በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ሆኖ የመጀመሪያው
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሥሪያ ቤት ሕንፃ ‹‹አፍሪካ
አዳራሽ›› በሚል ስያሜ በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ
ሥላሴና በወቅቱ ሹማምንት ይፋ ከተደረገ ከ56 ዓመታት በኋላ
20ኛውን ሕንፃ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና
የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን መረቁ፡፡ አዲስ አበባ በተመድ
ተቋማት እንቅስቃሴ፣ ከኒውዮርክና ከጄኔቫ በመቀጠል ሦስተኛዋ
ከተማ ለመሆን መብቃቷን ባን ኪ ሙን ገለጹ፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት በቀድሞ ጠቅላይ ሚስትር መለስ ዜናዊ
የመሠረት ድንጋዩ የተጣለው አዲሱ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን
ሕንፃ ለተመድ ልዩ ልዩ ተቋማት አገልግሎት የሚውል መሆኑን
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ካርሎስ ሎፔዝ
ተናግረዋል፡፡
ሕንፃውን በትናትናው ዕለት በይፋ ያስመረቁት ጠቅላይ
ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ከ50
ዓመታት በፊት የመጀመሪያውንና የአፍሪካ አዳራሽ ተብሎ
የተሰየመውን ሕንፃ ለአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አገልግሎት
እንዲውል በስጦታ አበርክታለች፡፡ በ1951 ዓ.ም. የአፍሪካ
ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሲመሠረት፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ
ሁኔታዎች ለአፍሪካ ኮምጫጫ ነበሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣
የአፍሪካ ሕዝቦች ከወቅቱ የቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት
የሚታገሉበት ጊዜ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ በውጭ የሚኖሩ
የአፍሪካ ልጆችም ለአኅጉሪቱ ነፃ መውጣት፣ ለሕዝቦች
እኩልነትና ክብር ሲታገሉ በነበረበት ወቅት ነበር የአፍሪካ
ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዕውን የሆነው፡፡
ዕድምተኛውን ፈገግ በማሰኘት ንግግራቸውን የጀመሩት የተመድ
ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ በዓለም ላይ
ደጋግመው ከጎበኟቸው ከተሞች አንደኛ ሆና እንደምትገኝ
በማስታወስ ንግግራቸውን አሰምተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር
ኃይለ ማርያምን የኢስቶኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር በማለት
በስህተት መጥቀሳቸው የታዳሚውን ፈገግታ ያጎረፈባቸው ባን
ኪ ሙን፣ ይቅርታ ጠይቀው የስም አጠራራቸውን በማስተካከል
ንግግራቸውን ቀጥለዋል፡፡
አዲሱ ሕንፃ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጃፓን
ሒሮሺማ ከተማ ላይ ከተጣለው የአውቶሚክ ቦምብ የተረፉ
ዛፎች መጥተው እንደተተከሉበት አስታውሰዋል፡፡ ሕንፃውን
አምስት የተባበሩት መንግሥታት መሥሪያ ቤቶች እንደሚጋሩት
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ካርሎስ ሎፔዝ
ተናግረዋል፡፡
ሕንፃውን የገነባው አገር በቀሉ ራማ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ
የተወሰነ የግል ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ባለሰባት ፎቅ የሆነውን
ዘመናዊ ሕንፃ ከኒውዮርክ በሚሰጠው ትዕዛዝና ቁጥጥር
እየታገዘ መገንባቱንና አረንጓዴ የግንባታ ይዘት ተብሎ
በሚጠቀሰው ቴክኖሎጂ መገንባቱን የኩባንያው ማኔጂንግ
ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ተድላ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡
ለሕንፃው ግንባታ አሥር ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን፣
በ1800 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እዚያው በአፍሪካ ኢኮኖሚክ
ኮሚሽን ቅጥረ ግቢ ውስጥ የተገነባ ነው፡፡
የሕንፃው ግንባታ በሁለት ዓመታት እንዲጠናቀቅ ታስቦ ግንታው
ቢጀመርም፣ ሦስት ዓመት ፈጅቷል፡፡ ይህም ከመጀመሪያውኑ
ከርክክብ ሒደቱ ጀምሮ የተለያዪ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ
በማስገባት ሒደት፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በማግኘትና
በመሳሰሉት ምክንያቶች እንደሆነ አቶ ፍሬው ተናግረዋል፡፡
ይህም ሆኖ ሕንፃው በሶላር ኢነርጂና በኃይል ቆጣቢ
ቴክኖሎጂዎች የታገዘ መሆኑን፣ ሰዎች ሕንፃው ውስጥ ሲሆኑ
የሚበሩ፣ ሰዎች በሌሉ ጊዜ ደግሞ በራሳቸው የሚጠፉ
የመብራት ይዘቶችንም አካትቷል፡፡
ራማ ኮንስትራክሽን በሐንኪን ቢራ ፋብሪካ ግንባታ፣ በወንጂ
ስኳር ማስፋፊያ፣ በአዲስ አዳማ የፍጥት መንገድ ግንባታ ላይ
የተሳተፈ ሲሆን፣ ከጥቂት ቀናት በፊት በፕሬዚዳንት ሙላቱ
ተሾመ የተመረቀውንና ቦሌ አካባቢ የሚገኘውን የኦሮሚያ ልማት
ማኅበር ሕንፃን ገንብቷል፡፡