ጥምረት ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለፍትህ
(ግንቦት 7) — የአፋር ሕዝብ ፓርቲ፣ ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነትና የፍትህ ንቅናቄ ተቀናጅተው “ጥምረት ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለፍትህ በኢትዮጵያን” መፍጠራቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብስረዋል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የዚህ ጥምረት መሥራች አባል በመሆኑ የተሰማውን ደስታ በድጋሚ ይገልፃል።
በአገራችን የተንሰራፋውን ዘረኛ አምባገነን አገዛዝ አስወግደን ለሁላችንም የምትስማማ አገር እንድትኖረን ለማድረግ በሁሉም የዲሞክራሲ ኃይሎች መካከል ጥብቅ ትብብር መፍጠር ግድ ነው። ኢትዮጵያዊያን ድርጅቶች ይህንን ሃቅ ከተረዳን ውሎ ያደረ ቢሆንም እስካዛሬ ድረስ ዘላቂነት ያለው ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት ግን ሳንችል ቀርተናል። ይህ ጥምረት በዚህ ረገድ ለሚደረገው ሰፊ ትግል መንገድ አመቻች ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ጥምረቱን የፈጠርን ድርጅቶች ከአሁን በኋላ እንደ አንድ ድርጅት ሆነን የምንደራደር በመሆኑ በመጠኑም ቢሆን የተደራዳሪዎችን ቁጥር በመቀነስ ረገድ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለን እናምናለን። ሌሎችም ድርጅቶች እንደዚሁ በዓላማ ከሚመሳሰሏቸውጋር ጥምረት ፈጥረው ቢመጡ የትብብር ጥረታችንን የበለጠ ፍሬዓማና ዘላቂ ያደርግልናል፤ ድካማችንንም ይቀንስልናል የሚል ፅኑ እምነት አለን።
ጥምረት ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለፍትህ በኢትዮጵያን የፈጠርን ድርጅቶች ወያኔን በጋራ ትግል አስወግደን በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ሥልጣን እስኪረከብ ድረስ አብረን ለመቆም ቃል ገብተናል። ጥምረታችንን አጠናክረን ወደ ውህደት ልናመራ የምንችልባቸውን መንገዶች ለመቀየስም ወስነናል። ውህደት እስኪፈጠር ድረስም በአንድ ድምጽ እንናገራለን፤ ቁሳዊና ቁሳዊ ያልሆኑ ኃይሎቻችንን እናቀናጃለን።
እንደሚታወቀው ከዚህ በፊት የታለመላቸውን ግብ ያልመቱ በርካታ የትብብር ጥረቶች ተደርገዋል። በዚህም ምክንያት ዛሬ የትብብር ጥያቄ ከየአቅጣጫው እየተነሳ ቢሆንም እንኳን በትብብሮች ዘላቂነት ላይ ሰዎች ጥርጣሬ ቢኖራቸው ሊገርመን አይገባም። ከአሁን በኋላ የምናደርጋቸው ትብብሮች ከቀድሞ ስህተቶቻችን የተማርን መሆናችንን የሚያሳዩ መሆን ይኖርባቸዋል። በዚህም ምክንያት ከመነሻው ጀምሮ ትብብሮቹ ሊያመጡት በሚፈልጉት ውጤትና በዘላቂነታቸው ላይ ግልጽ የሆነ መግባባት እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ አገራችን እና በአጠቃላይ የአፍሪቃ ቀንድ የሚገኝበት አሳሳቢ ሁኔታ እግምት ውስጥ በማስገባት ከድርጅት ፍላጎት አርቀን ትውልድን እያሰብን ለጋራ ትግል መዘጋጀት ይኖርብናል ብለን እናምናለን። ጥምረትን ስንፈጥር ይህን በልባችን ይዘን ነው።
ጥምረት ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለፍትህ በኢትዮጵያ በአደረጃጀትም ሆነ በትግል ስልት የተለየ መንገድ ከያዙ ፀረ-ወያኔ ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ሁሉ ጋር ተባብሮ ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት ራሱን ባስተዋወቀበት መግለጫ ገልጿል። በዚህም መሠረት ጥምረቱ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር ያለውን የትብብር አድማስ በማስፋት ሥራ ላይ ጠንክሮ ይሠራል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በዚህ ጥምረት የጀመረውን የትብብር ሂደት አጠናክሮ በመቀጠል ፍትህና እኩልነት የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች እንዲተባበሩ ጥሪውን ያድሳል። ሁላችንም በጋራ ስንቆም በተቀናጀ ትግል በአጭር ጊዜ ወያኔን አስወግደን ፍትህ፣ እኩልነትና ነፃነትን እንደምናሰፍን እርግጠኞች ነን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!