የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት ምስረታ ጉባኤ አጭር ዘገባ
ከአሰፋ ገብረማርያም ተሰማ
ከሁሉ አስቀድሜ የማክበር ሰላምታዬን ከ<እሳቱ ከተማ ወቁማሩ አውድማ>Las Vegas በትህትና አቀርባለሁ። ከሰኔ 24-26 ቀን 2004 አ.ም(July 1-3/12) በሰሜን አሜሪካ በቴክሳስ ዋና ከተማ
በዳላስ(Dallas,TX )በተደረገው<የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት ምስረታ ጉባኤ>ላይ በታዛቢነት እንድገኝ የላስ ቬጋስ ቻፕተር(Chapter-የአካባቢ ምክር ቤት) በጋበዘኝ መሰረት፤የጉባኤውን ሂደትና አፈፃፀም ሶስት ቀን ሙሉ በአንክሮና በጥሞና ተከታትያለሁ።ስለሆነም ይህን አጭር ዘገባ በትህትና አቀርባለሁ።
በጉባኤው ወቅት ያሰማሁትን ንግግርና ግጥም ከማቅረቤ በፊት፤ የምክር ቤቱን አላማና ግብ፧አወቃቀር፧ ምክር ቤቱን ማቋቋም ያስፈለገበትን ምክንያትና በምክር ቤቱ ጠንሳሽና ዋና ፀሃፊ በዶ/ር ፍስሃ እሸቱ ላይ የተሰነዘረውን ቅሬታና ስሞታ በቅድሚያ በጣም በአጭሩ መግለፁ ተገቢ ይመስለኛል።የተቀረውን ከምክር ቤቱ ድረገፅ etntc.org ማግኘት ይቻላል።
የምክር ቤቱ ዋና አላማና ግብ፧ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት፤ በህግ የበላይነትና በዴሞክራሲ የሚያምኑ የዲያስፖራው ኢትዮጵያውያን በራስ አነሳሽነትና ፈቃደኝነት በቅድሚያ በቻፕተር ተደራጅተው፤ በዋናው የጋራ ምክር ቤታቸው አማካይነት በአገር ቤትና በውጭ አገር ከሚገኙ ተመሳሳይና ተቀራራቢ አላማና ግብ ካላቸው የሲቪክና የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም የህዝብ መገናኛ ተቋሞች ጋር በመተባበርና የሰፊው ህዝብ ትግል አጋር በመሆን ፤በስልጣን ላይ ያለውን ዘረኛና ጨቋኝ አገዛዝ አስወግዶ የሽግግር መንግስት የሚቋቋምበትን ስልትና ስርአት ለማመቻቸትና ለመቀየስ ነው። የመስራች ጉባኤውን ጋዜጣዊ መግለጫ (Press Release) Etiopian Review እና Ethiomedia ላይ ይመለከቷል በተጨማሪ!
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት-Ethiopian National Transition Council (ENTC) ከታች (ከgrass root) ወደ ላይ የተዋቀረ ዴሞክራሳዊና ህዝባዊ ውክልና ያለው የሲቪክ ድርጅት ነው። ይሄውም በስድስት ወር ጊዜ ብቻ በአሜሪካ፧ በአውሮፓና በአፍሪካ ከተቋቋሙት ከአርባ ከሚበልጡ ቻፕተሮች (የአካባቢ ምክር ቤቶች) የተላኩ ተወካዮች (delegates) የተሳተፉበት፤ በርከት ያሉ ወንዶች ወጣቶችና በቁጥር ጥቂት ቢሆኑም የሴቶች ተወካዮች ንቁ ተሳትፎ ያሳዩበት፤ አንዳንድ የሲቪክና የፖለቲካ ድርጅቶች የቀድሞና አዳዲስ አባላት በግል የተካፈሉበት፤ በእድሜ እንደኔ ጠና ያሉ በተወካይነትና በታዛቢነት የተገኙበት፤ በተለይም በቅርቡ በካናዳ ዋና ከተማ በኦቶዋ ከተመሰረተው <የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ> ሁለት ከፍተኛ የአመራር አባላት፦ የሸንጎው ም/ሊቀመንበር ወዳጄ ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላና አቶ ነገሬ አዲስ ጠቃሚ ንግግርና ገንቢ አስተያየት የሰጡበት፤ በተለመደው ድርጅታዊ አሰራር ሳይሆን በግልፅ ውይይትና ክርክር፧ በጋራ በወል ስምምነት (consensus) ወይም በድምፅ ብልጫ ማንኛውም ውሳኔ የተላለፈበት ጉባኤ ነበር። ከዚህም በላይ የዋና ፀሃፊውም ሆነ የሌላ ተመራጭ የሰራ ዘመን አንድ አመት ብቻ እንዲሆንና ለሌላ አንድ አመት ከፈለገና ከተመረጠ ሊያገለግል እንደሚችል ተወስኗል። ይህም በድርጅቱ ውስጥ አምባገነንት እንዳይኖርና ሌላ አባልም የሃላፊነት ድርሻውን እንዲወጣ ያስችላል።
<ቀደም ብለው የተቋቋሙ የሲቪክና የፖለቲካ ድርጅቶች ስላሉ ENTC አስፈላጊ አይደለም! የተጀመረውን ትግል የሚያቀዘቅዝና የሚያደናቅፍ ነው!> ለተሰኘው አስተያየት ደግሞ የበኩሌ አጭር መልስ፤ <በዳላስ የተደረገው የENTC ምስረታ ጉባኤ አስፈላጊነቱን በሚገባ አረጋግጦአል ነው!>ሆኖም ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠቱ አይከፋምና እነሆ! በአሁኑ ወቅት በልዩ ልዩ ምክንያት ቀደም ብለው በተቋቋሙ የሲቪክና ፖለቲካ ድርጅቶች ያልታቀፉ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተለይም ወጣቶች ስላሉ፤ ENTC ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የላቀ አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል። በተለይም በቅርቡ ከተቋቋመው <የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ> ጋር የቅርብ ትብብርና ምክክር እንደሚኖረው ይታመናል።
በዋና ፀሃፊው በዶ/ር ፍስሃ እሸቱ ላይ በቅንነትና በመሰሪነት ከጉባኤው በፊት የተሰነዘረው ቅሬታና ስሞታ መሰረተቢስ መሆኑን በጉባኤው ወቅት ለመገንዘብ ችያለሁ። ዝርዝር ገለፃ ውስጥ ባልገባም! ወያኔ የላካቸው መሆኑ ጭምር ተወርቶ ነበር! በጉባኤው ወቅት ጉልህ ተሳትፎ ያደረጉት፤ በወያኔና በሼህ አላሙዲን የተወነጀሉትና የተከሰሱት አቶ ኤልያስ ክፍሌ ያሉበት ENTC የወያኔ መሳሪያ እንዳልሆነና እደማይሆን በበኩሌ በፅኑ አምናለሁ!
የዶ/ር ፍስሃን ዳራ (background) ባላውቅም፤ በላስ ቬጋስ ቻፕተር ምስረታ ላይ በሰጡት ገለፃ፧ ከESAT ጋር ባደረጉት ውይይትና በጉባኤው ወቅት በነበራቸው አስተያየት፤ ግልፅ፧ ሃቀኛና ትሁት፤ ከፍተኛ የሃገር ፍቅር ያላቸውና አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል በገንዘባቸው ብቻ ሳይሆን በህይወታቸው ጭምር የቆረጡ ተግባራዊና ሃይማኖተኛ ምሁር መሆናቸውን ለመገንዘብ ችያለሁ በበኩሌ። ከዚህም በቀር በጉባኤው መዝጊያ ላይ አንዳንድ ተወካዮችና ታዛቢዎች በተለይም <የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ> ሊቀ-መንበር ወጣቱ አቶ ማስረሻ ጥላሁን በስሜትና በሲቃ ያደረገው ንግግር የዶ/ር ፍስሃን ሃቀኛ ኢትዮጵያዊነት፤አገር ወዳድነትና የወገን ተቆርቋሪነት ሊያረጋግጥልኝ ችሏል። በተረፈ ዋና ፀሃፊው በተደጋጋሚ በአፅንኦት እንዳሉት ማንነታቸውን < ጊዜና ታሪክ ይመሰክራል!> ከመጋረጃ ጀርባ ሆኖ ወይም የገቡበትን ድርጅት ብቻ የሙጥኝ ብሎ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከማካሄድ ልንቆጠብ ይገባናል እላለሁ።
የአበውንም ዘመን የማይሽራቸውን ምሳሌያዊ ንግግሮች (Proverbs) ማስታወሱና ማጤኑ ተገቢ ነው!ከብዙዎቹ መካከል የስም ማጥፋትን በተመለከተ አበው < ጎረቤትህን ሲያማ ለእኔ ብለህ ስማ፤አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል! >ሲሉ፤ተባብሮና ተጋግዞ የጋራ ጠላትን ለማሸነፍ ደግሞ < ድር ቢያብር አንበሳ ያስር!> ብለዋል። ስለዚህ ተባብረንና ተጋግዘን የኢትዮጵያን ጠላት እናስወግድ!
አገር ሲጠፋና ሲፈራርስ ገለልተኛ፧ ተመልካችና ከንፈር መጣጭ፧ የወሬ አናፋሽና አራጋቢ መሆን፤ ከዘረኛውና ከአምባገነኑ ከወያኔ መንግስት ደጋፊነት ተለይቶ አይታይምና አገር ወዳድና ተቆርቋሪ የሆን ሁሉ፤ በምናምንበት
የሲቪክና የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ አባልና ደጋፊ በመሆን የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ግዴታችንን ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ወቅቱ አሁን ነው!ይህን ያለመፈፀም የግልና የቤተ ሰብን ታሪክ ያጎድፋል! ብሄራዊ ግዴታችንንም ለመወጣት ENTC ከአመቺ መድረኮች አንዱ ነው!
ውድ አንባቢዎቼ! አስተያየታችሁን በE-mail: [email protected] ብትመይሉልኝ ከወዲሁ ከልብ አመሰግናለሁ። በግእዝ ፊደል ትየባ ገና ተለማማጅ በመሆኔ፤ እንደ ጥራጥሬ ለቃሚ ዶሮ ሆህያት መለቃቀሙ ስለሰለቸኝና ስለደከመኝ ከይቅርታ ጋር አጭር ዘገባዬን እዚህ ላይ ላብቃና ንግግሩንና ግጥሙን ነገ ተነገ ወዲያ አቀርባለሁ። አመሰግናለሁ! በቸር ይግጠመን !