ኤርትራዊያን በደቡብ ሱዳን (ከአደፍርስ ተሰማ)
አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ደቡብ ሱዳን ከሰሜኑ ሱዳን መቆረስ ትክክል እንዳልሆነ አስምረውበታል። የሻቢያው መሪ ነገር ከተማታባቸው ውሎ ያደረ ቢሆንም እየቆየ ግን የሚሉት ሁሉ አስቂኝ እየሆነ እየመጣ ነው። ነፃነት ወይም ባርነትን ምረጥ ተብሎ ነጻነትን መረጠ የተባለለት የኤርትራ ህዝብ ቀንና ሌሊት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሃገሩን እየሸሸ ለሞትና ለእሥራት እየተጋለጠ ለመሆኑ የየጊዜው የዜና ዘገባዎች ያመላክታሉ።
በቅርቡ ለሥራ ጉዳይ ወደ ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጅባ ተጉዤ የገጠሙኝ ኤርትራዊያንን የኑሮ ሁኔታና የፓለቲካ ሽርክና ላጫውታችሁ። የጁባ ከተማ ይህ ነው የሚሉት ህንጻ የሌለባት፤ ሰው በደመነፍስ የሚመላለስባት፤ ጠበንጃ አንጋች የሚንጋጋባት፤ አሉ የተባሉት የደቡብ ሱዳን ተወላጆች በዘመናዊ ክሩዘር መኪና ከአጃቢ ጋር የሚፈላሰሱበት፤ ባጭሩ የህይወት እሰጣ ገባ አለቅጥ የተሰባጠረባት አሳዛኝ ምድር ናት። በዚህች ከተማ ምግብ ቤቱ፤ ሆቴሉ፤ ኢንሹራንሱ (አዎን ኢንሹራንስ)፤ ሱቆችና ሌሎች ነገሮች የተያዙት በኤርትራዊያን ነው። ለምሳሌ እኔ ያረፍኩበት ሆቴል ለአንድ ሌሊት መቶ ሰላሳ የአሜሪካን ዶላር ሲያስከፍል የሚሰጠው አገልግሎት ሲተመን ግን ሃያ ዶላር ሲበዛበት ነው። የሆቴሉ በዙ ክፍል የተያዘው በደቡብ ሱዳን የጦር ባልደረቦች ሲሆን፤ ቀሪው እንደ እኔው ለሥራ ጉዳይ ብቅ ባሉ የወጭ ሃገር ዜጎች ነው። ታዲያ በዚህ መካከል ነው በደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ባለስልጣናትና በኤርትራዊያን ነጋዴዎች መካከል ያለው ጥምረት ቁልጭ ብሎ የታየኝ። ኤርትራዊያን በዚህች ሃገር ለመነገድና ለመኖር የሚከፍሉት ዋጋ ድብቅና ጋሃዳዊ ነው። ድብቁ ጉቦ ነው። ገሃዳዊው ደግሞ ከአቶ ኢሳይያስ የመረረ አገዛዝ እየሸሹ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚገቡ ሴቶች ያለፈቃዳቸው ዋጋ እንዲከፍሉ መገደዳቸው ነው። አንድ ከሃማሴን የመጣች ሴት እንዳጫወተችኝ። በንግድ ሥራ ላይ የምታያቸው ሁሉም ባይሆኑ ብዙዎቹ የሻብያ ወኪሎች ናቸው። የመነገጃ ገንዘብም ለመነሻ የተሰጣቸው ከሻቢያ ነው። የተነገደው ገንዘብ ትርፍም ወደ ዓረብ ሃገሮች ይላክና ተመልሶ ዕቃ ተገዝቶበት አስመራ ይገባል አለችኝ። እዚህ የምታየን ብዙዎቻችን በኤርትራ ባለስልጣኖች በጎ ፈቃድ እንድንወጣ የተፈቀደልን ነን በማለት ከፍራቻ አንጻር ዙሪያዋን እየተገላመጠች አጫወተችኝ።
ለዚህም ይመስለኛል ሁሉት ነገሮችን ለመታዘብ የቻልኩት። ኤርትራዊያኑ ነጻ ሆነው ስለፓለቲካ መነጋገር አይመርጡም። ወሬው ሲነሳ ጫወታ እንቀይር በማለት በቀልድ ይሸፍኑታል። ለምሳሌ አንድ የድሮ ጀበሃ (ELF) አሁን በኤርትራ ስላለው ሁኔታ ሲያወራን በዙሪያው ተቀምጠው ቢራ ይጠጡ የነበሩ ኤርትራዊያን ሁሉ አንድ ባንድ ወጥተው ሄድ። የኢሳያስ እጅ በቅርብም በሩቅም ይሰራል ፈርተው ነው አለኝ። እናንተ ከኤርትራ ውጭ ያላቹህ እንዲህ የፈራቹሁ በሃገር ውስጥ እንዴት ይሆን በማለት ጠየኩት። እሱን በቃላት መናገር አይቻልም። ባጭሩ የምድር ቤት እሥር ቤት ናት ኤርትራ በማለት እሱም ሃዘንና ንዴት ይዞት ትቶኝ ተፈተለከ።
ከጁባ ወደ ናይሮቢ ለመሄድ አንድ ቀን ሲቀረኝ። ለቁርስ ቁጭ ባልኩበት ሆቴል ውስጥ ፊቱ ያበጠ ሰው ሲገባ አየሁ። ወደ እኔ ቀረብ ሲል ለየሁትና ቁጭ በል ቁርስ እንብላ ምን ሆነህ ነው አልኩት። ተሰብስበው ደበደቡኝ እኮ አለ። እነማን? ያኔ ቢራ እየጠጣን ጥለውኝ የወጡት ኤርትራዊያን። ለፓሊስ አላመለከትክም አልኩት። ወዳጄ ሁሉ በእጃቸው ነው። የሱዳን ፓሊስ (ወታደር) ገንዘብና ሴት ካገኘ ለመዳኘት ጊዜ የለውም። ግደል ብትለው ይገላል አለኝና በሰላም ያድርስህ በማለት ተሰናብቶኝ ወጣ።
ዜና ላይ ኢትዮጵያ ወደ አራት ሺህ የሚሆኑ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ወደ ሱዳን ለመላክ ተስማማች ይላል። በውነቱ ደቡብና ሰሜን ሱዳንን የሚያስታርቅ ምንም አይነት ሃይል አይኖርም። ነገር የተበላሽው ደቡብ ሱዳን ሃገር መሆን ስትመርጥ ነው። እዚህም ላይ ነው ከአቶ ኢሳይያስ ጋር የእኔም ሃሳብ የሚስማማው። ጦርነቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይቀጥላል። እሳቱ እንዳይጠፋ የሚያናፍሱት ብዙ ናቸው። አሁን በደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ጽ/ቤት የሚከፍቱ ሁሉ የሰላሙ ተካፋይ አይደሉም። የሚበልጡት እሳት ለመለኮስ እንዲመቻቸው ስፍራ ለመያዝ እንጂ። ወያኔም ከድሃ አብራክ የወጡ ወጣቶችን ወደማያውቁት ስፍራ በመላክ የእሳት ራት ማድረጉን ማቆም አለበት። ይህ ሰራዊት ተልኮውን(ተልኮ ካለው) እንዳይወጣ አቶ ኢሳይያስ፤ ግብፅና ሌሎችም የአረብ ሃገሮች በሱማሊያ አክራሪ ድርጅቶች በመደገፍ ስፍራ ስፍራ ይዘው እየጠበቁ ነው። የኤርትራዊያን የሰላሳ ዓመት እልቂት ምንም አይነት ለውጥ እንዳላመጣው ሁሉ የደቡብ ሱዳን ነጻነትም በስም ብቻ እንጂ ፍትሃዊነት ኑሮት የደቡብ ሱዳንን ህዝብ በሰላምና በደስታ ከራሱ ጋርና ከጎረቤቱ ጋር እንዲኖር የሚያስችል የነጻነት ድልድይ አይሆንም። በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ከበርቴ ኤርትራዊያንም የደቡብ ሱዳን ህዝብ ሲነቃባቸው የሚጠጉበት ሥፍራ አይኖርም። መዝባሪና ተመዝባሪ ዘለቄታዊ ሽርክና የላቸውምና!
ቆይተን እንይ