ወያኔ በሽብርተኝነት የከሰሳቸው 6 ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

በታምሩ ጽጌ | ሪፖርተር

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች መካከል፣ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን ጨምሮ ስድስት ተጠርጣሪዎች፣ ከትናንት በስቲያ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው፡፡ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ፖሊስ ጊዜ ቀጠሮ የጠየቀባቸው ስድስቱ ተጠርጣሪዎች፣ ከኢትዮጵያ ሪቪው አዘጋጅ ኤልያስ ክፍሌ ጋር ሲያደርጉት የነበረውን የመረጃ ልውውጥ ተርጉሞ ለማቅረብ ጊዜ ስላልበቃው ነው፡፡

ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሲጠይቅ፣ ስድስቱ ተጠርጣሪዎች የኤርትራ መልዕክተኛ ካለው ከኤልያስ ክፍሌ ጋር በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ኢትዮ ቴሌኮም ተቋማት ላይ ጥቃት ለማድረስ ያደረጉትን የኢንተርኔት የመረጃ ልውውጥ አትሞ መያዙን በማሳየት ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ያቀረበውን የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ተቀብሎ በመፍቀድ ለነሐሴ 9 ቀን 2003 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ካስታወቁዋቸው ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ውስጥ፣ መምህርትና የጋዜጣ አምደኛዋን ርዕዮት ዓለሙን ጨምሮ ሦስት ተጠርጣሪዎች አልቀረቡም፡፡