አቶ ፈቃዱ ደሪሎ ከአባቱ ከአቶ ደሪሎ ተክለማሪያምና ከናቱ ከወ/ሮ ጥሩነሽ ደረሳ መስከረም 6 ቀን 1948 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ።

አቶ ፈቃዱ በበረራ መሐንዲስነት ከ20 ዓመታት በላይ እጅግ የላቀ የሥራ ልምድ ነበረዉ። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በ1964-65 ዓ/ም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተግባረዕድ ት/ቤት ገባ። የሙያ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በሰኔ 15 ቀን 1965 ዓ/ም ዝነኛ በነበረዉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጠረ። የበረራ ፈቃድ በመያዝ በቦዪንግ 707/720 እና 727/737/767 ((Boeing 707/720 b/727/737/767) ላይ አገለገለ። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዉስጥ በመሥራቱ ወደ ተለያዩ የአዉሮፓ፤ ኢስያ፤ ኩባና አፍሪቃ አገሮች የመዘዋወርና የመሥራት ዕድል አገኘ። ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እድሜ ልኩን እጅግ የሚወዳቸዉን ጓደኞች አተረፈለት።

በ1985 ዓ/ም ሂትሮ አይሮፕላን ጣቢያ ላይ ለቦዪንግ 76 ጥገና በመመደብ በሎንዶን ከተማ እስከ 1990 ዓ/ም ድረስ ሠራ። በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በርክሼር ዉስጥ ላነግሌይ በሚባል ቦታ ከኖረ በኋላ በ1989 ዓ/ም ወደ ሎንዶን ከተማ ከቤተሰቡ ጋር በመዞር በምሥራቅ አክቶን ተቀመጠ። በነዚህ ዘመናት ከርሱ ጋር ያሳለፉትን ደስታ ቤተሰቦቹና ኋደኞቹ እስካሁን ያስታዉሳሉ።

ለተለያዩ ኩባኒያዎች የሠራ ሲሆን በመጨረሻ የሠራዉ ለኤየርክራፍት ሴርቪስ ኢንተርናሺናል ግሩፕ (Aircraft Service International Group) ነበር።

አቶ ፈቃዱ ከወ/ሮ አይናለም በሻህ ጋር በኢትዮጵያ ዉስጥ የተጋባዉ በ1974 ዓ/ም ነበር። በ1985 ዓ/ም ወደ ሎንዶን ከመላኩ በፊት ኑሮዉም ሥራዉም በኢትዮጵያ ዉስጥ ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ ቤተሰቦቹ መጥተዉ ተቀላቀሉት።

አቶ ፈቃዱ ተወልዶ ያደገዉ ጠንካራ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በሆኑት ቤተሰቦች መሃል ነዉ፤ ይሄም ለመልካም የዕድገት ደረጃና ጠንካራ አምልኮት አድርሶታል። በየዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ በሄደ ቁጥር ቤተሰቦቹንና ኋደኞቹን ከማየቱ በፊት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፀሎት ያደርስ ነበር። ጊዜዉን በደስታ የሚያሳልፈዉ ከቤተሰቦቹ ጋር እቤት ዉስጥ በመሆን ነዉ፤ ሰፖርት ፕሮግራሞችን ይመለከታል፤ የተሌቪዥን ጥያቄዎች ይከታተላል፤ የበረራ መጻሕፍትን ያነባል፤ መኪናዉን ያጥባል፤ ይጠግናል።

መልካም ባል፤ ጥሩ አባትና ቆራጥ አያት ነበረ። ቅርቡ የሆኑት የሥራ ባልደረቦቹና ቤተሰቦቹ ዝምተኛነቱንና ተቖርቋሪነቱን ይመሰክራሉ።

የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ አቶ ፈቃዱ በሰላም በተኛበት ቦታ በ65 ዓመቱ ማክሰኞ መስከረም 16 ቀን 2014 ዓ/ም ከዚህ ዐለም በሞት ተለየ፤ ሞቱም በተፈጥሮ ምክንያት መሆኑ በአጣሪዎቹ ኮሮኔሮች ተረጋግጧል።

ቤተሰቦቹም የሚከተሉት ናቸዉ፤ ባለቤቱ ወ/ሮ ዓይናለም፤ ሁለት ልጆቹ ዮናስና እዮብ፤ የልጅ ልጆቹ፤ ረዲኤት፤ አቤልና ሲሳይ ሲሆኑ 6 ወንድሞቹና እህቱ ግርማ፤ ሙሉ፤ ታምሩ፤ ታደለ፤ ብርሃኑና አክሊሉ ናቸዉ።

ቸሩ አምላካችን ነፍሱን በመንግሥተ ሰማያት ያኑርልን፤ ለቤተሰቦቹና ወገኖቹ በሙሉ ጽናቱን ይስጥልን አሜን።