አይ አንቺ ቤተክርስቲያን!

ይብራለም አማንኤል

“አይ አንቺ ቤተ ክርስቲያን፣ ስንቱ ይቀበርብሻል” ነበር ተረቱ:: ታዲያ እንደማስታውሰው ይሄ የተባለው በሀገራችን በኢትዮጵያ በየባላገሩ በከተማውም ጭምር ቤተክርስቲያን የማምለኪያም የመቀበሪያም ቦታ ስለሆነች የማታ ማታ የክፉውም የደጉም፣ የወንበዴውም የሕግ አክባሪውም፣ የስስታሙም የለጋሱም፣ የነፍሰ ገዳዩም የመሀሪውም፣ የጎጠኛውም የኢትዮጵያዊውም ገብአተ መሬቱ የሚፈጠምባት፣ የዐለሙ ዕልፈት ማለቂያ፣ መደምደሚያ በመሆኗ ነበር።

ኪዚህ ካለንበት አገር ግን ሁኔታው ለየት ያለ ነው። ቤተክርስቲያን፣ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ) መቀበሪያ ባትሆንም ማምለኪያነቷ ግን ባፈነገጠ መልኩ እንከል እንከል እያለም ቢሆን ያዘግማል ለማለት እደፍራለሁ። በአሁኑ ግዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሔር ጉዳይ እየቀዘቀዘ የገንዘብና፣ የጎጠኝነት (መንደረተኝነት) ጉዳይ እየጋለ እያየለ ከመጣ ሰንበት ብሏል። በአንዳንዱ ቤተክርስቲያንማ ለይቶለት እግዚአብሔር በፍቅረ ነዋይ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ በጎጠኝነት፣ በመንደረተኝነት ባፋጣኝ እየተተኩ መሆናቸውን ሳስተውል እንቅልፍ ይነሳኛል።

ክርክሬ ሃሳባዊ ብቻ አንዳይሆንብኝ በዚህ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ካሉት ቤተክርስቲያናት ውስጥ ሶስቱን በተምሳሌነት ወስጄ አጠር ባለ መልኩ መወያያ ባደርጋቸው ለአንባቢ ዕዝነ ልቦና ግቡ ይሆናሉ ብዬ እገምታለሁ።

በኖርዝ ኢስት ዋሽንግተን ዲሲ ብላደንስበርግ መንገድ ላይ የሚገኙትን የቅዱስ ሚካኤልን፣ ከሱም ቢበዛ አንድ ማይል ርቀት ላይ የሚገኘውን የደብረ ሀይል ቅዱስ ገብርኤልን እና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያንን ብንወስዳቸው የችግሩን ወርዱን ስፋቱን ጥልቀቱንና ቤተክርስቲያናቱንም ባንፃሩ ምንያህል እየናጣቸው እንዳለና ክፉኛ እንዳመረቀዘ ለማሳየት ውብ መንደርደሪያ ይሆናል።

የቅዱስ ሚካኤል ውዝግብ ብዙም ጥልቀት ያለው ትንተና የሚያሻው ሆኖ አልታየኝም። ከጎንና ከጎንም ሆነ ከላይና ከታች የተሰነቀረው ያው መርዘኛ መዘዘኛ የሳንቲም ጉዳይ እንደሆነ በሰፊው ተወርቶለታል። ሌላ ምን ቦቃ አለው ብላችሁ፣ መዋቅሩን ባምቻ በጋብቻ በዘመድ ማደራጀት አይደል? አሱን ደግሞ ከመነሻው አስበው አስልተው፣ ሌላው እምነቱን አምላኩን ሲያስብና ሲያገለግል እነሱ በእምነት መዘናጋቱን ልቡ ወደ አምላኩ ብቻ መሆኑን አይተው ሳይነቃ አስፈረዱበት! የቤተክርሰቲያን መሪነት ሥራ ተዝቆ የማያልቅ የወርቅ ማዕድን መሆኑን ከሌላው ቀደም ብለው ተገንዝበው ኖሮ ጥንብ እንዳየ አሞራ ተጠራርተው የመጡበት ጉዳይ ሆነ። የግዜ ጉዳይ እንጂ የተኛ ሁሉ ምንም ቢሆን የማታ ማታ መንቃቱ አይቀርምና የተኛው ሲነቃ ጉዳዩን ሁሉ ፀሐይ መታው፣ አደባባይ ወጣ። ፍቅረ ንዋይ ያመጣውን መዘዝ፣ የፍርድ ቤቱን ውጣ ውረድ፣ በሕዝብ ላብ የመጣውን ገንዘብ ለጠበቃ መዳረጉ በሙሉ ያደባባይ ሚስጥር፣ የቅርብ ግዜ ታሪክ ነውና በሱ አላሰለቻችሁም።

የቅድስት ማርያሙም እንዲሁ መነሻው ፍቅረ ንዋይ ሆነ። እዚያማ ትንንሽ የገንዘብ መሰብሰቢያ ሳጥን በየ ጥጉ ተቀምጧል። ምዕመኑም ከሁለት ተከፍሎ የዕድር አባል የሆኑት ከቤተክርስቲያኑ ወጣ ብሎ በግቢው ውስጥ በድንኳን ያስቀድሳሉ። የእድሩ አመራር ብዙውን የአመራሩን የውስጥ የተጨማለቀ ጉድ ገሃድ በማውጣት ትልቅ ሚና መጫወቱ ይነገርለታል። ብዙ ሰዎች በግል ኑሯቸውን እንደለወጡበት የሚነገርለት ይህ ቤተክርስቲያን ሂሳቡን በተመሰከረላቸው የአካውንቲንግ ድርጅቶች ማስመርመሩን ሰምቻለሁ። ጥፋቱ ግን የሚፈጸመው የተሰበሰበው ገንዘብ ወረቀት ሳይከትበው ለባንከ እይታ ሳይጋለጥ በየሙዳየ ምጽዋቱ አካባቢ በመሆኑ ሃያ አራት ሰዐት ቁጭ ብለው ካልጠበቁት በቀር ሺህ ምርመራ ሊደርስበት የማይችል የፀሀይ ብርሃን የማያገኘው ሸምቆ የሚጓዝ ሚስጥር ነው።

የቅዱስ ገብርኤል ካቴድራልን ጉዳይ ባካባቢው ካሉት ከማንኛውም ቤተክርስቲያን በጣም የተለየ የሚያደርገው የችግሩ መወሳሰብ ነው። ምንም ገዜ ቢሆን በምንም ዐይነት ችግር (ከጦርነት፣ ከተፈጥሮ አደጋ፣ ወዘተ) ውስጥ አንድ፣ ሁለት ሰው ወይም ቡድን ተጠቃሚ እንደሚኖር ምንም ጥርጥር አይግባችሁ። የዚህም ቤተክርስቲያን ጉዳይ እንደዚሁ ነው።

የዚህ ቤት ዝቅጠት በተናጠል እራሳቸውን ችለው በቆሙ ሶስት ጠምዛዛ አሳር የሚያህሉ ችግሮች ላይ የተመሠረተ ነው። የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዘውና የችግሩ ስር ያው ገንዘብ ሲሆን ሁለተኛነቱን የሚይዘው ደግም ጠባብ በሔረተኝነት፣ ጎጠኝነት ወይም መንደረተኝነት መሆኑን በሙሉ እርግጠኝነት ማናገር እችላለሁ። ይኸኛውን ችግር ወደ ሁለተኝነት ደረጃ ያወረደው ያመጣጡ ቅደም ተከተል እንጂ በመርዘኝነቱ የበላይ መሆኑን ከቅርብ ገዜ ወዲህ ከዘረኝነትን አስከፊ ገፅታ ፊት ለፊት የተፋጠጡት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይሰወርባቸዋል ብዬ አላስብም። በሶስተኛ ደረጃ የሚቀመጠው ችግር ደግሞ የስትራተጂክ ፕላን መላው የጠፋበት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሜዳውን መድፈር ተስኖት ከወያኔ ጋር ተጋፍጦ መሬት እነደመቀማት ቤተክርስቲያንን ከምዕመናን ለመቀማትና ምሽግ ለማድረግ በመታገል ላይ ያለ የፖለቲካ ቡድን ነው። የሚያሳዝነውና ልብን የሚሰብረው ጉዳይ ደግሞ ሊነጥቅ የተነሳው የስደተኛው ሲኖዶስን ማዕከል መንበረ ፓትርያርኩን መሆኑ ነው። በስደተኛው ሲኖዶስ አንተዳደርም ያሉ አፈንጋጭ ቤተክርስቲያናት ሞልተው? የተሻለ ህልም የላቸውም? ባቡራቸው እንፋሎቱን ጨረሰ? የመጨረሻ ህቅታውን ተያያዘ መሰል?

በመሠረቱ የቤተክርስቲያኒቱ ምዕመናን ስብጥር ዐይነቱ በርከት ያለ በመሆኑም ይመስለኛል በአንድ ሞገድ መስመር (ዌቭ ሌንግዝ) ለመነጋገርና ለመግባባት በፍጹም ያልተቻለው። ምዕመኑ በደርግ ግዜ በተካሄደው በሕዝብ ለሕዝብ ፕሮግራም ለሕዝብ እስክስታ ለመውረድ መጥተው በግልባጩ በሕዝብ ላይ እስክስታ እየወረዱ ከቀሩት ተወዛዋዦችና በቀይ ሽብር ቀውጢ ዘመን በወጣት ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች ደም የተበከለ ህልውናቸውን በአርበኝነት ካባ ሸሽገው ከሚያጓሩ እመቤቶችና አባወራዎች ጀምሮ ከኢ.ሕ.አ.ፓ እና ሌሎች ሐቀኛ ታጋይች ጋር ተደባልቀው ከየቀዬው ሞፈራቸውን ሰቅለው በገዳሪፍ አቋርጠው በካርቱም ሻይ ቤቶች አገግመው ዋሽንግተን ዲሲ የገቡትን ያጠቃልላል።

ከሐቀኛ ታጋዮች ተመሳስሎ መከራቸውን ሳይቀበል፣ ረሃባቸውን ሳይራብ ሞታቸውን ሳይሞት አሜሪካ የደረሰው ይህ የመጨረሻው ቡድን፣ ወደ ምዕራብ፣ ምሥራቅና ደቡብ ኢትዮጵያ ሳይዘልቅና የእናት አገራችንን ሕብረ ብሔራዊነቷን፣ ሕብረ ቀለማዊና ሕብረ ልሣናዊነቷን ሳያይ ሳያጣጥምና ሳያደንቅ፣ ሰምቶና አይቶ እማያውቀው ባሕል ውስጥ ተዘፈቀ። ታዲያ ምን ያደርጋል፣ የዘህ ቡድን አገባቡ በአካል ብቻ ሆነ ቀረ! አካላቸው ሲዘልቅ ምናባቸው፣ ህልውናቸው፣ እነሱነታቸው እተወለዱበት፣ እትብታቸው እተቀበረበት አገር የማይነቀል መልህቁን ተክሎ እዚያው ተከርችሞ የቀረባቸው ሁልቆ መሳፍርት ናቸው። ለነሱ ምንግዜም ኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ህልውናቸውን አይዘልቀውም! ኢትዮጵያን የት ያውቋታል? የማያውቁት አገር ደሞ አይናፍቅም።

ለዚህም ነው ቤተክርስቲያናቸው ከአሥራ አምስት ዐመታት በላይ ያለምንም ተጠያቂነት በገንዘቡም በንብረቱም ላይ ሲፈልጥ ሲቆርጥ በዘመድ አዝማድ ተከቦ ሲያብጥ ሲያስበጠብጥ የኖረውን የአመራር አካል በተጠያቂነት ለማስጠራት ሲሞከር ጥያቄያቸው ያለምንም ማጣራት ወደ አገር ልጅነት ጥቃት ተመንዝሮ፣ በእውነት ላይ ተመርኩዘው መነሳታቸው የሚነገርላቸውን ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች በጨካኝ የአሉባልታ ሞተሮቻቸው ሊፈጯቸውና ሊያጠፏቸው ተነስተው የነበረው። በነዚህን መሰል ምዕመናን የተሞላው ቤተክርስቲያን ማምለኪያነቱ ቀርቶ ጥላቻ ቢያጠላበት፣ ፍቅር ደብዛው ቢጠፋበት ምን ድንቅ ይባላል ። የሚያሳዝነው፣ ታዲያ እንዲህ ያሉ የዓመፃ ጦረኞች እውን እውነቱ ሳይዘልቃቸው ቀርቶ ሳይሆን የኛና የነሱ ሰው በሚሉት ጠባብ ፈሊጣቸው የኛን ወገን ማን ይነካዋል በሚል ጭፍን የግብዝ ድጋፍ ነው። “የማታ ማታ እውነት ይረታ” እንዲሉ እውነቱ የሀስት ጥላ እንዳጠለለበት የሚኖረው ላጭር ገዜ መሆኑን አለመገንዘባቸው ይገርማል።

አሁንማ እንደሚሰማው፣ ህሊናቸው የወቀሳቸው የአመራር አባላት ጥለው ከወጡ በሗላ በስንት ትግል እውን ሊሆን የተቃረበውን ምርጫ እስከ መጨረሻው የሙጢኝ ብለው የቀሩት አባላት ባይ! ባይ! ብለው በፊት ለፊት በር ወጥተው በጓሮ በኩል ተመልሰው ሊገቡ በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ጭምጭምታ ይነፍስ ጀመሯል። እንግዲህ ለማን ያዋያሉ? ማንንስ ያበቅላሉ? የቤተክርስቲያን አገልግሎት ነፃ መሆኑን፣ በላይኛው ቤት በስተቀር በምድር ምንም ጥቅም እንደማያስገኝ ይነገራል። የሚሠሩት ለላይኛው ቤት ከሆነ እስካሁን የሠሩትን እግዚአብሔር ያውቅላቸዋል። እስካሁን ያበረከቱትን ለነፍስ ያድርግላቸው! አለበለዚያ ለእግዚአብሔር ቤት የነፃ አገልግሎት ለማበርከት ይህ ሁሉ ግብግብ ይህ ሁሉ የሞት የሽረት ትግል ለምን እንዳስፈለገ ለሌላው አልተገለፀለትምና ለሌሎችም የኢትዮጵያ ልጆች ቢገልፁልን። አይ ጉድ! አይ አንቺ ቤተክርሲቲያን፣ ስንቱ ይቀበርብሻል?

እህታችሁ ይብራለም አማንኤል