መድረክ ከቅንጅትነት ወደ ግንባርነት እንዲሸጋገር ምክር ቤቱ ወሰነ !

አቡጊዳ – ሐምሌ 24 ቀን 2002

ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ እንደሚገልጸዉ ከእያንዳንዶቹ የመድረክ አባላት፣ ሰባት ሰባት ሰዎችን የያዘዉ የመድረክ ምክር ቤት፣ መድረክ ከቅንጅት ወደ ግንባር እንዲሸጋገር ወሰነ።

የመድረክ አባል ድርጅቶች ከመቼዉም በበለጠ በመከባበርና በመግባባት የሚሰሩ መሆናቸዉን የገለጹት አንድ ያነጋገርናቸዉ የፖለቲካ ተንታኝ መድረኩ ወደ ግንባር ለመሸጋገር ያደረገዉን ዉሳኔ «ከኢትዮጵያ ህዝብ ትርታ ጋር አብሮ የሚሄድ» ሲሉ አድንቀዉታል።

የመድረኩ ወደ ግንባር የመሸጋገር ዉሳኔን ቀጥሎ ፣ የመድረኩ አባል ድርጅቶች ከዚህ በፊት የመድረኩን መለስተኛ ፕሮግራም ሲያዘጋጁ ያስቀመጧቸዉን አንዳንድ ልዩነቶች የበለጠ ያጠቧቸዋል ተብሎም ይጠበቃል።

መድረኩ ዛሬ ባደረገዉ ስብሰባ፣ የአንድነት ምክትል ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸዉ የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር ሆነዉ የተመረጡ ሲሆን ፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ አቶ ገብሩ አሥራት የፋይናንስ ሃላፊ ሆነዉ ተመርጠዋል።

በተያያዘ ዜናም ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ እንደሚጠቁመዉ፣ የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከሚመራዉ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጋር አብሮ ለመስራት ብሎም ለመዋሃድ የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ በድርጅቱ ዉስጥ ሰፊ ዉይይቶች እየተደረጉ መሆናቸዉን ለማወቅ ችለናል።

በተለይም በየወረዳዉ ያሉ የመኢአድ ደጋፊዎችና አባላት በምርጫዉ ወቅት አብረዉ ከአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎችና አባላት ጋር የታሰሩ፣ የተቆሳቆሉና ወከባ የደረሰባቸዉ እንደመሆናቸዉ «በኛና በአንድነት አባላት መካከል ምንም ልዩነት የለም፤ የፖለቲካ ፕሮግራሞቻችን አንድ ናቸዉ። አላማችንና ራእያችን አንድ ነዉ» በማለት ከአንድነት ፓርቲ ጋር አብሮ የመሥራት ትልቅ ፍላጎት እንዳላቸዉና ግፊት እያደረጉ መሆናቸዉን ዘጋቢዎቻችን ይገልጻሉ።

መኢአድ ከምርጫ 2002 በኋላ ከመድረክ ጋር ተመሳሳይ አቋም ይዘዉ ይንቀሳቀሱ እንደነበረና የ2002 ምርጫ ዉጤትንም እንዳልተቀበሉ የሚታወቅ ነዉ።