ከምድር ውጭ ያሉ ህይወት ያላቸው ባዕድ ፍጥረታት (ከሌላ ፕላኔት የመጡ) / Aliens ወይም ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላት /UFOs

ከምድር ውጭ ያሉ ህይወት ያላቸው ባዕድ ፍጥረታት (ከሌላ ፕላኔት የመጡ) / Aliens ወይም ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላት /UFOs አሉ ?

ከዚህ ቀደም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዜዳንት ባራክ ኦባማ ‘ ብራያን ታይለር ኮኸን ፖድካስት ‘ ላይ ቀርበው ባዕድ ፍጥረታት (ከሌላ ፕላኔት የመጡ) / Aliens አሉ ወይ ? ተብለው ተጠይቀው ነበር።

ኦባማም፥ ” #አሉ! ነገር ግን እኔ አላየኋቸውም። ሆኖም ግን በ’ኤሪያ 51’ ውስጥ በሚስጥር ተደብቀው የሚገኙ አይደሉም ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

(ስለ ‘ ኤርያ 51 ‘  ፦ ኤርያ 51 የተባለው ከፍተኛ የአሜሪካ ሚስጥር ያለበት ቦታ ነው። በዓለማችን ላይ ካሉ እጅግ ምስጢራዊ ቦታዎች ውስጥም አንዱ ነው። ስለ ቦታው ብዙ የሚባሉ ነገሮች አሉ። በአሜሪካ ኔቫዳ ግዛት ውስጥ የሚገኘው ይኸው ሚስጥራዊ የጦር ሰፈር ፤ በዙሪያው ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግበታል።)

የኦባማ ቪዲዮ ከተጋራ በኋላ በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

በኋላ ላይ ” በጠፈር ስፋት አንጻር ሌላ ሕይወት ያለው ነገር ሊኖር እንደሚችል በሳይንሳዊ ስሌት መናገሬ ነው እንጂ ምድር ላይ በፕሬዝዳንትነት ዘመኔ ስለመምጣታቸው ምንም ማስረጃ አላየሁም ” ሲሉ ማብራሪያ እስከመስጠት ደርሰዋል።

አሁን ደሞ የፎክስ ኒውሱ ጋዜጠኛ በዚህ ጉዳይ ላይ ለፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጥያቄውን ማቅረቡን ተከትሎ ነገሩ እንደገና አነጋጋሪ ሆኗል።

ፕረዚዳንቱ ” እርሶስ ከምድር ውጭ ያሉ ህይወት ያላቸው ባዕድ ፍጥረታት (ከሌላ ፕላኔት የመጡ) / Aliens ስለመኖራቸው ያውቃሉ ? ” ተብለው ተጠይቀዋል።

ፕረዚዳንት ትራምፕ ፥ ” ባራክ ኦባማ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹና የሀገር ምሥጢር የሆኑ መረጃዎችን አጋርቷል ” ሲሉ ወቅሰዋል። ከወቀሳው ባሻገር በጥያቄው ላይ ሀሳብ ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

ትራምፕ ይህን ካሉ በኋላ ‘ ትሩዝ ‘ በሚሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ስለባዕድ ፍጥረታት (Aliens) ወይም ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላት (UFO) እና ምንነቱ ያልታወቀ የአየር ላይ ክስተት (UAP) የተመለከቱ ሚስጥራዊ ሰነዶች ይፋ እንዲደረጉ እንደሚያዙ ገልጸዋል።

​ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመንግሥት እጅ የሚገኙ ፦
– ከምድር ውጭ ሌላ ፕላኔት ላይ ስላሉ ህይወት ያላቸው ፍጥረታት/ባዕድ ፍጥረታት (Aliens)፣
– ያልታወቁ በራሪ አካላት (UFOs)
– ምንነቱ ያልታወቀ የአየር ላይ ክስተት፣ (UAPs) ጋር የተያያዙ ሚስጥራዊ ፋይሎች ለሕዝብ ይፋ እንዲሆኑ ትዕዛዝ እንደሚሰጡ አሳውቀዋል።

​” ለጉዳዩ የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት መሠረት በማድረግ የጦርነት ሚኒስትሩ (መከላከያው) እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት እና ኤጀንሲዎች መረጃዎቹን ለይተው እንዲያወጡ መመሪያ እሰጣለሁ ” ብለዋል።

” ከእነዚህ እጅግ ውስብስብ ግን ደግሞ በጣም አስደሳች እና አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ማናቸውንም መረጃዎች በሙሉ እንዲለቀቁ አደርጋለሁ። እግዚአብሔር አሜሪካን ይባርክ! ” ሲሉ አክለዋል።

ትራምፕ ቀደም ሲል ባራክ ኦባማ ሚስጥራዊ መረጃዎችን አውጥተዋል በሚል ተችተው ነበር።