በዘላለም ክብረት


ሐሙስ 20 – 01 – 2003፣ ጋምቤላ ከተማ፡

የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አዲሱን የስራ ዘመኑን የመጀመሪያውን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ በማጽደቅ ያጠናቀቀ ሲሆን፤ በመዝጊያው ስነ ስርዓት ላይ በጊዜው የክልሉ ፕሬዝደንት የነበሩት ኡሞት ኡባንግ ባደረጉት ንግግር፡

‹‹ጋምቤላን ወደ ቀድሞው ክብሯ እንመልሳታለን፡፡ ያችን አኙዋዎች፣ ኑዌሮች፣ መዠንገሮች፣ ኦፖዎች፣ ኮሞዎችና ደገኞች አንድ ላይ በሕብረት የሚኖሩባትን – ጋምቤላ፡፡ ሁላችንም አፍሪካዊያኖች ነን፡፡ ጥላቻና ልዩነት ለማናችንም አይበጁንም…››


በማለት የሁሉንም ተሰብሳቢዎች ልብ የሚነካ ሃሳብ አቀረቡ፡፡ 156 መቀመጫዎች ያሉት የክልሉ ምክር ቤትም በጭብጨባ ተናጋ፡፡ ኡሞት ይሄን ታሪካዊ ንግግር ሲያደርጉ ከኡሞት ጎን የተቀመጡት የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አሽኔ አስቲን ተከትለው ስለ ልማትና መከባበር ተናግረው አሁንም አዳራሹን በሌላ ጭብጨባ አናጉት፡፡ ከሚያጨበጭቡት የምክር ቤት አባላት መካከል ቁመተ ሎጋው የ50 ዓመቱ ከአኙዋ ዞን የተወከሉት አቶ በኳች ማሞ ይገኙበታል፡፡ 

እሁድ፡ 06 – 07 – 2007፣ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ፡

የቀድሞው የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል ሆኑት አቶ አሽኔ አስቲን በኬኒያ ናይሮቢ አኝዋ ሰርቫይቫል፣ Bread for All እና GRAIN በተባሉ ዓለማቀፍ ተቋማት የተዘጋጀውን ዓለማቀፍ የምግብ ኮንፈረንስ ላይ ለመሳተፍ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከሌሎች አራት ግለሰቦች ጋር (የዓለም ባንኩን አስተርጓሚ ፓስተር ኡሞት አግዋን ጨምሮ) ተገኙ፡፡ ነገሮች እንዳሰቡት ሳይሆን ቀረና አምስቱም ግለሰቦች በኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ተይዘው ወደ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ተወሰዱ፡፡

ከአንድ ቀን በኋ ሰኞ፣ 07 – 07 – 2007፡ 

‹ምርጫ 2007› ሊደረግ ስልሳ ሰባት ቀናት ይቀሩታል፡፡ ‹አፈ-መንግስቱ› ኢቢሲ ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን  ባወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች የቅስቀሳ የአየር ጊዜ መሰረት የዕለቱ (በቴሌቪዥን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ዜና በኋላ) ተረኛ በጋምቤላ የኢሕአዴግ አጋር ፓርቲ በመሆን ክልሉን እያስተዳደረ ያለው የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕአዴን) ነው፡፡ ጋሕአዴን በዕለቱ እየቀሰቀሰበት የነበረው ጉዳይ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ሲሆን፤ በዚሁም መሰረት የክልሉ ህዝብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጡ የፓርላማ አባላት በፌደራል እና በክልል ደረጃ እንደተወከለና የውክልና ዴሞክራሲም በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደላቀ ደረጃ እንደደረሰ ጠቅሶ ይቀሰቅሳል፡፡ በቅስቀሳው መሃል ከሚታዩት ምስሎች መሃል ግን አንዱ ጉዳዩን ለሚያውቅ ሰው ወይ ያስቃል አለያም ያስደነግጣል፡፡ አስቂኙ/አሳዛኙ ጉዳይ በ2002 ምርጫ የክልሉ ምክር ቤት ካለው 250 መቀመጫዎች መካከል አንዱን የያዙት የአኙዋ ዞን ተወካዩ አቶ በኳች ማሞ በክልሉ ፓርላማ ውስጥ የድምፅ አሰጣጥ ስርዓት ላይ እጃቸውን ሲያወጡ መታየታቸው ነው፡፡ ምክንያቱም አቶ በኳች ማሞ በቀን 07 – 07 – ’07 ‹‹መቀመጫውን ሀሬና፣ ኤርትራ ካደረገው ራሱን የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) ብሎ ከሚጠራ የሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት ፈጥረሃል፣ በሃላፊነትም እያገለገልክ ነው›› ተብለው በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ  አንቀፅ 7 (2) መሰረት ከ 20 ዓመት እስከ እድሜ ልክ ሊያስቀጣ የሚችል ክስ ቀርቦባቸው ያለመከሰስ መብታቸው እንኳን ሳይነሳ በእስር ላይ ይገኛሉና፡፡ በኳች ታስረዋል፡፡ ጋሕአዴን ደግሞ የውክልና ዴሞክራሲ መጎልበት ተምሳሌት አደርጎ ይቀሰቅስባቸዋል፡፡

ሰኞ፣ 17 – 09 – 2007፡ ጋምቤላ፣ ማጃንግ ዞን፡

በአስገራሚ ሁኔታ የቀድሞው የጋምቤላ ክልላዊ ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል አቶ አሽኔ አስቲን በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን መንድሽ የምርጫ ክልል በተካሔደው የክልል ምክር ቤት ምርጫ  ጋሕአዴንን በመወከል ምርጫውን በማሸነፋቸው የምርጫ ክልሉ ምርጫ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማቴዎስ ኤፍሬም የተፈረመ የተመራጭነት መታወቂያ የተዘጋጀላቸው ሲሆን ‹የተመራጩ ፊርማ› የሚለው ቦታ ላይ ግን ፊርማቸውን አላሳረፉም፡፡ 

ለምን? ምክንያቱም አቶ አሽኔ አስቲን ከመጋቢት 06 – 2007 ጀምሮ ‹‹መቀመጫውን ሀሬና፣ ኤርትራ ካደረገው ራሱን የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) ብሎ ከሚጠራ የሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት ፈጥረሃል›› ተብለው በፀረ-ሽብርተኝነት አቆጁ መሰረት ተከሰው በእስር ላይ ስለሆኑ፡፡ እንግዲህ አቶ አሽኔ አስቲን ምርጫ የተወዳደሩትም ያሸነፉትም በሌሉበት ሲሆን፤ በመጨረሻም በሌሉበት የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት  ተመራጭ ስለመሆናቸው በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ የተመራጭነት መታወቂያ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡

***

ኡሞት ኡባንግ በ2002 ምርጫ አሸንፎ ስልጣን የያዘውን የጋምቤላ ምክር ቤት አራተኛ የስራ ዘመን በ2003 መጀመሪያ ላይ ሲከፍቱ አሽኔ አስቲን በአፈ ጉባኤነት ከጎናቸው የነበሩ ሲሆን በኳች ማሞ ደግሞ የምክር ቤት አባል ሁነው ከፊት ለፊታቸው ተቀምጠው ነበር፡፡ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኡሞት ኡባንግ ከክልሉ ፕሬዝደንትነታቸው ተነስተው በፌደራል ደረጃ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ቢሾሙም የያዙትን ይዘው ከሀገር ኮበለሉ፣ የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል አሽኔ አስቲን በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ታስረው ይገኛሉ፣ የምክር ቤት አባሉ በኳች ማሞም እንዲሁ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

እውነት ይህ ሁሉ የሚሆነው ህግና ስርዓት ባለበት ሀገር ነው? ብሎ መጠየቅ እዚህ ጋር ተገቢ ነው፡፡ የጋምቤላ አበሳ ግን ከዚህም ይልቃል፡፡

1. ጋምቤላ

የኢፌዴሪ ሕገ – መንግስት በአንቀፅ 47 ካቋቋማቸው ዘጠኝ የክልል መስተዳደሮች አንዱ ነው፡፡ የሕዝብ ብዛቱ ትንሽ ከሚባሉ ክልሎች አንዱ ሲሆን (የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን የሃምሌ 2007 ግመታ የክልሉ ሕዝብ ብዛት ሶስት መቶ ዘጠና ስድስት ሺህ እንደሆነ ያሳያል)፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙት አስር ክፍለ ከተማዎች ውስጥ ‹በየካ ክፍለ ከተማ› ብቻ የሚኖረው ነዋሪ በአጠቃላይ በጋምቤላ ክልል ከሚኖረው ነዋሪ በእጅጉ ይበልጣል እንደ ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በጋምቤላ ክልል የሚኖረው ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ 0.4 በመቶውን ብቻ ይሸፍናል፡፡ (የሕዝብ ቁጥሩ ላይ የተለያዩ የክልሉ ልሂቃን ጥርጣሬ አላቸው) የሕዝብ ብዛቱ ከቆዳ ስፋቱ አንፃር ሲታይ ግን በኢትዮጵያ እንደ ጋምቤላ ህዝብ ሰፊ መሬት ላይ የሰፈረበት (sparsely populated) ክልል የለም፡፡ በንፅፅር ሲቀርብም ሃምሳ ከሚሆኑት የአውሮፓ ሀገራት ጋምቤላ አስራ ሶስት የሚሆኑትን በቆዳ ስፋት ይበልጣል፡፡ ጋምቤላ መሬቱ ሰፊ፣ የሕዝብ ብዛቱ ትንሽ እና እጅግ ለም ክልል ቢሆንም እንደ ጋምቤላ ጭቆናው፣ የመብት ጥሰቱ፣ ስደቱና መከራው የበዛበት ክልል የለም ማለት ደግሞ ስህተት ነው አያስብልም፡፡ 

በ1980ዎቹ አጋማሽ Cultural Survival በጋምቤላ የሚኖረውን የአኙዋ ዘውግ ‹አደጋ ላይ ያሉ ቡድኖች› ዝርዝር (endangered groups list) ውስጥ ካስገባው ጊዜ ጀምሮ ስለ ጋምቤላ ስቃይና መከራ እንደ Genocide Watch, Survival International, Oakland Institute, Inclusive Development, Human Rights Watch, Amnesty International, International Consortium of Investigative Journalists (ICIJ) የመሳሰሉ ፖሊሲ አፍላቂዎች (think tanks)፣ የመብት ተከራካሪዎች እንዲሁም ጋዜጠኞች ብዙ ሪፖርቶች፣ መግለጫዎችና ዘገባዎችን በተለያዩ ጊዜያት አውጥተዋል፡፡ የግጭት ተንታኞች (conflict analysts) የፌደራል ኢትዮጵያን የግጭት መንስኤና መፍትሄ ሲተነትኑ ከጋምቤላ የተሻለ ምሳሌ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ እዚህም እዛም ጋምቤላ ነው በምሳሌነት የሚቀርበው፡፡ ለምን ጋምቤላ?

2. ጋምቤላና: ‘የፌደሬሽኑ ፈተና’?

ኢትዮጵያ የዘውግ ፌደራሊዝምን (ethnic federalism) በሕገ መንግስት ደረጃ ተቀብላ ተግባራዊ ማድረግ በጀመረችበት ወቅት ሂደቱ ዘውግ ፌደራሊዝምን በሕግ ደረጃ ከከለከሉትና ዘውጌ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በሕግ ደረጃ ከሚያግዱት ከአብዛኖቹ የአፍሪካ ሀገራት የተለየ (divergent) በመሆኑ ትችትና ውዳሴ ከተለያዩ አካላት ይቀርብለት ነበር፡፡ ተችዎች ይህ ለአፍሪካዊያን መጥፎ ምሳሌ (precedent) ነው በማለት ከፋፋይ ነው ሲሉ ሲያጣጥሉት፤ አወዳሾቹ ደግሞ አፍሪካ ከተዘፈቀችበት የግጭት አዙሪት ለመውጣት ጥሩ መፍትሔ ነው በማለት ሲያሞግሱት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ዘውጌ ፌደራሊዝም ከሃያ ዓመታት በኋላ እንደ ተችዎቹ ሆነ ወይስ እንደ አወዳሾቱ የሚለው ኦዲቲንግ የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ባለመሆኑ በዚህ ፅሁፍ ለማየት አልተሞከረም፡፡

‹የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ብዙ ውይይት ሳይደረግበት ነው አሁን ባለው ደረጃ ሕገ መንግስታዊ የሆነው› የሚለው የምሁራን ትችት እንዳለ ሆኖ ዘጠኝ ክልሎችንና ሁለት የከተማ አስተዳደሮችን (ድሬዳዋን በኋላ ሕገ መንግስቱን እንኳን ማሻሻል ሳያስፈልገው በአዋጅ የከተማ አስተዳደር አድርጎ ተቀብሏታል) ይዞ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ይህ በዋነኛነት ዘውግን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም ግን የግጭትና መንስኤ መሆን የጀመረው በተግባራዊነቱ ማግስት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌደሬሽን ዋነኛ የግጭት መንስኤ የሆነባቸው ክልሎች ደግሞ አራቱ ብዙሃኑን የሚወክል ‹አውራ ዘውግ› (dominant ethnic group) የሌለባቸው ክልሎች ማለትም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ በጋምቤላ ሕዝቦች ክልል እና በሀረሪ ሕዝብ ክልል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አራት ክልሎች ተፎካካሪ ዘውጎች (competing ethnic groups) ያሉባቸው በመሆናቸው የሃብትና የስልጣን ፉክክሩ ነገሮችን በቀላሉ ወደ ግጭት እንዲያመሩ ያደርጓቸዋል፡፡ እንግዲህ ጋምቤላም ከነዚህ አራት ክልሎች አንዱ ነው፡፡
2.1. ‘አኙዋ’  ከ‘ኑዌር’

በአሁኑ ወቅት ያሉት ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የፌደራሉን ሕገ መንግስት መሰረት በማድረግ (በአብዛኛው ከፌደራሉ ሕገ መንግስት ቃል በቃል የተቀዳ) ራሳቸው የክልል ሕገ መንግስት አላቸው፡፡ የጋምቤላ ሕዝቦች ክልልም የራሱ የሆነ ሕገ መንግስት አለው፡፡ የጋምቤላ ሕዝቦች ሕገ መንግስትን ከሌሎች ክልሎች ሕገ መንግስትም ሆነ ከፌደራሉ ሕገ መንግስት በተለየ ‹የክልሉ መስራች አባላት› (titular groups) የሚል ሀሳብ ማካተቱ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል ሕገ መንግስት አንቀፅ 46 መሰረት የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስራች ብሔር ብሔረሰቦች አምስት ሲሆኑ የአኙዋ ብሔረሰብ፣ የኑዌር ብሔረሰብ፣ የመዠንገር ብሔረሰብ፣ የኦፖና ኮሞ ብሔረሰቦች ናቸው፡፡ ከነዚህ መስራች ብሔረሰቦች› መካከል የአኙዋና የኑዌር ብሔረሰቦች በድምሩ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነውን የህዝብ ቁጥር ሲይዙ ከአጠቃላይ የክልሉ ነዋሪዎች መካከል ደግሞ እነዚህ ሁለት ብሔረሰቦች ከሁለት ሶስተኛ የሚልቀውን ይይዛሉ፡፡ በመሆኑም የጋምቤላ ሕዝቦች ክልል ዋነኛ እጣ ፋንታ የሚወሰነው በሁለቱ ‹መስራች ብሔረሰቦች› ተፎካካሪ (competing) ግንኙነት ነው ማለት ነው፡፡

የተለያዩ የክልሉን ፖለቲካ ያጠኑ ግለሰቦች/ተቋማት ጋምቤላን ሰላም ካሳጧት ችግሮች አንዱና ዋነኛው በውስጡ ያሉት ዘውጎች የዕርስ በርስ ፉክክርና ግጭት (inter-ethnic conflict) ነው፡፡ ይህ ግጭትም የሃብት፣ የመሬት እና የስልጣን ፍክክር ነው በማለት ያብራራሉ፡፡ የግጭቶቹ መንስኤ በአጭሩ ይሄ ነው ማለት ከባድ ነገር ቢሆንም በዋናነት ግን ግጭቱና ቁርሾው በአኙዋና ኑዌር ዘውጎች መካከል እንደሆነ ጥናት ያደረጉ ቡድኖች ይገልፃሉ፡፡ የአኙዋ ዘውግ ልሒቃን ጋምቤላ በታሪክ የአኙዋ ምድር እንደሆነች ሌሎች ዘውጎች ከአሁኗ ደቡብ ሱዳንና ከአጎራባች ክልሎች በተለያዩ ጊዜያት እንደመጡ በመግለፅ የጋምቤላ ሃብትና ስልጣን ለባለታሪኩ (historical right) እንደሚገባ በመግለፅ ይሟገታሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አብዛኛው የዘውጉ አባላት በደቡብ ሱዳን የሚኖሩት የኑዌር ብሔረሰብ ልሂቃን ጋምቤላ የሁላችንም ናት ከሚል መነሻ “መጤ” የሚለው ስያሜ አይገባንም በማለት ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ መድሃኔ ታደሰ በተለምዶ የአኙዋ -ኑዌር ግጭት በኑዌሮች ‹ተስፋፊነት›ና በአኙዋዎች ከመሬታቸው ጋር ባለ ጥብቅ ቁርኝት መካከል የተፈጠረ አለመጣጣም እንደሆነ ሲገልፁ ‹‹Traditionally, the Anuak- Nuer conflict can be explained by the incompatibility (antithesis) of the expansionist nature of the Nuer and the Anuaks’ strong emotional ties with their land›› በማለት ነው፡፡

ይህን የተፎካካሪ ዘውጎች ውዝግብ ለመፍታት ተወሰደው ርምጃ ጋምቤላን የኑዌር፣ የአኙዋና የማጃንግ ዞኖች ብሎ በዘውግ መስመር በሶስት ዞኖች መክፈል ነው፡፡ ይህ መፍትሔ የበለጡ የድንበር ጥያቄዎችንና ከመፍጠር ባለፈ፣ የክልሉን ስልጣን ለመያዝ የሚደረገውን ፍክክር የበለጠ አጡዞ የባሰ ችግር ከማምጣት ባለፈ ለጋምቤላ ሕመም መድሃኒት ሊሆናት አልቻለም፡፡

2.2. ‘መስራቾቹ’ ከ’መጤዎቹ

ፖለቲካል ዲሞግራፊ በአካዳሚያው ውስጥ እንደ ጥናት መስክ ተቆጥሮ መጠናት ከጀመረ ከአንድ አስርት ዓመት ብዙም አላለፈም፡፡ ሳይንሱ በዋናነት የሚያጠናው በአንድ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ሰዎች (ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች፣ &#4660