ከአርአያ ተስፋማሪያም

ፍቅረኞቹ አሁን የሚኖሩት አሜሪካ ነው። ተማሪ እያሉ ሳያስቡት ልጅ አፈሩ። የሁለቱን ፍቅርና መዋደድ እንዴት እነደነበረ የሚያውቋቸው ምስክር ናቸው። 6 አመት በመዋደድ የዘለቀው ፍቅራቸው በድንገት እሷ ከአገር በመውጣቷ ለጊዜው ተቋረጠ። የምትፅፋቸው ደብዳቤዎች ውብና አስደናቂ ነበሩ። ልክ እንደውጫዊና ውስጣዊ ውበቷ አይነት ነበሩ። በተለይ «..ውድ ፍቅሬ ቅድሚያ ግን እወቅልኝ፤ ዛሬም ልቤ አንድ! ፍቅሬም ዘላለማዊ ወረት የሌለበት እንደሆነ! ..ብቸኝነት ጅራፍ ነው! የእሳት ጅራፍ!…የዚህ አለም ኑሮ አክትሞልኝ ፅዋዬን እስክጐነጭ ፣ ተራ ደርሶኝ አንደበቴ ተሸብቦ እጅና እግሬ እስከሚታሰር ለአንተ ያለኝን ጥልቅ ፍቅርና መውደድ ከመግለፅና ከመተግበር ወደኋላ አልልም። አንተ ከማጣ (ልብ ተነጥቆ መኖር ከተባለ) ሞቴን እመርጣለሁ..» የሚለው አስደማሚ ደብዳቤዋ ይጠቀሳል። ከ4 አመት በኋላ ስትመጣ ግን እሱ በማያውቀውና ባላደረገው ነገር ቤተሰብ በጠነሰሰው ሴራ ለመለያየት በቁ። በተደጋጋሚ ቀርቦ ሊያስረዳት ቢሞክርም ለማዳመጥ እንኳ ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። ልጃቸው ልታስታርቅ ብዙ ጥራለች፤ ግን አልሆነም ..ሌላ ሰው አፍቅራ አሜሪካ ገባች። እሱም ልጁን ይዞ ሄደ። ልጇን ለማየት እሱ ወዳለበት ከተማ ስትመጣ ሁሉንም ነገር አስረዳት። ታማኝ ሆኖ ለ4 አመት እንደጠበቃት አስረዳት። በጣም ተፀፀተች።..ጊዜው ግን አልፎ ነበር። ..በቅርቡ ልጅ መውለዷን ሲሰማ ሆስፒታል ድረስ በመሄድ ጠየቃት። የልጇን ግንባር ስሞ « እንኳን በሰላም ተገላገልሽ..ደስ ይበልሽ!» አላት። አንገቷን እንዳቀረቀረች ነበር። …እሱ አንድ እመነት አለው፤ ያፈቀርከውን ሰው ስትለያየው መጥፎውን የምትመኝ ከሆነ..መጀመሪያውኑ ፍቅር አልነበረህም ማለት ነው!..ይላል።..ደግሞም ምንም ክፋት የማታውቅ መልካም ሴት መሆኗን ይመስክርላታል።….ይህ እውነተኛ ታሪክ የእኔ ነው፤….ባለቷሪኳ ደግሞ የኢየሩስ እናት…

«..ለአይኔ ማመን ያቃተኝ ታላቅ ነገር ዛሬ ተከሰተ – ደብዳቤህ። ተመስገን አምላኬ!

በስራ የዛለ ሠውነቴ ከእረፍት አስበልጦ ከአንተ ሊያወጋ የተወሰኑ ረድፎችን መጓዙን አይኖቼ አስተዋሉ። ስቀጥል፥ ከምንም በላይ በሀገርህ ላይ ሠላምህን፣ በቤትህ ውስጥ የሠከነ ሕይወትን፣ ከሰዎች ጋር መልካም ግንኙነትን፣ ለፈጣሪህ ቅን ልቦናን፣ ለቤተሰብህ መታዘዝን፣ እምነት ማተብህን ማጥበቅን፣ ለሰውነትህ ምቾትን፣ ለአይምሮህ መረጋጋትን፣ በስራህ አስተዋይነትን፣ በማህበራዊ ህይወትህ ጥሩ ግንኙነትን፣ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነትን፣ እንዲያድልህ ፥ ለፈጣሪዬ – ለፈጣሪህ፣ ለአምላኬ – ለአምላክህ፣ ፃድቅም ባልሆን ለሃጢያተኞች ሲል መከራን ለተቀበለ፣ በበደሉት መጠን ቂም ለማይዝ፣ በጠሩት ጊዜ ለሚሰማ ለሕያው አምላክ – በልኡል መንበሩ ተቀምጦ አዳርህን – አዳሬን፣ ውሎህን – ውሎዬን፣ ለሚቃኝ ለሚመለከት፣ እውነተኛ ሚዛንና ፍርድን በእጁ ለያዘ ፈጣሪ አምላክ የእጁን በረከት እንዲዘረጋልህ የዘወትር ፀሎቴ ነው!!

ውድ ፍቅሬ፥ ቅድሚያ ግን እወቅልኝ፤ ዛሬም ልቤ አንድ፣ ፍቅሬም ዘላለማዊ ወረት የሌለበት እንደሆነ!! በቀዘቀዘና በሰከነ አነጋገር ክንድህን ተንተርሼ….ጠረንህን እያሸተትኩ ..አ. ፈ..ቅ..ር..ሀ..ለ..ሁ…የምልህን! በቀን የሰው አይን፣ በጠፍ ጨረቃ ጋኔን ሳልፈራ ..አንተን እያልኩ ድፍን ሰፈርህን እያሰስኩ « ፍቅሬን.. ውለዱ» እያልኩ ሳስሥህ የምከርመውን፤ ይህን ስፅፍልህም ወደኋላ በትዝታ እየተቃጠልኩ ትርሃስ ላይ ተደፍቼ እያነባሁ መሆኑን ብታየኝ.. “አዝንልሻለሁ” ከምትለኝ በላይ ዛሬ ታዝንልኝ ነበር። የሚያባብለኝ የለ፤ የሚያፅናናኝ። ብቻዬን ልብህን እያሰብኩና እየፈለኩ፣ እንዲያጫውተኝ እየዳሠስኩ – ፍቅርን ከትርሃስ ጋር በእንባ ሌሊቱን በመገላበጥ አነጋለሁ፤ ናፈቅከኝ!!…በካፊያ ዝናብ ከአንተ ጋር መሆን ምን ያህል እንደሚያስደስተኝ አንተም ታውቃለህ፤ ምን ብዬ ልንገርህ!?…ቢያንስ ያንተ ይሻላል- ቤተሰብን አይቶ መፅናናት ቀላል ነገር እንዳይመስልህ!! ብቸኝነት ጅራፍ ነው፤ የእሳት ጅራፍ!!!..ከስራ መልስ አረፍ ባልኩ ቁጥር ቀልቤ አዲስ አበባ….ሰፈር ልቤ ከአንተ ጋር በምናብ ሲጨዋወት ያመሻል።

« …የምወድህ ፍቅሬ፥ አጀማመራችን እኮ ብንተማመን – ልንፋቀር፣ ብንዋደድ ልንዛለቅ፣ ብንተሳሰብ ልንስማማ፣ ብንከባበር ላንናቆር፣ ብንቀያየም ላንለያይ ነበር። ታዲያ ዛሬ ማዶና ማዶ ሆነን እየተሰቃየን ተግባብተን ላንስማማ በየራሳችን ሃሳብ እየተጓዝን የፍቅራችንን መንገድ አጣመምነው። ሃላፊነቱን በእኔ ላይ ብቻ እንደማትጥልብኝ አምናለሁ፤ እንዲሁም የጥፋተኝነትን ፅዋ። ካጠፋሁ ይቅርታ! ግን ጥፋቴ ምን እንደሆነ አልታየኝም። እዚህ ያለሁበትን አጣብቂኝና ፈተና፣ ስቃይ፣ ችግር፣ መከራ ብትመለከት እንኳን ቅያሞት ሃዘን ይገልህ ነበር። እኔ አንተን የማልቀየምህ ለምን መሰለህ?..ሁሉን ነገር ስለማታየው፣ የስደትን ኑሮ በሰው ሃገር ስላልተረዳህልኝ፣ እኔም ኢትዮጲያ እያለሁ እዚህ ችግር ያለ ስለማይመስለኝ፣ አንተም ከእኔ የተለየ አስተሳሰብ ስለሌለህ፥ ለዚህ ነው ብዙም ያላመረርኩብህ። ተስፋ ነበረኝ ከአንድ ከ8 ወራቶች በኋላ አይንህን የማየት፤ ሁሉን ነገር ተወያይተን አምላካችንን በመሃከላችን አኑረን ቃሌን ልሰጥህ፣ ቃልህን ልቀበልህ!! በቃ ተስፋዬ ተሟጠጠ፤ የጓጓሁለትም የመምጫዬ ጊዜ አጠራጠረኝ። ገላዬ እኮ ከምንም በላይ ይናፍቅሃል! እውነተኛ ፍቅር በልቤ ስለመኖሩ መሀላና ምስክር የምትሻ አይመስለኝም። እወድሃለው እኮ! አልተለወጥኩም! ኑሮ አስመርሮኝ፣ ጤና ማጣት ማንነቴን እየተፈታተነ መኖር ስላስጠላኝ እንጂ በአንተም የጨከነ አንጀት ኖሮኝ አይደለም። አንተን ከማጣ ፍቅርህን በልቤ እንደሰነቅኩ ወደ መቃብሬ መውረድን እመርጣለሁ!!..የማይካድ እውነታ ተለያይተን ላንረሳሳ ትልቅ ምሰሶ የብረት ማገር በመካከላችን ጋርደን (ቃልን) በትዝታ እየተንገላታን ማዶና ማዶ ሆነን <ነበረን> መጨዋወት ከጀመርን ሁለት አመታት ተቆጠሩ። ወደ ኋላ ትንሽ ልመልስህ፥ በአብሮነት የፍቅር ጊዜያችን በአንተ ያለወጥኩት ፍጥረት አልነበረም፤ ቢኖር እንኳ አንድ እናቴ ብቻ ነች። ከተጣላኸው ተጣልቼ፣ ከተቀየምከው ተቀይሜ፣ የወደድከውን ወድጄ፣ ያቀረብከውን አቅርቤ፣ አንተን መስዬ ሣይሆን ሆኜህ አብሬህ ዘልቄ ነበር ፍፃሚያችን ያምር መስሎኝ – በተስፋ ጓጉቼ!! ከሁሉ ጋር እንደ ሺህ ዘመን የርስት ባላጋራ የጐሪጥ ስተያይ ኖሬያለሁ። የፍቅር ሃይማኖተኛ ባህታዊ መሆኔና መገዛቴ ጥሩ ባሪያ ተብዬ ያስመሰግነኛል እንጂ አያስንቀኝም! በጥሩ አፍቃሪነቴም እኮራለሁ እንጂ አላፍርም! አንተም ብትሆን እንደማትጠላኝ አውቃለሁ!..»

« .. ውድ የሆንከው ፍቅሬ ሆይ፥ የዚህ አለም ኑሮ አክትሞልኝ ፅዋዬን እስክጎነጭ፣ ተራ ደርሶኝ አንደበቴ ተሸብቦ እጅና እግሬ እስከሚታሰር፣እስትንፋሴ እስከቆመበት፣ በድኔ ወደከርሰ መቃብር ወርዶ የዘላለም እረፍቱን እስካገኘበት እለት የመጨረሻ ደቂቃና ሰኮንድ ድረስ አንተን ከማድነቅና የሕይወቴ እስትንፋስ መሆንህን ከመናገር ወደኋላ አልልም!! እወድሃለሁ! አፈቅርሃለሁና የሚደርስብኝን ችግር፣ የሚገጥመኝን ፈተና አንተን በማስታወስ ፍቅር ትዕግስቱን ሰጥቶኝ በደስታ ለማሳለፍ የቆረጥኩት ዛሬ አይደለም። ወደኋላ ሳስብ “አንተን አፍቅሬ የተሰቃየሁበት፣ በቤተሰቤ የደረሰብኝ የስድብ ናዳ …ሁሉም ትዝታ ሆኖ፥ እንዳያልፍ የለም አለፈ። ያንተ ፍቅር ግን ምንግዜም በልቤ ውስጥ የማይቀልጥ የዘላለም ሻማውን እንዳበራ ይኖራል። መቼም ቢሆን የማይለወጥ ቃል ኪዳኔ ነው!! ከአምላኬ በታች ያመለኩህ አንተን ብቻ ነው!! ብትጠላኝ ላልጠላህ፣ ብትክደኝ ላልከዳህ፣ ብትርቀኝ ላልርቅህ፣ ብትሰድበኝ ብትንቀኝና ብታዋርደኝ፣ ላልሰድብህ ላልንቅህ ላላዋርድህ፣ ከትእዛዝህ ውጭ ላልወጣ “እሺ” ከማለት በቀር መጥፎ ቃላት ላልሰነዝር..ፍቅር ሸብቦ የያዘኝ የአንተው ምርኮኝ ነኝ!! ልቤ ፍቅርህን ከማሽበልበል ውጭ መርዝ አይተፋም። አንደበቴ ፍቅርህን( አንተነትህን) ከማድነቅ በቀር ሬት አይተፋም!! ፍቅርህ ጣፋጭ ነው!! ቁጣህ አስደንጋጭ – ንግግርህ አስፈሪ፣ ቁልምጫህ አጥጋቢ – ፀብህ መራራ፣ ልብህ የዋህ – አስተሳሰብህ ጠንካራ (አስተዋይ)፣ ተክለቁመናህ ማራኪ – ቁም ነገር አዋቂ፣ አላማህ ተወዳጅ – ለችግር ፈጥኖ ደራሽ፣ በአጠቃላይ አምላክ ሲፈጥርህ ከሁሉም ነገር አድሎሃል። እወድሃለሁ! ልቤ ንፁህ ነው፤ ያንተን ፍቅር ብቻ የሚያስተናግድ!! አንደበቴ ቁጥብ ነው፥ አንተን ብቻ የሚያደንቅ!! ለእኔ ምንጊዜም ቢሆን ውድ ነህ!! ከማንም – ከምንም በላይ አፈቅርሃለሁ፤ እወድሃለሁ!! ”አፈቅርሃለሁ” ለሚለው ቃል መተኪያ ባገኝለትና የልቤን ብገልፅልህ ምንኛ ደስ ይለኝ ነበር መሰለህ!?..

ፍቅሬ ሆይ፥ ሁልጊዜ እሰጋለሁ፣ እጨነቃለሁ። አንተ ከእኔ ጋር የመኖር አላማ የሌለህ ስለሚመስለኝ ኑሮዬ የስጋት፣የጭንቀት፣ የብስጭት ይሆናል። ሌላ ምንም አያሳስበኝም። ደግሞም ከአንተ ተለይቼ ከምኖር (ልብ ተነጥቆ መኖር ከተባለ) ሞቴን እመርጣለሁና አደራ የገደል ላይ ሳር የሆነውን ሕይወቴን ነፍስ ዝራበት፤ በደመነፍስ የሚመራ ሕይወቴን፣ አላማቢስ የሆነብኝን ጭንቅላቴን፣ በጭንቀት የሚሸማቀቅ አካላቴን፣ አዝናናው፣ አበረታታው፣ ደባብሰው፣ ነፍሴ በአንተ ትለምልም፤ ካለአንተ ማን አለኝ፤!? አገር ቤት እያለሁ የሰራህልኝን ውለታ እስከ እለተ ሞቴ የማልረሳው ትልቅ ሸክም ነው። < ሸክም ነው ያለኩህ> ከፍዬ ስለማልጨርሰው ነው!! የእኔ ፍቅር አንድ ነገር ልንገርህ?፤ እኔን የአሜሪካ ኑሮ የሚያስደስተኝ፣ እዚህ ያለው ብልጭልጭ ነገር የሚያዘናጋኝ አይደለም። …አንድ ነገር ልብ በል፤ እየፃፍኩልህ ያለሁት ከሌሊቱ 7፡30 በኢትዮ.ሰዓት አቆጣጠር እንደሆነ እወቅ። ከእንቅልፌ ሠአት ላይ ቆጥቤ ነው በድቅድቅ ሌሊት የምፅፍልህ፤ እንጂ ቀንማ ትንፋሽም የለኝ። ምን ያክል ስለፋ እንደዋልኩ ፈጣሪ አይቷል!! የድካሙ ነገር አይነሳ.. እስቲ ተከድኖ ይቀመጥ፤ ስደትን ያየ ይፍረደኝ!?….ግን ዛሬ ደግሞ ደስ ያለኝ ነገር አንተ ማንንም እንዳልተላመድክ ገለፅክልኝ፤ ጥሩ ጌታ ያፅናህ! እኔስ ፀንቻለሁ በአካልም፣ በልብም፣ በመንፈስም። አምንሃለሁ! ባላምንህ ኖሮ መልስ አልፅፍልህም ነበር። አንተስ ታምነኛለህ?..እንደድሮው?..

ውድ ፍቅሬ፥ መኝታዬ ክፍል ጥግ ላይ ተቀምጬ እንባዎቼ በጉንጬ ላይ እየተሽኳለሉ ዱብ.. ዱብ..ዱብ ይላሉ። ፎቶዎችህን አስተውላቸዋለሁ፤ ድብዳቤዎችህን መላልሼ አነባቸዋለሁ፤ ደግሞ እፅፋለሁ። ልቤ ግን ድም -ድልቅታውን አያቋርጥም፤ የመገናኘት ምኞቴን በደውሉ ያስተጋባልኛል!! ያሳለፍነው እኮ እንኳን በነዚህ አመታት ቀርቶ መቼም የሚረሳ አይደለም፤ አይረሳም። አንተ ትረሳለህ ወይ?..ሰሞኑንማ ከመስሪያ ቤትህ ጀምሮ አዘውትረን እናድርበት የነበረው ..ሆቴል ድረስ ጣፋጩ ትዝታ በአእምሮዬ ይመላለሳል። ትዝ ይልህ እንደሆነ በዛ ሰሞን ፍቅር በዝቶ ቅብጥብጥ ሲያደርገን « ውዴ ፍቅር በዛ፤ ልንለያይ ነው መሰለኝ » ስትለኝ እኔም < እባክህ ፍቅሬ እንደዚህ አትበለኝ?> ብዬ አንገትህ ስር ሽጉጥ የምለው፣ በደረትህ የምንፈላሰሰው፣ አትዩብኝ የምለው አይንህ፣ አትንኩብኝ የምለው እጅህ…አረ ስንቱን…ስንቱን ልዘርዝረው!?…ውድ ነህ፣ እንቁ ነህ!

ውድ ፍቅሬ ሆይ፥ ግን አንድ ነገር የማልደብቅህና ከዚህ በፊት ደግሜ ደጋግሜ የፃፍኩልህ፣ በህልሜም ተደጋጋሚ ነገር ስላየሁ ሰጋሁ። አንተን በርግጥ ልመንህ?..እንዴት ነው ልቤ ያምንሃል፤ ህልሜ ግን አስፈራኝ። ስለዚህም ጉዳይ ገልፀህ ፃፍልኝ። ኩርት ያልክ ሁንልኝ!! ልክ እንደቀድሞህ። እንዲያ ከሆንክ ስመጣ አይኔን ለማየት አታፍርም። ከምንም በላይ ደግሞ ሕሊናህ ነፃ ይሆናል!! ካልሆነ ግን ከእኔ ይበልጥ እራስህን ሰላም ታሳጣለህና ጠንቀቅ፣ ሰቅጠጥ በል!! “ምነው ይህቺ ልጅ ጨቀጨቀችኝ” እንደማትለኝ ነው!?..ፍቅር የወለደው የስጋት ጭንቀት ነውና አትፍረድብኝ። ..ቦሌ ላይ ስትሸኘኝ አንድ ጥያቄ ጠይቀኸኝ ነበር፤ < አንቺ ግን ቃልሽን ጠብቀሽ፣ አስችሎች ሌላ ሳትላመጂ እንገናኛለን? > ስትለኝ እኔም “ራሴን የምፈትንበት ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል፤” ብዬህ ነበር። አዎ! አንተን ካላሰብኩ በቀር ገላዬ ፈተናውን በቅጡ ተወጥቷል። በፈጣሪ እርዳታ!! …በብዙ ፈተና ተፈትኜ አለፍኩ፤ ማለፍ ያቃተኝ ግን የልቤን ፈተና ነው። ጊዜ ይፈታዋል!!…አሁን ላበቃ ጥቂት መስመሮች ቀርተውኛል። የደስታ ብስራት ላቋድስህ፤ ከ6 ወራት በኋላ ልመጣ ነው..» አበቃ።…..ይህ እውነተኛ ታሪክ ሲሆን የፍቅር ሴረኞች ለያዩዋቸው። ባለታሪኮቹ….