። በሕዝቧ ላይ ጅምላ ጭፍጨፋ ሲያካሄድ አይተናል። ሰሜናዊውን ክፍለ ሀገራችንን፣ ኤርትራን፣ ገንጥሉልኝ ብሎ የዓለም መንግስታትን አስጨንቆ ሌላ ባእድ አገር እንድትሆን ሲያደርግ ተመልክተናል። የባህር በር ኢትዮጵያን ያስፈልጋታል ብለው የሌሎች ባእድ አገር መንግስቶች አሰብ ወደ ኢትዮጵያ እንድትሆን ቢያሳስቡ አያገባችሁም ብሎ ሲከራከራቸው አስተውለናል። ምዕራባዊውን ለም የእርሻ መሬትና ሰፊና ረጅም የአገራችንን ድንበር ለሱዳን ገምሶ ሲሰጥና በቦታው ላይ ኗሪ የሆኑ ኢትዮጵያኖችን ከሱዳን ወታደሮች ጋር በመተባበር ሲያስርና ሲረሽን ልብ ብለናል። በደቡብና በመሀል የአገሪቱ ክፍሎች ያሉትን ለም የእርሻና የግጦሽ መሬቶችን ለህንድ፣ ለፓኪስታን፣ ለቻይና፣ ለዓረብ…. መንግስቶችና ኩባኒያዎች ይህ ነው ሊባል በማይችል ክፍያ ሲቸበችብና ሲያከፋፍል ታዝበናል። አቶ መለስ ዜናዊ በለመደው አፋቸው በአንድ ወቅት “ምኒልክ በሰይፍና በጎራዴ ለፈጠረው ድንበር ዘብ አንቆምም” ብለው መናገራቸውንም አንዘነጋም። አቶ ስብሃት ነጋም፣ በአንዱ የሸራተን መዝናኛ ምሽታቸው ላይ ለአንድ የትውውቅ ጓደኛቸው፣ “የማይቻለን ከሆነ ኢትዮጵያን ለአማራ ትተን እንደማንወጣ እርግጠኞች ሆነናል” ብለው የልባቸውን እንዳጫወቱት ከጆሮአችን ገብቷል። ጀኔራል ሳሞራ ዩኑስ “አማራ ዳግም እንዳያንሰራራ አረጋግጠናል” ብለው ስብሰባ ላይ መናገራቸውን አድምጠናል።
እንግዲህ፣ እነኝህ ምሳሌያዊ መረጃዎች የሚያመለክቱን አንድ ዋና ቁምነገር ካለ፣ ኤርትራን አንድ ሌላ የባእድ አገር አድርጎ ለመፍጠር እንድተቻለው ሁሉ፣ ኢትዮጵያ የምትባለው አገርም እንደ አገርና መንግስት ከዓለም ካርታ ላይ በአንድ የወያኔ ትንሽ የብዕር ጭረት ልትጠፋ እንደምትችል ነው። ይህ ሊሆን አይችልም/አይገባውም ብሎ ገዋውን የሚሞላና ለግዛታዊ አንድነቷ ሊቆም የሚችል “የአንድነት ኃይል” የለማ!! ወያኔ በፈጠረው የዘር ክልል መሰረት አገሪቷን ቢያቀረማምታት የተደራጁትና የታጠቁት የዘር ድርጅቶች አይከፋቸውማ!! መራር ሀቅ።
ታዲያ ምን ይደረግ?
እውነት አገርንና ሕዝብን እንወዳለን፣ ለአገርና ለሕዝብ እንሰራለን ከተባለ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ወደፊት ሊሆን ይችላል በሚል ባዶ ተስፋና በምኞታዊ ፈላጎት ብቻ ላይ ተሞርክዞ አካኪ ዘራፍ ከማለት እውነታውን ለመገንዘብ ግራ ቅኙን መርምሮ ጊዜው የሚጠይቀውን ወይም የሚፈቅደውን ለማድረግ እራስን ማዘጋጀት ይጠበቃል። ከላይ የጠቀስኳቸው የኮሶ ምሬት ያላቸው ሀቆችና እውነታዎች፣ በተለይም “የአንድነት ኃይሎች” ነን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች፣ አደብ እንዲገዙና የየራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት ገታ አድርገው አገርንና ሕዝብን ለማስቀደም መቻል እንዳለባቸው ያስገነዝባል። ሦስት ቁርጠኛ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ብዬ አምናለሁ።
አንደኛ፡ አንድ ብሄራዊ ድርጅት ሊፈጠር ይገባዋል
ኢትዮጵያ በወያኔ ዘረኛና አምባገነናዊ መንግሰት ስር ያሳለፈችው ሀያ የመከራ ዓመታት በግልጽ ያሳየው አንድ ትልቅ የፖለቲካ ችግር “የአንድነት ኃይሎች” ነን የሚሉት ድርጅቶች ቀጣይነት ያለው የህብረት ድርጅት ሊፈጥሩ እንደማይችሉ ነው። ህብረት እስካሁን ተፈጥሮ ሕዝቡን በአንድ ድርጅታዊ ጥላ ስር አሰባስቦ ለማታገል ያልተቻለው የህብረት መፈጠርን የሚያስገድዱ አስከፊ የፖለቲካ ሁኔታዎች በአገሪቱ ውስጥ ባለመኖራቸው አይደለም። ህዝቡም ለእንደዚህ ዓይነት ድርጅት መፈጠር ፍላጎቱንና ምኞቱን ሳይገልጥ ወይም ድጋፉን ሳያበረክት ቀርቶ አይደለም። ያልተፈጠረው ወይም የተፈጠረው ሊስመርና ሊቀጥል ያልቻለው የአንዳንዶቹ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ግለኛና ቡድነኛ በመሆን የየራስቸውን ግላዊና ቡድናዊ ጥቅም የሚያዩ በመሆናቸው ብቻ ነው። አሁንም፣ እነኝሁ መሪዎች ድርጅቶቹን አንቀው እስከያዙ ድረስ የህብረት ድርጅት ሊፈጠር አይችልም። እነኝህ መሪዎች በቂም፣ በጥላቻ፣ በክፋት፣ በተንኮልና በጥቅም ፈላጊነት የተመረዙና ስለአገርና ስለሕዝብ ተብለው ቢለመኑ እንኳን ሊታረቁና ሊግባቡ የማይችሉ ናቸው። ስለዚህ፣ የድርጅቶች ህብረት ከነኝህ ሰዎች አይገኝም ወይም በነኝህ ሰዎች አማካይነት ሊመጣ አይችልም። ብዙ ጊዜ ተሞክረው የከሸፉት ጅምሮች በቂ ምስክሮች ናቸው። በእነኝሁ ሰዎች ይህንኑ ደጋግሞ መውቀጥና የተለየ ውጤት መጠበቅ ደግሞ ሌላ ስም ያሰጣል ብለዋል አዋቂዎች።
ስለዚህ፣ ለአገር አሳቢ የሆኑ ወገኖች፣ ለግለሰቦች ጥቅምና ለድርጅቶች ዝና ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ነጻነት በሀቅ ለመታገል ከፈለጉ፣ በአንድ የጋራ ድርጀት ውስጥ ለመሰባሰብ መጣር ይገባቸዋል። እነዚህ እስካሁን እንቅፋት ሆነው የቆዩ መሪዎችና ጭፍን ተከታዮቻቸው ይህንን ሀሳብ ገና ካሁኑ በጥፍራቸውና በጥርሳቸው እንደሚዋጉት አልጠራጠርም፤ የኑሮና የጥቅም ጉዳይ ነውና።
በኛ ሁኔታ፣ የአንድነት ኃይሎች ነን በሚለው ወገን በኩል ማለት ነው፣ ከህብረት ይልቅ አንድ ብሄራዊ ድርጅት አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያቱ በጣም ቀላል ነው። ካሁን ቀደም እያንዳንዱ ድርጅት የመሪዎቹ የየግል ኩባኒያዎች ስለነበሩና ወደ ህብረት ድርጅት ምስረታ ሲመጡ የነበረው የመሪዎች ግላዊ ጥቅም እንዳይጓደል ሁሉም የህብረት ድርጅቱን መሪነት ለመያዝ ወይም ለመቆጣጠር ይሻኮታሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የህብረት ድርጅቱ ተመስርቶ ከሆነ ይፈርሳል፣ በጅምር ላይ ከሆነ ደግሞ ይከሽፋል። ይህ ዓይነት ከሻፊ ሂደት እንደገና ሊወሰድ አይገባውም፣ ውጤቱ ቀድሞ የታወቀ ነውና። በቦታው፣ ለአገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪነት ያላቸው ኢትዮጵያኖች ዘር፣ ሀይማኖት፣ ፆታ፣ እድሜ፣ የቀድሞ የፖለቲካ አባልነት ሳይለዩ በአንድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ድርጅት ውስጥ በመሰባሰብ ወያኔን ለመታገል፣ ከመንግስት የፖለቲካ ስልጣን ውጭ ካሉት የዘር ድርጅቶች ጋር ለመደራደርና እንደ አማራጭ ለመቅረብ ቢችሉ የሚጠቅምና የሚመረጥ ይሆናል።
ሁለተኛ፡ የዘር ድርጅቶች የትግሉ አካል እንዲሆኑ መጣር ያስፈልጋል
ይህ አዲስ ሀሳብ አይደለም፣ ያልተጀመረ ሙከራም አይደለም። በዚህ ረገድ፣ድርጀት ለድርጅት ውይይት ለጀመሩትና አንዳንድ ትብብሮችን እያሳዩ ላሉት የፖለቲካ ኃይሎች፣ ማለትም ለግንቦት 7፣ ለኦነግ፣ ለኦብነግ፣ ለአፋር ድርጅትና ተባባሪ ለሆኑት ሌሎችም ያለኝን ምስጋናና አድናቆት ለመግለጥ ይፈቀድልኝ። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የዘር ድርጅቶችን፣ በተለይም ኦነግን፣ እንደ ፀረ-አንድነትና እንደ ጠላት በመፈረጅ፣ ምናልባት ወንዝ ለማታሻግር ትንሽ ጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ለመሸመት ባዶ የመግለጫ ጋጋታና ፍሬ-ቢስ ጫጫታ የሚረጩ እንዳሉ መገንዘብ ይበጃል። በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሕዝብ መሀል ጥላቻን የሚዘሩና በድርጅቶች መሀል ሊኖር የሚችለውን መግባባትና መተባበር ለማደፍረስ የሚያከሄዱት ኃላፊነት የጎደለው ተግባራቸውም ሊጋለጥ ይገባል።
(ሀ) አደብ ይገዛ
በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ድርጅቶችንና ድርጅቶቹ እንወክላቸዋለን የሚሏቸውን ዜጎች ያላካተተ እንቅስቃሴ ከጅምሩ የከሸፈ ሙከራ ይሆናል። የዘር ድርጅቶች ትግላቸውን የጀመሩባቸው ታሪካዊ ምክንያቶች እንዳሏቸው አለመግንዘብና እንኝህን የዘር ድርጅቶች የመግፋትና የመተንኮስ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ አንድነት ከሁሉም የባሰ አደጋን ያረገዘ ቀቢፀ ተስፋ ፖለቲካ መሆኑን መረዳት የግድ ይሆናል። አሁን፣ በዚህች ሰዓት፣ ይህችን ጽሁፍ በምናነብባት ሰዓት እንኳን፣ ወያኔ በኢትዮጵያ መንግስትነት፣ ሲያስቡት የሚሰቀጥጥ ግፍና ጭቆና፣ ግድያና ማፈናቀል በኦጋደን፣ በጋምቤላና በኦሮሚያ ውስጥ ባሉ ወገኖቻችን ላይ እያካሄደ ባለበት ሰዓት፣ ረሀብንና ምግብን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ በሕዝባችን ላይ እየተጠቀመ በዜጎች ስቃይ እየተደሰት በሚገኝበት ሰዓት፣ ሳይቸግር የዘር ድርጅቶችን ማውገዝና በጠላትነት መፈረጅ የዘመኑ ታላቅ የፖለቲካ ክስረት ከመሆኑ ሌላ የጨካኝ አረመኔ ባህሪይ ሆኖ ይታያል።
ለመሆኑ፣ በመጀመሪያ ደረጃ፣ እነኝህ “በኢትዮጵያ አንድነት” ስም ይህንን ያህል የዘር ጥላቻ የሚነዙ ከፋፋይ ኃይሎች ዛሬ ማን ሆነው ነው፣ ዬት ቆመው ነው፣ ማንን ይዘው ነው የዘር ድርጅቶችን እንዋጋቸዋለን የሚሉት? ለአገር አስባለሁ የሚለው ወገን እውነት ለአገር አሳቢ ከሆነ በመጀመሪያ የራሱን ድርጅታዊ ድርሻና አቅም ከነዚህ ሁሉ የዘር ድርጅቶች ጋር አነጻጽሮና አወዳድሮ ይመለከታል፤በዚያም የሚናገረውን ይመጥናል፤ የሚጽፋቸውና የሚያስተላልፋቸው መልእክቶች በሕዝበ የወደፊትና የዛሬ ህይወት ላይ ምን የፖለቲካ ውጤት እንደሚኖራቸው ይመረመራል፣ በዚህም ኃላፊነትን ይወስዳል።
እስቲ ስለ እውነት እንጠይቅና ከእነኝህ ድርጅት ኮናኞች ውስጥ ዬትኛው “የአንድነት ኃይል” ነው፣ ዛሬና ወደፊት፣ ይህን የሚቀፈቅፈውን የጠላትነት አቋሙን ይዞ ኦሮሚያና ኦጋዴን ተብለው በተከለሉ ግዛቶች ውስጥ ሄዶ ለማደራጀት፣ ለመመልመል ለማስታጠቅና የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ የሚችለው? ምነው ሁኔታዎችን ቢለዩና የሚናገሩትን ቢያውቁ፤ ምነው አቅማቸውን ቢመዝኑና አደብ ቢገዙ።
(ለ) መከባበር፣ መነጋገርና መተባበር ይጀመር
ወያኔ የሁሉም ጠላት ነው። በእርግጥ አማራን ግን ከሁሉ አብልጦ ይጠላል። ሌሎች ዘሮችን የሚወድ ከመሰለ እስከጠቀሙትና እስካልተፎካከሩት ብቻ ነው። ዛሬ ተነስቶ ሀረሬዎችን ወይም ሲዳማዎችን ወደድኩ ካለ፣ እነርሱም ከርሱ ጋር አብረው ሌሎችን እስከጠሉለት ድረስ ብቻ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ዛሬ ከኦነግ ወይም ከኦብነግ ጋር ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ ለመደራደርና ለመተባበር እፈልጋለሁ ካለ የጨነቀው ነገር ወይም ያሰበው ተንኮል አለ ማለት ነው። ስለዚህ፣ ማንኛውም ድርጅት ለዚህ ተልካሻ የወያኔ ሽረባ መውደቅ ያለበት አይመስለኝም። በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች፣ በተለይም በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በኦጋዴን፣ በጋምቤላና በሌሎች ቦታዎች የፈጸማቸው ፀረ-ሕዝብ ፍጅቶቹ ትምህርት የሚሆኑ ከሆኑ። ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎችና ዘሮች፣ ትግሬዎችንም ጨምሮ፣ የጋራ እድልና እጣ-ፈንታ ነው ያላቸው። ሁሉም ድርጅቶች፣ የዘር ይሁኑ ዘር-አቀፍ፣ የጋራ እድልና እጣ-ፈንታ ነው ያላቸው። ካለው መዓት ለመውጣት፣ የባሰ እልቂት ውስጥ ላለመግባት፣ ድርጅቶች በሙሉ በጋራ እንደ አንድ ሰው ለመንቀሳቀስ መቻል ይኖርባቸዋል።
ለመተባበር መነጋገር ያስፈልጋል፣ ለመነጋገር መከባበር የግድ ይሆናል። የአገራችንና የሕዝባችን እድል ሆኖ ድርጅቶቻችን፣ እንኳን በጋዜጣዊ መግለጫ ተወጋግዘውና ተዛዝተው፣ መሪዎቹ ብቻ በጎን ዓይናቸው የጎሪጥ ከተያዩ፣ አዲዮስ፣ ድርጅታዊ ጠላትነት ለዘላለም ይሰፍናል፣ ሕዝብ ለጭዳነት ይቀርባል። ይህ ነው የድርጅቶቻችን ታሪክ፣ ዛሬም ሲደገም የምንታዘበው። ለዚህ ነው፣ ሕዝባችን የዚህ የአለመተባበርና የጠላትነት አባዜ የተጠናወታቸውና ምንም የመሪነት ብቃት የሌላቸው የንዑስ አምባገነኖች እዳ ተሸካሚዎች መሆን የሌለባቸው። ሕዝባችንና በሀቅ ለአገርና ለሕዝብ የሚታገሉ የድርጅት አባሎች እንደዚህ ዓይነት ሰንጣሪና ከፋፋይ መሪዎችን አስወግደው ውህደትና ትብብር በድርጅቶች መሀል እንዲፈጠር መታገል ይጠበቅባቸዋል፣ የመከራ ዘመኑን ለማሳጠርና የተዘጋጀላቸውን የወደፊት እልቂት ለማክሸፍ ከፈለጉ። ይህ ትግል ዘርን አይለይም፣ የድርጅት መልክና ዓይነት አይመለከትም። በጋራ የሁሉም ሀላፊነት ነው። ይህንን የማይረዱና ሕዝብንና ድርጅቶችን የሚለያዩ ከወያኔ ያልተናነሱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች ናቸው።
ሐ፡ ኦነግና ኦብነግ ላይ ልዩ ትኩረት ይደረግ
ኦነግና ኦብነግ የሚወስዱት የፖለቲካ አቅጣጫ በኢትዮጵያ የአንድነት ጥያቄ ላይ ዛሬ ቁጭ ብለን ልናስበው ከምንችለው በላይ ጥሩ ወይም መጥፎ ውጤቶችን ሊያስከትል ይችላል። እንኝህ ሁለት ድርጅቶች ችግሮቻቸውን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነን ለመፍታት እንችላለን ብለው ካሰቡና ለዚያም በሀቅና በቀጥተኝነት ከሰሩ የኢትዮጵያ አንድነት ትግል መሰረታዊ ማረጋገጫ ያገኛል። ይህ ሲሆን፣ ወያኔ ትግራይን ገንጥሎ ውጫዊ ጦርነትን በጎንደርና በወሎ ዙሪያ ሊያካሄድ እንደሚሞክር ከግምት ውስጥ ሳናስወጣ። በአንጻሩ ደግሞ፣ የለም፣ እኛ ኦሮሚያና ኦጋዴን ተብለው አሁን ተከልለው ያሉትን ቦታዎች ከኢትዮጵያ ገንጥለን ነጻ መንግስቶች እንመሰርታለን ብለው ወታደራዊ መፍትሄ ብቻ ከፈለጉ ሊከተል የሚችለው የሕዝብ እርስ በርስ መተላለቅ ብቻ ይሆናል። ወያኔ ደግሞ ይህ እንዲሆን ከማድረግ እንደማይመለስ ለመገመት ካቃተንና ከወዲሁ ምኑንም ሳንጨብጥ እነኝህን “አገር ከፋፋዮች እንዋጋቸዋለን” እያልን በባዶ ብንፎክር ከግምት ላይ ይጥለናል፣ ልናደርገው ስለማንችል።
ካሁን ቀደም እዚህ ላይ በጠቀስኩት ንግግሬ ውስጥ ኦሮሞዎች ለኦነግ ያላቸው ድጋፍ የተጋነነ ነው ቢባልም፣ አሁንም አብዛኛው የኦሮሞ ተወላጅ ኦነግን ይደግፋል ብዬ አምናለሁ። ኦነግ በቦታው ላይ ሳይኖር፣ ለኦሮሞ ዜጎች ምንም የረባ ነገር ሳያደርግ፣ ዛሬ ወያኔ በሚፈጽምባቸው ግፍና መከራ ብቻ አንድ ቀን “አቢኦ” (ኦነግ ማለት ነው በኦሮሚፋ) መጥቶ ነጻ ያወጣናል የሚሉ የኦሮሞ ተወላጆች በቀላል የሚቆጠሩ እንዳልሆኑ ብዙ ታዛቢዎች ይናገራሉ። በዚህ የወያኔ የግፍና የመከራ ዘመን፣ ማንም በለስ የቀናው ጫካ ቢገባና ጥይት ለመተኮስ ቢችል ሊያገኘው የሚችለውን የሰው፣ የወታደራዊና የገንዘብ እርዳታ ለመገመት አለመቻል የአስተሳሰብ ድክመትን ብቻ ነው የሚያሳየው። ኦነግ የራሱን ውስጣዊ ችግር ተወጥቶና ከኤርትራ ቁጥጥር ራሱን አላቆ ብዙ ጊዜ ቃል የሚገባውን የትጥቅ ትግል ከጀመረ በአገራችን ውስጥ የፖለቲካ ጨዋታውን የሚለውጥ ግዙፍ የፖለቲካ ኃይል እንደሚሆን አልጠራጠርም። ወያኔ አሁን ባለው መልኩ ለመግዛት ካቃተውና አገሪቱን ወደ መቆራረስ ዓላማው ከዞረ ለኦነግ የሚፈጠሩት የፖለቲክ እድሎች ወሰን አይኖራቸውም። ስለዚህ፣ ወደድነውም ጠላነው፣ ከኦነግ ጋር መነጋገርና መተባበር በሳልነት ነው፤ የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት ለመጠበቅም ቀላሉና አስተማማኝ መንገድ ይኼው ብቻ ነው፤ ኦነግንና ኦብነግን አስረናቸው ወይም ደብድበናቸው ልናመጣቸው ስለማንችል።
መ፡ AFD አይደገም
ይህ ከኦነግ ጋር መነጋገርና መተባበር የሚባል ነገር ሲነሳ፣ አንዳንዶች የሚያመለክቱት ካሁን ቀደም በቅንጅት፣ በኦነግ፣ በኦብነግና በሲዳማ ድርጅቶች መሀል ለአጭር ጊዜ ተመስርቶ ስለነበረው ስምምነት (AFD በመባል ስለሚታወቀው) ነው። ይህ ሆን ተብሎ ነገሮችን ለማጣመምና ዋናውን የውይይት ርእሱን ለማሳት ካልሆነ በስተቀር፣ በዋና ተቃዋሚነት አደባባይ ወጥተው ከተከራከሩት መሀል አንዱ እኔው እራሴ ነበርኩ። ይህንን ተቃውሞዬንም ደግሞ ሁሉም የኦነግ መሪዎች ያውቁታል። የተቃውሞዬ ዋና ምክንያቶች አራት ነበሩ። (1) በዚያን ጊዜ ጠርቀም ያለ የአንድነት ኃይሎችን ይዞ ይንቀሳቀስ የነበረውንና እኔም የምደግፈውን ኢዴኃህን ያገለለ በመሆኑ፣ (2) የስምምነቱ ዶኩመንት (Memorandum of Understanding) በምንም መልኩ ኢትዮጵያን የማይጠራና የኢትዮጵያኖች ይሁን የሌላ አገር ድርጅቶች ስምምነት መሆኑ የማይታወቅ በመሆኑ፣ (3) ድርጅቱን ለመቆጣጠር አስፈላጊ የሆኑትን ዋና ዋና ቁልፍ የስልጣን/ሀላፊነት ቦታዎች በሙሉ በኦነግ ብቻ በመያዛቸውና (4) የስምምነቱን ዝግጅትና ሂደት በሙሉ ይቆጣጠር የነበረው የኤርትራ መንግስት በመሆኑ ነው። ዛሬስ፣ ይህንን የሚመስል ሁኔታ አለ? እኔ እስከማውቀው ድረስ ተቀራርቦና ተከባብሮ መነጋገርና አንዳንድ ሕዝባዊ ፕሮጀክቶችን አብሮ የመከወን እንጂ የተፈራረሙት የትብብር ውልና ስምምነት (AFD 2 እያሉ አሁን ሌሎች የሚጠሩት) የለም፣ቢያንስ እኔ ያዬሁት ነገር የለም። AFD እንደገና በሌላ መልኩ ተመልሶ ቢመጣስ ዝም ብለን አጨብጭበን እንቀበለዋለን? ድርጅቶቹም ካለፈው የAFD ውጤት የተማሩ ይመስለኛል፤ አይደግሙትም ብዬ እገምታለሁ። እኔንም ከድሮ አቋሜና አመለካከቴ የሚነቀንቀኝ አንዳችም የተለወጠ ነገር የለም። ለኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት፣ ለሕዝቧ ተፋቅሮ፣ ተካባብሮና ተፈቃቅዶ በእኩልነት አብሮ መኖር ያለኝ ጽኑ አቋም እየጠነከረ ይሄድ እንደሆን እንጂ የሚያላላው አንዳችም ነገር የለም። ይህ አቋም ደግሞ በስሜት ብቻ የተገፋ ሳይሆን በተቆራረሰች ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም በሰላም ለመኖር ስለማይችልና በእርግጠኝነት የሕዝብ እልቂት ሊከተል እንደሚችል ስለሚገባኝ ጭምር ነው። ስለዚህ፣ ኦነግ ብቻ በበላይነት የሚመራው ትብብር ከአነሳሱ የከሽፈና የሕዝባችንን ትግል ወደኋላ መልሶ የሚወረውር የተሳሳተ የፖለቲካ እርምጃ ይሆናል፤ አጥብቀን ልንከላከለውና ልንታገለው የሚገባ የትግላችን ዒላማም ይሆናል።
ሦስተኛ፡ የወጣቶችንና ሌሎችን የብዙሀን እንቅስቃሴዎችን መደገፍና ማስፋፋት
አሁን በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ስለተጀመረ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሁሌ የለውጥ መሪዎችና አርበኞች ስለመሆናቸው ታሪክ የመዘገበው የአገራችን እውነታ ነው። ደርግና የወቅቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ባስከተሉት ጨለማ የሽብር ዘመን የወጣቶች እንቅስቃሴ ለተወሰነ ጊዜ ተዳፍኖ ቢቆይም፣ በተለይ ከወያኔ ስልጣን መያዝ በኋላ የኢትዮጵያ ወጣቶች በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ መስዋእትነትን እየከፈሉና የወያኔን ፀረ-ኢትዮጵያ እርምጃዎች በተከታታይ እየተፋለሙ መሆናቸውን እየታዘብን ያለን ይመስለኛል። የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊና ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለማስገንጠል ከአቶ መለስ ዜናዊ ቀጥሎ ከፍተኛውን ሚና ከተጫወቱት ውስጥ አንዱ የነበረው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ በ1993 ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣትና ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት ያላቸውን ቁርጠኛ ታማኝነት በመግለጽ ውድ ህይወታቸውንና አካላዊ ጉዳት የከፈሉት፣ እንዲሁም ለስደት የተዳረጉት የኢትዮጵያ ወጣቶች ናቸው። ከዚያም፣ ወያኔ በ2005 ምርጫ ተሸንፎ በጉልበት የሕዝብን ድምጽ ሰርቆ አሸንፌአለሁ ሲል፣ የለም፣ የሕዝብ ድምጽ ይከበር ብለው ለፋሺስታዊው አግዓዝ ቅልብ ጦር የጥይት እሩምታ እራሳቸውን አጋልጠው የሰጡት የኢትዮጵያ ወጣቶች ናቸው። ዛሬም፣ ለቀጣዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነትና አገራዊና ብሄራዊ አንድነት በቁርጥ ለመሰለፍ ቆርጠው የተነሱና ለዚህም የኢትዮጵያ ብሄራዊ የወጣቶች እንቅስቃሴን ያውጁት የኢትዮጵያ ወጣቶች ናቸው።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ኃላፊነት ለመቀበልና ለመታገል እራሳቸውን አላቀረቡም የሚባለው ውንጀላ ዛሬ ሀሰት ነው። በዘግናኙ የወያኔ እስር ቤት ብዙ እንግልት የደረሰባትና ለመገመት የሚያቅተንን እዳ የከፈለችው ታላቅ መሪያችንና የመብት ተሟጋች የሆነችው ዳኛ ብርትኳን ሚዴቅሳ ወጣት ናት። አንዱ የአንድነት ለዴምክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌና በርካታ ሌሎች የአመራር አባላት ወጣቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ እንቅስቃሴ መሪ አቶ ማስረሻ ጥላሁንና ተባባሪዎቹ ወጣቶች ናቸው። ብዙዎቹ የግንቦት 7 መሪዎችና አባላት ወጣቶች ናቸው። በርካታውን የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች ተግባሮች የሚያቀናጀውና ሌት ተቀን ደከመኝ ሳይል የወያኔ የውስጥ እግር እሳት የሆነው ታጋይና አታጋይ ነዓምን ዘለቀ ወጣት ነው። የተለያዩ ድረ-ገጾችንና የሬዲዮና የተሌቪዥን ፕሮግራሞችን በማዘጋጀትና በመምራት ለሚደረገው ትግል አቅጣጫ እየሰጡና እየመሩ ያሉት እንደ አበበ ገላው፣ አበበ በለው፣ ሲሳይ አጌና እና ብዙዎች ስማቸውን ዘርዝሬ ለመጨረስ የማልችላቸው ብርቅ የኢትዮጵያ ወጣቶች በየቦታውና በየትግሉ ዘርፍ ይገኛሉ። ዛሬ፣ ለወጣት መሪዎች ችግር ሆነው ያሉት ለዓመታት በድርጅት የመሪነት ቦታ ላይ ካረጀው አመለካከታቸው ጋር ሙጭጭ ብለው የቀሩት አዛውንቶች ናቸው። ጊዜው የወጣቶች ነው፣ ችግሩን በውል የሚረዱትና ከጊዜው ጋር ሊሄድ የሚችለውን መፍትሄ ለማምጣት የሚችሉትም ወጣቶች ናቸው። ስለዚህ፣ ፈቀቅ ማለትና ቦታውን ወጣቶች እንዲይዙት ማድረግና መርዳት የኢትዮጵያን አንድነት ማረጋገጥ ነው። ወጣቶች ያለፈው የፖለቲካ ጉድፍና የቂምና ጥላቻ ተሸካሚዎች አይደሉምና።
እንዲሁም፣ ይህንን የወያኔ ስርዓት ለመጣል “በቃ” ብለው ለክተት የተነሱ ወገኖችም እንዳሉ ለማወቅ ችያለሁ። በተለያዩ ቦታዎች የአገራቸውን የፖለቲካ ሁኔታ ለመቀየር በተለያዩ የብዙሀን ማኅበራት መልኮች እየተሰባሰቡ ያሉ ኢትዮጵያኖች እንዳሉ አውቃለሁ። እንኝህን በርካታ የብዙሀን ማኅበራትን ደግሞ በአንድ ጥላ ስር ለማሰባሰብ የሚጥር ቀደም ብሎ የተፈጠረና በርካታ አገራዊ ጉዳዮችን ሲያከናውን የቆየ (የፖለቲካ ድርጅቶችን የማሰባሰብ ሙከራዎችን ጭምር) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ጉባኤ (ኢሀጉ) የሚባል እንቅስቃሴም እንዳለ አውቃለሁ። እነኝህ ሁሉ የሚያበረታቱና ተስፋ የሚሰጡ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ናቸው።
አንድ ቀን ከአንድ የልብ ወዳጄ ጋር ስለምናያቸው የድርጅቶች ችግር ስንጫወት፣ “ላምባ ያለቀበት ኩራዝ በምን ይበራል?” ብሎ ጠየቀኝ። “በክሩ ወይም በጨርቁ” አልኩት። መልሶ፣ “ምን ይወጠዋል?” ብሎ ሲጠይቀኝ፣ “ጪስ” ብዬ መለስኩለት። “አዎ፣ ከሚሰጠው መብራት፣ የሚተፋው ጪስ ያፍናል፤ የድርጅቶቻችን ሁኔታም እንዲሁ” አለኝና ምን ጊዜም የማልረሳውን ትምህርታዊ ጥቅስ ሰጠኝ፣ እጅግ አመሰገንኩት፣ አከበርኩት። አሁን ባለንበት ሁኔታ አንዳንድ ድርጅቶቻችን ከሚሰጡት ጥቅም የሚፈጥሩት እንቅፋት ይበልጣል። አዳዲስ አባላትን ለመመልመልና ለማደግ አለመቻላቸው አንሶ፣ ከነርሱ ጋር ሆኖ በቀና ለአገሩና ለሕዝቡ ሊታገል ወስኖ በነበረው ወገን ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተጽእኖ የበለጠ እየጎዳ መጥቷል። እራሳቸውን አሻሽለው እንደመቅረብና የትግል አጋር እንደመሆን፣ ከነርሱ ውጭ ያለውን እንቅስቃሴ በሞላ (ሕዝባዊ ይሁን የፖለቲካ ድርጅት) በቅናት በመመልከት ለማደናቀፍ ይጥራሉ፣ ቅራኔና ጥላቻን በመፍጠር የኢትዮጵያን ሕዝብ የነጻነት ትግል ክፉኛ ያዳክማሉ። ስለዚህ፣ ከእንደነዚህ ዓይነቶቹ አሉታዊ ኃይሎች ውጭ ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉትን የብዙሀን ማኅበራትንና ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን መደገፍና ማጠናከር የኢትዮጵያ አንድነትን ለማረጋገጥ ከሚደረጉት ዘርፈ-ብዙ የትግል ሙከራዎች አንዱ ይሆናል።
ማጠቃለያ
አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ ለኦነግም ለኦብነግም ትጠቅማለች
እኔ፣ በኦነግ ውስጥ ብዙ የሚያበረታቱ ለውጦችና እድገቶች እንዳሉ ይታየኛል። አዲስ አመለካከት፣ አዲስ ራእይ፣ አዲስ የኃይል አሰላለፍ እየመጣ መሆኑን እሰማለሁ፣አያለሁ። የኦሮሞን ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ በሆነች ኢትዮጵያ ውስጥ ለመፍታት ይቻላል የሚል አመለካከት እየሰፋና እያደገ መጥቷል። አስተዋይ አንባቢ አቶ ኢብሳ ጉተማ In Defense of Bilisummaa ብለው በቅርቡ በበተኑት ጽሁፍ ውስጥ ይህንን ለማዬት ይችላል። ለውጥ ጊዜንና ሁኔታን ይጠይቃል። ለዚህ ለውጥ ጎላ ብሎ መውጣትና ዋነኛው የኦነግ የፖለቲካ መስመር ሆኖ መገኘቱን ለማዬት ሰከን ሰብሰብ ብሎ አደብ ገዝቶ ሳይዘናጉ መጠበቅ ያስፈልጋል። በኦነግ በኩል አሁን የተሻለ ሁኔታ እየመጣ ባለበት ሰዓትና ለመተባበር ቀዳዳና እድል ሲገኝ ስድብን፣ ትንኮሳንና ባዶ ኩፈሳን (posturing) ምን አመጣው? ተስፋ የቆረጠ የስድብ መግለጫ የሚያስወጣስ ምን አዲስ ብሄራዊ ክስተት ከኦነግ ጋር ተያይዞ ተፈጠረ? እፍኝ የማይሞሉ አባላትን ይዞ እንዲያው አለን አለን ለማለት ካልሆነ፣ ለዚያውም አገራዊ አንድነትን ለባሰ አደጋ በሚያጋልጥ መልኩ።
የኢትዮጵያን አንድነት የሚሻ ሀቀኛ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦነግ፣ የኦብነግና የሌሎች ኢትዮጵያዊ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች አባላት በጋራ የሚያከናውኗቸውን ሕዝባዊ ክንዋኔዎች እያደነቁና እያመሰገኑ ይገኛሉ። ካሁን ቀደም፣ ምናልባት ከአንድ አራት ወራት በፊት፣ በዚህ በውጭ አገር የጋራ ጠላታቸው የሆነውን ወያኔን እንኳን በጋራ ሆነው አብረው በዝተው ደምቀው ለመቃወም አይችሉም ነበር። የኦነግና የኦብነግ አባላት የየግላቸውን ባንዲራዎች ይዘው በአንድ በኩል፣ ሌሎች ኢትዮጵያኖች ደግሞ የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዘው በሌላ በኩል፣ አንድነት አጥተው፣ የጎሪጥ እይተያዩ፣ አንዳንዴም እየተሰዳደቡና እየተገፈታተሩ ሲጮሁ ይታዩ ነበር። አሁን ግን ይህ መጠላላቱና መራራቁ ቀርቶ፣ ሁሉም በጋራ አብረው ደምቀውና ጎልተው፣ ወያኔን ሲያስጨንቁ ስናይ የኢትዮጵያን አንድነት በጋራ የማስጠበቁ ጉዞ የተጀመረ ይመስላል።
አዎ፣ የዘርና የኢትዮጵያ ባንዲራ እኩል ጎን ለጎን ሲታዩ ደስ የማይለን አንዳንድ ሰዎች ልንኖር እንችላለን። ነገር ግን፣ እስቲ ቆም ብለን እራሳችንን እንጠይቅ። እንደ ድሮው ተለያይተንና አንሰን ከየባንዲራችን ጋር መታየቱ ነው ወይስ ሁሉንም ባንዲራ በአንድነት ይዘን አብረን ደምቀንና ጎልተን መታየቱ ነው የሚሻለው? እኔም እንደናንተው አንዳንዴ ካለብን ፍራቻና ጭንቀት ስነሳ፣ አይይ፣ እንዲያው ምናለ ሁላችንም በአንድ ባንዲራ (አሬንጓዴ ብጫ ቀይ) ስር ብቻ ብንሰባሰብ ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን፣ ሌላኛው፣ እኔም የራሴ የሆነ ባንዲራ አለኝና ያንተን ሳልቃወም የራሴን መያዝ መብቴ ነው ካለኝ እኔ እርሱን የመከልከል መብት ይኖረኛል? ቅር ልሰኝበትስ ይገባኛል? አይመስለኝም። ብዙው ችግር የሚፈጠረው ለመከልከል ስንሞክር ነው፤ ላንተ የሚሻለውን እኔ ነኝ የማውቅልህ፣ የምወስንልህ ስንለው። የዘር ጥላቻንና መለያዬትን ከመጀመሪያውስ የፈጠረው ይህ ዓይነቱ አስተሳሰባና አስተዳደር አልነበረምን? እስቲ እዚህ ያለንበትን አገር እንደ ምሳሌ እንውሰድና የጣሊያን፣ የአየርላንድ፣ የግሪክ፣ የፖሊሽ … ተወላጆች፣ የኮሩ አሜሪካኖች ሆነው፣ አንዳንድ የየራሳቸውን ብሄራዊ በዓሎች ይሁን ማህበራዊ ተግባሮችን ሲያከናውኑ የየአገራቸውን ባንዲራ ያወጣሉ፣ በርግጥ ከአሜሪካ ባንዲራ ጎን። እኛም እንዲሁ። አሁን፣ እኔን ደስ የሚለኝ በጋራ በአንድ ቦታ ላይ መገኘታችንና መተባበራችን ነው። በዚሁም ልዩነቶቻችንና አንድነቶቻችንን እናከብራለን፣ መልካም ባህል ይሆነናል ለወደፊቱም። እንዳትረሱ፣ እዚህ በአሜሪካ ውስጥ ስቴቶች (ግዛቶች) ከአሜሪካው ባንዲራ ጎን የየራሳቸው ባንዲራዎች አሏቸው። ይህ አሜሪካዊነታቸውን አልቀነሰም፣ ወይም የአሜሪካንን ብሄራዊ አንድነትና ስምምነት አልጎዳም። በኢትዮጵያ ባንዲራ መደሰትና መኩራት አንድ፣ በሌሎች ባንዲራዎች መከፋትና የሌሎችን ምርጫ ማፈን ግን ሌላ።
የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መሞከር በእርስ በርስ ጦርነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ማጫረስ ብቻ እንደሆነ ባንድ ወቅት በነበረኝ የምክክር ስብሰባ እድል አግኝቼ ለኦነግ አመራር አባላት ገልጬ ነበር። በውል የተከለለና የታወቀ የዘር ክልሎች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ብዬ አላምንም። ለዚህ ነው በ1993 የቻርተር መፈረሚያ ወቅት ሁሉም የዘር ድርጅቶች ክልላችን ይህ ነው ብለው ያቀረቧቸው ካርታዎች በአንድ ላይ ሲደመሩ የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ሦስት ጊዜ መስፋት ነበረበት ሁሉንም ለማቻቻል ከተፈለገ። ይህ ማለት፣ አንዱ የኔ ክልል ነው የሚለውን ሌላኛውም የኔ ነው ይላል ማለት ነው። ለዚያውም፣ ይህ ሁሉ የክልል ቅርሚያ ሲደረግ ያልተወከሉና ያልተሳተፉ ወገኖች (ለምሳሌ አማሮች) እያሉ ነው። እንግዲህ፣ አሁን ኢትዮጵያን በዘር ክልል እንቀረማመታት ቢባል ውጤቱ ምን ሊሆን እንድሚችል መገመት ነቢይነትን የሚጠይቅ አይመስለኝም። እንኝህም የተሰጣቸውን ብቻ ተቀብለው እስካሁን ያሉትም እኮ የኔ ድርሻ ይኼ ብቻ አይደለም ሳይሉ አይቀሩም ብዬ እጠረጥራለሁ።
ለዚህ ነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስባለሁ የሚል የፖለቲካ ኅብረተሰብ ይህንን የኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄ በታላቅ ጥንቃቄ መያዝ የሚኖርበት። እንኳን በወታደራዊ መፍትሄ፣ በመግባባትና በመተባበር የተደረገው የኤርትራ ግንጠላ ውጤቱ ምን እንደሆን በዓይናችን አይተናል። ያለቀውንና የተፈናቀለውን ሕዝብ ቆጥረናል። ይህንን እንደገና፣ ለዚያውም በላቀ ደረጃ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ደግመን ማምጣት ጨካኝነትና ፀረ-ሕዝብነት ነው። ማንም ሕዝብ፣ ኦሮሞ ይሁን አማራ፣ ሶማሌ ይሁን ትግሬ … ከዚህ የሚያገኘው ጥቅም የለም። ለዚያውም፣ በዚያ ንግግሬ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጥኩት ለዘር ድርጅቶችና እንቅስቃሴዎች መነሳት ምክንያት የነበሩት የኤኮኖሚና ባህላዊ ምክንያቶች በተወገዱበት ጊዜ። ይህ የጦርነት እልቂት አደጋ ሕዝባችንን እንዳይጎብኝ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ አንድነት የሚሉ እውነተኛ የፖለቲካ ኃይሎችና የዘር ድርጅቶች መከባበር፣ መነጋገር፣ መተባበርና መስማማት ካሁኑ መመጀመር አለባቸው።
ደስ የሚለው ነገር፣ ይብዛም ይነስ፣ የዚህ የትብብር ባቡር ጉዞውን ጀምሯል፣ ለዚያውም በመሰረታዊ የሕዝብ ግንኙነት (grass-root) ደረጃ። እዚህ ቨርጂኒያ ውስጥ ካደረግነው ሌላ ሰሞኑን በአውሮፓ ከተማዎች የተካሄዱትን የኦነግ፣ የኦብነግ፣ የአፋር፣ የግንቦት 7 ስብሰባዎችን ተመልከቱ። የሰዎችን አቀባበልና ደስታ ልብ በሉ። ይህ ደግሞ ወዴት ሊወስድ እንደሚችል ገምቱ። ይህንን የጋራ ጥረት በክፉ ዓይን እየተመለከታችህ ያላችሁት አሉታዊ ኃይሎች፣ የባቡሩን ሀዲድ ለመጠምዘዝ ከመሞከር ባቡሩ ላይ ለመሳፈር ሞክሩ፣ ቀይዶ የያዛችሁ ችግር የሚፈቅድላችሁ ከሆናችሁ። ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ለመያዝ ያለው ሀዲድ አንድና አንድ ብቻ ነው፣ የድርጅቶች ህብረት ሀዲድ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!