ኢትዮጵያ አውሮፓ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችል ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ዜጎቿን ተቀብላለች

አውሮፓ ኅብረት፣ ኢትዮጵያ አውሮፓ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችል ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ዜጎቿን ተቀብላለች በማለት አደነቀ። የካቲት 11 በአዲስ አበባ የተካሄደው 6ኛው የኢትዮጵያና የኅብረቱ የጋራ የሥራ ቡድን ስብሰባ፣ አውሮፓ ውስጥ የመቆየት ፍቃድ የሌላቸውን ኢትዮጵያዊያን ለመቀበል የተነደፈውን የጋራ አሠራር አተገባበር መገምገሙን የኅብረቱ የውጭ አገልግሎት ቢሮ አስታውቋል። ቢሮው፣ ኢትዮጵያ ዜጎቿን በመቀበል ረገድ ከኅብረቱ ጋር ያላትን ትብብር “በአጋርነት” እና “በጋራ የመከባበር መንፈስ” ይበልጥ ለማሻሻልና የትብብሩን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በዚሁ ስብሰባ ላይ ቁርጠኝነቷን መግለጧንም ጠቅሷል። የኢትዮጵያ መንግሥት እና አውሮፓ ኅብረት፣ በኅብረቱ አባል አገራት ውስጥ የመቆየት መብት የሌላቸውን ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ለመመለስ በሚያስችል የጋራ አሠራር ላይ ከስምምነት ላይ የደረሱት ከስምንት ዓመት በፊት ነበር።