ይቅርታ የማልጠይቅበት ሐቅ ነው!

ለክቡራን አንባቢያን

ሰው የሚሰማውም ሆነ የሚያነበው መስማትና ማንበብ የሚፈልገውን ብቻ ለመሆኑ ምንም አያጠያይቀንም። በድንገትም ሆነ በአጋጣሚ ያበጃጀው መስመር ስቶ ሌላ መንደር የተቀላቀለ ወቅት ሊፈጠር የሚችለውን ሁኔታ ለማመን በሚያዳግት መልኩ ጠበል የነካው ሰይጣን የሚያሰማው ጭሆትና የሚያሳየው “የሰውነት” መፈራገጥ ያክል ግርግር መፍጠሩ አይቀርም። ከዚህ ቀደም በጻፍኳቸው ተቃውሞ ያላስነሳ አንድም ጽሑፍ የለኝም። በጻፍኩ ቁጥር የስድብና የእርግማን መዓት ማስተናገድ ለእኔ እንግዳ አይደለም። ምንም እንኳን በቁጥር ሲቀመጥ “ቃለ ህይወት ያሰማን” በማለት ከሚመርቁኝ አንባቢያን ቁጥር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ቁጥር ያለው ቢሆንም ጥቂቶች ናቸውና “የት ይደርሳሉ” በማለት በቸልታ ማለፉ አልታየኝም ከዚህ ቀደምም አላደረግኩትም። በተቻለኝ መጠንም ለማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ሲነበብ የትርጉም ልዩነት ይኖር ይሆን? በሚል ስጋት በጻፍኩ ቁጥር ራሴን ግልጽ መድረጌን ትቼ ጽሑፎቹ ጻሐፊው ሊያተላልፈው ከሚፈለገው መልዕክት ውጭ እንዳይተረጎሙ የጽሑፉ ዓላማ በማቀመጥ ችግሩ ይቀረፍ ይሆናል የሚል እምነት ነበረኝ። ይህን ማድረጌ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ብችልም በትናንት ዕለት “የሙስሊሞች ጥያቄ የሥልጣንና የፖለቲካ ጥያቄ ነው!” በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቃሁት ጽሑፍ ተክትሎ ሃያ አራት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እየደረሱኝ ያሉ የኢሜይል መልዕክቶች ከብዛቱ የተነሳ ለእያንዳንዱ ኢሜይል መልስ መስጠት ስለማልችል ይህን መልዕክት ለመጻፍ ግድ ብሎኛል።

በበኩሌ ከማናቸውም ግልሰቦች ሆነ ድርጅት የግል ጽብ እንዲሁም የርስት ጥያቄ የለኝም። ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት ያገናኘን የሀገር ጉዳይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያ እንደ አንድ አገር እስካለችና እስከቆመች ድረስ ደግሞ ሌሎች ሀገሬ ሕዝቤ የሚሉትን ያህል ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት ሕዝቦችዋም ሕዝቤ ነው። ስለሆነም ሌላው ቢቀር በኢትዮጵያዊነቴ ስለ ሀገሬና ስለ ሕዝቤ እንደማንኛውም ዜጋ ሃሳቤን በነጻነት የመግለጽ የማንሸራሸርና የመጻፍ ባለ መሉ መብት መሆኔን ሊታወቅ ይገባል። ይህን ሕጋዊ መብቴ በምለማመድበት ሰዓት ደግሞ የሃሳብ ልዩነት መፈጠሩ አይቀርም። ሁሉም በአንድ ጊዜ ማስደሰት አይቻልምና የሃሳብ ልዩነት መፈጠሩ ግድ ነው። የሃሳብ ልዩነት ደግሞ አሁን በእኛ የተጀመረ እንግዳ ልምምድ ሳይሆን ያለ የነበረ ሃሳባችን መግለጽ እስከቻልን ድረስም የሚቀጥልም ነው። ታድያ የሃሳብ ልዩነቶች በመወያያትና በመነጋጋር ማለትም በማጥበብ የግራ ሀገር የመገንባት፣ የመፍጠርና ያለችው ኢትዮጵያ የመጠበቅ የእያንዳንዳችን ግዴታ መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ ልዩነቶቻችን ከሚገባ በላይ በመወጠርና በመለጠጥ ማለትም በማስፋት አንድ የነበርችው ሀገር የመበተንና ልዩነቶቻችንን በልዩነት ለመፍታት መሞከር ደግሞ ምርጫ መሆኑን ግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል።

እዚህ ላይ ግልጽ ለማድረግ የምፈልገው ቁምነገር ቢኖር የሃሳብ ልዩነት እንደ ልዩነት ከማስተናገድና መድረኩን በመጠቀም ተቃውሞውን በተመሳሳይ መንገድ ከመግለጽ ይልቅ ስድብ እርግማን አልፎ ተርፎም ዛቻና ማስፈራርያ (እኔ እንደሆንኩ ለFBI አልጠቁምቦትም) የትም እንደማያደርስ ለመግለጽ እወዳለሁ። እስከማውቀና እስከሚገባኝ ድረስም ይህ ሁሉ ውርዥብኝ የሽንፈት ምልክት ከመሆኑ አልፎ ሌላ ሊሆን እንደማይችል ነው የማውቀው የሚገባኝም። ቅር ለተሰኛችሁ ወዳዶቼም እንደሆነ በእውነቱ ነገር የቅሬታዎ መንስኤ ምክንያታዊ ሆኖ ስላላገኘሁት የጻፍኩት ይቅርታ የማልጠይቅበት ሐቅ ነው በማለት አቋሜን በድጋሜ ስገልጽ በአክብሮት ነው። በተረፈ ጃፓናዊው ጸሐፊ ሓሩኪ ሙራካሚ ለሰሚ ጆሮ በለገሱት ምክር ልስናበት “If you only read what everyone else is reading, you can only think what everyone else is thinking.”

አመሰግናለሁ

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል