የአትላንታው ሙቀት
ክንፉ አሰፋ
ጁላይ 1፣ አርብ ምሽት አትላንታ ጆርጂያ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረስኩ እንደቅድሞው ብዙ አበሻ ሲርመሰመስ አላየሁም። የአበሻው ትርምስ በ2005 አትላንታ ላይ ተመሳሳይ ፌስቲቫል በተዘጋጀ ግዜ ከነበረው እጅግ ቀዝቀዝ ብሎ ነበር። ይልቁንም ዝግጅቱ አልቆ አትላንታን ስንስነባበት አውሮፕላን ማረፍያው በአበሻ ተጨናንቆ አሜሪካ ሳይሆን፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ነበር የሚመስለው።
ከአውሮፕላን ማረፍያው እንደደረስኩ፡ አበሻ ወገኔን ሳፈለልግ መውጫው በር አካባቢ አንድ በእድሜ ጠና ያሉ ሰው ላይ አይኔ አረፈ። በቆዳ የተሰራ ሶፋ ላይ ቁጭ ብለው እግራቸውን በዘመናዊ የጫማ መጥረግያ ላይ አሳርፈዋል። ጫማ ጠራጊ (ሊስትሮ) መሆናቸው ነው። አለባበሳቸውም ሆነ መልካቸው ጫማ አስጠራጊ እንጂ ጠራጊ እንኳን አይመስሉም። የኳሱንና የአትላንታውን ሁኔታ ለመጠየቅ ስለጓጓሁ ወደ እኚህ መልከ መልካም አዛውንት አመራሁ። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ፡ ወደጥያቄዬ ገባሁ፡
“ዘንድሮ እንዴት ነው፡ አበሻው በብዛት እየገባ ነው?”
“ለ ሳከሩ (እግር ኳሱ) ማለትህ ነው?”
“አዎ ለእግር ኳሱ”
“ዘንድሮ ብዙ ሰው አላየሁም። ለነገሩ ሰዉ ከሮብ ጀምሮ ነው የሚገባወ። ግን ምን እግር ኳስ አለ ብለህ ነው። ኢትዮጵያና ሶማሌዎች እሱን ትተው፡ ሆኪ ቢጫወቱ ያዋጣቸው ነበር።” ሲሉ ቀልድ ጣል አደረጉ።
የሊስትሮው አባባል ቶሎ አልገባኝም። ረጅም ዱላ ይዞ ውልወላ (ጽዳት) የሚሰራ “ሆኪ ተጫዋች” እንደሚባል የተገነዘብኩት ከቀን በሁዋላ ነበር።
ቅኔው የገባኝ ደግሞ ዘግይቶ ነው። በአንድ በኩል አበሻ ወገኔ ከሃገሩ ሲወጣ ስራ ማክብሩን እና በውጭ ሃገር የስራ ዲሲፕሊን መማሩን ያስተውሏል። ኢትዮጵያዊ በባእድ ሃገር ስራ አክባሪ በመሆኑ ምክንያት ተከብሮ እና ራሱን ቀና አድርጎ እንዲሄድ አድርጎታል። ችግሩ ያለው በማህበራዊ ህይወት፡ በጋራ እና በተደራጀ መልኩ በሚከናወኑ ስራዎች አካባቢ ብቻ ነው።…. አዛውንቱ ሊስትሮ ሊሉኝ የፈለጉትም ይህንኑ ነበር። አበሻ በግል እንጂ በጋራ (ቲም) የተዋጣለት ህዝብ አይደለም። በዚህ ረገድ ፈጽሞ አልታደልንም።
ወዳጅ ከወዳጅ፣ ዘመድ ከዘመድ፣ ሊገናኝ፣ የቤተሰብ ስብስብ እና ቅልቅል፣ ጓደኛ የሌለው ለአዲስ የጾታ ጓደኛ ፍለጋ፣ ነጋዴው ለንግድ ስራ፣ የጥበብ ሰው ስራውን ሊያስተዋውቅ፣ ስፖርተኛው ለዋንጫ፣ ጋዜጠኛው ክንውኑን እና ትዝብቱን ሊዘግብ፡ ወጣቱ ሊዝናና… በየአመቱ ሰሜን አሜሪካ ስቴቶች ይዘዋወራል። የኢትዮጵያውያን ስፖርት እና ባህል የሰሜን አሜሪካ ፌስቲቫል ለበርካታ አዘውታሪዎች እንደ ሱስ ሆኗል።
ዘንድሮ የአትላንታን ሙቀት ከወትሮው ለየት ያለ ሆኖ አግኝተነዋል። የአየሩ ሙቀት ከፍ ከማለቱ የተነሳም ከማቃጠል አልፎ እንፋሎቱ (ሁሚዲቲ) ለመተንፈስም አስቸጋሪ ነበር። ከአየሩ ግለት እንዳለ ሆኖ በሰፖርት ፌዴሬሽኑ ዙርያ ተጋግሎ የነበረው ሙቀትም እንደነበረ ቀጥሎ ነው የሰነበተው።
በፌደሬሽኑ ስራ አመራር እና በቦርድ አባላቱ መካከል የተፈጠረው ውጥረት አጀማመሩ ላይ የረገበ ይምሰል እንጂ እንዲያውም ብሶበታል። ቀርበን እንደሰማነው ቦርዱ በሙሉ ድምጽ አስተላልፎት የነበረው ውሳኔ የስራ አመራር ኮሚቴውን ለሶስት ከፍሎታል።
ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከተው፡ ይኽ የቦርድ ውሳኔ ተግባራዊ ባይሆን ኖሮ ጆርጂያ ዶም ሳምንቱን ኦና ሆኖ ይሰነብት ፡ 28 አመታት ኢትዮጵያውያንን ሲያሰባስብ የቆየው ብቸኛ ተቋምም ዛሬ ፈርሶ እናየው ነበር።
ከቡድኖቹ አንዱ በሼኩ ሰዎች ጥላ አመራር (ሻዶው) የሚመራው አንጃ ሲሆን፡ ሌላኛው የቦርዱ ውሳኔ ይከበር የሚለው የስራ አስፈጻሚ ክፍል ነው። በሶስተኛ ደረጃ ያለው ደግሞ በመሃል የአስታራቂነት ሚና ሲጫወት የነበረው አካል እንደሆነ አስተውለናል። የህዝብ ግንኙነቱ ፋሲል አበበ ማስታረቁ ላይ ከፍተኛውን ሚና ሲጫውት ቆይቶ የኋላ ኋላ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ሲሆንበት፡ ሜዳውን ዳግም ላይመለስበት ተሰናብቶት ሲውጣ ተመለከትን። ከዱላ የተረፈው የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት፡ አብይ ኑርልኝም ተበሳጭቶ በወሳኙ የመዝጊያ ዝግጅት ላይ ሳይገኝ መቅረቱ ችግሩ ምን ያህል እንደከረረ ያሳየናል።
በፕሬዚዳንቱ በመኮንን ደምሴ እና በምክትሉ አብይ ኑርልኝ መካከል የተፈጠረው የማይታረቅ የሚመስል ቅራኔ የዚሁ የቡድን ስሜት ውጤት እንደሆነ ነው የቦርድ አባላቱ የሚናገሩት። ኢትዮጵያኑ ባረፉበት ሆቴል ተፈጥሮ የነበረው የሁለቱ አመራር አባላት ብጥብጥ እና ጸብ ስፖርታዊ ስነ-ምግባርን ፈጽሞ የሚጻረር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ጨዋነትም እንዳልሆነ ይገነዘቡታል። አንዳንዶች ሲቀልዱ በመሃላቸው የገባው በቻርተር አውሮፕላን ተጭኖ ከአዲስ አበባ የመጣ ሰይጣን ነው ይሉ ነበር። የጸቡ መንስኤ ምንም ይሁን ምን አመራር አባላቱ በእንግዶቻቸው ፊት ለጸብ ሲሯሯጡ፡ 28 ክለቦችን ወክለው፣ ከ20 ሺ ህዝብ በላይ በማስተናገድ ላይ ያሉ ስለመሆናቸው ያስተዋሉ አይመሰሉም። በዚህም የተነሳ አጠቃላይ የዝግጅቱ ሁኔታ በትርምስ ተጀምሮ በትርምስ እንዲያልቅ ግድ ሆነ። አንዳቸውም ጨዋታዎች ሆነ ዝግጅቶች በተያዘላቸው ፕሮግራም አልተካሄዱም።
በተለይ የአርቡ የኢትዮጵያ ቀን ዝግጅት በመርሃ ግብሩ ከተያዘለት አምሰት ሰአት በኋላ በመጀመሩ ምክንያት ዘግጅቱ በእጅጉ ተዘበራረርቆ፡ እነግዶችን አማርሮ አልፏል። በዚህ ረገድ የሼኩ ሰዎች ተሳክቶላቸው ሊሆን ይችላል፡ የበአሉን ድምቅት እና ለክብር እንግዳዋ የተደረገውን ሞቅ ያለ አቀባበል ግን ፈጽሞ ሊያስቆሙት አልቻሉም።
ከበርካታ ውጣ ውረድ፡ ከብዙ ግርግር እና አታካራ በኋላ የአትላነታው ዝግጅት መቀጠል ያጠራጠራቸው ኢትዮጵያውያነ ቁጥር ይህ ነው የሚባል አልነበረም። የሼኩ ሰዎች የሰጡትን $240,000 ዶላር እንዲመለስ መጠየቃቸው ተደምሮበት በየጎራው ይደረግ የነበረው የማእቀብ ዘመቻ ጥርጣሬውን ጎላ አድርጎትም ነበር።
ሁሉም አልፎ ቀኑ ደረሰ። እሁድ በመክፈቻው ስነስርአት ላይ የክብር እነግዳዋ ዳኛ ብርቱካን መገኘት ባትችልም፡ ዘግጅቱ ከሞላ ጎደል ሞቅ ብሎ ነበር ያለፈው። በተለይ የኮንግረስማን ጆን ሊዊስ በመክፈቻው ላይ መገኘት በአሉን የበለጠ አድምቆታል። ከሰኞ እስከ ሃሙስ የነበረውን ዝግጅት ግን ከህዝብ ቁጥር አንጻር ከወተሮው የቀዘቀዘ ሆኖ ነው ያገኘሁት።
ለዚህም ብዙ ምክንያቶች ሲሰጡ ሰንብተዋል። በፌዴሬሽኑ አመራር አካባቢ የተፈጠረው ውዝግብ ብዙዎች ግራ ተጋብተዋል። አንዳንዶች በነበረው ግርግር ተበሳጭተው ቀርተዋል፡ አልያም ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ሄሪቴጅ ዝግጅት አቅንተዋል።
በአንድ በኩል በኤልያስ ክፍሌ፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሼኩ ሰዎች ይጧጧፍ የነበረው የ ‘ቦይኮት’ (ማእቀብ) ዘመቻው በሰው ላይ የፈጠረው የስነ-ልቦና ቀውስ ይህ ነው ባይባልም ግምት ውስጥ የሚገባ ጉዳይ ነው። በተለይ በግል አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ተጭነው ለዚሁ ዘመቻ አትላንታ የገቡት የሼኩ ሰዎች፡ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ሁሉ በቫን በመሆን ህዝቡ ወደ ጆርጅያ ዶም (ሜዳ) እንዳይገባ ሲቀሰቅሱ አስተውለናል። እነዚሁ ሰዎች የፌደሬሽኑን የምሽት ዝግጅትም ለማሰናከል በተመሳሳይ ቀን በቅዳሜ መሽት ያደረጉት ተደራቢ ዝግጅት በፌደሬሽኑ ላይ ያስከተለው ጉዳት ቀላል አይደለም።
በአቶ አብነት መሪነት፡ በነተስፋዬ ቅቤ አጃቢነት በግል (ቻርተር) አውሮፕላን ዲሲ አርፈው እና መክረው አትላንታ ከገቡት ውስጥ አንድ ሁለቱ ሜዳ ብቅ ብለው፡ ሹክ ያሉትን ሰማን። አቶ አብነት ፈርቶም ይሁን አኩርፎ፡ በፌዴሬሽኑ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በጆረጂያ ዶም ሳይታይ ወደመጣበት ተመልሷል። ከቶውንም ስታዲየም ገብቶ ዝግጅቶችን ማየት ካልፈለገ አትላንታ ድረስ መጥቶ፡ ዝግጅቱ ሲያልቅ ለምን ተመለሰ? በእርግጥ ዝግጅቱን ለማወክ እና ለመበጥበጥ?… ይኽ የብዙዎች ጥያቄ ነበር።
በገንዘብ ሃይል ሰዎችን በመደለል የ ‘ቦይኮት’ እና የብጥበጣ ዘመቻ ለመምራት መጡ የተባሉትም እንደጠበቁት አልተሳካላቸውም። በተለይ አርብ እለት፡ 8 ጁላይ የኢትዮጵያ ቀን ሲከበር የዳኛ ብርቱካንን ንግግር ለመስማት የመጣው ህዝብ ብዛት እና ተፈጥሮ የነበረው የህዘቡ የአንድነት መንፈስ (ሙድ) ሊረብሹ የተላኩትንም ያስደነገጠ ክስተት ሆኖ ነበረ ያለፈው።
በእለቱ ታቅዶ የነበረው ግርግር የአደባባይ ምስጢር ነበርና፡ ክስተቱ ቢፈጠር ኖሮ አጻፋውን ለመመለስ የተዘጋጁም እንደነበሩ ስለታወቀ የሜዲያው ሰዎች ካሜራቸውን ደግነው ሲጠባበቁ፡ የግቢውሴኩሪቲ አባላት እና የአትላንታ ፖሊሶችም ባይነ ቁራኛ ይከታተሏቸው እንደነበር ተመለከትን።
ዳኛ ብርቱካን ንግግር በምታደርግበት ጊዜ እነ አያያም ከመድረኩ ጎን ነርቨስ ሆነው ሲቁነጠነጡ የካሜራ አይን ውስጥ ገብተዋል። ፕሮግራሙ በጣም ዘግይቶ እንዲጀመር መደረጉ፡ የድምጽ ማጉያው እንዳይሰማ የተደረገው ተነኮል… ወዘተ የሼኩን ሰዎች ሊያስደስታቸው ይችል ይሆናል እንጂ ህዘቡ መልእክቱን እንዳያዳምጥ አላደረገውም።
የክብር እንግዳዋ ንግግር የፈጠረው ሙድ እነ እያያን ለምን እረፍት እንደነሳቸው የሚደንቅ ነው። ምናልባት እነዚህ ወገኖች ንግግሩን ሰሙ እንጂ አላዳመጡት ይሆናል። ንግግሩን ቢያደምጡት ኖሮ ስለ ይቅር ማለት፡ ስለ መዋደድ እና ሰለ አንድነት ዳኛ ብርቱካን በመናገርዋ ይልቁንም በተደሰቱ ነበር።
የአትላንታው አድማስ ራዲዮ ላይ ቴዲ እና ሰይፉ ፋንታሁን፡ ውስጥ አዋቂዎችን በማጣቀስ የሼኩ ገንዘብ ተከፋፍሎ ሊመለስ መሆኑን፡ ሁለቱ ወገኖችም በዚህ መሰማማታቸውን ሲናገሩ ተደምጠዋል:: እነ አብነት በገንዘቡ ተቋሙን በቁጥጥር ስር ማድረግ ስለተሳናቸው በእርዳታ መልክ የስጡትን 240,000 ዶላር ለማስመለስ: ከዚያ በላይ ወጭ ማድረግ ነበረባቸው። ያም ሆነ ይህ ብሩ ሲሄድ ችግሩንም ይዞት ይሄዳል የሚሉ ወገኖች ጥቂት አይደሉምና ለነዚህ ውገኖች ይህ በበጎ የታየ ጥሩ ዜና ነው::
አትላንታ በዚህ አይነት ሊጠናቀቅ ቻለ። የወደፊቱን ግን ማወቅ በጣም ከባድ ነው:: ፌዴሬሽኑ ብዙ ትናንሽ ችገሮች – እና ትልቅ የአመራር ችግር ላይ ነው የሚገኘው። ከትናንሽ ችግሮቹ ይልቅ ትልቁን ችግር መፍታቱ የሚቀል ይመስላል። አመራሩ በቅርቡ በአዲስ ኮሚቴ ይተካል። አዲሱ አመራር ካለፈው ስህተት ይማርና የብዙሃኑን ፍላጎት ይጠብቃል የሚል እምነት አለ። ይህ ካልሆነም ብዙ አያሰጋም። ምክንያቱም ኢትዮጵያን የሚያሰባሰብ ሌላ አማራጭም ብቅ ብሏል። … የኢትዮጵያ ውርስ እና ቅርስ!
በጥቅሉ ስናየው የአትላንታው ዝግጅት ልዩ ነበር። የህዝብ ድምጽ የገንዝብን ሃይል ያሸነፈበት፣ መርህ ህገ-ወጥነትን የረታበት፡ የብዙሃኑ ውሳኔ የጸናበት፡…
ከዚህ ክስተት ብዙ ነገር እንማራለን። ሼኩም ሆኑ ሰዎቻቸው እንደ ጃኬት ከሚቀየረው አንባገነን ስርአት ወግነው ከህዝብ ጋር እልህ ከመጋባት የልቅ ወደ ህሊናቸው ተመልሰው ከብዙሃኑ ቢሆኑ ይበጃቸዋል። በገንዝብ የሚገዛ ሁሉ ግዚያዊ እና አርተፊሻል መሆኑን መገንዘብ አስተዋይነት ነው።
በመጨረሻም ሰለሞን ተካልኝ …
እለተ አርብ፣ ከላውረንስቪል ካውንቲ ወደ አትላንታ ስንጓዝ በክላርክስተን ማቋረጥ ነበረብን። እዛ ካሉት የኢትዮጵያ ሱቆች መካከል ‘ሶል ሙዚቃ ቤት’ አንዱ ነው። የሰለሞን ተካልኝ ሙዚቃ ቤት እንደሆነ ወዳጄ ዳዊት ነገረኝ እና ሰለሞንን ለማግኘት ወደዚያው አመራሁ።
ከውጭ በሩን ከፈቼ ወደ ውሰጥ ዘለቅኩ። በግራ በኩል የሚታዩ ተናንሽ ክፈሎችን አልፌ ወደ ሙዚቃው ቤት አመራሁ። ግራና ቀኝ ባማትር ምንም ሰው ስላላየሁ ወደመጣሁበት ተመለሰኩ። ከሱቁ ለመውጣት እበር ላይ ስደርስ ሰለሞን ከውስጥ ሆኖ ‘ክንፉ’ ሲል ጠራኝ።
“ከውስጥ በካሜራ አይቼህ ነው የመጣሁት። ና ግባ።” ብሎ ወደ ሱቁ ጋበዘኝ።
ሰለሞን ብሶቱን መናገር የጀመረው ገና ቁጭ በል ከማለቱ አስቀድሞ ነበር።
“እንደ እናንተ የጥላቻ ዘመቻ ቢሆን እንዲህ ቆሜ ባልሄድኩ ነበር። እንደምታየኝ ግን ከአርቲሰቶቹ ሁሉ በላይ ሆኜ ነው የምኖረው። ከዚህ ሱቅ ጎን የምታያቸዉ ሁሉ እኔ ያከራየኋቸው ንብረቶቼ ናቸው።… ”
ሰለሞን ፋታ አልሰጠኝም መናገሩን ቀጠለ..
“ያኔ ከአስመራ እንደተመለሰኩ የጥላቻ ፖለቲካ አራማጆቹ ጉዳዩን እነዳስረዳቸው የሳምንት ጊዜ እነኳን አልሰጡኝም ነበር። ተረባርበው ዘመቱበኝ… ይህ ዘመቻ በኔ ላይ ብቻ አላበቃም … የዚህ ሰለባ የሆኑ በርካታ ሰዎች እየተገፉ ወደ ወያኔ እየገቡ ይገኛሉ…”
“ወደ ኳስ ሜዳው ለምን ብቅ አላልክም?” ስል ንግግሩን አቋረጥኩት። ቀጥታ መልስ አልሰጠኝም።
“ፌዴሬሸኑን የምታውቀው ነው። አንተ ራስህ የነበርክበት አንድ ዝግጅት ላይ ስለ ኢትዮጵያ እንዳልዘፍን ከለከሉኝ። አገር ወዳድ ዘፋኞችን አይወዱም። በዛ ላይ እኔን በአምስት መቶ ሲያሰሩኝ ለነ አስቴር አወቀ ግን በሺዎች ይከፍሏቸዋል።… እኔ የፈለግኩትን የመሆን መብት የለኝም እነዴ?” መልሶ እኔኑ ጠየቀኝ።
“አምነህበት ከገባህ ወያኔ የመሆን መብትህ እንደተጠበቀ ነው። ስራህን በተመለከተ ግን ስለሚያልፍ ስርአት እና ግለሰብ ከመዝፈን ይልቅ ስለ ሃገር ለምን አትዘፍንም?”
“ጥሩ ስራ የሰራን መሪ ባወድስ ምን አለበት? የእስክንድር ነጋን ጽሁፎች እያነበባችሁ ወደ ስህትት እንዳትገቡ…” ሲል ቀጠለ።
ሰለሞን ስለ መለስ ስራ ሳይሆን ስለ ቅንድቡ እና ውበቱ መዝፈኑን ለአፍታ የዘነጋው መሰለኝ። እናም ይቅርታ ብዬ አቋረጥኩት። በርግጥ ሰው ውጭ አቁሚያለሁ። አመጣጤም ቀጠሮ ይዤ ለረጅም ሰዓት ለመነጋገር ነበረ። ደውልልኝ እና በሰፊው እንነጋገራለን ብሎ ቢዝነስ ካርዱን ሰጥቶኝ ተለያየን።
ቶሮንቶ፡ ጁላይ 2011