መስታወት ራሱን አያይም ! ቀልዶ-አደር ክበበው ገዳና
ሜሮን ጌትነት ፤
አበበ ተካ ፤

ይህን ፅሁፍ እንድፅፍ ያነሳሳኝ በቅርቡ በሁሉም ዌብ- ሳይቶች ላይ ማለት ይቻላል ፣ የወጣ አንድ የአድናቆት ፅሁፍ ነው ። ጽሁፉ አንዲት ገጣሚትን ለማድነቅ የተፃፈ ነው ። የፅሁፉ ርእስ “ሐገሬ ፤ ሕዝቤ ፤ ክብሬ ” የሚል ሲሆን በእንግሊዝኛ እንዲህ ተተርጉሟል ፤ “My Country, My People, My Honor” :: ይህ የአድናቆት ፅሁፍ የሚያጠነጥነው ፤ ሚሮን ጌትነት በምትባል ኢትዮጵያዊት ዘመናዊ የፊልም ተዋናይ ችሎታና
በግጥሙ ታክኮ ለሃገሯ ያላት ልዩ ፍቅር ላይ ነው ።
ፅሁፉ ገና ሲጀምር ነው “The poet-artist with an “unconquerable soul?” በማለት ተዋናዩዋን ማንቆለጳጰስ የሚጀምረው ። ፀሃፊዋና አድናቂዋ ደግሞ በእንግሊዝኛ መፃፍ የሚቀናቸው አል ማርያም ናቸው ። እናም አል ማርያም ናቸው ከላይ እንደጠቀስኩት በሁሉም ዌብ ሳይቶች ላይ አድናቆታቸውን የናኙት ። የግል አድናቆታቸውን ትክክል ነው አይደለም የሚል ክርክር ወስጥ አልገባም ። ከዚህ በፊትም ይህቺው ሜሮን ጌትነት የተባለች ተዋናይ የተሳተፈችበትን “ድፍረት” የሚል ፊልምን ክሊፕ አይቼ በጣም ተደነቅኩባት ብለው አሞካሽተዋት ነበር ። ካለፈው ሙገሳቸው ላይ እንዲህ ሲሉ በመጨረሻ ባወጡት ፅሁፍ ላይም ቀንጭበው አስቀምጠዋል ፡፤

“… The beautiful young actress Meron Getnet sat stunned and speechless. She is visibly shocked and confused. She looked around in total disbelief trying to get someone to tell her what she has just heard is not true… In her seat, Meron clasps her palms in the traditional praying position as if to implore God’s intervention to save her and her country from such cruel public humiliation. An unidentified interviewer asks her how she feels. (How does one really feel when one’s heart is yanked out before the entire world!?) Meron is visibly brokenhearted. But she puts on a calm and brave face. She is struggling to hide her outrage and fury. She is fighting tears; but she does not breakdown though she is manifestly broken-hearted…”

እንዲህ ይተረጎማል ።

“…..ውቢቱ ወጣት ተዋናይ ሜሮን ጌትነት ፍዝዝ ብላ በዝምታ ተቀምጣለች ፤ እንደሚታየው ደንግጣለች ግራ ተጋብታለችም ። የሰማችውን ነገር ማመን ስላቃታት ዙሪያዋን እየቃኘች እውነት አይደለም የሚላት ሰው ፈለገች…… እንደተቀመጠች ሜሮን የእጆቿን መዳፎች በተለመደው የፀሎት አይነት ገጥማ፤ እግዚአብሄር እሷንና አገሯን ከህዝባዊ ውርደት እንዲያድናቸው ጣልቃ ገብነቱን እንዲያሳያት ተመኘች ። ያልታወቀ ቃለ መጠይቅ አድራጊ ምን እንደሚሰማት ጠየቃት ። (አንድ ሰው በመላው አለም ፊት ልቡ ቡጥርቅ ብሎ ሲወጣ ምን ሊሰማው ይችላል ? ) ሜሮን ልቧ እንደተሰበረ ይታያል ። ሆኖም ግን መረጋጋትና ጀግንነት ይታይባታል ። ብስጭትና ንዴቷን ለመደበቅ ትታገላለች። እንቧዋ ይተናነቃታል ፤ ግን እንባዋ አልወረደም ይሁንና ልቧ የተሰበረ መሆኑ በግልፅ ይታይባታል…….”
የትርጉሙ መጨረሻ ።

አል ማርያም ይህን ከላይ የሰጡትን ሙገሳ ያደረጉት የፊልሙን ቅንጫቢ ብቻ አይተው ነው። ሙሉውን ገና አላዩትም ከፅሁፍዎ እንደተረዳሁት ። እንዴት ነው በቅንጫቢው ብቻ ይህን ያህል ሙገሳ ያፈሰሱላት ። በፊልሙ ውስጥስ ከሷ ሌላ ተዋናዮች አልነበሩም ፤ የነሱስ ሚና ምን ነበር ? ብየ ልጠይቅ እገደዳለሁ ፤ መቼም አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብ ። እንደተመልካችና እንደ ውበቷ አድናቂ ቀደምብየ እንዳልኩት የተዋናይዋ የግል አድናቂዋ ከሆኑ የግል አመለካከትዎ ነውና ነውር የለበትም ። ፍቅር እንደ አፍቃሪው አይን ነው እንደሚባለው ፤ አድናቂም እንደዚያው ነው ። አድናቂና አፍቃሪ አለምንና ህይወትን እንደሚያይበት መነፅርም ይለያያል ።
“ድፍረት” የሚለውን ፊልም ወያኔ/ኢሕዲጎች እንዳይታይ ከለከሉ ። ይህ ዘረኛ አገዛዝ ይህን አደረገ ያን አደረገ ሲሉ የተቹት ግን አልገባኝም ። ፊልሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊታይ ከነበረበት ቦታ በፖሊሶች መከልከሉ እሙን ነው ። የፊልሙ ዳይሬክተር ዘረሰናይ መሃሪ እንደተናገረው በፍርድ ቤት ፊልሙ ክስ አለበት ተብለን ነው እንዳይታይ የተደረገው ሲል በጊዜው ለገባው ታዳሚ ገልጿል ። ዘረሰናይን ለሚያውቀው ደሞ ከማንም በላይ ለወያኔው ስርአት የተሻለ ቀረቤታ አለው ። እኔ እዚህ ላይ አል ማርያም ወያኒያዊውን አገዛዝ አይተቹ አይንቀፉ የሚል ፍላጎት የለኝም ።
“ድፍረት” ፊልም ግን በታገደ ጥቂት ቀናት ውስጥ እንዲታይ ተፈቅዶ እየተየ ነው ። የፊልሙ ይዘትም ከወያኔ ስርአት ጋር ፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ ተቃርኖ የለውም ። ወያኔ ለምን ሲል ያግደዋል ? የጠለፋ ጋብቻ ከወያኔያዊው ስርአት በፊትም ነበረ ፤ አሁንም አልፎ አልፎ ይኖራል ብዬ እገምታለሁ ። ይህው ሰሞኑን የሰማነው በታዳጊዋ በሃና ላላንጎ ላይ የተፈፀመ የደቦ አስገድዶ ድፍረት አንዱ ማሳያ ነው ። “ድፍረት” የሚለው ፊልም በራሱ እንዲያውም አገራችን ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድ በጎ አስተወኦ አለው ብዬ አላምንም ። ይህ ራሱን የቻለ ሌላ ርእስ ስለሆነ በሌላ ጊዜ ልመለስበት እችላለሁ ።

አሁን ተመልሰን ወደ ተዋናይቷ ሜሮን ጌትነት እንምጣ ። የተዋናይነት ብቃቷንም ሆነ ገጣሚነቷ ላይ ዛሬ ልተች አልፈልግም ፤ የራሴ አስተያየት ቢኖረኝም ። አል ማርያም ሆይ የሚያደንቋትን የሜሮንን ግጥም እንደገና ያዳምጡና ወደራስዎ እንዲመለከቱ በዚህ አጋጣሚ ጋብዤዎታለሁ ።
“….መቼም የአሳ ዝላይ መልሶ ከውሃው ነው እመጣለሁ ዞሬ ፣ ስሜን ቀያይሬ ፣
ያኔ ይቀበለኛል ፤ ፍቅር ያጠግበኛል ህዝቤ ፤ አገሬ ፤ ክብሬ ፤”.. ….. ይላል አንዱ የገጣሚዋ ስንኝ ። አቶ አለማየሁ ገ/ማርያም የሚለው ስምዎን አል ማርያም ካሉት ጋር አይገጥም ይሆን ይህ ስንኝ ።
በተረፈ ሜሮን ጌትነት በወያኔው ቴሌቪዥን ላይ የወያኒው የልማት ፕሮግራም ውድድር አዘጋጅነቷንና አቅራቢነቷን ነው እኛ የምናውቀው ። “The poet-artist with an “unconquerable soul”? የሚለው ሙገሳዎ አለቦታው የገባ ነው ብየ እከራከርዎታለሁ ፤ የሜሮን ጌትነት ነፍሷ በወያኔ/ኢሓዲጎችconquer ከተደረገ ከረመ። እንዲያውም ሰሞኑን አሶሳ ወስጥ እየተደረገ ባለው የወያኔ ብሄር ብሄረሰቦች በአል ላይ ይመልከቷት፤ የህገ/መንግስቱ አወዳሽና ቀዳሽ አስተዋዋቂ ናት ። ይህ ከልክ ያለፈ ሙገሳዎ፤ ይህን እያወቁ ከሆነ እታዘብዎታለሁ ፤ ካላወቁ ደግሞ ይቅርታ አደርጋለሁ ። ወይም የፅሁፍዎ አቢይ አላማ ሜሮን ጌትነትን የማስተዋወቅ የPR ስራ ከሆነ ደግሞ ከጋራ አገራችን ፍቅርና ደህንነትና ጋር አይለውሱብኝ ። ኢትዮጵያንና ሚሮንን አንድ ላይ ሳይለውሱ ኢትዮጵያን ለቀቅ አድርገው ሜሮንን ጠበቅ ያድርጉ ። እዚህ ላይ እንዲታውቅልኝ የምፈልገው ነገር አለ ። ሜሮን ከወያኔ/ኢሕአዲግ ጋር ሰራች አልሰራች የራሷ ምርጫ ነው ፤ ስሪ ወይም አትስሪ ብዬ ልጫናት መብቱም ሆነ አቅሙ የለኝም ። አል ማርያም ሆይ ፤ እኔ የምመክረዎ ፤ መስታወት ራሱን አያይምና ዘውር ብለው እንደገና ያሞገሱላትን ግጥም “….ህዝቤ ፤ አገሬ ፤ ክብሬ …” የሚለውን ከራስዎ ጋር አያይዘው እንዲመለከቱ ነው ። ለዛሬው በሜሮን ጌትነት ላይ በዚሁ አበቃለሁ ። አስፈላጊ ሆኖ ካገኘሁት ደግሞ በግጥሙም ሆነ በተዋናይነት ብቃቷ ላይ እመለስበታለሁ ። ከዚያው ከሜሮን ጌትነት የግጥም ንባብ ላይ ለወደፊቱ ፅሁፌ ታግዘኝ ዘንድ አንድ ስንኝ ጥዬ ልለፍ ።

“……እድሜህን ቀርጥፈህ ብትሆን ባለ ዲግሪ ፣ ማስትሬት ዶክትሬት ብትደክም ብትለፋ ፤
እውነቱን ልንገርህ በሃገሬ ሂሳብ ፤ ከውጪ የመጣ የሶስት ወር ኮርስ ነው ሚዛን የሚደፋ ፡…….”

…………………………………………………….

ውድ አንባቢዬ ሆይ እንግዲህ ይህን አጋጣሚ አግኝቻለሁና አንዳንድ ተዋንያንና ድምፃውያን ላይ በየዌብ-ሳይቱ ተለጥፈው ካገኘኋቸው ዜናዎችና እኒም ከታዘብኳቸው ውስጥ ጥቂቶቹን ላጋራችሁ ።
ከጥቂት ወራት በፊት ነው አበበ ተካ የሚባል ነዋሪነቱን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገ ድምፃዊ ላይ “አበበ ተካ ለሴት ሲል አገሩን የከዳ ” በሚል ርእስ አንድ ዜና በተወሰኑ ዌብ-ሳይቶች ላይ ተሰራጭቶ ያየሁት ። ይህ አበበ ተካ የሚባል ድምፃዊ የምን አገር ዜጋ አግብቶ ነው ሙዚቃ ያስተወችው ? የሚል ጥርጣሬ ነው በውስጤ ያደረው ። ምክንያቱም በአበበ ተካና በአገሩ መካከል ያለውን ግንኙነት ፤( በአድናቂዎቹና በሱ መካከል እንዳለ ግንኙነት አድርጌ በመገመት) አበበ ተካም ሆነ ባለቤቱ ትዳራቸውን የሚወዱ ባልና ሚስት አድርጌ ገምቼም ነበር ። ለሚወዳት ባለቤቱ ሲል አንድ ያለችውን ሙያ ትቶ በፍቅር ተሰብስቦ የሚኖር ግለሰብ አድርጌ ገምቼውም ነበር ። ህይ ዜና በወጣ በጥቂት ወራት ውስጥ አበበ ተካን ባለቤቱ አስገድዶ ደፈረኝ ብላ ከሰሰችው የሚል ሌላ ዜና ደግሞ በነዚሁ ዌብ-ሳይቶች ላይ ብቅ አለ ። ምንድነው ነገሩ ! ያቺ ስሙ የጠፋላት ሚስቱ ነች ወይስ ስለሌላ አበበ ተካነው የምሰማው እያልኩ ሳስብ ፡ የአስገድዶ ደፈረኝ ክስ ተነስቶለት ልጆቹን የማየት እድል እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቀ ተባለ ። ከፍርድ ቤት ሲወጣ ፤ በዩ-ቲዩብ ላይ አጥር ያለች ቃለ መጠይቅ ቢጤ ሰጥቶ ስለነበር ያችኑ ሳዳምጥ አበበ ከባለቤቱ ጋር የነበረው አለመግባባት ስር የሰደደ እንደነበር በግልፅ ይታይ ነበር ፤ የወራት ሳይሆን አመታት የተቆጠሩበት አለመግባባትም ነበር ። ስለዚህ ከወራት በፊት አገሩን የከዳ ሲል የተጻፈው ዜና ከንቱና ባዶ ፈጠራ ሆኖ አገኘሁት ። እንግዲህ ጉዳዩ የቤተስብ ቢሆንም አንዴ አደባባይ ወጥቷል ፤ በዚህ ላይ አበበ ተካ Public Figure ታዋቂ ግለ-ሰብ ስለሆነ ነው እንጂ ብዙ አበሻ እሱን ከገጠመው በባሰ ሁኔታ ትዳሩ ተፈቷል ፤ መፋታት አዲስ አይደለም ለማለት ነው ። ይህንና ግን ባለቤቱ እንዲህ አደረገችው እንዲህ በደለችው እየተባለ ነው ወሬው የሚናፈሰው ።ስለዚህ የአንድ ወገን የአበበ ተካን ብሶት ብቻ ከመስማት የባለቤቱን ብሶትም መጠየቅ ተገቢ ነው። አለዚያ ለፍርድ አይመችም ።

……………………………………..

ሌላው ትዝብቴ ደግሞ ቀልዶ-አደሩን ክበበው ገዳን ይመለከታል ። ክበበው ገዳ ከኢትዮጵያ ቀልዶ-አደሮች ውስጥ ቁንጮ ነው ብየ ብናገር ማጋነን አይሆንም ። የቀልድ ስራዎቹ ላይ እንደማንኛው ሰው ችግሮች ሊታዩበት ይችላሉ ።
ተመልካችም በቀልደኛው ንግግር እየሳቀ ሲሰደብ እንኳን መሰደቡ አይገባውም ። ወይም እየገባው ያው የአበሻ ባህሪይ ሆኖበት ዝም ብሎ ያልፈዋል ። የአበሻ ባህሪይ ያልኩት አንድ የምናደንቀው ሰው ላይ ዛሬ የምናየውን ስህተት በይሉኝታ ፤ ወይም ይቅርታ እንድናደርግ ሳንጠየቅ በይቅርታ ፤ እናሳልፈውና ነገ በላያችን ላይ ሲጨፍርብን ፀጉራችንን መነጨት መጀመራችንን ነው ።
ዛሬ በሰለጠነው ዘመን ማንኛውም ሙያ በትምህርት ሲደገፍ ጥቀሜታ አለው ። ሁሉም የቁም ቀልዶ-አደር Stand-Up Comedian በአሜሪካም ቢሆን እንኳ ፤ የመድረክ ላይ ትምህርት አለው ማለት አይደለም ፤ ሆኖም ግን በሙያው የሰለጠኑ ባለሙያዎች ያማክሩታል ፤ ቀልዶቹን ይመርጡለታል ፡ቃላቱን ይቀርፁለተል ፤ መድረኩን ይመሩለታል ፤ ሰአቱን ያቅቡለታል ። በኛ ሃገር ግን ከፈረንጆቹ በተለይ ከአሜሪካ ሁሉንም ነገር እየኮረጅን መሟላት ከሚገባቸው ሁነታዎች አንዱን እንኳ ሳናሟላ የምንገባበት ሙያ ላይ ብዙ ስህተቶች ሲፈጠሩ እንመለከታለን ። ከነዚህ ሙያዎች ውስጥ የቁም-ቀልድ Stand-up comedy ሙያ አንዱ ነው ።

ሌላ ሌላውን እንተወውና ከአስኮራጃችን አሜሪካን ሃገር አንድ የቁም ቀልዶ-አደር ፤ ቢያንስ ፕሮግራሙን የሚመራለት ዳይሬክተር ብሎም አማካሪ ይፈልጋል ። እንደፈለገና አፉ እንዳመጣለት ያሻውን አይዘላብድም ። በተለይ ለተመልካቹ ያለው ክብር ከፍተኛ ነው ። ምክንያቱም ኑሮው የተመሰረተው እንጀራው የሚጋገረው በተመልካቹ ላይ ነውና ። ኒውዮርክ ሾው ላይ የነበረውን ተመልካቹን አትላንታ ሄዶ አይቀልድበትም ። በሌሎቹ የአውሮፓ አገሮችም እንደዚሁ ነው ።
ቀልዶ-አደር ክበበው ገዳ የታዳሚውን የልብ ትርታ ማዳመጥና አድናቂዎቹ መኖሪያቸው ኢትዮጵያም ይሁን አሜሪካ ፤ ካናዳም ይሁን ቻይና ማክበር ይገባዋል ። እንደ አለቅላቂ ሴት አንዱ አገር ሲሄድ ቀደም ብሎ የሄደበትን ከተማ ማንቋሸሽ ወይም መዝለፍ አይገባውም ። ይህን እንድል ያነሳሳኝ ክበበው ገዳ ከተወሰኑ አመታት በፊት ወደ ኮሎምበስ ኦሃዮ ብቅ ብሎ ነበር ። ከተመልካቹ መሃል ቀልዱ ያላስደሰተው አንድ ግለ-ሰብ ጋርም መጣላቱን ሰምቻለሁ ። ከዚያ ወደዋሽንግቶን ዲሲ ሲመለስ መድረክ ላይ ወጥቶ “ ኢትዮጵያ እያለሁ አገሬ መራቧን እሰማ ነበር ። አሁን ግን ኦሃዮ ደርሼ ከመጣሁ በኋላ አገሬ ለምን እንደተራበች ገባኝ ፤ ለካ ገበሬው ሁሉ ተሰብስቦ ኦሃዮ ገብቶ ነው ሲል ቀለደ ።” ዋሺንግቶን ዲሲም ኦሃዮ በብዛት የወልቃይት ፀገዴ ተወላጆች እንደሚኖሩበት በማውቅ ለቀልዶ-አደሩ ክበበው ገዳ ሳቀለት አስካካለት ።
የአንተን የቀልዶ-አደሩን ሆድ ለመሙላት ውልቃይት ፀገዴ ማረስ ነበረበት ? ቀልዶ-አደሩ ወንድሜ አገራችን ረሃብተኛ መባሏን ከሰማህና ገበሬው ሁሉ ኦሃዮ መመጣቱን ከተገነዘብክ ለምን ራስህ ገብተህ አታርስም ነበር ። በዚህ አጋጣሚ አገር የምትለማው በአርሶ አደሮች እንጂ በቀልዶ አደሮች እንዳልሆነ ልገልፅልህ እወዳለሁ ። ታዲያ ይህን አባባልህን ሳትወቀስበት በዋሽንግተን ተስቆልህ አለፍክ ።
ውድ አንባቢዬ ፤ አሁን በቅርቡ ደግሞ ይባስ ብሎ አውሮፓ አንድ የፋሽን ትርኢት ላይ እንደሟሟያ ሆኖ ቀርቦ ነበር ክበበው ገዳ ። የአዲስ አበባ ጆክ ነው ብሎ አንድ ቀልድ አወራ ። “ጎስቋላዎቹና ማዲያታሞቹ ሴቶች ሁሉ አሜሪካና ካናዳ ነው ያሉት” ሲል ቀለደ ። ጆኩ እንደጆክ ተወርቶ በዚያ ቢያበቃ መልካም ነበር ። “ለነገሩ እውነት ነው እኔ ዘወር ዘውር ብየ አይቻለሁ” ማንከሽከሻ ብቻ ናቸው ሲል አሾፈ ። ይህን አባባሉን ለመመልከት የሚቀጥለውን ሊንክ ይመልከቱhttps://www.youtube.com/watch?v=t0-qU60ik3E ።ወይም ክበበው ገዳ ብለው ጉግል ያድርጉና “ ቆንጆዋን እንካ ግን አትንካ ” የሚለውን ርዕስ ይጫኑ ።
ቀደም ብየ እንዳልኩት እንደ አለቅላቂ የመንደር ሴት የኦሃዮን ዲሲ የአሜሪካና ካናዳን አውሮፓ እየወሰደ ያለቀልቃል ። ቀልዶ አደሩ ወንድሜ ክበበው! እነዚህ ማንከሽከሻ ፤ ጎስቋላ፤ ያልካቸው የአሜሪካና የካናዳ ኢትዮጵያውያን እህቶቻችን ሚስቶቻችንና እናቶቻችን ናቸው ። አዎ ማዲያታም ሊሆኑን ይችላሉ ሊጎሳቆሉም ይችላሉ ። አንተ ኢትዮጵያ ወስጥ ያውም አዲስ አበባ ብቻ እንደምታውቃቸው ፤ ምሽት-አደር ሴቶች ላይቆነጁ ይችላሉ ። ሰርተው ጥረው ግረው በላባቸው በወዛቸው የሚያድሩ ናቸውና ። በዚህ በፈጣኑ አለም ውስጥ ልጆች አሳድገው አስተምረው ትዳራቸውን ጠብቀው ከዚያም አልፈው ኢትዮጵያ ወስጥ ቤተ-ሰብና ዘመድ ረድተው የሚኖሩ ሴቶች ናቸው ፤ ቢጎሳቆሉ ይነሳቸው ፤ ማዲያት ቢወጣባቸው ይብዛባቸው ።
የአንተ የአዲስ አበባ ቆነጃጅት ሴቶች ለፀጉራቸው ሶስት ሰአት ፤ ለጥፍራቸው ሁለት ሰአት ለቅንድባቸው ሌላ ሁለት ሰአት ለማጥፋት በቂ ጊዜ ያላቸው ናቸው ፤ ምነው አይቆነጁ ። ስለዚህ ስትቀልድም የምትናገረውን እወቅ ። በአንድ አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ስትቀልድም እዚያው እፊታቸው ላይ ቀልድ ። አንዱን ካንዱ አታምታታ ። አንድ እውነታ ግን ልንገርህ ። ኦሃዮም ካናዳም ሆነ አሜሪካ አንተ መጣህባቸው እንጂ እነሱ አንተን ብለው አልመጡብህም ። ኦሃዮም ካናዳም አሜሪካም ያላንተ ኖረዋል መኖርም ይችላሉ ። አስር አመት ቀልደህ ከአዲስ አበባ ቆነጃጅት ሴቶች የማታገኘውን ገንዘብም በአንድ ትርኢት የምታገኘው ከነዚህ ማንከሽከሻዎች ፤ ማዲያታሞችና ባሎቻቸው ነው ። ዘወር ዘወር ብየ አለምን አይቻለሁ ብለሀናልና እግርህ ተፍታቶ ክንፍ አውጥተህ ዘወር ዘወር ያልከው ከነዚሁ ከማዲታሞቹ በተገኘ ገንዘብ እንደሆነ ልትረዳው ይገባል ። ይህ እውነት አይደለም እንዴ ወንድሜ? መቼም ቀልደኛ ነህና ፤ አይደለም ከአባቴ በወረስኩት ገንዘብ ነው ብለህ እንዳታስቀኝ ።

ውድ አንባቢየ ለዛሬው በዚሁ ላብቃ !

ከአንበሳው ይብራ

እ.ኤ.አ ዲሴምበር 2 2014

]በአሉ ግርማና አስፋው ዳምጤ

[email protected]

ባለፉት ወራት የአገር ቤቶቹንም ሆነ ውጪ ያሉትን የሚዲያ አውታሮች በተለያየ መልክ ያነጋገረው የበአሉ ግርማ አሟሟት ላለፉት 30 አመታት ሲያነታርክ ቆይቶአል ። እስከደርግ መጨረሻ ድረስ በድብቅ ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ በግልፅ አነታርኳል ። ይህም የሆነው በሁለት ምክንያቶች ነው ። አንደኛው ምክንያት በአሉ ግርማ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ስነ-ፅሁፍ አቻ የማይገኝለት ደራሲ በመሆኑና በብዙ አንባቢዎቹ ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ ያለው መሆኑ ሲሆን ፣ ሁለተኛው ደግሞ ፍትህንና እውነትን ፈላጊ ተስፋ የማይቆርጥ ቤተሰብ ስላለው ነው ። በተለይ ደግሞ ባለቤቱ ወ/ሮ አልማዝ አበራ ። ለፍትህ እታገላለሁ የሚል ወገን ሁሉ ለበአሉ ግርማ ቤተሰብ ፍትህ ማግኘት የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ ። ይህን ያልኩበት ምክንያት በውጪም ሆነ በአገርቤት “በቃ በአሉ ግርማን ደርግ ገድሎታል ሁላችንም የምናውቀው ነውና እንተወው ፦ የሚሉ ወገኖች ስላሉ ፤ በተለይ የእያንዳንዱ ግለሰብ የግል ነጻነት ተከብሮ በሚኖርበት አውሮጳና አሜሪካ እየተኖረ ይህን የመሰለ ድፍን ያለ ድምዳሜ ላይ መድረስ በስደት ከየምንኖርበት አገር የፍትህ ስርአት የተማርነው እንደሌለና ሆዳችንን ከመሙላት በቀር ምንም ትርፍ እንዳላመጣን ማሳያ ይሆናልና ነው ።

ይህን ካልኩ በኋላ ለዛሬ አብይ ነው ብዬ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልምጣ ።

አቶ አስፋው ዳምጤ “በበአሉ ግርማ ጉዳይ ላይ ከህሊና እዳ ነፃ ነኝ” በሚል ርዕስ ስለ በአሉ ግርማ መሰወር ጉዳይ የሰጡትን ቃለ- መጠይቅ ፍቱን ከምትባል መፅሄት ላይ ተወስዶ በአንድ ዌብ ሳይት ላይ ተለጥፎ አግኝቼ አነበብኩትና ከቃለ መጠይቁ የተረዳሁትን ለአንባቢ ለማሳወቅ ፈልጌ ነው ።
አቶ አስፋው ፤ በመጀመሪያ በራስዎ ስም መልስ ለመስጠት በመሞከርዎ ላድንቅዎ እፈልጋለሁ ።የሰጡት መልስ አሳማኝም ይሁን አይሁን ዋናው ለቀረበብዎት ጥያቄ በቃለ-መጠይቅ መልክ መልስ ለመስጠት ሞክረዋል ። ያስመሰግንዎታል ። ከቃለ መጠይቅ ይልቅ በራስዎ ፅሁፍ የነበረውን ሁኔታ ቢገልፁልን ኖሮ ደግሞ ተመራጭ ይሆን ነበር ። አዲስ አበባ ተወልደው ስላደጉም ይሆናል በወዳጅ በዘመድ አፅፈው በጎን ለማለፍ አለመፈለግዎ ፤ ትልቅ ነገር ነው ።(በጋዜጠኛው አቀራረብ ላይ ጥያቄ ቢኖረኝም)።
ያነጋገርዎ ጋዜጠኛ እንደነገረን የመጀመሪያ ዲግሪዎን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛውን ደግሞ ከካምብሪጅ አግኝተዋል ። ከዚያም ለረጂም ዘመናት በገንዘብ ሚኒስቴር ሰርተዋል ። ከዚህ በመነሳት ትምህርትዎ የጋዜጠኝነት ወይም የስነ-ፅሁፍ እንዳልሆነና economics ሊሆን እንደሚችል ጠርጥሬአለሁ ። ተሳስቼ እንደሆን ለመታረም ዝግጁ ነኝ ። ከዚያም በመፅሃፍ ድርጅትና በኩራዝ አሳታሚ ሰርተዋል ።
ይህን ካልኩ በኋላ በቀጥታ ወደርስዎ ቃለ-ምልልስ ልምጣ ።
የደራሲ በዓሉ ግርማ ባለቤት፣ ወ/ሮ አልማዝ አበራ፣
‹‹…የካቲት 24 ቀን 1976 ዓ.ም. ቀን ላይ አስፋው ዳምጤ እቤት ስልክ ደወለ :: በዓሉ ቤት አልነበረምና፣ ስልኩን አንሥቼ ያነጋገርኩት እኔ ነበርኩ :: የእግዜር ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ፣ ‹… በዓሉ እንደመጣ እዚያ እቀጠሯችን ቦታ ባስቸኳይ እንድትመጣ ብሎሃል በዪልኝ …› ብሎ ስልኩን ዘጋ ::››
አቶ አስፋው ፡ የዚህ አጭር መልሱ “ሃሰት” ነው ። ብለዋል ።
አበራ ለማ ከበአሉ ባለቤት ከወይዘሮ አልማዝ አገኘሁት ብሎ ካቀረበው ፅሁፍ ላይ ለእርስዎ ቃለ መጠይቅ መንደርደሪያ ሃሳብ ሆኖ የቀረበው ከፊሉ ብቻ ነው ። የአበራ ለማ ሙሉውን ምእራፍ ስናነብ ነው ፈታ ያለ ግንዛቤ የሚኖረን ። እንዲህ ይነበባል ፤ እጠቅሳለሁ፦
“….የካቲት 24 ቀን 1976 ዓ.ም. ቀን ላይ አስፋው ዳምጤ እቤት ስልክ ደወለ፡፡ በዓሉ ቤት አልነበረምና ስልኩን አነስቼ ያነጋገርኩት እኔ ነበርኩ፡፡ የእግዜር ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ’… በዓሉ እንደመጣ እዚያ እቀጠሯችን ቦታ ባስቸኳይ እንድትመጣ ብሎሃል በዪልኝ…’ ብሎ ስልኩን ዘጋ፡፡ በዓሉ ወደ አሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ወደ ቤት ሲመጣ መልእክቱን ነገርኩት፡፡ ወዲያው ሻወር ወስዶ ወጣና ለመሄድ ሲጣደፍ፣ ’እደጅ ውለህ መምጣትህ ነውና እባክህ ትንሽ እህል ብጤ ቀምሰህ ውጣ’ ብለው፤ ’አልችልም… ብርቱ ቀጠሮ አለንና ወደዚያው መፍጥን አለብኝ’ ብሎኝ ፈጥኖ ከቤት ወጣ::” የጥቅሱ መጨረሻ ።
መርምሮ ለሚያነብ ሰው የነገሩ ጭብጥ ያለው ወ/ሮ አልማዝ ከጠየቁትና አበራ ለማ ካቀረበው ከላይኛው ጥቅስ ጋር የተያያዘ ነው ። ወ/ሮ አልማዝ በስልክ መልእክት ከአቶ አስፋው ተቀብዬ ለባለቤቴ ነገርኩትና በመልእክቱ መሰረት ወደ ጓደኛው ወደ አቶ አስፋው ሄደ ነው የሚሉት ።
አቶ አስፋው የሚሉት ደግሞ የለም ስልክ አልደወልኩም ፤ ቀጠሮም አላደረኩም ፤ ሆኖም ግን ያለቀጠሮ በዚያች የመጨረሻዋ ምሽት በአሉን አግኝቼዋለሁ ነው ። እዚህ ላይ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ይነሳል ። ይኸውም ወይዘሮ አልማዝ ከአቶ አስፋው ጋር ጠብም ወዳጅነትም ቅርርብም የላቸውም አቶ አስፋው ዳምጤ እንደነገሩን ። ይህ ከሆነ ደግሞ ለምን ወይዘሮ አልማዝ እስካሁን ድረስ የምታውቀው ነገር አለና ንገረኝ ብለው አቶ አስፋውን ያስጨንቃሉ ፤ ለምን ሌሎቹን የበአሉ ጓደኞች አንደ አቶ አስፋው ሁሉ ጠይቀው አያውቁም ? ሌላው ደግሞ በመጨረሻዋ በአሉ በተሰወረባት ምሽት ፤ በአሉ ወደቤቱ ስላልተመለሰ ለወይዘሮ አልማዝ ከአስፋው ጋር አመሸሁ ብሎ አልነገራቸው ፤ ከእርስዎ ጋር ማምሸቱንስ ወ/ሮ አልማዝ እንዴት አወቁና ነው ወደቤትዎ የደወሉት ፤ ቀድመው ወደቤት ደውለው በወይዘሮ አልማዝ በኩል ለበአሉ ቀጠሮ ካልሰጡ ? አቶ አስፋው ወ/ሮ አልማዝ ወደቤቴ አልደወለችም ብለው ቢያስተባብሉም ጠዋት ላይ ወደስራዎ ደውለው እንደተነጋገሩ ደግሞ አልካዱም ። ወይዘሮ አልማዝ ባለቤቴ በአሉ ግርማ ማታ አልገባምና የምታውቀውን ንገረኝ ብለው ሲጠዩቅዎ “ አይቼዋለሁ ግን” ብየ የምለው ጠፋኝና ፤ የምለው ጠፋኝና ነው ያሉት ! ለምን የሚሉት ጠፋዎት ? አሁን የሚነግሩንን መገናኛችሁ አጠገብ ቆመን አንድ አንድ ብለን ተለያየን ብለው ለምን አልነገሯቸውም ለወ/ሮ አልማዝ ። ይህን ብለዋቸው እስቲ ደግሞ ከሌሎች ሰዎች ላጣራ ብለው ቢሆን ኖሮ የተናገሩት እውነት ይመስል ነበር ። አንድ ሰው የሚለው የሚጠፋው አንድ የሚያውቀው ነገር ሲኖርና ለዚያ መልስ ሳይዘጋጅ ድንገት ጥያቄ ሲቀርብበት ነው ። ወዲያው የሚያስገድደው ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ የመዘጋጃ ጊዜ ለመግዛት ዘዴ ይቀይሳል ። አቶ አስፋው ለርስዎ ጊዜ መግዣ አድርገው የተጠቀሙበት “ አሁን አንድ ትልቅ ባለስልጣን ዘንድ ስለምሄድ እሱን ጠይቄ እነግርሻለሁ ብለው ዛሬ በህይወት የሌሉትን ሰው ለማ ጉተማን ምስክርነት መጥራት ነው ። እስቲ ቆም ብለው ያስቡት ለራስዎም አልገረመዎትም ?
ሌላው ወ/ አልማዝ የተናገሩትን ለማስተባበል ማስረጃ አድርገው የተጠቀሙበት የሬይደልፍ ኬ ሞልቬርን Reidulf K. Molvaerን ብላክ ላዮንስ Black Lions የተባለው መፅሃፍ ላይ ደራሲው በአሉ ግርማ በጠፋባት በዚያች ምሽት ያቀረበውን ትንተና ነው ። በአጭሩ መፅሃፉ ላይ እርስዎ በአሉን መጥተው ከቤቱ ወሰዱት አይነት አቀራረብ ስለሆነ አንዴ ስልክ ደውሎ ቀጠሮ ሰጠው ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከቤቱ መጥቶ ወሰደው ተብሏልና አንዱን ይምረጡ ነው አባባልዎ ። መፅሃፉ ላይ እኮ ወ/ሮ አልማዝ እንደነገሩኝ ብሎ አልፃፈም ሞልቬር ፤ ስለዚህ ሞልቬር ይህን ነጥብ ከየትም ሊያገኘው ይችላል ። ሞልቤር ስህተት ፈፅሞ ከሆነ እንኳን ወ/ሮ አልማዝን ምርጪ አትምረጪ ሊያሰኛቸው አይችልም ። መፅሃፉ ላይ ለወጣው ፅሁፍ ተጠያቂ መሆን ያለበት ሞልቬር ብቻ ነው ። ታዲያ እኮ ሞልቬር እዚያው ገፅ ላይና እዛው ፓራግራፍ ላይ የጠቀሳቸው ነጥቦች ነበሩ ፤ እርስዎ ሳያዩአቸው አልፈዋል ወይም ሆን ብለው ዘለዋቸዋል ። ሞልቬር እንዲህ ይላል እዚያ ላይ ፤ እርስዎ አቶ አስፋው በአሉ ከተሰወረባት ከመጨረሻዋ ቀን አስራ አምስት ቀን በፊት ነው በአሉን ያየሁት ብለው ለሌሎች ሰዎች ተናግረዋል ብሏል ። ይህም ወ/ሮ አልማዝ ከተናገሩትና ከሚሉት ጋር ባለመግጠሙ ሰዎች ደንቆቸዋል ሲል ፅፏል ፤ ይህን ነጥብ ይያዙ ። ቀጥሎም እንዲህ ይላል ሞልቬር (ስም ባይጠቅስም) ምንልባትም ይህ ጓደኛው ፤ ላደረገው አብዮታዊ አስተዋፅኦ መንግስታዊ ለሆነው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በዚያኑ ሰሞን ስልጣን ተሰጠው ፤ ብሏል ። ሞልቬር ብላክ ላዮንስ በሚለው መጽሃፉ ላይ ያስቀመጠው እንዲህ ይነበባል ገፅ 348 ፦ To other people he ( the friend ) said that he had not seen Be’alu for two weeks before he disappeared, and they were surprised to hear another story from Be’alu’s wife . Soon after the friend got ( perhaps as areward for his contribution to the revolutinary cause ) a high position with Kurraz , the government publishers.
እዚህ ላይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ ። አበራ ለማ የሰዎች ስም አጠፋ የርስዎን የአቶ አስፋው ዳምጤን ጨምሮ እየተባለ ሲጠቀስ በየመጣጥፉ ላይ አንብቤ ነበር ። የእርስዎም ብሶት አበራ ለማ ስሜን አጥፍቷል ነው ። ከዛሬ 17 አመታት በፊት በ1997 እ.አ.ኤ ሞልቬር ይህንኑ ፅፎት የለም እንዴ ያውም ዘላለማዊ ሆኖ በሚቀር መፅሃፍ ላይ ! ምነው አበራ ለማ እንዚህን መረጃዎች ሰብስቦ ሲፅፍ ድንቅ ሆነ ?
አቶ አስፋው ሌላው ያሳዘነኝን ሳልገልፅልዎ ማለፍ አልፈልግም ። ጋዜጠኛው ከአበራ ለማ ጋር ቅራኔ ነበራችሁ ? ብሎ ይጠይቅዎታል ። መሆን የነበረበት ከቮልቴር ጋር ቅራኔ ነበራችሁ ? ነው ። እርስዎም ሲመልሱ “ እኔ ከእርሱ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቻለሁ ብየ አስቤ አላውቅም ብለው ነበር ። ይህ የጨዋ መልስ በቂ ነበር ። በተረፈ ከዚያ አልፎ ከዛሬ 37 አመታት በፊት የተደረገን ስነፅሁፋዊ ክርክር ቂም በቀል አድርጎ ለማቅረብ መሞከርና በዚያ አስታኮ ስሙ ያልተጠቀሰ አስተማሪው እንዲህ ብሎ አለው ብሎ በማለት ሰውን በሾርኒ ለመስደብ መሞከር ትንሽነትን የሚያስይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ። በስነፅሁፍ ቅስሙ ቢሰበር ኖሮማ አበራ ለማ አሁን ይህን የመሰለ ኢንቬስቲጌቲቭ ስራ ባላቀረበልን ነበር ። በነገራችን ላይ አበራ ለማን ከፅሁፉ በስተቀር ጥቁር ይሁን ቀይ ሰልካካ ይሁን ኩርፋድ አላቀውም ። አስተያየቴ በሙሉ በአሉ ግርማን አስመልክቶ ከፃፈው ጋር የየያያዘ ነው ። በርግጥ ሌሎች የግጥም ስራዎቹንም አውቃለሁ ቅስሙ አልተሰበረም ህያው ነው ለማለት ነው ። እውነቱን ለመናገር እርስዎን ቃለ-መጠይቅ ካደረገልዎ ጋዜጠኛ ነው የድርሰት ስራዎች እንዳሉዎትም የሰማሁት ። ልጅ ሆኜ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ነው መፅሕፍትን የማንበብ ልምድ የተጥናወተኝ ። ካነበብኳቸው ውስጥ አንዱ ርዕሱ “ከልታማዋ እህቴ” ይላል አሁን የዚህን መፅሃፍ ደራሲ ማን እንደ ደራሲ ቆጥሮ ያስታውሰዋል !
ወደ ወ/ሮ አልማዝ አበራ ልመለስ ። እኔ እንደገባኝ ከሆነ የወ/ሮ አልማዝ ጥያቄ አቶ አስፋው ባለቤቴን በአሉን ገድለዋል ፤ ወይም በግድያው ላይ እጃቸው አለበት አይደለም ። በኦሮማይ ምክንያት ህይወቱ እንዳለፈም ያውቃሉ ። የሳቸው ጥያቄ ግን አንድና አንድ ብቻ ነው ። የሟች ባለቤቴን የሞት መንገድ ፍለጋ ላይ ነኝ መዳረሻውን ላለፉት 30 አመታት እየፈለኩ ነው ። የዚያች መንገድ መግቢያ ቁልፍ አቶ አስፋው እርስዎ እጅ ላይ ይገኛልና ለፍትህ ብሎም ለህሊናዎ ሲሉ ይጠቁሙኝ ነው ። አቶ አስፋው ወ/ ሮ አልማዝ ልብ ውስጥ እንደማንኛውም ሰው ሊመላለስ የሚችለውን ስሜት ሊረዱት ይገባል ። የውድ ባለቤታቸውን ደብዛ እየፈለጉ ያሉ ናቸውና ። ቀያፋ ላዘዛቸው ሮማውያን ወታደሮች ጲላጦስ እየሱስን በግላጭ ጉንጩን ስሞ አሳልፎ ሰጥቶታል ብለው ቢያስቡስ ወ/ሮ አልማዝ ላይ ይፈረዳል ?
አቶ አስፋው ሌላው ያሳዘነኝን ሳልገልፅልዎ ማለፍ አልፈልግም ። ወ/ሮ አልማዝ ላይ ለምን ጠየቀችኝ ከሚል ቅሬታ ተሰምቶዎታል ስለዚህም አቂመውባቸዋል ። ወ/ሮ አልማዝ ጋር በስራ ምክንያት የሚያገናኛችሁና በዚህ ተቀይማኛለች በማለት ሊያቀርቡት የሚችሉት ምክንያት ሊኖር አልቻለም ። እና የሞተውን ባላቸውን በአሉን ሌላ ውሽማ ነበረችው በማለት የሴትነት ብቃታቸውን ለማዋርድ ሞከሩ ። ባልሻረ ቁስላቸው ላይ ጨው ነሰነሱበት ። ምን አይነት ጭካኔ ነው ! አዝናለሁ እንዲህ በማለቴ ፤ እንዲያውም ወራዳነት ነው ። የገባበትና አፅሙ እንኳ የት እንደወደቀ ያልታወቀ ሙት ወዳጁን አጽም ፤ ሰው እንዴት ይግጣል ። ቤተሰቡን ለማስቀየምስ ለምን ይቸኩላል ። ከራስዎ ጥያቄና መልስ ልነሳና ይህን ራስዎ የፈጠሩት መሆኑን ደግሞ ላስረዳዎ አቶ አስፋው ።
ጠያቂው ጋዜጠኛ ቀድሞ የተዘጋጀበት በሚመስል መልኩ ከመሬት ተነስቶ አንድ ጥያቄ ያቀርብልዎታል ። በአሉ እርስዎጋ ከመድረሱ በፊት ይት ቆየ ብለው ነው የገመቱት ? ይልዎታል ። ከዚያ አስቀድመው እርስዎ ካላዘጋጁት በቀር የበአሉን መቆያ ቦታ ሐሳብ ከዬተ አመጣው ? የቃለ- መጠይቁን ቁራሽ እነሆ
ፍቱን ፦ በአሉ እርሶ ጋ ከመድረሱ በፊት የት ቆየ ብለው ነበር የገመቱት ?
አቶ አስፋው፦ጥቂት ቀደምብሎ እዚያው አካባቢ ወዳጅ እንደነበረው ተገንዝቤ ነበር ።
ፍቱን፦ የማን ቤት ነው?
አቶ አስፋው ፦ እሱን አልውቅም ።
ፍቱን፦ወንድ ሴት?
አቶ አስፋው ሴት ።
ፍቱን፦ በዚያች እለት ምሽት እዚያ ቆይቶ ከተመለሰ በኋላ ነበር ከእርሶ ጋር የተገናኛችሁት ?
አቶ አስፋው፦ እንደዚያ ነበር አመጣጡን ሳይ የገመትኩት ።
ወዳጅ እንደነበረው ተገንዝቤ ነበር ። ተገንዝቤ ነበር የሚለውን ቃል መጠቀም የሚቻለው ለትምርት ለእውቀት ሲሆን ነው ። ውሽማ ነበረችው ለማለት ግንዛቤ አያሻውም አውቅ ነበር ነው የሚባለው ፤ ፈጠራዎን ግዝፈት ለመስጠት ግዙፍ ቃል ተጠቀሙ ። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ራስዎም የተናገሩትን እንዳላመኑበት ነው ። እዚያው ላይ ዝቅ እንበልና የማን ቤት ነው ? ሲል ይጠይቃል ጋዜጠኛው ። አቶ አስፋው እሱን አላውቅም ሲሉ ይመልሳሉ ። ወንድ ሴት ይልዎታል ጋዜጠኛው ። የእርስዎ መልስ ደግሞ ሴት ይላል ። የማን ቤት መሆኑን ከላይ ሲጠቅሱ አልውቅም ካሉ በኋላ ፤እንዴት የሴት ቤት መሆኑን አወቁ ? እርስዎ ጋር ከመገናኘቱ በፊት ደግሞ ውሽማውጋ ቆይቶ ነው የመጣው ? ሲልዎ ጋዜጠኛው ፣ እንደዚያ ነበር አመጣጡን ሳይ የገመትኩት ይላሉ እርስዎ ። ለካ ግምት ነው የተረጋገጠ ማስረጃ የለዎትም ! ታዲያ በስድስት አረፍተ ነገሮች ወስጥ ሶስት የተለያዩ የተምታቱ ነገሮችን ማቅረብ ወ/ሮ አልማዝን ለመስደብ የተፈጠረ ቅጥፈት መሆኑን አያሳይም ?
አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳ ፤
1)በአሉ ግርማ ከወደአንዲት ሴት ቤት መምጣቱን ገመትኩ አሉ፡
2) ኮማንደር ለማ ጉተማን ምስክርነት ጠሩ ፤በህይወት የሌለ ሰው ፡
3)ስሙን ያልጠቀሱትን የአበራ ለማን መምህር ፤ እንዲህ ብሎ አለው አሉ ፡
4)ወ/ሮ አልማዝ መስሪያ ቤትዎ ደውለው ሲያነጋግሩዎ የሚሉት ጠፋብዎ ፡
5)አበራ ለማ በግጥሙ ምክንያት አደረገ ላሉት ክርክር ምስክር አድርገው አሁንም ያቀረቡት በህይወት የሌለውን ስብሃት ገ/እግዚአብሄርን ነው ።
ከተደረገልዎ ቃለ-መጠይቅ ላይ ከሰጧቸው መልሶች የቱን ተቀብለን የቱን እንተው ፤ የትኛው እውነት የትኛው ሃሰት እንደሆነስ በምን እናረጋግጥ ?
እስቲ እኔም እንደርስዎ ልገምት speculate ላድርግ በአሉ ግርማ ከሌላ ሴት ቤት መጣ ብየ ገመትኩ እንዳሉት ማለት ነው ። ከዚያ በፊት በደህናው ጊዜ በአሉ ከደሞዙ ሌላ በድርሰት ስራዎቹ የሚያገኘው ጠቀም ያለ ገንዘብ ነበረው ። እርስዎም ተቸግረው ከበአሉ ገንዘብ ተበድረው ነበር ። ያን ገንዘብ ሊከፍሉት አልቻሉም ወይም አልፈለጉም ። በመጨረሻዋ እለት ላለፉት 6 ወራት ስራ ስላልነበረው የተበደረውን ገንዘብ ሊከፍለኝ ነው ብሎ ይሆን እንዴ ለወይዘሮ አልማዝ በሰጧቸው ቀጠሮ አማካይነት ከቀጠሮው ስፍራ የደረሰው ። በቃለ- መጠይቅዎም ላይ እኔና እሱን ብቻ የምትመለከት የግል ጉዳይ ነበረችን ብለዋል ከገንዘብ ብድር ጋር የተያያዘች ትሆን ? በአሉን ሰዋራ ስፍራ ድረስ በመውሰድ ለደርግ ሰዎች ማስረከብ እርስዎን ከገንዘብ እዳ ነጻ ሲያደርግዎ ፤ ደርግ ተረጋጋሁ ባለበት በዚያ ዘመን በኦሮማይ እርቃኑን ያስቀረውን የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣኑን በአሉን ያለግርግር እርስዎ ከወሰዱበት ስፍራ በቀላሉ ማፈን ችሏል ማለት ይሆን ?
አቶ አስፋው ፤ አንድ ነገር እንዲያስቡ እፈልጋለሁ ። ላለፉት 30 አመታት የውድ ባለቤቴን መውደቂያ እፈልጋለሁ ብላ ያለድካም የምትተጋ አንድ ወይዘሮ በቤቷ ውስጥ ምን ያህል ፍቅር እንዳለ ማሳያ ናት ። ለባለቤቷም ሆነ ለራሷ የፍቅር ተምሳሌት ናት ። እንዲህ አይነት ሴት ደግሞ ለማይነጥፍ የቤት ውስጥ ፍቅር ምንጭ ናት ። እንደማናቸውም ድንቅ ደራስያን ሁሉ በአሉ ግርማም ከቤቱ ያገኘው የነበረው ፍቅር ለድርሰት ስራዎቹ ሁሉ ፅኑ መሰረት ሆኖት ለኛም ለአንባቢዎቹና ለአድናቂዎቹ የድርሰቶቹ ትሩፋት ደርሰውናል ።
ለዛሬው በዚሁ ላብቃ ።

ከአንበሳው ይብራ !