ኢትዮጵያዊነት፤ ዘር? መሬት? ሃይማኖት? ወይስ ምን?

ግርማ ከበደ ከሚኒሶታ

ኢትዮጵያዊነት፡ ሰባቱን ቃል ኪዳናት አክብሮ መፈጸም ነው፡፡ ስለሆነም፡ የአምልኮና ያኗኗር ሥርዓት እንጂ፡ የዘር ወይም የአንዲት አገር ብቻ ስም ሊሆን አልተሠራም ነበር፡፡ ነገር ግን፡ ሰባቱን ቃልኪዳናት፡ ከተመሠረቱ ጀምሮ፡ እስከፍጻሜው ድረስ፡ ከሌላው ቦታ ካለሕዝብይልቅ፡ በኢትዮጵያና አካባቢዋ የነበረው ሕዝብ ጠብቆት የነበረ በመሆኑ ምክንያት፡ ዛሬ የምናውቃት፡ የኛ አገር ብቻ፡ ኢትዮጵያየሚለውን ስም ይዛ ቀርታለች፡፡ የ 7ቱ ቃል ኪዳናት ተዋዋዮች ራሳቸው፡ ሙሉ፡ ከመጀመርያው አንስቶ ኢትዮጵያዊ የነበሩ፥ አልያም በሃይማኖትና በአምልኮ ሥርዓት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ናቸው፡፡

፩ . አዳም እና ሔዋን፡ – ራሳቸው በኢትዮጵያ ምድር፡ በግዮን ፈሳሽ ዙርያ የነበሩ፡ የሰው ዘር ሁሉ መገኛ፡ እናትና አባት ኢትዮጵያውያን

፪ . ኖኅ፡ – በኢትዮጵያ ምድር ይኖር የነበረ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ፤ ለአዳምና ለሔዋን የተሰጠውን የጋብቻ ቃልኪዳን፡ ሳያፋልስ፡ አክብሮ የጠበቀ (ኢትዮጵያዊነቱን አጽንቶ የጠበቀ )፤ ልጆቹም (ሴም ካም ያፌት )፡ ኤደን ገነትንና የአባይ ወንዝ ተፋሰስን መነሻ አድርገው፡ ርስት የተከፋፈሉ የኢትዮጵያ ትውልዶች

፫ . መልከጼዴቅ፡ – ሴም ካምና ያፌት ሶስት ትውልድ ሆነው ሲለያዩ፡ አንዱ ካንዱ ተለይቶ ርስት ሲይዝ፡ የሕዝቦች መከፋፈል ሲመጣ ፡ የእግዚአብሔር ዕቅድ ሁሉን ለማዋሐድ እንጂ ለመለያየት እንዳልሆነ ለማሳየት፡ የክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ በኢየሩሳሌም የተቀመጠ፡ ከሶስቱም ዘር በአራተኛው ትውልድ ላይ የተወለደ፡ ኢትዮጵያዊ ውሕደት ነው፡፡ (አዳምና ኖኅ አንድ ኢትዮጵያውያን ሆነው ከነርሱ አብራክ ብዙ አይነት ሰው ቢወጣም፡ እነዛ ሁሉ ተመልሰው ተዋሕደው፡ በመልከጼዴቅ ሰውነት ውስጥ፡ አንድ ዘር ሆነው፡ ኢትዮጵያውያን ሆነዋል፡፡ ስለዚህም፡ ስሙ “ኢትዮጲስ ” በነበረው መልከጼዴቅ አማካኝነት፡ ይህ ቅይጥ ትውልድ-“ኢትዮጵያ ” ተባለ ፡፡ ) በኋላ ላይ፡ መልከጼዴቅ ኢየሩሳሌምን ከቆረቆረ በሁዋላ፡ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ወደኢትዮጵያ ሲመጡ፡፡ የአዳምና ሔዋን መነሻ መሬት በርሱ ስም ኢትዮጵያ ተብላ ተጠራች፡፡ ሕዝቡም “ኢትዮጵያዊ ” ተብሎ፡ የበለጠ፡ ስሙ ጸና፡፡

፬ . አብርሃም፡ – እግዚአብሔር፡ ይህን የኢትዮጵያዊነት የአኗኗር ጸጋ፡ ለሁሉም ሕዝብ እንጂ፡ በኢትዮጵያ ምድር ለሚኖሩ የመልከጼዴቅ ልጆች ብቻ ሊሰጥ ያልፈቀደ በመሆኑ፡ ለሚፈልግ ሁሉ፡ እጁን ዘርግቶ ሊሰጠው የተዘጋጀ ሆኖ ሳለ፡ ከሴም ትውልዶች መሃል፡ እግዚአብሔርን ምርጫው ያደረገ አብርሃም ተገኘ፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን ሃይማኖት አስተማረው፡፡ ቆርኔሌዎስን ወደ ጴጥሮስ : ሳውልን ወደ አናንያ እየላከ የእግዚአብሔርን ነገር እንዳስተማረ ሁሉ፡ በዚያ ጊዜም፡ አብርሃምን ወደ መልከጼዴቅ ልኮ፡ በመጨረሻው ዘመን፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚፈጸመውን የስንዴና የወይን መስዋዕት (ቅዱስ ቁርባን ) ምሳሌ አሳየው፡፡ አብርሃም፡ ከተገረዘ በሁዋላ፡ ኢትዮጵያዊቷን ኬጡራን አገባ፡፡ ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆነውን የአኗኗር ሥርዓት (በእግዚአብሔር መንግሥት መመራት : በታረመ ሥርዓት መኖር ) ተቀብሎ፡ በስተመጨረሻ ዐረፈ፡፡ ስለሆነም በተጋድሎ ኢትዮጵያዊ ሆነ፡፡

፭ . ሙሴ፡ – ሌላኛው እስራኤላዊ፡ ራሱን ለኢትዮጵያዊነት ያበቃ ደግሞ ሙሴ ነው፡፡ እርሱም፡ በትሕትናው፡ የኢትዮጵያውያንን ማንነት ሳይንቅ፡ ሕዝቤ አይደሉም ወይም እኔ ሴማዊ ነኝ ሳይል፡ የኢትዮጵያዊውን መልከጼዴቅ የዮቶርን የከብት መንጋ እየጠበቀና፡ ከርሱ ሃይማኖትና ሥርዓተ መንግሥትን እየተማረ ፡ 40 ዓመት በኢትዮጵያ ምድር ኖረ፡፡ እግዚአብሔርም በኮሬብ ተገለጠለት፡፡ ኢትዮጵያዊት ሚስትም አገባ፡፡ እስራኤልንም ከኢትዮጵያውያን ጋር በአምልኮም ሆነ በሥጋ ውሕደት አንድ ሕዝብ ያደርጋቸው ዘንድ፡ እርሱ ምንም አድልዎ ባያደርግም፡ እሥራኤላውያን ግን በትዕቢታቸው ጸኑ፡፡ “እኛ ከኢትዮጵያውያን በምን እናንሳለን ? እግዚአብሔር በእኛ ላይ አድሮስ ተናግሮ የለምን?” እያሉ፡ እንደ ሙሴ እኅት ማርያም በማጉረምረማቸውም፡ እግዚአብሔር አዘነባቸው፡፡ ሙሴ ግን በትሕትናው ጸንቶ፡ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተዋሕዶ፡ እስራኤልን ወደመልከጼዴቅ ምድር (ኢየሩሳሌም ) ከሸኛቸው በኋላ፡ እርሱ በአፍሪካ ምድር፡ በምድያም (በኢትዮጵያ ) ግዛት ቀርቷል፡፡

፮ . ዳዊት፡ – ሌላኛው ኢትዮጵያዊ የአኗኗር ሥርዓትን የተቀበለ እስራኤላዊ : ቅዱስ ዳዊት ነው፡፡ በርግጥ ቅዱስ ዳዊት ራሱ፡ ከግብጥምድር አብረው ከነበሩት ከእሥራኤላውያንና ከኢትዮጵያውያን የዘር ውሕደት የተገኘ ነው፡፡ መልከ ጤዴቅ የክርስቶስ ክህነት ምሳሌ እንደነበረ ሁሉ፡ ዳዊት የክርስቶስ መንግስት ምሳሌ ነበረ፡፡ ክርስቶስ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀመጠ ማለትም ይህ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ኦርዮን፡ በሃይማኖት የጸና ወታደር፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ወታደር፡ በዳዊት በተገደለ ጊዜ፡ ኢትዮጵያዊት ሚስቱ ቤርሳቤህ (ቤተሳባ)- የዳዊት ሚስት ሆናለች፡፡ ከርሱዋም ሶሎሞን ተወልዷል፡፡ በሶሎሞንም ዘመን፡ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ መጣች፡፡

እስራኤል፡ ቀድሞ፡ በሙሴ ጊዜ፡ የናቁትን ሥርዓተ መንግሥት፡ የአምልኮ ሥርዓትና የቤተሕዝብነት ሥርዓት፡ መልሳ፡ በርሷ መሣርያነት ወደ ኢትዮጵያ ልታስገባው መጣች፡ ያም፡ የርሷ ሳይሆን፡ የእግዚአብሔር ዕቅድ ነበረ፡፡ እስራኤልም ታቦታቸውን አጡ፤ ተማረኩ፤ ተበተኑ ፤ ብዙ ጊዜም ነብያት እየተነሱ ገሰጻኦቸው፤አልሰሙም፡፡ እነ ነብዩ ኤርምያስን እንኩዋ፡ ይታደጉዋቸው የነበሩት፡ መጽሐፍ ቅዱሱ እንደተገለጠው፡ እነኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ነበሩ እንጂ፡ እስራኤላውያኑ ደንታ አልነበራቸውም፡፡ ለኢየሩሳሌም አለመጥፋት ሲጸልዩ የነበሩ ኢትዮጵያውያኑ ነበሩ እንጂ፡ እስራኤላውያኑ በባዕድ አምልኮ ተጠምደው በትዕቢት “ማን ይነካናል” ሲሉ ነበረ፡፡ ስለሆነም፡ ከመንግሥታቸው፡ ከካህናቶቻቸውና ከነዋያተ ቅድሳቶቻቸው ዋና ዋና የሆነውን ሁሉ፡ በንግሥተ -ሳባ ልጅ በሚኒሊክ አማካኝነት፡ እግዚ አብሔር ወደ ኢትዮጵያ መለሰው፡፡ ከዮቶር ያገኙት ወደዮቶር ሃገር ተመለሰ፡፡ እስራኤልም፡ እስከ ክርስቶስ ድረስ በእግዚ አብሔር ቸርነት አንዴ እየተወረሩ : አንዴ እየተመለሱ ኖሩ፡፡

፯ . ቅድስት ድንግል ማርያምና ልጁዋ ኢየሱስ ክርስቶስ፡ – ሰባተኛውና ዋናው ቃል ኪዳን – “ኢትዮጵያ ” የምትባለዋ ጽንሰ ሃሳብ፡ ኢትዮጵያዊነትም የተባለው ሃይማኖት፡ ሳትሸራረፍ፡ ሳትቀናነስ፡ በትክክል በሕይወት የተገበረቻት አንዲት ሴት ተገኘች፡፡ ያችውም ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ እርሷም፡ ከንግሥተ -ሳባ እና ከሶሎምን የዘር ውኅደት የተገኘች ናት፡፡ ሶሎሞን፡ በመሃልየ መሀልይ ውበቷን እያደነቀ፡ (በተለይም ሃይማኖታዊ ውበቷን )፡ በንግስተ ሳባ ውስጥ በትንቢት መነጽርነት እያየ፡ ብዙ ጽፎላታል፡፡ አባቱ ዳዊትም እንደዚያው፡፡ በኢየሩሳሌም የሚፈጸመው የመልከጼዴቅ ሥርዓት (በኅብስቱና ወይኑ አምሳል ስጋውና ደሙ መፈተቱ ) ጊዜው ስለደረሰ : ጌታን ጸነሰች፤ ወለደችው :: የሆነው ሁሉ ሆነ : አዲስ ሥርዓትን ተሠራ :: እስራኤላውያን ግን እርሱዋን አሳድዱዋት፤ ልጁዋንም ሰቅለው ገደሉት :: እነርሱ የፈለጉት፡ የነርሱን ታላቅነትና ገናንነት እንዲያስከብር ብቻ እንጂ : ሁሉም አንድ ወደሚሆንበትና የዘር ልዩነት ወደሌለበት ኢትዮጵያዊ ሥርዓትን እንዲመራቸው አልነበረም :: ስለሆነም : ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከጸጋው ራቁ !

ኢትዮጵያውያኑ ግን፡ ሲጠብቁት የነበሩት በመሆኑ፡ በጃንደረባው አማካኝነት ጌታን አምነው፡ ተቀበሉት :: ኢየሱስ በሃይማኖት ሊነግስባቸው ፈልጎ የነበሩት እስራኤላውያን ግን አመጹ :: እንዲሁም ሮም : ግሪክ ወዘተ የመሳሰሉት ሀገራትም፡ እንኩዋን ክርስቶስ ንጉሳችን ሊሉ፡ ጭራሱኑ ክርስቲያኖችን አሳደዱ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ግን : “ከይሁዳ ነገድ የወጣው አንበሳ ንጉሣችንና ካህናችን ነው :: ሹመቱም እንደመልከጼዴቅ ካህን ነው ” በማለት “ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ” በማለት ሰባቱን ቃል ኪዳናት አተሟቸው !! ኢየሱስ ክርስቶስም በኢትዮጵያውያን ላይ ነገሰ :: ያም፡ ወደው ፈቅደው ያነገሱት እነርሱ ብቻ ሆነው ስለተገኙ እንጂ፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሌላው ሕዝብ ላይ ሊነግስ ስላልፈቀደ አይደለም :: ክብር ይግባውና እርሱ የሰማይም የምድርም ንጉሥ ነው፡፡ እኒህ ናቸው ሰባቱ ቃል ኪዳናት :: እኒህን አምኖባቸው : በውስጧቸው ያዘሏቸውን ተግባራዊ መመርያና ምግባራት ፈጽሟቸው የሚኖር ሁሉ፡ ኢትዮጵያዊ ይባላል :: ካልሆነ ግን አይደለም :: ሌላ ማንም ሰው “አንተ ኢትዮጵያዊ አይደለህም ” ሳይለው በፊት፡ እርሱ ራሱ “እኔ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ” ብሎ ይመሰክራል :: ዛሬ፡ ከኢትዮጵያ መገንጠል የሚፈልጉ አክራሪዎችና መናፍቃን ወገኖችን : እንዲሁም አረማውያንና እግዚአብሔር የለሾች : ሁሉ፡ ሲናገሩ እንደምንሰማቸው፡ ኢትዮጵያዊ ከመባል : በአሜሪካ ውስጥ የተተከለ ዛፍ መሆን ይሻላል እስከማለትና “ኢትዮጵያዊ አይደለንም : በኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት የተገዛን ነን እንጂ ” እስከማለት ደረሱ :: ስለሆነም : ከ 7ቱ ቃል ኪዳን ውጭ ወጥተው ስለተገኙ : በዳዊት ቃል ኪዳን፡ ክርስቶስ በዳዊት መንበር የነገሰ ንጉሳችን ነው ሳይሉ፡ ድንግል ማርያምንም ኢትዮጵያ እናታችን ሳይሉዋት፡ ማንም ማን ሳይላቸው በፊት ራሳቸውን ከኢትዮጵያነት በፈቃዳቸው አወጡ :: “ኢትዮጵያዊ ሃይማኖተኛ ነኝ ” የሚለውም ራሱ በባዕድ አምልኮ : በዘረኝነት : በሙስና : በተለያየ ኃጥያት ተይዞ : በአፉ ኢትዮጵያዊ ነኝ ቢልም : በተግባር ሳይሆነው ቀረ :: መልኩን ለውጦ የፈለገውን ለመሆን ግን አልቻለም :: ኢትዮጵያዊነቱ ያሳድደዋል :: ነብሩ መልኩን መለወጥ እንደማይችል ሁሉ : ኢትዮጵያዊም መልኩን ለውጦ ሌላ መሆን አልቻለም :: ሌላውን ለመሆን በሚሞክር ጊዜ ሁሉ : አላምርበት እያለ : ወይም አልሆንለት እያለ አጉል ይሆናል : ጥፋትም ይወድቃል ::

በዚህ ርእስ ጉዳይ የበለጠ ግንዛቤ ለመያዝ www.ethkogserv.org መመልከት ጥሩ ገጽ ነው::

(source: zehabesha newspaper)