ሰሞኑን የትግሬ-ወያኔ እጀታ የሆነው የምርጫ ቦርድ፣ በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና በአንድነት ለፍትሕና ዲሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ላይ «ከምርጫ ውድድር የማገድ» ውሣኔ ማሣለፉን ሰምተናል። ይህም ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ፣ አቃቢ ሕግ፣ መከላከያ ሠራዊቱ እና መሰል በ«ሕገ-መንግሥቱ ተቋቋሙ» የተባሉት ተቋሞች በሞላ የወያኔ ሕዝባዊ ድርጅቶች መሆናቸውን በይፋ እና በማያሻማ መንገድ ከታዩባቸው አያሌ ተግባሮች መካከል አንዱ ሆኖ የሚጠቀስ ነው። የምርጫ ቦርዱ ውሣኔ በራሱ ምርጫ ቦርድ የወያኔ ሕዝባዊ ድርጅትና እጀታ ከመሆኑ የመነጨ ብቻ ሣይሆን፣ የተቃዋሚው ጎራ ደጋግሞ በሄደበት እና ምንም ዓይነት ውጤት ባላስመዘገበበት መንገድ መጓዙ ጭምር እንደሆነ ሊስተዋል ይገባል።

የትግሬ-ወያኔ በምርጫ ተሸንፎ ሥልጣን እንደማይለቅ ያለፉት አራት የይስሙላ ምርጫዎች ከበቂ በላይ ነቃሾች ናቸው። ይህን በተመለከተ የ1997ቱን የምርጫ ውጤት ተከትሎ የትግሬ-ወያኔ በወሰደው የድምፅ ነጠቃ፣ ታዛቢ የነበሩት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር አቶ መለስን ለማለስለስ ባደረጉት የማግባባት ሙከራ ያረጋገጡት ሃቅ ነው። አቶ መለስ በወቅቱ የሰጣቸው መልስ፦ «ኢሕአዴግ በምርጫም ሆነ በኃይል ሥልጣን ከለቀቀ የሚጠብቀን አንድ እና አንድ ብቻ ነው። ይኸውም በአገር ክህደት ተከሰን ወህኒ መውረድ ነው። በመሆኑም ለ፲፯(አሥራ ሰባት) ዓመታት አፈር ግጠን የጨበጥነውን ሥልጣን በሕዝብ ድምፅ አንለቅም።» ሲል ነበር እቅጩን እና የማይለወጠውን የትግሬ-ወያኔን ዓላማ የገለጸው። በተመሣሣይ ሁኔታ የሕወሓት እና የኢሕአዴግ የፖሊት ቢሮ አባል የነበረው አቶ ገብሩ አሥራትም «ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ» በሚለው መጽሐፉ የሚነግረን ይህንኑ ነው። ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን የሰጠውም ውሣኔ የዚሁ ተከታይ አካል በመሆኑ፣ ድርጊቱ አስገራሚም፣ አስደንጋጭም አይሆንም። ባለፉት ፳፬ (ሃያ አራት) ዓመታት የኖርንበት ዓለም የታዘበው ዕውነታ ነውና። አስገራሚና አስደንጋጭ የሆነው ተቃዋሚው በወያኔ ሁለንተናዊ ፍላጎት ቁጥጥር ሥር መሆኑን አለመገንዘቡ ነው። እኒህ ተቃዋሚዎች ጉዟቸው ያልተለወጠ እና በየአምስት ዓመቱ በሚደረግ የምርጫ ዘመቻ የተገዛ ነው። ይህ ጉዞ ለውጤት ያላበቃ መሆኑ ተደጋግሞ እየታዬ፣ ውጤት እንደማያስገኝ በታወቀ መንገድ መጓዙ፣ ችግሩ ከመንገዱ ሣይሆን፣ ከተጓዡ እንደሆነ ትግሉ የሚገኝበት ሁኔታ ያሣያል። ስለሆነም ተቃዋሚ ኃይሎች ከ1997ቱ የምርጫ ሂደት እና ውጤት ከታዩት አዎንታዊ እና አሉታዊ የጉዞ አቅጣጫዎች ትምህር የቀሰሙ አይመስልም።

ሁለተኛው የተቃዋሚ ድርጅቶች መሠረታዊ ችግር በአደረጃጀታቸው ላይ ያጠነጠነ ነው። የትግሬ-ወያኔ በማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ብቻ ሣይሆን በዕድሮች ሣይቀር የራሱን ሥውር መዋቅር አስርጎ አደራጅቷል። ሰሞኑን በመኢአድ እና በአንድነት ላይ የተከሰተው ችግር ግን፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች የትግሬ-ወያኔን የሤራ ስልት ባለመገንዘብ ከነ አየለ ጫሚሶ ዓይነት ሠጎ ገቦች ድርጅቶቻቸውን ማጽዳት አለመቻላቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሣያል። ሰለዚህ የአደረጃጀት ሥልታቸው የወያኔን ሠርጎ ገቦች ሊያንተረትር በሚችል መልክ እስካልተቃኘ ድረስ፣ በምንም ሁኔታ የትግል ጉዞ አቅጣጫቸው በወያኔ እና በአጋሮቹ ላይ ተጽዕኖ ሊያሣድር አይችልም። ይህም ብቻ አይደለም፤ ተቃዋሚው የሙጥኝ ብሎ የያዘው «በሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ብቻ የትግሬ-ወያኔን በምርጫ አሸንፈን ሥልጣን እንይዛለን» የሚለውን ብቸኛ የትግል መሣሪያው አድርጎ መያዙ፣ ለትግሬ-ወያኔ ሠርጎ መግባት የተመቻቸ ሁኔታ ከመፍጠሩ ባሻገር፣ የነቁትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀላሉ የአገዛዙ ዒላማ እንዲሆኑ አድርጓል። ይህም ትግሉን ተተኪ መሪዎች በማሣጣት መሪ አልባ በማድረጉ፣ የሕዝቡን የወኔ ሥንቅ እንዳሟጠጠ በድርጅቶቹ ውስጥ በቂ ትኩረት የተሰጠው ያለመሆኑን ያመለክታል።

የተቃዋሚው ኃይል የትግሬ-ወያኔን ባሕሪ የሚመጥን የትግል ሥልት መከተል ባለመቻላቸው፣ ወያኔ «ግሞ» ሲል «ጥንቦ» ማለት አልቻሉም። በተደጋጋሚ በአገር ቤት ካሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚደመጠው የትግል ስልት፦ «በሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ብቻ የትግሬ-ወያኔን በምርጫ አሸንፈን ሥልጣን እንይዛለን» የሚል ነው። ሆኖም የሰላማዊ ትግል ሥልት በምርጫ ዘመቻ ብቻ የተገደበ አይደለም። የምርጫ ዘመቻ ለሰላማዊ ትግል ጠቃሚ የሚሆነው ዲሞክራሲያዊ ተቋሞች የሚባሉት ማለትም፦ ነፃ እና ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች፣ አቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት እና ወገንተኛ ያልሆኑ የብዙኃን መገናኛ ተቋሞች መኖር፣ ወዘተርፈ፣ በአጠቃላይ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ከማንም ተፅዕኖ ውጭ በነፃ የመሥራት የዜግነት መብት ሲረጋገጥ ነው። እነዚህ ተቋሞች በሌሉበት ሁኔታ ግን፣ በምርጫ ፖለቲካ ወያኔን ከሥልጣን እናወርዳለን ብሎ ምርጫን በብቸኛ የትግል መሣሪያነት የሙጢኝ ብሎ መያዝ፣ ታጋዩ ሕዝብ ሥቃይን እና በደልን ተለማምዶ የ፵(አርባ) ቀን ዕድሌ ነው ብሎ እንዲያምን እና ለወያኔ አገዛዝ ምቹ እንዲሆን ሠፊ በር የሚከፍት መሆኑ በግልፅ ሊታመንበት ይገባል። በተግባርም የሚታየው ይኼው ነው። የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ መዋቅር፣ የፍትህ አካሎች እና የብዙሃን መገናኛ ተቋሞች በአንድ ዘረኛ ቡድን ፍላጎት እና ቁጥጥር ሥር በዋሉበት ሀገር፣ በምርጫ ሥልጣን እረከባለሁ ማለት ሸንበቆ ያፈራል፣ በቅሎ ትወልዳለች፣ ዝንብ ማር ትጋግራለች፣ ፀሐይ በምሥራቅ ትጠልቃለች እንደማለት ይቆጠራል። እንደሞረሽ-ወገኔ እምነት፣ ሰላማዊ ትግሉ የተለየ መንገድ መከተል ይኖርበታል። ወቅታዊ የትግሉ መፈክር «ለዲሞክራሲ፣ ለዕኩልነት እና ለብልጽግና» ሣይሆን ቅድሚያ ለነፃነት ትግል መሆን አለበት። አገር እና ሕዝብ ሳይኖሩ፣ ዲሞክራሲ እና ዕኩልነት ሊታሰቡ የሚችሉ ጉዳዮች አይደሉምና!

በመሆኑም፣ የተቃዋሚው ጎራ፣ የትግሬ-ወያኔን እንደተኩላ ከብቦ የሚቦጫጭቅበትን፣ አጠቃላይ ሕዝባዊ እንቢተኝነትን የትግሉ መርህ አድርጎ ሊንቀሣቀስ ይገባዋል። ስለዚህ ቀዳሚው የትኩረት አቅጣጫ መሆን ያለበት በየአካባቢው ያለውን የትግሬ-ወያኔን የስለላ መዋቅር በመበጣጠስ፣ ሕዝቡ የራሱ አለቃ የሚሆንበትን ዘዴ በመሻት፣ የትግሬ-ወያኔን እና አጋሮቹን ለነፋስ በመስጠት፣ የአገዛዝ ዕድሜያቸውን ለማሳጠር መንቀሣቀስ ነው። ይህ ደግሞ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከመሀል እስከዳር ሕዝቡን በማደራጀት በእንቢተኝነት ስሜት እንዲነሣ ማነቃነቅ ያስፈልጋል። የትግሬ-ወያኔ አፋኝ ቡድን የኃይል መከፋፈል የሚፈጠርበት፣ ለቅልብ ጦሩ ሆድ መሙያ የሚከፍለው በጄት የሚያጣበት፣ በገዥው ቡድን መካከል የኃሣብ መከፋፈል የሚፈጠርበት፣ የማስፈጸም አቅሙ የሚሟሽሽበት፣ እርስ በርሳቸው የሚጠራጠሩበት ሁኔታን የሚፈጥር ሥራ መሠራት አለበት። ለዚህም በደህንነቱ፣ በሠራዊቱ፣ በፖሊሱ፣ በቢሮክራሲው መሀል ሠርጎ በመግባት ዓላማ እና ዕቅዳቸውን ማክሸፍ ያስፈልጋል። ሕዝቡም «ላልወከልነው አካል ግብር አንከፍልም፣ የእኛ ባልሆኑ ተቋሞች አንገዛም፣» የሚለውን ስሜት እና እምነቱን ሊያጎለብት ይገባል። በትግሬ-ወያኔ የተለያዩ የንግድ እና የአገልግሎት ተቋሞች፣ ማለትም፥ የትራንስፖርት፣ የሆቴል፣ የንግድ ቤቶች እንዳይጠቀም በልዩ ልዩ መንገዶች በማስተማር ወያኔ እና አባሎቹን ከማናቸውም ማህበራዊ እና ባህላዊ እንቅስቃሴዎች በማግለል ብቻቸው እንዲቆሙ መደረግ አለበት። «መጡብን» ሳይሆን፣ «መጣንባችሁ» ሊባሉ ይገባል። ከእንግዲህ ተቃዋሚው ጎራ ሙሾ ማውረዱን ማቆም አለበት። መርዶ የሽንፈት እንጂ፣ የድል ምልክት ባለመሆኑ፣ «እንዲህ ሆን፣ እንዲ,ህ ተደረገን» የሚሉት እሮሮዎች ሊገቱ ይገባል።

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት የትግሬ-ወያኔ በሁለቱ የሰላማዊ ትግል አራማጅ ድርጅቶች ላይ የወሰደውን እርምጃ የተመለከተው ከትግሬ-ወያኔ ጉዞ እና ዓላማ አንፃር የሚጠበቅ እንጂ፣ ዱብ ዕዳ እና እንግዳ ነገር አድርጎ አይደለም። በአንፃሩ «ማሽላ ሲያር ይስቃል» እንዲሉ፣ ይህ እርምጃ ለፀረ-ወያኔ ትግል እልህ፣ ቁጭትና የመጠቃት ስሜትን የሚፈጥር ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም የተቃዋሚው ጎራ በአንድ ብሔራዊ ዓላማ ዙሪያ እንኳን መሰባሰብ ባይችል፣ በፀረ-ወያኔ አቋሙ በአንድ ግንባር ወይም ኅብረት ሥር እንዲሰለፍ ሠፊ በር የከፈተ ያህል ይቆጥረዋል። ስለዚህ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የሚገኘው ተቃዋሚ ኃይል ከምንጊዜውም በበለጠ ተቀራርቦ በመነጋገር በትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ላይ የተጠናከረ እና ሁሉን- አቀፍ ትግል እንዲያደርግ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት ስም ጥሪያችንን እ,ናቀርባለን።

ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!
ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!
የትግሬ-ወያኔ ዘረኛ ቡድን ነው፤ በመሆኑም መወገድ አለበት!

የአማራ ክልል ባለስልጣናት የኮንስትራክሺንና ቤቶች ልማት ኤጀንሲ በባህርዳሩ ግዮን ሆቴል ላይ ያለውን የባለቤትነት መብት እስካሁን ማስከበር አልቻሉም፡፡

ታኀሳስ ፲፮(አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከፌደራል ፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት የልማት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ተረክቦ ቦታውን ለልማት ለማዋል ዝግጅት የጀመረው የክልሉ የኮንስትራክሺንና ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ሆቴሉን ነጻ ለማድረግ ከህዳር 15 ቀን ጀምሮ አገልግሎቱን እንዲያቋርጥ እና በውስጡ ያሉትን የግለሰብ ንብረቶች ለማስወጣት ያደረገው እንቅስቃሴ ለአንድ ወር ያህል አለመሳካቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ኤጀንሲው በቁጥር ኮቤልኤ-ዋሥ/32/1108 በቀን 16/ 03/07ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ በግቢው ውስጥ የሚገኙትን የግለሰብ ንብረቶች ከ15/03/07 ዓ.ም ጀምሮ በህጋዊ መንገድ እንዲያወጡ በመጠየቅ፣ ንብረቱ ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ የማያወጡ ከሆነ በቤቱና በግቢው ውስጥ ለቆዩበት ጊዜ ሁሉ በቀን ሃያ ሽህ ብር እና ሌሎች ኪሳራዎችን የቤቱ ባለቤት የሆነው የክልሉ መንግስት ተወካይ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ኤጀንሲ የሚያስከፍል መሆኑን በመግለጽ ንብረቱ እንዲነሳ በመጠየቅ ሆቴሉን አሽጎ ሰራተኞችን መበተኑ ታውቋል፡፡

ለአስራ አምስት ቀናት ቢጠብቅም ምንም ውጤት ያላየው ኤጀንሲ በ01/04/07 ዓ.ም ባወጣው ድጋሚ ደብዳቤ « መንግስት በቦታው ላይ ያቀደውን የልማት ስራ እርስዎ ንብረትዎትን ባለማውጣትዎ ምክንያት ሊያቆም ስለማይገባ በግቢው ውስጥ ያለውን ንብረት ወደ አንድ ቦታ በማሰባሰብ የልማት ስራውን ለማስቀጠል ስላስፈለገ እቃው በሚሰባሰብበት ወቅት በእርስዎ በኩል በታዛቢነት የሚኖር ሰው ሰኞ ታህሳስ 8ቀን 2007 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ሆቴሉ መግቢያ በር እንዲገኝ እያሳሰብን የእርስዎ ተወካይ ወይም ታዛቢ ባይገኝ ሌሎች ታዛቢዎች በተገኙበት በግቢው ውስጥ ያለውን ዕቃ ወደ አንድ ክፍል የሚያሰባሰብ መሆኑን እየገልጽን መንግስት ይህንን እና ሌሎች ለስራው የሚያስፈልጉ ወጭዎችን ቀደም ሲል በተሰጠዎ ማስጠንቀቂያ መሰረት ከእርስዎ እንደሚጠበቅ አንዲያውቁት እናሳስባለን፡፡” ብሎአል።

በባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት የአቶ መለስ ዜናዊ የቅርብ ዘመድ አቶ ወልዱ ወልደ አረጋይ መንግስት ማግኘት የነበረበትን ከ900 መቶ ሺህ ብር በላይ እንዳያገኝ ያደረገ ታክሰ በማጭበርበር ወንጀል ተከሰው ወልዱና ቤተሰቡ ኃላፊነት የተወሰነ የግል ማህበር በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ የምዕራብ ጎጃም ዞን የባህርዳር ምድብ ችሎት ውሳኔ ማስተላለፉን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የውሳኔ መዛግብት ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።

የምዕራብ ጎጃም ፍርድ ቤት ባህርዳር ምድብ ችሎት ወልዱና ቤተሰቡ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ አቶ ወልዱ ወልደ አረጋይ እና አቶ ብስራት ወልዱ ወልዳረጋይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብስቦ ያለማሳወቅና ያለመክፈል እንዲሁም የተጨማሪ እሴት ታክስ ባልሆነ ደረሰኝ ግብይት በማካሔድ ወንጀል በአመት ስድስት ነጥብ ሶስት ሚልዩን ብር መሰብሰባቸው መጠቀሱንና ከዚህም ለመንግስት መግባት የነበረበት ከስድስት መቶ ሺ ብር በላይ ለግል ጥቀማቸው አውለዋል በማለት ተከሳሽ ወልዱ ወልዳረጋይ በ7 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ አንደኛ ተከሳሽ ወልዱና ቤተሰቡ ሀላፊነቱ የግል ማህበርን በተመለከተ በህገ-ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በመሆኑ በወንጀል ህግ አንቀፅ 90/3 መሰረት የተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብስቦ ያለማሳወቅ፣ ያለመክፈል ወንጀልና ግብር ለመንግስት ያለመክፈል ወንጀል ክሶች እያንዳንዳቸው የብር 10 ሽህ መነሻ ቅጣት፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ባልሆነ የደረሰኝ ግብይት ማካሔድ ወንጀል ክስ ደግሞ ብር 5 ሺህ ባጠቃላይ 25 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጫ እንዲከፍሉ ውሳኔ መተላለፉን ዘግበናል፡የባህርዳር ነዋሪዎች በድርጅቱና በልጅቻው ላይ የተሰጠውን ውሳኔ ቀልድ ነው ማለታቸውም ይታወሳል ፡፡

ከ10 ቀን በፊት ከባህር ዳር ማረሚያ ቤት ከገዢው መንግስት ባለስልጣናት በተሰጠ ቀጭን ትዕዛዝ የእስር ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁ ሳይሆን ሳይጀምሩ የተፈቱት አቶ ወልዱ ወልደ አረጋይ ፣ ኤጀንሲው በሰጠው ማስጠንቀቂያ መሰረት ንብረታቸውን ያላነሱ ሲሆን በኤጀንሲው ውሳኔ መሰረት ንብረታቸውን ላላነሱበትና ልማቱን ላደናቀፉበት 30 ቀናት ከ600 ሽህ ብር በላይ እንደሚጠበቅባቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡፡የባህርዳሩ ግዮን ሆቴልን ለረዢም አመታት በአምስት ሽህ ብር የክራይ ዋጋ ሲጠቀሙበት የነበሩት አቶ ወልዱ ወልደ አረጋይ ኤጀንሲው እንዲከፍሉ የወሰነባቸውን ገንዘብ መክፈል ሳይሆን በሌሉበት እና በህግ ጥላ ስር እያሉ በማናለብኝነት ሆቴሉ በመዘጋቱና ሰራተኞችንም በመበተኑ ላደረሰባቸው ኪሳራ የክልሉን የኮንስትራክሺንና ቤቶች ልማት ኤጀንሲን በህግ ለመጠየቅ ከጠበቆቻቸው ጋር እየተመካከሩ መሆኑን እማኞች ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

አቶ ወልዱ ግዮን ሆቴልን የሚያክል ድርጅት የአቶ መለስ ዜናዊ ዘመድ በመሆናቸውና በትጥቅ ትግሉ ወቅት መረጃ በማቀበል ላገለገሉበት እንደውለታ ተቆርጦላቸው እጅግ እርካሽ በሆነ መንገድ በሆቴሉ ከ20 አመታት በላይ ሲጠቀሙበት መቆየታቸው በክልሉ ህዝብ ከፍተኛ ቅሬታ ያስነሳ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። አሁንም ባለስልጣናት ደፍረው የፍርድ ቤት ትእዛዝ ለማስፈጸም እንዳልቻሉ ታውቋል።

ወያኔ/ህወሓት ያደራጃቸው ምሊሽያዎች በአፋር ነዋሪዎች ላይ ተኩስ ከፈቱ

አኩ ኢብን አፋር ለዘ-ሐበሻ እንደዘገበው፦

ትናንት ማክሰኞ 18/02/2007 በአፋር ክልል በሰሜናዊ ዞን በኮናባ ወረዳ በትግራይ ታጥቂ ሚሊሻዎች በኮናባ ፈራስዳገ ቀበሌ ነዋሪዎች ላይ ጦርነት የከፈቱ ሲሆን ቦታውን በቶክስ እሩምታ ሲያምሱት ማርፈዳቸውን ከቦታው የሚወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ለጊዜው ከአፋር ነዋሪዎች በኩል የቶክስ ምላሽ አላገኙም! ከቀኑ 8:00 ሰዓት ሲሆን የተጀመረው ይህ ቶክስን ተከትሎ ከኮናባ ወረዳ ብዙ ወጣቶች ተሰብሰበው በፍጥነት ወደ ቦታው የደረሱ ሲሆን በዛን ጊዜ የኔትዎርክ አገልግሎት ወዲያው ተቋርጧል። እስካሁን ከአፋር ነዋሪዎች በኩል የተተኮሰ አንድ ጥይት የለም።

የቦታው ምንጮች አያይዘውም «ይህ ደግሞ የአፋር ወጣቶች ለሰላም ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ነው። ነገር ግን አስገዳጅ ነገር ከተፈጠረ የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመከላከል ከየቦታው ተሰብስበው ዝግጅት ላይ ናቸው።» ብለዋል። ከኮናባ አንድ ስሙን ሊናገር ያልፈለገ ወጣት እንደነገረኝ «ይሄ በህወሓት ሆን ተበሎ የሚደረግ ትንኮሳ በመሆኑ የአፋር ወጣቶች በበሰለ አስተሳሰብ ለሰላም ያላቸው ፈለጎት በትዕግስት አሳይተዋል።» ብሏል። አያይዞም «ኔትወርክ ራሱ የጠፋው ለሌሎች መረጃ እንዳይደርስና የአፋር ህዝብ እንዳይነሳ በመፍራት ነው» ሲል አክሏል። አሁንም ቦታው ውጥረት እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ የኮናባ ወረዳ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊን አስተያየት ለማካተት ያደረኩት ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

ምንጭ ዘሃበሻ አማርኛ ገጽ