የኢትዮጵያዊነት ፌስቲቫል የግል ዘገባ – በልጅ ተክሌ

ብዙዎች አስቦክተውን፡ ብዙዎችም አስጠንቅቀውን ነበር

አንዳንዶቹ፡ “አይ አይሳካላችሁም፡ እንደው ነው የምትደክሙት” ብለው አስፈራርተውን ነበር። ገሚሶቹም፡ “ባዶ ሜዳ ታቅፋችሁ ትቀራላችሁ” ብለው ፈልፍለውብን ነበር። የተቀሩት ግን “በርቱ፡ እኛም እንመጣለን” አሉን። እነሆ ገሚሱን ታቅፈን፡ ገሚሱንም አዝለን ወደፊት ገሰገስን፤ የዛሬ አስር ወር በሀሳብ ደረጃ፡ የዛሬ ስድስት ወር በህግ ደረጃ፡ የዛሬ ሁለት ወር ወዲህ ደግሞ በተጨባች የተያዘውን ፌስቲቫል አርብ ስንከፍት ግን፡ ገና ከመክፈቻው ሰዓት አስቀድሞ የመክፈቻው አዳራሽ ላይ የተጠራቀሙት ሰዎች ቁጥር ተስፋ ፈንጣቂ ነበር። ትልቁ ስጋቴ የመክፈቻው እለት ነበር። አርብ ጁላይ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ግን ሰዉ አዳራሹን ጢም አድርጎ ሞልቶ፡ ውጪው ሁሉ ተትረፍርፎ ሳይ፡ እንደተሳካልን፡ እንደሚሳካልንም አወቅሁ። የአርቡን የመክፈቻውን ዝግጅት ዝርዝር ዘገባ እዚህ ይመልከቱ። በሆነው ሁሉ ልቤ ሀሴትን አደረገች።

ከስድስት ወራት በፊት መሰለኝ የፌስቲቫሉን እቅድ አውጥተን የፌስቲቫል ቦታ አሰሳ የተያያዝነው። እንደ ዲሲ ባለ ለፌስቲቫል አይደለም ለሰርግም፤ ቦታ ከአመት አንዳንዴም ከአመታት በፊት መያዝ ባለበት ከተማ (ታላቁ የዋሽንግተን ዲሲ የስብሰባ ማእከል ቢያንስ ከ16 ወራት በፊት መያዝ እንዳለበት ይናገራል) በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያስተናግድ ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። የቦርድ አባሎቻችንና ጓደኞቻቸው፡ ኢትዮጵያዊያን የሚያውቋቸውን ቦታዎች ሁሉ አሰስናቸው። ባልደረቦቻችን ወደየስቴዲየሙ ወረዱ። አንዱ ቦታ ሳቁባቸው። “በጣም ዘግይታችኋል፤ ለሚቀጥለው ዓመት ከሆነ እናስብበታለን” አሏቸው። የዲሲ ቦታዎች ሁሉ ሊሳኩ አልቻሉም። ወይ በምንፈልገው ቀን ተይዘዋል፡ ወይንም ላንድ ቀን ነው ያላቸው፡ ወይንም ዋጋቸው አይቀመስም። አንዱ ቦታ በቀን 10 ሺህ ዶላር ይጠይቃሉ። ሌላኛው ቦታ በቀን 15 ሺህ ይላሉ። ይሄ ጸጥታንና የመድህን ዋስትናን አይጨምርም። ጽዳትና ድንኳን፡ መብራትና እንትን ሲታከልበት ምን ያህል እንደሚፈጅ አስቡት። ለኛ ቢጤ ባለጸጋ ጠባቂ ለሌለው ህዝባዊ ድርጅት ደግሞ በቀን 20 ሺህ ዶላር ከየት ይመጣል? እኔ እንጃ።

ወደ ሜሪላንድ፣ ወደቨርጂኒያ፣ ወደጎረቤት ከተሞች፣ ወደባልቲሞር ሁሉ መሄድ አስበን ነበር። ቦታ ልናገኝ አልቻልንም። በዚህም የተነሳ እስከ ሚያዚያ መጨረሻ ድረስ በኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበር መስራቾች ዘንድ ሽብርና ስጋት ነበር። አይታችሁ እንደሆነ ዝግጅታችን አንድ ወር እስኪቀረው ድረስ በየድረ-ገጹ የለጠፍነው፡ በየመንደሩ የበተንነው ማስታወቂያ “የኢትዮጵያዊነት ፌስቲቫል በዋሽንግተን ዲሲ” ይላል እንጂ የት እንደሆነ ዝርዝር መረጃ አልነበረውም። እነሆ ሁላችንም በያቅጣጫው ምህላ ያዝን። አንዳንዶቹ ዱአም ሳያደርጉ አልቀሩም። የተሳሉም አይጠፉም። እነሆ በመጨረሻ ጥናዊው ጆርጅታውን ዩኒቨርስቲን ከሰማይ ተጣለልን። እ/ር ረዳን። አላህም ተመለከተን። የቦታው መገኘት በተበሰረ ግዜ፡ የነበረው ደስታና ፌሽታ ወደር አልነበረውም። የቴሌኮንፈረንሱ ክፍል በጭብጨባና በደስታ ተናጋ። ለዝግጅታችን አንድ ወር ከምናምን ጉዳይ ቦታ ተገኘ። እነሆ በዚያም መሰረት የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ፌስቲቫል በሰሜን አሜሪካ በጥቂት ኢትዮጵያዊያን ያላሳለሰ የ24 ሰዓት ትጋት፣ በአያሌ ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ፣ በሺሆች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ድል፣ ከጁላይ 1 እስከ ጁላይ 3 በዋሽንግተን ዲሲ ተደረገ። ይሄ ታሪክ ነው። እንግዲህ ታሪክ ጀመረ ማለት ነው።

አርብ፡ ጁላይ 1፡ 2011 ከሰዓት በኋላ

የዚህ የሶስት ቀን ፌስቲቫል በጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ አርት ጋለሪ ሲከፈት፡ መክብብና አምሳል የተሰኙ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ሰዓሊያን የስእል ስራዎች፤ የአርበኞች የፎቶግራፎች ስብስቦች በጆርጅ ታውን ዩኒቨርስቲ የአርት ፕሮፌሰር የሆኑት ፕሮፍሰር ክሊፎርድ የመክፈቻና ንግግር እንዲሁም የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበረሰብ ሊቀመንበር አቶ ሼክስፒር ፈይሳም የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ለረጅም ግዜ ከኢትዮጵያዊያን አይን ተሰውራ የቆየችውና የዚህ ፌስቲቫል የክብር እንግዳ፡ የቀድሞዋ የፖለቲካ እስረኛ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ሰላምታ፣ የመጻህፍት ፍርሚያ፣ የግጥም ንባቦች፣ የታሪክ ማስታወሻዎችና የሙዚቃ ቅምሻዎች በታዋቂ ገጣምያን የቀረቡ ሲሆን አርቲስት ማርታ ቀጸላ፣ አርቲስት መኮንን፣ እነ አቶ ንጉሴ፣ እነ ልጅ ናትናኤል፡ ብዙ ኢትዮጵያዊነትን ያስታወሱ ስሜት ቀስቃሽ ስራዎች ቀርበዋል። የመጀመሪያውን ቀን ዘገባ እዚህ ላይ ይመልከቱ። እኔ ራሴ፡ እኔ ተክሌም የሰው ስራዎችን አቅርቤያለሁ። የበድሉ ዋቅጅራን፡ “አገር ማለት የኔ ልጅ” የተሰኘ ግጥም።

ሀገር ማለት ልጄ…

ሀገር ማለት ምስል ነው፤ በህሊና የምታኖሪው …

… የስኬት ሰንደቅ የምታደርጊው፣

ቢያስጠላሽ የማትቀይሪው፡፡

እሱ አይደል የሚያሰቃየን የሚያንገላታን፤ የሚያሳብደን? ኢትዮጵያዊነታችንን አንቀይረው ነገር። በድሉ ወርቅ አድርጎ ገጠመው። እኔም ወርቅ አድርጌ ነው ያቀረብኩት። ያንን በተደረገልኝ ጭብጨባ ማወቅ ትችላላችሁ።

ስነቃሎችም ነበሩ፡

አልቤኑ ሰው ለምዶ፣ በልጅጉ ሰው ለምዶ

እንደ ላም እረኛ፣ ይሰማራል ማልዶ።

ጎበዝ ይሙትና፤ ፈሪ ይኑር ቢሻው

አተላ መሸከም ይችላል ትከሻው።

እሳት ቢያዳፍኑት፤ ይመስላል ይጠፋ

እውነት አይምሰልህ፤ አንገቴን ብደፋ። …. አሁን እንኩዋን አንገታችንን ቀና እያደረግን ነው። ሀተታውን ልቀጥል።

ቅዳሜ፡ ጁላይ 2፡ 2011

የሁለተኛው ቀን ዝግጅትም የተሳካ ነበር። ዝርዝሩን እዚህ ላይ ይመልከቱ። በሁለተኛው ቀን ተጨማሪዎቹ ዝግጅቶች፡ ከሰዓት በፊት፡ የስምንት ቡድኖች የማጣሪያ የእግር ኳስ ጨዋታ ተደርጓል። እንዲሁም፡ ኢትዮጵያዊውን የቀድሞ የአለማቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ባለስልጣን አቶ ፍቅሩ ኪዳኔንና ዶ/ር ዳንኤል ክንዴን ያሳተፈ አስደሳች ውይይይት ተካሄዷል። በተለይ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ስለኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ከጉግስና ገና ጨዋታ እስከ ቅርብ ግዜ ታሪኩ፡ እያዋዙና ተሰብሳቢውን እያዝናኑ ተናግረዋል። በሩጫ ውድድሩ፡ ወጣት ቤተልሄም ከቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ያሸነፈች ሲሆን፡ በእግር ኳሱም እንዲሁ ለዋንጫው ውድድር ያለፉት ቡድኖች ታውቀዋል። በዚህ እለት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በድጋሚ ወደ ሜዳው ወጥታ ለህዝቡ ሰላምታ ሰጥታለች። የመጀመሪያው የነጻነት ሰላምታ። ያንድ ደቂቃ ከግማሽ ንግግርም አድርጋለች።

ከዚያ ቀደም ብሎ ግን ጠዋት ወ/ት ብርቱካንና ሌሎች አገር ወዳድ ሴቶች የቁርስ መርሀ-ግብር ነበራቸው። ሴቶቹ የሆድ የሆዳቸውን ተጫውተዋል። ንግግራቸው እኛን ወንዶቹን የማይጎዳ እንደሆነ ነው የተነገረኝ። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበረሰብን የተለየ ሚያደርገው፡ በመስራችነት፡ በቦረድ አባልነት፡ እንዲሁም በበላይ ጠባቂነት ሴቶች ያላቸው ከፍተኛ ድርሻ ነው። ቅዳሜም፡ በሁዋላ እንደማነሳው እሁድም፡ ከምንም በላይ ማራኪና የኛን ስብስብ የተለየ የሚያደርገው ሌላው ነገር የልጆች አምባ ነው። ወ/ሮ ዳያናና ጓደኞቿ የዚህን የልጆች አምባ ወጪ ሙሉ በሙሉ ሸፍነው ህጻናትን ሲያዝናኑ፣ ሲያስተምሩ እንዲሁም ሲያመራምሩ ውለዋል። እነሆ መለስተኛ የድምጽ ችግር ቢታይም የቅኝት ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን፣ የአቢሲኒያ ተወዛዋዦች አመታት ወደሁዋላ እየወሰዱ ወደፊት እየመለሱ ሲያጫውቱን ውለዋል። ቅኝትን ሁሉም ስለሚያውቃቸው ብዙ ማንሳት አያስልጋቸውም። የቅኝት የባህል ቡድን በሁለቱም ቀን ባሳየው ትጋት ሊመሰገን ይገባዋል። አቢሲኒያ የዳንስ ቡድንም በደንብ ይጠቀስ። የጥላሁን ገሰሰን “ውባይናማ … እያየችኝ በፈገግታ … ጉድ ሰራችን፡ እኔም ሳያት …” የሚለውን ዘፈን ከነነፍሱ መስማት ከፈለጋችሁ፡ ጥላሁን ገሰሰን የናፈቀ፡ አቢሲኒያ የዳንስ ቡድንን እዩት። ዘወትር አርብና ቅዳሜ በጂ 2 ጂዮርጂያ መንገድ ላይ። ዲሲ። አቢሲኒያዎች፡ ጥላሁንን ከነነፍሱ እንዳስታውሰው ረድተውኛል። ማለፊያ ነበሩ።

ከዚያ እሁድ መጣ፡ ጁላይ 3፡ 2011 መዝጊያው፡

የልጆች አምባ በጠዋቱ ተሰናድቷል። ጠዋት እስከ ከሰዓት የዘለቀ እግር ኳስ ነበር። ገመድ ጉተታም እንዲሁ። የጆንያ ሩጫ። የ4 ሺህ ክንድ ሩጫም ነበር። የሸቀጥና ምግብ መሸጫዎች ሰዉን ሲያገለግሉ ነበር። በር ላይ ቆሜ ስለነበር ከቨርጂኒያ ሪችመንድ፤ ከሰሜን ካሮላይና ከአትላንታ፣ ከዴንቨር፣ ከካሊፎርኒያ፣ ከሲያትል፣ ከዳላስ፣ ሂውስተን፣ ላስ ቬጋስ፣ ቶሮንቶ፣ ኦታዋ የመጡ ሰዎችን ተመልክቻለሁ። እሁድ፡ የሙዚቃ መሳሪያው ድምጽ ተስተካክሎ፤ ብሄራዊ ስሜት ቀስቃሽ የባህል ጨዋታዎች ተሰምተዋል። ለሰላሳ ደቂቃ የዘነበ ድንገተኛ ዝናብ ቢያቋርጠውም ከግማሽ በላይ ህዝብ ከዝናቡም በኋላ ተገኝቶ በሙዚቃና በብርቱካን ንግግር ተጠናቋል። ዝናቡ ሲያወርደው ደንግጬ፣ አዝኜ ደግሞም ተሸማቅቄም ነበር። የኛ ጥፋት መስሎኝ ነበር። የጸሀዩ መክረር፤ የዶፉ መውረድ የኛ ጥፋት እንደሆነ ቢሰማንም የህዝቡ ማጽናኛ አበረታች ነበር። የዋንጫውን የእግር ኳስ ጨዋታ ትንሽ አንድ ሰዓት ቀደም ብለን ጀምረን ቢሆን ኖሮ ምናልባት ብርቱካን ሚደቅሳ ያለጥድፊያ ዋንጫውንና ሰርቲፊኬቱን አበርክታ በጽሁፍ ያዘጋጀችውን ንግግር ትናገር ነበር። ነገር ግን ብርቱካንና ዝናቡ የተነጋገሩ ይመስል እነሆ እሷ ወደመድረክ ስትወጣ ህዝቡም ሲያጨበጭብ፤ ዝናቡ ለሱ የተጨበጨበለት መስሎት ዶፉን አወረደው።

ሰው ግን በድርቅ የከረመ ህዝብ ይመስል፤ ዝናቡ እየደበደበውም፡ ፊቱ ላይ ደስታ እንጂ ቁጣ ወይንም ክስ አይነበብበትም። “በጣም ይቅርታ ይሄንን ቀድመን መገመት ነበረብን፡ በጣም ይቅርታ ስል” ሰዉ ግን በመልሱ “እንዴ እናንተ አላመጣችሁት ምን ታደርጉት ነበር። እንደመውም እንኩዋን ዘነበ” እያለ ያበረታታን ነበር። ዝናቡን እንደ መዓት ላየው ስሞክር፡ ህዝቡ ግን እንደበረከት እንዳየው አደረገኝ። ዝናቡ ሲጋረፍ፡ ሰዉ በድንኳን ውስጥ ተቃቅፎ ቆሟል። ህጻናት ዝናብ እንዳይመታቸው ሰዉ ርስ በርሱ ይጠባበቅ ነበር። ካሁን አሁን ያባራል ስንል፡ 15 ሀያ 25 ሰላሳ ደቂቃ ጣለ። አንዳንድ ሰዎች ወደመኪናቸው እየገቡ መውጣት ሲጀምሩ ሳይ፡ ተስፋ ቆርጬ ነበር። መርሀ ግብራችን ካሰብነው ሰዓት ሁለት ሰዓት ቀደም ብሎ ተጠናቀቀ ብየ፤ ቆጭቶን ነበር። ነገር ግን ትንሽ ማባራት ሲጀምር ሰዉ ከየመሸገበት ብቅ ብቅ ማለት ጀመረ። ወጣ። ሁሉም ወደመቀመጫው መመለስና የሚሆነውን መጠባበበቅ ጀመረ።

ከዝናብ በኋላ ህይወት፡ እነሆ ብርቱካን ልትናገር ነው

የድምጽ መሀንዲሱ መጎርጎር ጀመረ፤ የተወሰኑት መሳሪያዎች አይሰሩም። በውሀ ርሰዋል። የተወሰኑት ግን ይሰራሉ። ትናንት አንድ ቀን አስቀድሞ ያበሳጨኝ ብርሀኑ ተዘራና ጓደኞቹ መስፍን ዘበርጋ እንዲሁም አበባ ደሳለኝ ካልተጫወትን እያሉ የድምጽ መሀንዲሱን መጎትጎት ያዙ። በመጨረሻም ተስፋ ቆርጬ የምግብና የሸቀጥ ድንኳኖቹ ጋር ስንጎዳጎድ የድምጽ ማጉያውን ድምጽ ሰማሁት። ደስ አለኝ። ወደ ሜዳው ስመለስ ሰዎች መከማችት ጀምረዋል። ከዝናቡ በፊት ከነበረው ህዝብ 2/3ኛው ወደ ስቴዲየሙ ተመልሷል። ሌሎችም በስልክ እየተጠራሩ በመኪና መምጣት ጀምረዋል። እነሻምበል በላይነህ፣ እነማሪቱ ለገሰ እንዳሉ ነው። ህዝቡ ይጠብቃል። ይህ ህዝብ ምስኪን ነው። ዝናብም ጥይትም እየመታው ይጠብቃል። ይህ ህዝብ ሲያምንና ሲወድ እንዲህ ነው። ብርቱካንስ ትናገራለች? ትመጣለች? ጥያቄ ጀመረ። ትመጣለች ተባልን።

በዝናቡ ወቅት ከምንም በላይ ያሳዘነኝ ግን ከቅድስት ማሪያም ቤ/ክ ለመጡት ሯጮች ያዘጋጀነው ሰርቲፊኬት እንዲሰጣቸው ማድረግ አለመቻላችን ነው። ቤተሰቦቻቸውና የቤተክርስቲያኑ አባት ባሉበት ሽልማታቸውን አበርክተንላቸው ቢሆን ያምር፣ ብርታትም ይሆን ነበር። ቤተክርስቲያኗ ላደረገችልን ትብብር ሳላመሰግን ባልፍ በጎም አይደለም። ይልመድባችሁ። የአሜሪካዊው “የውቦች ስደት” ፊልም ደራሲ ክሪስ ፍላህርቲ ከዝናቡ አንድ ደቂቃ ቀደም ብሎ ሽልማት ተበርክቶለታል። ፈረንጅ ደስ የሚለው እንኳንስ ሰማዩ ደመና አርግዞ እንዲሁም ነገር ማስረዘም አይወድም። ክሪስ ባጭሩ በኋላ ብርቱካንም በንግግሯ የጠቀሰችውን “ኢትዮጵያም እንደቱኒዚያ እንደግብጽ፤ እንደ ሊቢያ ቀን ይወጣላታል” የያዘ ንግግር አድርጓል። በመጨረሻም፡ ብርቱካን መጣች።

ብዙዎች የብርቱካን ነገር እንቆቅልሽ ሆኖባቸው፤ ግራ ግብት ብሎባቸውም ነበር። እንደውም ይህቺ ሴት ከዚህ በሁዋላ ሰው ሆና አደባባይ ወጥታ ትናገር ይሆን? እንደው ምን አገኛት? ምንስ ተስፋ አላት ብለው? ድምጿን ሊሰሙ ፊቷን ሊያዩ ጓጉተው ነበር። በመጨረሻም ብርቱካን በጥንቃቄም ቢሆን፡ ሰዎቹ አንዳች አሁንም ድረስ ያለተገለጠልን ነገር አድርገው ሞራሏን ለመግደልና እነዳትነሳ አድርገው ሊሰብረቷት ቢጥሩም፡ ያንኑ ሰላም-ተኮር ወርቃማ ንግግሯን አሰማችን። ብርቱካን ያደረገችው ንግግር ላይ የኢትዮጵያ ህዝብም እንደነ ቱኒዚያ ለውጥ እንደሚመጣለት ተንብያለች። በመጨረሻም ብርቱካን ሚደቅሳ ሌላ የሚያሳስር ንግግር ተናገረች፤ ኢትዮጵያ ትወደስ፣ ኢትዮጵያ ትደነቅ። ነገር ግን አሁን “ኢትዮጵያ የነጻነት አገር አይደለችም፤ ኢትዮጵያ የፍትህ አገር አይደለችም” አለች። እሁድ ጁላይ 3፡ 2011 ዓ.ም.። ደግመው እንዳያስሯት አልመኝም። እንዳያስሯት ነው ያልኩት። እናዳያስሯት።

እንደ ማጠቃለያ፡

በቦታው ያልነበራችሁ ሰዎች እንዴት እንደምገልጽላችሁ አላውቅም። በመጨረሻም፡ ሁሉም በያቅጣጫው እንኩዋን ደስ ያላችሁ ይለን ጀመር። የተሳካ ነበር። በተለይ ለቤተሰብና ለልጆች ምቹ የሆነ ዝግጅት ነበር። ከሚድሁት እስከሚራመዱት፤ ከሚሮጡት እስከሚዘሉት ኢትዮጵያዊያን ህጻናትና ታዳጊ ልጆች ሜዳ ላይ ወጥተው ሲርመሰመሱ ማየት እንዴት ያስደስታል። እዚያ በቆየሁበት ወቅት የያዘውን ሆቴል ያጋራኝ፡ እንዲሁም የደርሶ-መልስ ትኬቴን የከፈለው ደጉ የድርጅታችን ሊቀመንበር ሼክስፒር ፈይሳ፡ ቅዳሜ ማታና ቀን ባየው ነገር የተሰማውንና አንጀቱን የበላውን ክስተት ሲገልጽልኝ “አንዲት ሴት የሷም ልጅ ከሜዳው ወጥቶ እንዲቦርቅ ፈልጋ” ‘እባክህ የኔም ልጅ ተደባልቆ ይጫወትልኝ’ ብላ ልጇን ባጥር ላይ አቀበለኝ አለኝ። ይሄ ህዝብ እንደተራበ ያየሁት ዛሬ ባይሆንም በሶስቱ ቀናት ግን ህዝቡ ምን ያህል የባህልና ብሄራዊ መድረክ እንደተጠማ፤ መገናኛ እንደራበው፤ አገሩንና ባህሉን፤ ማንነቱንና ኩራቱን የሚዘክርበት፤ የባሌው ከቦሌው፤ የአሰላው ከከሚሴው፤ ተገናኝቶ ከኳስና ጭፈራ ባሻገር ስነጽሁፍን የሚያድንቅበት፣ ስእልን የሚያነብበት፣ ታሪክን የሚያደምጥበት፤ ታሪኩን የሚያተርክበት፡ ውርሱን የሚቆጥርበት መድረክ እንደራበው ተጨማሪ መረጃ ነው ያገኘሁት።

ይሄ ዝግጅት የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ሰዎች ብዙ ናቸው። አንዳንዶቹ ግን እጅግ በጣም አሁንም ይሄንን ጽሁፍ እያነበባችሁ ልታጨበጭቡላቸው የሚገባ፡ እናንተም እንደነሱ ባመት የተወሰኑ ቀናት፣ የተወሰኑ ሰዓታት በፍቃደኝነት ግዜ ሰጥታችሁ ልታገለግሉ እንደሚገባ የሚያስተምሩ ናቸው። ጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ ይመስገን ዘንድ የግድ ነው። ከነአመላችን ስለቻለን። ነጻ የመኪና ማቆሚያቸው ይመች ነበር። አቶ ለማና ጓደኞቹ ለእግረኞችም ከፎጊ ቦተም ባቡር ጣቢያ ድረስ ወደ ስቴዲየሙ የሚያመላልስ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰናድተው ሲያመላልሱ ነው ዋሉት። እንዴት ደስ ይላል። አንዳንድ በጎ ፈቃደኞች ከሰዓታቸው ቀድመው በመገኘት በገንዘብ አሰባሰብ፣ በሱቅ ጥበቃ፣ መንገድና ቦታ በመምራት፣ በጸጥታ ጥበቃ፣ በመስተንግዶ ያገዙን ሲሆን፡ እንደባህል ሆኖ አንዳንዶቻችን ግን በሰዓት ያልተገኘንም ነበርን። አርፍደውም የመጡትን ግን እናመሰግናለን። ዘንድሮ ሳይሳካላቸው የቀሩትን ወደፊትም እንደሚመጡ እንጠብቃለን። በመጨረሻ ግን ሌባ በለጠን። የዚህ ዝግጅት መሳካት ትልቅ ሚና ከተጫወቱት አንዱ ሰዋችን ነዳጅ ሞልተው ገንዘብ ሊከፍሉ ሲሄዱ አንድ ሰው ከአኩራ መኪና ዘሎ ወጥቶ መኪናቸውን አስነስቶ ሄደ። መኪናቸው ተሰረቀ። ሌባውን ይቅር ይበለው።

አመት አውድ- ዓመት፡ ድገምና አመት

የኢትዮጵያዊነት ፌስቲቫል በደማቅ ሁኔታ ተጀመሮ እነሆ ለሚቀጠለው አመት በተመሳሳይ ቦታ በተመሳሳይ ሰዓት ነገር ግን ቢያንስ አንድ ቀን ጨምሮ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዞ በደማቅ ሁኔታ ተጠናቀቀ። የመጨረሻው የድርጅቱ ሪፖርት ይፋ ባይወጣም ይሄ ዝግጅት ቢያንስ ወጪዎቹን ሁሉ እንደሚሸፍንና ለሚቀጥለው አመትም ስንቅ የሚሆን መጠነኛ ገቢ እንደተገኘበት ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይናገራሉ። ባናተርፍም ግን አትርፈናል። በሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሲደሰቱ ከመመልከት በላይ ምን ትርፍ አለ? ኢትዮጵያዊነት ሲገንና ሲከበር ከመመልከት የላቀ ምን ትርፍ አለ? አንዳንዶቹ ምኞታቸውን ይሁን ህልማቸውን ሲናገሩ ለሚቀጥለው አመት፡ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል፣ የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ የታሪክ ሊቁ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ እንዲሁም ወጣቱ ገጣሚና ጸሀፊ፣ በእውቀት ስዩም ለክብር እንግድነት እንደታጩ ይተነብያሉ። እንዳፋቸው ያርግልን። ግን ማን አመት ይጠብቃል። መስከረም ይመጣል። የፈረንጆች አዲስ አመትም ይመጣል። ከምንም በላይ ግን አመቱን ሙሉ፡ የኢትዮጵያዊነት ውርስ ማህበሩ አንደኛው ዋንኛ ዓለማ የሆነውን “የኢትዮጵያዊነት ማእከልን” የመገንባት ስራ ይጀመራል።

በሰዓት አከባበር፣ በድምጽ መሳሪያዎች መሰናክል በኛ በኩል በነበሩ አንዳንድ ግድፈቶች የተበሳጫችሁ ከነበራችሁ ይሄ የመጀመሪያ ዓመት ዝግጅት እንደመሆኑ መጠን እስከመጨረሻው እንደማትከፉ እናምናለን። ይቅርታ ደግሞ ወርቅ ነው። ስፖንሰሮቻችን፡ በቁጥር ብዙ ባትሆኑም፡ ልገሳችሁ ግን ብርታት ሆኖናል፡ ጉልበትም ሰጥቶናል። አንባቢአን፡ ካስታወሳችሁ፡ ባለፈው ያገኛችሁኝ፡ ከኦታዋ ወደ ዲሲ የአሜሪካንን ድንበር ሳቋርጥ ነበር። እነሆ የካናዳን ድንበር አቋርጬ፡ “ንሴብሖ፡ ንሴብሖ” እያልኩ፡ ከዲሲ የተነሳው አውቶብስ ከ12 ሰዓታት ጉዞ በኋላ ወደ ቶሮንቶ እየገባ ነው። ቶሮንቶ የላሊበላ ዱለት ናፍቆኛል። እሱን ልክክ አድርጌ (መንገደኛ፣ በሽተኛ፣ ነገረኛ እና ፖለቲከኛ ከሰኔ ጾም ነጻ ነው) ወደ ኦታዋ ደግሞ ሌላ የአምስት ሰዓት እጓዛለሁ። በሌላ ርእስ እስክንገናኝ … ደህና ሰንብቱ።

የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ድርጅት በሰሜን አሜሪካ፡ የኢትዮጵያዊነትን ውርስ ለማስጠበቅና ኢትዮጵያዊነትን ለመጠበቅ የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆንና ለትርፍ ያልተቋቋመ፡ ድርጅት ነው። አባል መሆን የፈለጋችሁ ወይንም ለማናቸውም መረጃ፡ ethiopianheritagesociety.org ላይ ግቡ።

ልጅ ተክሌ፡ ዲሲ-ቶሮንቶ-ኦታዋ፡ ሰኔ፡ 2011