የመድረክ አባላት ወደ እስር ቤት እየተጋዙ ነው
የካቲት 22 ቀን 2003 ዓ.ም መሳሪያ ደብቃችኋል በሚል ሰበብ የመድረክ አባል ፓርቲ የሆኑትን የኦፍዴንና የኦህኮ አባላትን ማሰር፣ ከስራ ማባረርና ከቀያቸው ወዳልታወቀ ቦታ መሰወር የጀመረው የመለስ አገዛዝ ድርጊቱን በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀጠለበት የመድረክ ዋና ፀሀፊ አቶ አለሙ ኮይራ አስታወቁ፡፡
ዋና ፀሀፊው እንዳስታወቁት፥ በ30/6/2003 ዓ.ም ከአካባቢው የደረሳቸው ሪፖርት እንደሚያስረዳው በጉጂ ዞን ብቻ 217 የኦፌዴን አባላት እስራትና መፈናቀል ደርሶባቸዋል፡፡ አቶ አለሙ በትላንትናዉ እለት እንደደረሳቸው የገለፁልን ሪፖርት ደግሞ 6 ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን ኢህአዴግ መሳሪያ ደብቃችኋል ብሎ እያሰቃያቸው የሚገኘው የኦፌዴን እና የኦህኮ አባላት በአብዛኛው ባለፈው ግንቦት ወር በተደረገው አገር አቀፍ ምርጫ መድረክን ወክለው የተወዳደሩ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ኢታና ሰንበቶ የተባሉ እና በቀለም ወለጋ ዞን ተወዳዳሪ የሆኑ ግለሰብ በ4/7/2003 ዓ.ም ቤታቸውን በታጣቂ እንዲፈተሽ ከተደረገ በኋላ በታጣቂዎች ተይዘው የደረሱበት አልታወቀም፡፡
በምስራቅ ወለጋ በባኮ ከተማ ተወዳዳሪ የነበሩት የኦፌዴን አባል አቶ መለሰ ጫላም በተመሳሳይ ቀን ቤታቸው ከተፈተሸ እና የእሳቸው እና የባለቤታቸው ተንቀሳቃሽ ስልክ በታጣቂዎች ከተወሰደ በኋላ ያልታወቀ ስፍራ ተወስዷል፡፡
በቀለም ወለጋ ዞን ደንቢዶሎ ከተማ ተወዳዳሪ የነበሩት አቶ አሰፋ ገለታ ደግሞ ለ3 ሳምንት ከታሰሩና ደመወዛቸውን ከተከለከሉ በኋላ ከደረጃቸው ዝቅ ብለው እንዲሰሩ ተደርገዋል፡፡
ባለፈው ምርጫ የኦፊዴን – መድረክ የፓርላማ እጩ ከነበሩት ውስጥ የኢሊባቡር ዞን በደሌ ወረዳ ተወዳዳሪ መቶ አለቃ ምትኩ ጉደታ በ4/7/2003 ዓ.ም ከመኖሪያ ቤታቸው በታጣቂዎች ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ የደረሱበትን ማወቅ አልታወቀም፡፡
ከተዘረዘሩት በተጨማሪ በኢሉባቡር ዳሪሙ ወረዳ የካቲት አጋማሽ ላይ 15 የኦፊዴን አባላት በታጣቂዎች መደብደባቸውን ያስረዳል፡፡
ከሪፖርቱ ያገኘነው ሌላው መረጃ እንደሚያስረዳው ደግሞ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ከተማ ተወዳዳሪ የነበሩት የአቶ ሙላቱ ሽፈራው ልጆች የሆኑት ተማሪ ደበላ ሙላቱ እና ተማሪ ሀብታሙ ሙላቱ በ1/7/2003 ዓ.ም ከት/ቤታቸው ወደቤታቸው ሲመለሱ ተይዘው በአባታቸው ምትክ እንዲታሰሩ ተደርጓል፡፡ ሁለቱ ልጆች ለአቅመ አዳም ያልደረሱ የ14 እና 15 ዓመት እድሜ ያላቸው መሆናቸውም ታዉቋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸው እንዲሰጡ ከጠየቅናቸው መሐል አንዱ የሆነው እና የኦህኮ አባል መሆኑን የነገረን ወጣት ደምሴ ደበሎ ባለፈው ምርጫ ምዕራብ ሸዋ ሜታ ሮቢ ወረዳ እጩ የጨፌ አባል እንደነበር ገልፆ ከዚህ ወረዳ ብቻ 5 አባሎቻቸውን መታሰራቸውን አስረድተዋል፡፡
“ገዢው ፓርቲ በሰሜን አፍሪካና በአረብ ሀገራት የተፈጠረው ቀውስ እዚህም እንዳይፈጠር ካለው ከፍተኛ ስጋት የመነጨ የከፈተው ጥቃት” በማለት የመንግስትን እርምጃ የገለፀው ወጣት ደምሴ መሳሪያ አከማችታችኋል በሚል አባሎቻቸው ከመንግስት የቀረበባቸውን ክስም መሠረት ቢስ ብሎታል፡፡
ይህን ያለበትን ምክንያት ሲያስረዳ “ሰዎቹ በሰላማዊ ትግል አምነው በሕጋዊ ፓርቲ ውስጥ ያሉና ከዚህ አነስ ሲልም የሕጋዊ ፓርቲ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ እንዴት መሳሪያ በማከማቸት ሊከሰሱ ይችላሉ?” ብሏል፡፡