ለርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላትና ወዳጆች ሁሉ

የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላትና ወዳጆች፤ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና በህዝቧ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍና ሰቆቃ የምትቃወሙና ከሃገራችሁና ከህዝባችሁ ጎን የተሰለፋችሁ መላ ኢትዮጵያውያን ሁሉ።

የለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት ቆሞስ አባ ግርማ ከበደ በህይወት የሌሉትን አባ ጳውሎስን የፊታችን እሑድ (26/08/12) ወደ ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሊያመጧቸው ነው።

አባ ጳውሎስንና ክርስቲያናዊ ያልሆነውን ሥራቸውን በማውገዝ ጠንካራና እውነተኛ አቋም በመውሰድ በመላው ዓለም በሚገኘው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የምትታወቀው የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ግርማ ከበደ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን አባ ጳውሎስን ብጹዕ ብለው በማወደስ የክብር ፍትሐት በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ እንደሚፈጸምላቸው በይፋ አሳወቁ!!

በተለይ ከ6 ዓመት ጀምሮ አባ ጳውሎስን እውቅና የማትሰጠውና አባ ጳውሎስን በማውገዝ እንደ ፓትርያርክ ስማቸውን ብጹዕ ወቅዱስ ብላ ላለመጥራት አቋም ወስዳ አቋሟንም ኢትዮጵያ ለሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስና ለዓለም ሁሉ ጭምር ያሳወቀችው የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ግርማ ከበደ በ19/08/2012 እሑድ ዕለት ከቅዳሴ በኋላ በህይወት የሌሉትን አባ ጳውሎስን ብጹዕ ወቅዱስ በሚል ስማቸውን በማወደስና በክብር በመጥራት ቤተ ክርስቲያኗ በሚቀጥለው እሑድ ማለትም በ26/08/2012 ለአባ ጳውሎስ የክብር ፍትሐት እንደምትፈጽም ለተሰበሰበው ሕዝበ ክርስቲያን ሲያሳውቁ፡

በቤተ ክርስቲያኗ የአስተዳደር ሕግና ደንብ መሠረት በህዝብ የተወከለውን የሰበካ አስተዳደሩንም ሆነ የጥምር ጉባኤ ተብሎ የሚጠራውን ከፍተኛውን የቤተ ክርስቲያኗን የውሳኔ ሰጪ አካል ሳያስፈቅዱና ሳያማክሩ ህዝብንም ሆነ ህዝብ የመረጣቸውን የኮሚቴ አባላት በመናቅ ሕግና ደንብን ጥሰው በራሳቸው ስልጣንና ውሳኔ በህዝበ ክርስቲያኑ የተወሰደውን አቋም ሁሉ በመሻር ፍጹም እብሪት በተሞላበት ሁኔታ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

ይህንን የአባ ግርማን ድንገተኛ ማስታወቂያ ካዳመጠው ሕዝበ ክርስቲያን ውስጥ አንዳንዱ በየዋህነት መንፈስ መቸም ምንም ሆነ ምን ሰው ከሞተ ሞተ ነው በሚል በቸልተኝነት እንደሚያልፉት ቢገመትም፤ በሌላ በኩል ግን በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያኗንና ያፈራቸውን ንብረት ለመቆጣጠር በቋመጡ አካላት የሚካሄደውን ደባ አባ ግርማ የሚፈጽሙትን መጠነ ሰፊ ተንኮልና ቅጥፈት ለሚከታተሉና ለሚረዱ የሰሜን አሜሪካው አባ መላኩ ለጵጵስና ሹመትና ለፈላጭ ቆራጭነት ስልጣን ሲሉ የፈጸሙትን ክህደትና የፈጸሙትን ወንጀል ዛሬ አባ ግርማ በለንደን ሕዝበ ክርቲያን ላይ ሊደግሙት ከመጋረጃው በስተጀርባ ሥራቸውን ሲሰሩ መኖራቸውን በይፋ ያረጋገጡበት ዕለት መሆኑን በግልጽ የተረዱበት ዕለት ነበር።

አባ ግርማ ከበደ ይህንን የድፍረትና የንቀት ድርጊት የፈጸሙት በድንገት ተነሳስተው ሳይሆን በህይወት ዘመናቸው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንንና ገዳማትን ሳይቀር በመከፋፈልና በመነጣጠል በህዝብም ሆነ በሃገርና በሃይማኖት ላይ ከፍተኛ በደል የፈጸሙት አባ ጳውሎስ ህይወታቸውም ካለፈ በኋላ ፍትሓት ይደረግላቸው አይደረግላቸው በሚል ደግሞ ልክ በህይወት ዘመናቸው እንደተደረገው ሁሉ በሕዝበ ክርስቲያኑ መሃል ክፍፍልና ብጥብጥ ሲነሳ አባ ግርማ ባቀዱት መሠረት የደንቡ መጽደቅ እንዲከሽፍና እሳቸውም የቤተ ክርስቲያኗ ንብረት ካርታ ፈራሚነታቸውን እንደያዙ ወደ ወያኔ ጎራ በመጠጋት በምላሹ የጵጵስና ሹመታቸውን በማግኘት የሁሉም የበላይና ፈላጭ ቆራጭ በመሆን ተደላድለው ለመኖር እንደሆነ ግልጽ መሆን ይኖርበታል።

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እየጎላ የመጣው የአባ ግርማ ከበደ ክርስቲያናዊ ያልሆነ ተግባር ክፉ መንፈስን በመላበስ የዋህና ለሃይማኖቱ ሟች የሆነውን ህዝብ በመሃሉ ልዩ ልዩ የሃሰት ወሬ እያናፈሱ ጨርሶ እውነትነት የሌለውን መረጃ በማሰራጨት ካህን፤ ምእመንና ሰንበት ት/ቤት በሚል እርስ በርሱ በመከፋፈል አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ በማድረግ ህብረቱን አጥቶ ጠንካራ ውሳኔ የማያሳልፍ ስንኩል እያደረጉት በሌላ በኩል ግን ዓላማቸውን ለማሳካት ይረዳኛል ከሚሉት የወያኔ ቡድን ጋር ራሳቸውን በማቆራኘት በወሬ ያሰከሩትን የካህንም ሆነ የሰንበት ት/ቤትና የምእመናን ቡድን ለተነሱለት ግላዊ ዓላማ የሚጠቅማቸውን ተግባር ብቻ እንዲከናውንላቸው ሲያደርጉት ቆይተዋል።

እዚህ ላይ ጉዳዩ የሞተ ሰው ይጸለይለት? ወይስ አይጸለይለት በሚል አይደለም፤ ጸሎት ለጸላዩም ሆነ ለሚጸለይለት በጎ እንጂ ከቶ ክፉ ነገር ሊሆን አይችልም። ሆኖም ግን ዛሬ ፍትሐት እንዲደረግላቸው አባ ግርማ በቤተ ክርስቲያኗ አውደ ምሕረት ላይ ብጹዕነታቸው ብለው የጠሯቸው አባ ጳውሎስ በሃገሪቱ አጠቃላይና በተለይም ደግሞ በርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ ከቶ ምን የፈጸሙ ነበሩ?

በአሁኑ ወቅትስ እኚህ ህወታቸው ያለፈን ሰው አምጥቶ የክብር ፍትሐት ማድረግ ማንን ያስደስታል? ማንን ያሳዝናል? ማንንስ ያስቆጣል?

እንደሚታወቀው ሁሉ በዘር በጎሳና በመንደር ልጅነት ተመርጠው ፍጹም ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የፓትርያርክ ስልጣን ላይ እንዲወጡ የተደረጉት አባ ጳውሎስ፤ ስልጣን ላይ ላለው አገዛዝ የቅርብ ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ቤተ ክርስቲያንን በዘርና በጎሳ ከመከፋፈል አልፈው በአገዛዙ የመንግሥት መዋቅር እንደተደረገው ሁሉ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያሉት ቁልፍ ቦታዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአንድ ጎሳና ከዛም ወርደው በመንደር ልጅነት የበላይነትና አዛዥነት እንዲያዝ ያደረጉ ናቸው።

አባ ጳውሎስ በስልጣን ዘመናቸው ከፈጸሟቸው በደሎችና ድርጊቶች ውስጥ፡

· ባህታዊ መነኩሴ በአደባባይ አስገድለዋል፤

· በልደታ መድሐኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ካህናት ቆባቸው እየወለቀ እንዲደበደቡና እንዲገረፉ አድርገዋል፤

· በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ የአባ ጳውሎስን አለ አግባብ ስልጣንን መጠቀም፤ ሙስናና የመሳሰሉትን ሕገ ወጥነታቸውን ያጋለጡ ጳጳሳት የያዙትን የእውነት ሥራ ለማሰናከል በየመኖሪያ ቤታቸው የደህንነት ሰዎች እየተላኩ እንዲደበድቧቸውና እንዲያስፈራሯቸው አድርገዋል፤ ከዚህም ጥቃት ሳያገግሙ ህይወታቸው ያለፈ ጳጳሳት እንዳሉ ይታወቃል፤

· የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖናን በመጣስ ገና በህይወት እያሉ ምስላቸውን የያዘ ሃውልት በማሰራት፤ ይህንንም ሕገ ወጥ ተግባር እንዲያርሙና ሃውልቱም እንዲፈርስ በቅዱስ ሲኖዶስ ሲወሰንባቸው ውሳኔውን አልቀበልም በማለት እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ ሕግን በመጣስ በእንቢተኝነት ኖረዋል።

· የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ የሆኑት አለቃ አያሌው በህይወት ዘመናቸው አባ ጳውሎስ የሚፈጽሙትን ከሃይማኖት የወጣ ተግባር በመኮነናቸው ሲሞቱ መቀበሪያ እንዲከለከሉ በማድረግ የሞተ ሬሳን ተበቅለዋል።

· በቅርቡ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ በአጠቃላይ ለሃገሪቱ ታላቅ ታሪካዊ፤ መንፈሳዊና ቅዱስ ቦታ የሆነውን የዋልድባን ገዳም አገዛዙ ቤተ ክርስቲያንን በማፍረስና መነኮሳትን በማሳደድ ለስኳር ፋብሪካ ማስፋፊያነት ለማዋል ሲል በቤተ ክርስቲያና ላይና በመነኮሳቱ ላይ የሚደርስርውን ሰቆቅና በደል በጸጋ በመቀበል መነኩሴዎችን ሳይቀር በጎሳና በዘር ክፋፍለው ከፍተኛ በደልና ጥፋት እንዲደረስ አድርገዋል፤

· የአሰቦትና የዙቃላ ገዳሞች ሲቃጠሉም ሆነ ክርስቲያኖች ከነ ቤተ ክርስቲያናቸው ሲቃጠሉና ሲታረዱ አባ ጳውሎስ በዝምታ ተመልክተዋል።

· ከአገዛዙ ነፍሰ በላ ወታደሮች ሸሽተው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተጠለሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለገዳዮች አሳልፈው ሰጥተዋል፤

· በ1997 ዓ/ም ከቅንጅት መመረጥ ጋር ተያይዞ ምንም ከማያውቅ የሰባት ዓመት ህጻን ልጅ ጀምሮ የ10 ልጆች እናት ያሉበትን ወንድ፤ ሴት፤ ልጅ አዋቂ ሳይል 200 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን አገዛዙ ሲገድል አባ ጳውሎስ ግድያውን ማውገዝ ሲጠበቅባቸው ይባስ ብለው ለነዚህ የሞቱ ዜጎች ምንም ዓይነት ጸሎትና ፍትሐት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳይደረግ ጥብቅ መመሪያ ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማስተላለፍ አገዛዙ ከፈጸመው ያላነሰ በክርስትና ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ግፍ ፈጽመዋል።

· አገዛዙ ለገዳላቸው ዜጎች ጸሎት አይደረግ የሚለው የአባ ጳውሎስ መመሪያና ትዕዛዝ ከኢትዮጵያም ድንበር አቋርጦ ወጥቶ በውጪ ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በወኪሎቻቸው አማካኝነት ተግባራዊ እንዲያደርጉት ተሞክሮ በተለይ የለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላት በህብረት በመነሳት መመሪያውን በመቃወም በግፍ ለተገደሉት የኢትዮጵያ ልጆች ጸሎት በማድረግ የእውነተኛ ክርስቲያን ሥራ ለሰራ ተችሏል።

· ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከ6 ዓመት በፊት በወሰደችው አቋማ ምክንያት ከማንም ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖ ነጻ በመውጣት ፈጣሪ አምላክን ብቻ በመከተል እሱ መድሐኒአለም ረድቷት ባካሄደችው ከፍተኛ እንቅስቃሰ በጥቂት አመታት ውስጥ አባሎቿ በዝተውና ተጠናክረው የከፍተኛ ንብረት ባለቤት ለመሆን በመብቃቷ ይህንን የቤተ ክርስቲያኗን ዕድገት የተመለከቱት አባ ጳውሎስ የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ልትገዛ ነው የሚል ወሬ እንደሰሙ ለእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ኦፊሻል ደብዳቤ በመጻፍ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን ህንጻ እንዳይሸጡላቸው ከፍተኛ ተቃውሞ አቅርበው ለመበቀል ጥረዋል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህንን ሁሉ ሁኔታ አይቶና ገምቶ በአባ ጳውሎስ ላይ የወሰደውን አቋም ነው አባ ግርማ ከበደ ዛሬ ህዝብን ንቀውና ተዳፍረው የሕዝብን አቋምና ውሳኔ በራሳቸው ስልጣን ለማፍረስ የሚሞክሩት። ታዲያ ሕዝበ ክርስቲያን ዛሬ ለቤተ ክርስቲያንህና ለመብትህ ያልቆምክ መች ልትቆም ነው?