ቅዥት በእውቀት ሲፈታ! ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል በወ/ሮ አዜብ መስፍን ንግግር ዙሪያ

“ተናጋሪ አፍ ያስወጣል” የሚባለው ነገር እውነት ነው። እንደ ዛሬ ጥብብ ጭንቅ ብሎኝ አያውቅም በምን እንደምጀምር ሁላ ጠላቶቻችን ግራ ግብት ይበላቸው (የሰው ጠላት የለንም እንጂ) ፈር የሌለውን ንግግር ፈር ለማስያዝ ደቂቃዎች ፈጅቶብኛል። ወላጆች ሲመርቁ “ከተናግሮ አናጋሪ ይጠብቅህ” ቢሉም ዕዳችንና አበሳችን የማያልቅ ሆኖ ዛሬ ደግሞ ባለቤታቸውን አዘዘልን። ተናጋሪ-አፍ ከመናገር ካልተቆጠበ ጆሮም ሰምቶ ማሳለፍ ካላስቻለው ምን ይደረጋል? እንደምንም ብዬ እኔም በተራዬ እንዲህ የቀን ቅጀት አሳች ንግግር ለመፍታት፤ በተጨማሪም ነገሩ ከቅነት ይሁን ከልብ ጥመት የተነገረ ቃለ ምልልስ ለመሆኑ አብረን እየመዝንን በግልባጭ ደግሞ ጥያቄ ለወ/ሮ አዜብ መስፍን አያቀረብኩ የያዘጋጀኋትን ጽሑፍ እነሆይ ብያለሁ። በቅድሚያ ግን እንዲህ ያሉ ምልክቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት የሚያበስሩ መሆናቸውን እየጠቆምኩ ከስንፍናችን የተነሳ የምናሻትንና የምንናፍቃትን ቀን እንዳታልፈን በጊዜውም አለጊዜውም ወገብችንን ታጥቀን ስለ ፍትህ ራሳችንን አሳልፈን ለመስጠት፣ ስለ ነጻነታችን ለመቆሞ እንነሳ ዘንድ ነው በዚህ አጋጣሚ ጥርዬን ለማቅረብ የምወደው። (የምስል ቃለ ምልልሱ ያገኘሁት ከኢትዮሚድያ ዳት ካም ድህረ ገጽ ነው)

የጠያቂው አካል ጥያቄ ምን እንደሚል በምስል ከተቀረጸ ድምጽ ለመስማት ባይቻልም ወ/ሮ አዜብ የልጆቻቸውን አስተዳደግና የትምህርት ሁኔታ መጠነኛ መግለጫ በመስጠት ይጀምራሉ። ባልና ሚስት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለፉ ልጆቻቸውን እንደሚያስተምሩ ሲገልጹ ወ/ሮ አዜብ እንዲህ ያላሉ “እንደዚህ ነው የምናገጣጥመው” በሌላ አገላለጽ ከእጅ ወደ አፍ በሆነችው ኑሮአችን ነው ልጆቻችንን የምናስተምረው ነው። አክለው በቤተ-መንግሥት ቅጽር ግቢ ስለሚመሩት የኑሮ ዓይነትም ሲያብራሩ “በግልጽ በምትሰጠን በማንኝውም ሰዓት ተቆጥራ ልትጣራ በምትችል ፍራንክ ነው የምንኖረው” ይላሉ።

በእውነቱ ነገር እንዲህ ያለ አነጋገር ማለት “በግልጽ በምትሰጠን በማንኝውም ሰዓት ተቆጥራ ልትጣራ በምትችል ፍራንክ ነው የምንኖረው” ሲሉ የተደመጡ ወ/ሮ አዜብ ከራሳቸው አእምሮ የሚመነጭ ዓይነት አባባል ሳይሆን በቀንም በለሌትም ነገር ከሚፈትሉና ያለ የጥፋትና የአመጻ ምክር ሌላ ከማያውቁ ቀለብ እየተሰፈረላቸው ኑሮአቸውን ከሚገፉ አእምሮአቸውን ከጣሉ አሽከሮች ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ንግግሩ ሰጪና ቆጣሪ በግልጽ ሁኔታ ባለማካተቱ  ድፍን 80 ሚሊዮን ሕዝብ ላይ በስላቅ፣ በንቀት፣ በትዕቢትና ዕብርትነት በወረሰው ልብ የተነገረ ምጸታዊ ንግግር ያደርገዋል።

አሰራራችሁ ለህዝብ ግለጽ ይሁን፣ የህዝብ አደራን (ህገ መንግሥታዊ ግዴታችሁን) በአግባቡ እየተወጣችሁ አይደለም፣ ሹሞቻችሁ ዓይናቸውን በስብ ተሸፍኖ የወፍጮ ቤት አህያ (የደለበ) እስኪመስሉ ደረስ የራሳቸውንና የቤተ-ዘመዶቻቸውን ቤት ሲያሞቁ ሰፊውን ህዝን እየተበደለ፣ እየተራበ፣ እየተራቆተ፣ እየተሰደደ ነው ያለው፣ ሀብት ንብረታችሁ ይቆጠር፣ የህዝብ ነን ካላችሁ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ኑና በጠረጴዛ ዙሪያ እንቀመጥ ያሉማ እንደ ጨው ተበትነው የእንግድነት/የስደት ኑሮ ገፈጥ ቀማሾች ሆነዋል በተረፈ ደግሞ በየበርሃው በተቆፈሩ እስር-ቤቶች እየማቀቁ  ያሉ ዜጎችስ ምን ቢያጠፉ ነው በባለቤትዎ አባት ርስት ወይንስ ደግሞ በእርስዎ ቀሚስ ስር ተገኝተው ነው? የገቡበትን ሳይታወቅ የቀሩስ የሉም ወይ? ለሕዝብ ግልጽ አሰራር ይኑራችሁ፣ ይቆጠር ባሉ አይደለም ወይ “እናንተ ደግሞ ከየት የመጣችሁ ናችሁ ይህ ወንበር እኮ የደም ዋጋ የተከፈለበት ነው” እየተባለ አይደለም ወይ ዜጎች ከስር ከስር እንደ ጎመን የተቀነጠሱ?

በማስከተልም “እኔ” ይላሉ ወይዘሮ አዜብ “እኔ በጣም ብዙ ጊዜ ኪሴ ላይ ብር ነሮኝ አያውቅም” ያላሉ በእርግጥ መንፈሱ (አገላለጹ ባይችሉበትም ምን ለማለት እንደፈለጉ) በሚገባ ይገባኛል ዳሩ ግን አሁንም ከአንደባቸው የሚወጣ ቃል ከመሰሪዎች ሰፈር ተሰፍሮ በቀመር የተሰጣቸው እስከ ሆነ ድረስ እኛም ነገርን ከግራ ቀኝ ማየቱ አይቀርም ምን ነው ቢሉ? እባብ ለሰለሰ ተብሎ አይረገጥምና።

በመጀምሪያ ደረጃ በኪሱ ብር ይዞ የሚዞር ቱጃር በልቡ ንጹህ፣ የወደቀ፣ የተራበ፣ የቸገረው፣ መሄጃ ያጣ፣ ምድር ሲፊ ሳለች ከኑሮ ሁኔታው የተነሳ ጠባብ ሆና የተስማችው፣ እርዳታ የሚሻ፣ ሰማይ ምድሩ የጨላለመበት ወንድም እህት አባት እናት ትልቅ ትንሽ ያገኘሁ እንደሆነ በማለት ድሎት ያሰከረውን ፊቱ ደንበኛ ፀሐይ እያስመታ የልብ ተርታውን ጨምሮ ላቡን እያንተፋተፈ ድሃን ፍለጋ የሚንከራተት ነው። ከዚህ ባሻገር ደግሞ በኪስ ብር ተይዞ ለመያዞር ውሎ ይወስነዋል ነው የምሎት ወይዘሮ አዜብ። እርስዎ ምን ለመሆን ነው በኪስዎ ብር ይዘው የሚዘሩት? አየር በአየር እያለ!! ቁማሩም እንደሆነ በኪስ በሚወሰን ገንዘብ አይቆምሩ። በአውሮፓ ምድርም ሆነ በአሜሪካ ምድር ይቅር የተንጣለለ ቪላ ለማስገንባትም በአንዲት ሌሊት የሚያወጡትን ወጪ በኪስዎትን ይዘውት በሚዞሩት ብር በቂ ነው ብለው ያማናሉ ብለንም ራሳችንን አናታልልም።

ስለዚህ በኪስዎት ብር ይዘው አለ መዞርዎትን ድህነትዎትን የሚያሳይ ካለመሆኑ በንግግርዎ ለትዕዝብት ካልሆነ በስተቀር ምንም እንድናዝንሎት አያባባንም። ደግሞም ጥፋቱ የእርስዎ ሳይሆን የጥያቄው አቅራቢ ነው። ካርድዋስ? ብሎ መጠይቅ ነበረበትና።  በተረፈ ንግግርዎ ከምር የሆነ እንደሆነ እውነቱ ይህ ነው፥ ድኃን በዓይኑ ለማየት እንደ እሬት የሚከነክነው ቤተሰብ ምን ለመሆን ነው ብርን በኪሱ ይዞ የሚዞረው? በወርቅ ማንኪያ ከሚበሉ መሰሎቹ ተሰባስቦ ያውካካ እንጂ። እንዲህ ያለ ፖለቲካዊ ንግግርዎትን ደግሞ ህዝብን የሚያስቆጣ የብላቴናዎች ምክር እንጂ ቁምነገር ያለው ሆኖ አልተገኘምና የሚሻለው ጊዜ ሳይመሽ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ከእርስዎ ባለቤት (እኔ እርስዎን የፖለቲካ ሰው ኖት ብዬ የተቀበልኩበት ቅጽበት የለም) የሚሻውን ፍትሕን እንጂ ልቃቄ ሳንቲም አይደለምና ጥያቄአችን ሲመለስ በነጭ መዳፋችን ትተን በጥቁሩ የእጃችን ጀርባ ሰርተን ለሌላ እንደምንተርፍ ነው አስረግጬ ልገልጽሎት የምወደው።

“ካገኘሁ ያገኘሁትን ሰው ነው የምሰጠው” ወደው አያለቅሱ!! መጀመሪያውኑ ማጣት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሲይውቁ አይደል ወይ ወይዘሮ? ለጊዜው ቀልዱ ይቅርና እስቲ ከምቾት የተነሳ መፈጠሩን የዘነጋ፣ በቀንም በለሌትም ድግስና ፌሽታ ከማይለየው ዘወርትር ግብዣ ከማይጠፋበት ቤት ቤተሰብዎትን ይዘው  ወጣ በማለት ሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ባለ ሁኔታ እየኖረ እናዳለ ይጎብኙ። ማለቴ የእርስዎ ማጣት ኩልል ብሎ ይታይዎት እንደሆነ ብዬ አስቤ ነበር ነገር ግን ለካ በሕዝብ ፊት ላለመውጣትም በእጅዎ ደም አለቦት። ወይዘሮ አዜብ፥ አይደለም ዛሬ ጓዳዬ እንዲህና እንዲህ ነው ማለት እዘኑልን ሊሉን በምድሪትዋ በተለይ በትግራይ ሕዝብ የማይፋቅ ጥቁት ጠባሳ ጥሎ ያለውፍን ታሪክ (የ77 ዓ.ም የረሀብ ዘመን) እንኳ ወላጆች ልጆቻቸውን አይናቸውን እይየየ በየደቂቃው ሲቀብሩና የትግራይ ሕዝብ ለሰማይ አሞራዎች ቀለብ ሲሆን በርሃብተኞች ስም የተገኘውን “ፍራንክ” ተገዝቶ ከውጭ አገር በገባውን “ውስኪ” ከስካርዎ ተርፎ እጆዎትን መታጠቢያ ያውሉት እንደነበር እኮ በመካልም ጊዜ ሊመጣ ካለው ፍርድ ያመለጡ ከማዕድዎ የተካፈሉ ወገኖች ምስክሮች ናቸው።

“ያገኘሁትን” ማለትዎ ምን ማለት ነው? እርስዎን ማንን ሲያገኞት ነው? ኧረ ለመሆኑ ከመቼ ነው “ቤተስኪያን” ሳሚ፣ የታመመውን ጠያቂ፣ የታሰረውን አጽናኝ የሆኑና ሰው የሚያገኞት? ሰውም የሚገኘው እኮ ሰው በሚንቀሳቀስበት ስፍራ ላይ ሲገኙና ሲንቀሳቀሱ ነው። በተረፈ ግን የት ያገኙት ሰው ነው የእርስዎ የዝርፍያ ብር ተካፋይ የሆነ? አባ ቤት ነው? ሌላው ይቅር ከፈጣሪ ሳይቀር ጸበኛ ይመስሉ እርስዎና ባለቤትዎ ከላይ ሳይቀር አይደለም ወይ እንደ ቅንፊዝ በተናዳፊዎች ታጅበው የሚንቀሳቀሱ? እንደ ዜጎችና የኢትዮጵያ ሕዝብ “መሪዎች” መቼ ነው በሕዝብ መካከል የተገኛችሁ? ጥይት በማይበሳው መስተዋት ውስጥ ራስህን ደብቀህ መለፍለፍ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያላችሁን መልካም ግኑኝነት የሚያመላክት ዕርዳታውም ይህ ከሆነ መልካም! ለሁሉም ጊዜ የሚያመጣውን ለማየት ዕድሜ ይስጠን ከማለት ውጭ ምንም አንድምታ የለውም።

“እስከ አሁን አምስት ሳንቲም በተፈለገውን መንገድ ሊጣራ ይችላል ማለቴ ዓለም ያውቀናል ለነገሩ አሜሪካ ብትጠይቁ ያውቃል” እንዴት ያለ ነገር ነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓይኑ የሚያየው በጀሮው የሚሰማውና በሁለመናው የሚዳስሰው አንሶት ደግሞ ስለ እናንተ ጉዳይ አሜሪካ ድረስ ሄዶ ይጠይቅ? ምን ተብሎስ ነው አሜሪካ የሚጠየቀው? እየተበላ ያለ ሕዝብ የኢዮጵያ ሕዝብ፣ እየተመዘበረ ያለውን ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ እየተራቆተ ያለው ህዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወይስ አበው “መባእ የሰረቀ መኖክሴ ራሱ ይለፋለፋል” ዓይነት ነው ነገሩ። መጠየቅ/የዓይን ምስክሮች መጥራትም ካስፈለገ ምን ሩቅ ያስኪደናል በትግራይ ክልል ከተሞች በተተከሉ የአይጥ ምሽጎች፣ የጊንጥ መተላለፊያዎች፣ የእባብ መገኛዎች ሆነው የደከረቱና በሸረሪት ድር አጊጠው መልካቸውን ያጡ ፋብሪካዎች አከባቢ የሚኖሩትን ለምስክርነት መጥራት መጠየቅ አይቀልም? አሜሪካም እንደሆነችም እኮ ሀገርንና ትውልድን እየሸጣችሁ ለምዕራባውያን ጥቅም ቅምጦች ሆናችሁ እስካገለገላችሁና እስከተቀመጣችሁ ድረስ ለእኛ ደግሞ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቆረጠች ዕለት እስክ ትደርስልን ድረስ ጉዳችሁን የሚያውቁላችሁና ያሰለጠንዋችሁ ከጎናችሁ መቆማቸው አይቀርም።

“እስከ አሁን አምስት ሳንቲም በተፈለገውን መንገድ ሊጣራ ይችላል”  ፍራንክን ፉት ብላችሁ አጣርታችሁ ጨረሳችሁ ይህም አልጠቅም ብሎአችሁ የሰውን ደም እንደ ጎርፍ ማፍሰስ ከጀመራችሁ በኃላ ሆነ እንዴ ኑ ና ገንዘባችሁን አጣሩ ማለት? ወይዘሮ አዜብ ወዴት ነው ወደኋላ የሚመልሱን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእርስዎም ሆነ ከባለቤትዎ እጅ የሚሻው እኮ ገንዘብ ሳይሆን ነፍስ ነው።

“ለነገሩ …” ማለትዎስ ምን ማለት ነው? በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ማላገጥዎ፣ በ በስውር ቋንቋ ንቀትዎትን መግለጽዎት ነው? ዓለምስ እንደሆነ በምናችሁ ነው የሚያውቃችሁ? ኢትዮጵያ የዓለም ክፍል አይደለችም ወይ? እውነት ካሎት የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀናል ማለት አይቀሎትም ነበር? ወይስ የኢትዮጵያ ሕዝብ እናንተን የሚያውቃችሁ በነፍሰ ገዳይነታችሁ፣ በሌብነታችሁ፣ በዘራፊነታችሁ፣ በስስታችሁ፣ በስግብግብነታችሁ ኧረ ስንቱን ጽፌ እዘልቀዋለሁ ስለሆነ ነው? በአጠቃላይ የዓለምም ሕዝብ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚያውቃችሁ በተለየ መልኩ አያውቃችሁምና ግራ ተጋብታችሁ ግራ ለመጋባት ታጥቃችሁ ከምትሰለፉ የሚያዋጣው በጊዜ መመለስን ነው።

ማር ጣፈጠ ብለህ አትብላው “እኔ ብፈልግ ገንዘብ መለስን ከዛ ሥራ ነው የማስለቅቀው  ምክንያቱም የመለስ ጭንቅላት ለእኔ ለቤት መግዢያ ይበቃል” አሁን ገና እውነት እውነቱ ነገሩን። እውነት ብለዋል ወይዘሮ አዜብ እኛም የሚያስጩኸን ይህንኑ ነው በራስዎ አንደበት እንደገለጹት የባለቤትዋ “ቅንጭላት” እንደሆነ ቤት አይሰራም እንጂ የተሰራውን ቤት መውርስ፣ ያላበበትን ያራሱን ማድረግ ያውቅበታል “ለስራ ያልታደለ አእምሮ ለተንኮል ተወዳዳሪ የለውም” እንዲሉ። ጨምረውም የባለቤትዎ “ቅንጭላት” ልጆቻችሁን ለማስተማር በቂ እንደሆነ ነግረውናል መማር ስላለባቸው ይሁን በአባታቸው ወንበር ተክተው እንዲፈራረቁብን በግልጽ ባይነግሩንም። ያም ሆነ ይህ ግን ልጆቻችሁን ማስተማር የሁላችሁን ደስታ ቢሆንም አሁንም ለመብላት ከሆነ የተቀረውም ዜጋ ላለመበላት ዋጋ መክፈሉ አይቀርምና እርካታ የማታውቅ ነፍሳችሁን ለማርካት ሲባል በልጆቻችሁ ቀጣይ የህይወት ምዕራፍ ጣልቃ ባትገቡ ነው ምክሬን የምለግሰው።

በመጨረሻም  “አልሳሳም ለገንዘብ” ሲሉ ተደምጠዋል እንግዲህ ምን እንላለን ለመሆኑ ወይዘሮ አዜብ ስስትዎ ገንዘብ ካልሆነ የእርስዎና የባለቤትዎ እንዲሁም የመላ ቤተሰብዎ ጥማት ደም ስለ ሆነ ይሆን እንዴ እንዲህ ምርድሪትዋ ፍዳዋን የሚያሳይዋት? ገንዘብ የአለመርካት መጨረሻው ይህን ነውና።

መንገደ ብዙ እግዚአብሔር ይርዳን!

(ጸሃፊውን በዚህ Email አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡ [email protected])