http://www.eaglewingss.com/
እስከመቼ ነው?
ዛሬ ውስጤን የሚያናውጠው ማዕበል፡ ከጥቂት ግለሰቦች በስተቀር የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ አእምሮ እንደ ትንሽ ታንኳ እያናጋ፡ አንዴ ከራሱ ምናብ የሃሳብ ቋጥኝ ጋር፡ አንዴም ከአምላክ ምስጢራዊ ፈቃድ ዓለት ጋር እያጋጨው እንዳለ ይገባኛል። ታዲያ፥ ስሜት በቀላሉ ሰብረው በማያመልጡት የምሬት ሠራዊት ሲከበብ፣ ተስፋ በድቅድቅ የሞት ጭጋግ ውስጥ ሲደበቅ፣ ለነፍስና – ለስጋ፡ ለአእምሮና – ለእጅ፡ እንደ መፃፍ ያለ ከባድ ህመም የለም። ልብ ብርቱ በሆነ የሀዘን ጦር ሲቆፈር፡ ጉልበትን ሰብስቦ ሃሳብን አምጦ መውለድ አይደለም፡ እውነታንም ቁጭ ብሎ መታዘብ ይከብዳል። ያኔ፥ እፅፋለሁ ላለ ጣት፡ ብዕር እንደ ብረት ለሽክም ይከብዳል። ቢሆንም ግን፡ የቆሰለው አእምሮዪ በተደጋጋሚ አንድ ጥያቄ ይጠይቀኛልና፡ በዝምታ ከማስታምመው – ይኸው ተንፍሼ ልገላገለው ሞከርኩ።

የማከብርህ ኢትዮጵያዊ ወገኔ፥ ተፈጥሮ ሳትሰስት፡ ከዓለም ሁሉ አብልጣና አድልታ የሰጠችንን የዘፍጥረት እና የስልጣኔ ብኩርና፡ እንደ ኤሳው ለሆዳችን – ለምስር ወጥ – ሸጠን፡ እስከመቼ ነው እንደ ዝቃጭ እንደ አተላ፡ ህይወታችን ክብር፣ ሞታችን ዝክር የሚያጣው? እስከመቼ ነው ዘረኞች የዘሩልንን አዝመራ ስናጭድ – ስንውቃ ውለን፡ ሲመሽ ምርት ሳይሆን ምሬት ሰብስበን ወደ ቤታችን የምንገባው? እስከመቼ ነው ሰሜን ጫፍ ተቀምጠው፡ ከደቡብ ጫፍ የተወረወረ ጠጠር ሊስታቸው እስከሚሳነው ድረስ እየሰፉ እና እየሰቡ ያሉት የፖለቲካ መሪዎቻችን፡ ከአፍንጫችን በላይ ያንጠለጠሉልንን የነፃነት ካሮት ላንደርስበት-ላንበላው አህያ ሆነን ስንጋልብ እና ስን’ጋለብ ዘመን የሚያልፈው? እስከመቼስ ነው ምስኪኑ ወገናችን ደረቱ ላይ ተደግኖ የተተኮሰበት የመሳሪያ ጥይት እስኪስተው ድረስ በየሰከንዱ-በየደቂቃው በረሃብ እየከሳ እና እያነሰ፡ በየበራሃው በኖ ተኖ፣ በየባህሩ ዝሎ ሰጥሞ የሚያልቀው?

በወንደሞችህ የግፍ ሞት ልብህ የተሰበረው ኢትዮጵያዊ ወገኔየነፃነት ትግል እኮ ዓላማ እንጂ ባህል አይደለም። ተጀምሮ ማለቅ፤ መነሻ አምድ፣ መደምደሚያ ግብ ሊኖረው ይገባል። የባርነት ሰንሰለት አልበጠስ ብሎ ከከረረ፡ አልቋጭ ብሎ ከረዘመ፡ እንደ ወግ-ባህል ከዘመን ዘመን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ከተሻገረ፡ ቆም ብሎ ማስተዋል፤ መሪ ተመሪን መቃኘት ግድ ይላል።

ዛሬ በኣራቱም የዓለም ማዕዘናት ህዝባችን እየቆጠረ ላለው ፍዳና ሰቆቃ መነሻ ምክንያቱ ፖቲካዊ እንጂ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አንዳልሆነ ለመረዳት፡ ማንም የርዕዮተ ዓለም ፈላስፋ አሊያም የምጣኔ ሃብት ሊቅ መሆን አይጠበቅበትም። ፖለቲካዊ ችግር ደግሞ ከምንም በላይ ፖለቲካዊ መፍትሔን ይሻልና፡ ፖለቲካችን እንዴት እና ወዴት ነው? ዜጎቻችን ትላንት- ሳውድ ዓረቢያ፡ ዛሬ- የመንደቡብ ኣፍሪካሊቢያ ላይ እየተጋቱ ያሉትን መከራ ከምንጩ ለማድረቅ፣ ነገም ተመሳሳይ ጥፋት ካይሮ ላይ ከመከሰቱ በፊት ችግሩን ከችካሉ ለመንቀል ልምን ተሳነን? ጉድለታችን የመሪ? የተመሪ? ወይንስ አጠቃላይ የድርጀታዊ መዋቅር እንከን ነው የሚለውን መጠየቅ እና በአፋጣኝ መመለስ ወቅቱ ይመስለኛል። እርግጥ ነው ዛሬም ቢሆን፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጀቶች ከብሉይ ኪዳን የመማፀኛ ግንብ በተለየ መልኩ መዋቀርና ተቀዳሚ ዓላማቸው ተገዳዩን ማትረፍ እንጂ ገዳዩን ማቀፍ መሆን የለበትም ብዪ አምናለሁ። ዘራፊው ዘርፎ፣ ገዳዩም ገድሎ እጁ ሲዝል እና ሲደከም፡ ሀጢያቱን ለማስተሰረይ፣ ከህዝብ ለመታረቅ ዘሎ የሚቀላቀለው እና የሚያንቀላፋበት ጎራ – እንደ እኔ ግለሰባዊ እምነት- ወህኒ-ቤት እንጂ አንድነት፣ መድረክ፣ ሸንጎ ወይንም ግንቦት ሰባት መሆን ያለበት አይመስለኝም።

አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ በምድርህ መካከል ሦስት ከተሞችን ለራስህ ትለያለህ። ነፍሰ ገዳይ ይሸሽባቸው ዘንድ ወደ እነርሱ የሚወስደውን መንገድ ታዘጋጃለህ … (ኦሪት ዘዳግም / ምዕራፍ 19 : 2)

ላለፉት በርካታ አመታት እንደታዘብነው ግን፦ ሀገር እንደ ቡሄ ሙልሙል ገምሶ፣ ህዝብ እንደ አክርማ ቀጭቶ፣ ዘርፎ እና አዘርፎ የበቃው ባለስልጣን መሽሽጊያው አንድም ቤተ-መቅደስ ኣለበለዚያም የተቃዋሚው ድርጅት ነው። ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፡ ወንጀለኞች ሰይጣናዊ ባህሪያቸውን በሃይማኖታዊ ጠበል አርጥበው፣ በተቃዋሚ ፎጣ አድርቀው በአዲስ ካባ ብቅ ሲሉ እንደ ቅዱስ መላዕክት የሚሰገድላቸው የአይሁዳውያኑ የመማፀኛ ቅጥር መሆናቸው እስካላበቃ ድረስ፡ የነፃነት ኣላማችን ዕውን የሚሆነው፣ የመከራችን ቋጠሮ በዘላቂነት የሚፈታው – በዕድል እንጂ በትግል እንዳልሆነ መጠርጠር የለብንም።

ከረሃብ ወደ ስድብና ውርደት ተመሳሌነት ያሻገሩህ ኢትዮጵያዊ ወገኔ፥ ጽሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት ዛሬም እንደ ትላንቱ የማሰምርበት እውነት ቢኖር፦ ህዝባችን ከእንሰሳ ባነሰ ክብር በየመንገዱ ተቀጥቅጦ ሲገደል ዝም ብሎ ከማየት የከፋ የወገን በደል የለምና፡ እንደ ዜጋ የሚጠበቅብንን ሁሉ በማድረግ የተረፉትን ለመታደግ፣ የረገፉትንም ቤተሰቦች ለማፅናናት ዛሬ! አሁን! ቃል ብቻ ሳይሆን ከትግሉም መሃል መግባት ይኖርብናል።

መፈራረሳችን፣ ስድባችን፣ መዋረድና መታረዳችን ዓላማቸው ብቻ ሳይሆን አለማቸውም ለሆነው ጎጠኞች፡ የሃዘን ሲቃችን ብሔራዊም ባይሆን ጎሳዊ መዝሙራቸው ነው። የድረሱልን ለቅሶና ጩኸታችን፡ “አከርካሪውን ሰበርነው – ጥርሱን አወለቅነው” ብለው ለተሳለቁብን ዘረኞች፡ የዓላማቸውን መሳካት የሚያበስር ደወል፣ የግባቸውን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ቃጭል ከመሆን ባሻገር ፋይዳ እንደሌለው ተረድተን፤ ራሰን፣ ወገንን እና ሃገርን የማዳን ዘመቻውን ከራሳችን በራሳችን መጀመር ብልህነት ነው። የዓባይን ውሃ ለኣባዮቹ ትተን፡ የወገናችንን፣ የአዛውንት እናትና አባቶቻችንን የኣይን ፍሳሽ- ዕንባ – ለመገደብ፡ የትግል ቦንድ (ውህደት) መፍጠሩ ከመቼውም በላይ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ላይ ደርሰናልና ወንድ – ሴት፣ እስላም – ክርስቲያን ሳንል በተግባር በስነ-ምግባር እንተባበር።

ኤግል-ዊንግስ-ሶሳይቲ በደቡብ ኣፍሪካ፣ በየመን፡ አንዲሁም በሊቢያ ህይወታቸው ለጠፋው ዜጎቻችን የተሰማንን ከፈተኛ ሃዘን ስንገልፅ፡ ለቤተሰቦቻቸውም አምላካዊ መፅናናትን እየተመኘን ነው። ችግሩ ከመሠረቱ አልተወገደምና፤ በኣሁኑ ወቅትም በአደጋ ወስጥ ላሉት ወንድሞችና እህቶቻችን፡ ከበረከታችን ሳንሰስት በጉልበት፣ በዕውቀትና በገንዘብ የምንችለውን ሁሉ ከማደረግ ባሻገር ትግሉ ለመከራው ዘለቄታዊ መፍትሔ እስኪያመጣ ድረስ፡ የአምላክ ሰፊ መዳፍ የመጠለያ ድንኳን እንዲሆናቸሁ ምኞትና ፀሎታችን ነው።

http://www.eaglewingss.com/
ተከለከለ አሉ የንጉስ ኣዳራሽ … የክት ያልለበሰ አይገባም በጭራሽ!

ተከለከለ አሉ … የንጉስ ኣዳራሽ
የክት ያልለበሰ … አይገባም በጭራሽ

የክት ልብሱን’ማ የሃገሪቱን ኣንጡራ ሃብት እንክት አድርገው ከበሉት በላይ ማን አሳምሮ ሊለብሰው? ባይሆን በኮፒ ራይት ካልተጠየኩ- እኔው ራሴ አሻሽዬ ብዘፍነውስ? ተከለከለ አሉ የንጉስ ኣዳራሽ … ተኩሶ ያልለበሰ አይገባም በጭራሽ !

ምርጫ እና ተቃዋሚ ድርጀቶችን በለመለከተ፡ ሰሞኑን የጦር ሰራዊቱ ልበል የጦር ኣራዊቱ አውራ ያሳዩት ንቀትና ዛቻ ሲገርመን፤ የፖሊስ ኣራዊቱ እርግጫ ተከተለ። ይኼ ነገርርር … ብለን ገና የጀመርነውን ዓረፍተ-ነገር ሳንጨረስ፡ ምርጫ ቦርድ ድሞን ደመደመው ፦ ምርጫ’ም መኢአድ’ም አንድነት’ም የሉም አለን። ለነገሩ ”ምን ተስፋ አይቆርጥም” ሆኖብን አንጂ፡ ሰዎቹ ከ-እምበር ተጋዳላይ ወደ እብሪተኛ ገዳይ የተሻገሩበት የ97ቱ ምርጫ፡ አሳፋሪም አስተማሪም ምዕራፍ ነበር።

ተቃዋሚ ድርጅቶች አድገው እና ረዝመው ከንጉሱ አዳራሽ በተጠጉ ቁጥር፡ መንግስት እንደ ሸገር መናፈሻ ጥድ በራሱ መልክ እና ቅርጽ አሳጥሮ ይከረክማቸዋል። ትላንት ቅንጅት፣ ዛሬ ደግሞ አንድነት እና መኢአድ። ታዲያ ምን ተሻለ ጓበዝ? በክቱ ልብስ ካልሆነ፥ ያው ያዘቦቱን (የልምዱን) ተኩሶ መግባት እንጂ.

ፍቅርሽ አስጨንቆ … መላወስ አቃተኝ
ተደናበርኩለሽ … ጥይት እንደሳተኝ
ሳተና ነበርኩኝ … ተኳሽ በመውዘሬ
ለዘበናይ ብቻ … እጄን ሰጠሁ ዛሬ

እርግጥ ነው የሩቁንም ሆነ የቅርቡን ሰላማዊ ሰልፍ ስንታዘብ፡ ህዝባችን ከፍተኛ ጨዋነት ይታይበታል። ፖሊስ ከሰራዊት ምግባርና ተግባር ወጥቶ አራዊት ሆኖ ሲናከስና ሲራገጥ፡ ህዝቡ ዱላወን በትዕግስት ተቀብሎ፦ ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱን ስብሮ ወደ ቤቱ በወሳንሳ ይገባል። በወገናዊነቴ ስቃዩና መከራው ቆጭቶኝ ስሜታዊነት ቢፈታተነኝም፥ ትዕግስቱን ግን ከምስራቅ አውሮፓና ከሰሜን አፍሪካ ሰልፈኞች ጋር አወዳድሬ ”ለምን?” ብዬ አልጠይቅም። ወያኔ እንጂ ዘረኛው፡ ህዝቡ አይደለ’ማ። መንግስት እንጂ ለህዝቡ ፍቅር ያጣው፡ ህዝቡ ዛሬም ቢሆን በመቻቻል አብሮ የመኖር ባህሉን አልጣለውም። ጫካ ውሎ ጫካ አድሮ፡ አውሬ ሆኖ ለመናከስ፣ ያደገበትን የከተማ ስርዓትና ህብረተሰባዊ ገብረ-ገብ ለመፈረካከስ ህዝቡ ወያኔ ወይንም የዱር እንስሳ አይደለም። ያ ባይሆን ኑሮ’ማ ሳተናነቱና ተኳሽነቱ የዘር ነበር። የትላንቱ የአያት ቅድመ-አያቶቻችን እልህ ኣሻራ፡ በዚህ ትውልድ ደም ወስጥ ደብዛው ጠፍቷል የሚል ዜጋ የለም።

ውስጡን እንፈትሽው ከተባለም፥ የዩክሬንና የካይሮ አብዮተኛ እንደ ረሃብተኛ በአዉሮፓና አሜሪካ፡ አልፎም በሀይማኖትና በወገንተኝነት በተደራጁ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት እየታገዘ፦ ከብስኩት እስከ ወተት፣ ከውስጥ-ልብስ እስከ ብርድ-ልብስ በሬሽን እየታደለው ጌታዋን እንደተማመነችው በግ ላት ውጪ አደረ እንጂ፥ እንደኛዎቹ ደፋር ወንዶች፡ አንድ ሃገሩን አፍቅሮ አንድ ራሱን ሆኖ መች ተሰለፈ? መቼ ተቀጣቀጠ? ባይሆን፦ ሰልፉ እና ተቃውሞው የተፈለገውን ትኩሳት እንዲያሳይ ”ዲያስፖራው ምን ሰራ? ምን አገዘ?” የሚለውን ጥያቄ ማንሳት አግባብ ነው። ከመደብደብ፡ ይደባደብ ካልን፦ ለደሙ ማድረቂያ፣ ለቁስሉን ማጠቢያ፣ ለራሱ እና ለቤተሰቡ መደገፊያ፣ ጉልበት ሞራል የሚሆነው ምን ረብ ያለው ስራ ተሰራ? ፖለቲካችን- የአፄ ምኒልክ አብራክ ፡የአቦይ ስብሃት በረከት፡ የሌንጮ ለታ ብላቴና እያለ ከራሳችን አልፎ ግቢ ውስጥ ኣንድ ሆኖ የሚኖረውን ህዝብ እንዲበታተን ከመመረዝ ወጪ ምን ወዝ ኣለው? ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው።

በፍቅር ማነቂያው … ዶሮ እንዳይል በከንቱ ኧሪ አንቺን ወዶ
ክራሩን ሰት ሰሚ … ብቅ በይ ቆሜያለሁ ከበርሽ ማዶ

እስቲ ዘር፣ ድርጅት ሳይከፋፍል፡ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይል፡ በአደባባይ በዱላና በሰደፍ የሚቆስለውን ሰልፈኛ የሚያሳክም የሚያግዝ አንድ የጋራ ጥሪት (fund) ይኑረን? እስቲ የወገን ድካም እና ኧሪታ ከንቱ እንዳይሆን ከጎኑ ሆነን ትግሉን እናክርረው? በሰለፉ እና በእምቢተኝነቱ ሂደት የሚደሙትን፣ የሚቆስሉትን፣ ኣልፎም ከስራና ከትምህርት ገበታቸው ላይ የሚታገዱትን የሚበዥ ኣንድ ኣካል ሲቋቋም፣ ወገናዊነቱና የትግል አጋርነቱ በተግባር ሲረጋገጥ፡ ያኔ የተፈለገውን ትኩሳት በአደባባይ ማየት ይቻላል። ለዚህም በጎ ተግባር፡ ራሳችንንም ሆነ እኛን የመሰሉትን ለማሳመን፣ አምነንም ግዴታችንን ለመወጣት አቅም እና ጉልበት እንዳለን ለአፈታ አልጠራጠርም።

አፈር ጭቃው ሲቆፈር፣ በማጥ በድጡ ህዝብ ሲያልቅ ዳር ቆመን ስንታዘብ ውልን፤ ደልድዩ ተሰርቶ ሲያልቅ’ና ሲመረቅ፥ መቀስ ይዞ ሪቫን ለመቁረጥ፣ አበባ ታቅፎ ከፊት ለመራመድ መሽቀዳደም፡ ያስተዛዝባል። ዛሬ ህዝባችን መሻገሪያው እንጂ የጠፋው አሻጋሪው አይደለም። ስልጣኔ እና ዕውቀት ወረርሽኝ ሆነው፡ በትንፋሽ’ና በንክኪ እንደማይተላለፉ የመጣነው አየነው፡ የቀሩትም አደመጡት። ውጭ ሃገር መኖሩ፡ ከፈረንጅ ጋር ውሎ ማደሩ፡ ሀገርቤት ያለውን ፖለቲካና ፖለቲከኛ አስንቆ እኔ ድልድይ ሆኜ አሻግርሃለሁ ለማለት ድፍረት አይሆንም። ይልቅስ ብቅ ብሎ ተቀላቅሎ፡ ትግሉን ጎን ለጎን –በብረት እና በብልሃት- ማስኬዱ ይበጃል።

አይወጣም ደረጃ … ቢፎክር ሴቼንቶ
እንደ እኔ ካልሄደ … በፍቅር ተገፍቶ
መድፈሪያሽ ወርቅ ነው … ብርም አይገዛሽ
ልብ የሌለው ሀብል … ግድም አይሰጥሽ

ወያኔ “ተፎካካሪ ድርጅት ስለሌ እንጂ ስልጣኔን በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ“ ብሎ ሰለፎከረ፣ ይወጣል፣ ይሄዳል ብሎ ማሰቡ ዘበት ነው። ሰባ የጦር ጄነራል፣ ሺህ መቶ-አለቃ (ቼንቶ) – በፍቅርም ይሁን በፀብ፣ በአጥንትም ይሁን በብረት ካልተገፋ በስተቀር እንዴት ይነቃነቃል? ዛሬማ ብሩንም ወርቁንም ይዘውታል፤ ምን ያስደነግጣቸዋል? ከኪሳቸው ተርፎ- ህዝቡ የባለቤትነት ጥያቄ ቢያነሳ እንኳ በሚል ስጋት፡ “የዲያስፖራው የጋራ ሃብት ነው” ብለው ሊያታልሉት፡ ህዝብ ዘርፈው፣ ቅዬ ንደው እራሳቸው ለሚገነቡት ፋብሪካ ተለጣፊ ባለሃብት የሚሆን ውሻና ድመት ከባህር-ማዶ ማፈላለግ ጀምረዋል። ምናለ – ህዝቡም ደደብ፣ አዲስም ደደቢት አንዳይደሉ ቢገባችው? ለነገሩማ ንቀት ይዟቸው እንጂ ልዩነታችንንስ ተረድተወታል።

እስቲ ላለመናቅ ትግላችን ሀሞት ይኑረው፤ የምር ሆኖ ይምረር። እንደዛ ጥርሱን እንደ በቆሎ እሸት ፈለፍሎ አንደበላው ሆዳም ቀልደኞች አንሁን። እነሱም ግድ ያላሉን፦ ከማወራትና ሀ-ብሎ አፍን ከመክፈት ውጪ ልብ የላቸውም ብለው ነው። ያለውን አለ፣ የሌለውን ደግሞ የለም እንበል። በባዶ መኮፈስ፣ ገብስ ሳይሆን ወረቀት እየበላ የሚዘለውን ፈረስ መጋለብ አስናቀን እንጂ ወንዝም አላሻገረን። ታላላቆቻችን በኣዲስ ዘመን በሳተላይት ያደሉን ኣዲስ የትግል ስልትም ቢሆን፡ አንደ ታናናሾቻችን የእንቁጣጣሽ ንድፍ- በወረቀትና በቀለም አሽብርቆ ቀረ። የወሬ ሳይሆን የስራ፣ የተግባር ዓመት ነው የተባለለትም 2007፡ ይኸው ፀጥ ረጭ እንዳለ የስነ-ምግባር ዓመት መስሏል፤ ፀባይ የምንገዛበት። ጆሮዬ የቱንም ያህል ቢረዝም፡ በእግሮቼ ኣውራ ጣት ቆሜ ብንጠራራም፡ ከገመትኩት አካባቢና ድንበር 7000 ማይልስ ርቆ ዲሲ ላይ ጠቢቡ ሳይሆን ጠባቡ ሰለሞን ከተኮሳት ጥይት በስተቀር፡ የሰማሁት ኮሽታ፣ ያየሁት ብልጭታ የለም። እኛ ሳንተኩስ ቀኑ ተተኩሶ ዓመቱ ተጋመሰ። ነው ወይስ- ዘመኑ ሰልጥኖ፣ መሳሪያውም ዘምኖ – ታንክ እና ክላሹም አንደሽጉጡ ሳይለንሰር (silencer) ተገጠመለት?

ጓበዝ፥ ብዙ ከማውራት ትንሽም ብትሆን የአቅምን መስራት ይበጃል – ያስከብራል። የመሀሉ ጦር ደፍሮ ለጨበጣው ሲቁነጠነጥ፡ እኛ “አቅም አለን” ካልን- ዳር ሆነን ለቀናት ቢያንስ ለሰዓታት የተኩስ ሽፋን መስጠት ይሳነናል? አለበለዚያ፦ መድረኩ ስለቀረበ ብቻ ሀ፡ብሎ አፍን መክፈቱ ሌላ ትርጉም እስካልተሰጠው ድረስ ለጠላት ማዛጋት፡ ለወዳጅ ማዘናጋት ነው። አሁን ይበቃል። እውነትን ተናግሮ ህዝብን ወደ ኣንድ አቅጣጫ መመለሱ፡ ሀይልን አጠናክሮ ትግልን ያጎለብታል፣ ድልን ያቀርባል። ልብ ሳይኖረኝ አፌን ከፍቼ ሀ-ብል፡ ማን ግድ ሊለው?

ይውጣ ይወጣ … እግሬ ይዛል በእርምጃው
ከሷ አይብስም … ሰባ ደረጃው

የዛሬ ፅሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት፡ የአንድነት ሃይሎች በድፍረት የቆረጡለትን- ተመልሶ አደባባይ የመውጣት ወሳኔ ላደንቅ እወዳለሁ። እርግጥ ነው የተከፈለውና የሚከፈለው መስዋዕትነት ከባድ ነው። ሆኖም ግን፡ ለእናት ሃገር ሺ ጊዜ ቢሰለፉላት፣ እግር ቢዝል – ቢደክምላት ያንስባታል እንጂ አይበዛባትም። የሶስት ሺህ ዘመን ማንነትን፣ የአብሮነት ፍቅርንና አንድነትን ለመጠበቅ ሲባል፦ ሰባ አይደለም ሰባ ጊዜ ሰባ-ሰባት ደረጃ ይወጣል፤ ሰባ አይደለም ሰባ ጊዜ ሰባ-ሰባት መሰናክል ይዘለላል።

መጣሁ ከኮሪያ ይዤልሽ ሰዓት … ይቀጥላል

*PS. የዘፈኑ ስንኝ ትርጉም ሙሉ በሙሉ የዚህ ፅሁፍ ፀሀፊ እንጂ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከግጥሙ ደራሲም ሆነ ከዘፋኙ ፍቺ ጋር መስተሳስር የለውም