ከወያኔ ጋር የሚሰሩ ድርጅቶችና አባላቶቻቸው ነፃነታቸውን የሚናፍቁ ናቸው
ዋለልኝ መኮንን
የወያኔ/ኢህአዲግ መንግስት ምንም ህዝብ ህዝብ ሳይሸት ላለፉ ሀያ አመታት የኢትዮጵያ ህዝብ የይሁንታ ድምፅ አግኝቻለው የበብሄር ብሄረሰብ መብትና እኩልነት አስከብሬያለው እያለ በማምታታትና በማጭበርበር ስልጣኑን የሙጥኝ ብሎዋል:: በሌላው በኩል ደግሞ ህዝቡና ከወያኔ ውጭ ያሉት የኢህአዴግ ካድሬዎችና የአጋር ድርጅቶች አባላቶች በተለያየ ዘዴዎች በመጠቀም አገራዊና ህዝባዊ መሰረትና ውክልና እንደሌለው ለማሳየትና ወያኔ/ኢህአዴግ የአንድን ብሄር ብቻ መብትና ጥቅም የሚታስጠብቅ መሆኑን በማጋለጥ ብቻውን እርቃኑን እንዲቀር እያደረጉት ይገኛሉ::
ከህወሃት ውጭ ያሉት የኢህአዲግ ድርጅቶች (ደህዴን ኦህዴድ ብአዴን) የዛሬ ሀያ አመት በወያኔ ፋብሪካ ሲመሰረቱም ሆነ ካድሬዎቻችው ሲሰበሰቡ ዋነኛ አላማው ህዝባዊ መሰረት እንዳለው በማስመሰል ብዙ መስዋትነት የተከፈለበትን የኢትዮጵያውያንን ትግል የተጠበቀውንና የታለመለትን ውጤት እንዳያመጣ አድርጎ የህዝብን ስልጣን ለመቆናጠጥ ሲባል ነበር:: ለዚህም አላማችው ብዙ ህዝብ የብዛት ያላቸውን ብሄሮች አቅም በማይፈጥሩበት አካሁዋን በወያኔ ስር እንዲደራጁ ማድረግ ነበር ይህንን አድርገውም ይኸው ስልጣናችውን ለሁለት አስርት አመታት እየተንገዳገዱም ቢሆን ቆይተዋል::
ወያኔ ይህንን የማጭበርበሪያ ዘዴ በመጠቀም ስልጣን ከያዘ በሁዋላ ከሞላ ጎደል በሙሉ ሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን የስልጣን ክፍፍሎቹን በራሱ በህወሃት ሰዎች እጅ ውስጥ አስገብቶዋል:: እጅግ በጣም ጥቂት የስልጣን መደቦችን ከሌሎች ብሄረሰቦች ለተሰባሰቡ በርቀት መቆጣጠሪያ ለሚጠበቁ የኢሀአዴግ ተብዬ ካድሬዎች ለይምሰል ሰጠ:: ነገር ግን እነዚሁ ከህወሃት ውጭ ያሉት የኢህአዴግ ካድሬዎች (ኦህዴድ ደህዴን ብአዴን) በሀገር ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት ውሳኔ ሰጭነት ጉልበት የላቸውም:: ኢህአዴግ ለይስሙላና ለማጭብርበር ቀጥቅጦ የሰራቸው ኦህዴድ ደህዴን ብአዴን ክልላችውን ይቅርና አነስተኛ ቀበሌ እንኩዋን በክልላቸው የማስተዳደር ስልጣን እስካሁን አልተሰጣችውም::
ህወሃትና/ኢህአዴግ የስም መቀያየር እንጂ ያው ወያኔ/ህወሃት ማለት ነው እንደውም አንዳንድ ግለሰቦች ኢህአዴግ የወያኔ ክርስትና ስሙ ነው ብለውታል:: መላው የኢትዮጵያ ዝብና ህወሃት ውጭ ያሉት የኢህአዲግ ድርጅቶች አባላቶች (ደህዴን ኦህዴድ ብአዴን) በተለያዩ ጊዜያት የወያኔና የኢህአዴግን አንድነትና ሁለትነትን ግልፅ አድርገውልናል የህወሃትና የኢህአዴግ አንድነት ለኢትዮጵያውያንና ለመላው አለም ከተገለፁበት ክስተቶች መካከል::
፠ ኢህአዴግ ላይ የጠነከረ ተቃውሞ ሲደርስበት በመጀመሪያ የሚጮሁት ህወሃት ወያኔዎች ብቻ ናቸው:: ሚያዚያ 30 ቅንጅትን በጠራው ሰልፍ ላይ አንድ የድርጅቱ አባል ኢህአዴጎችን ወደመጡበት እንመልሳቸዋለን ብለው ነበር ነገር ግን ለዚህ ንግግራችው ወያኔ ህወሃት ብቻውን ነው መልስ ሲሰጥ የነበረው ህወሃት ውጭ ያሉት የኢህአዲግ ድርጅቶች አባላቶች (ደህዴን ኦህዴድ ብአዴን) ምንም አይነት መልስ አልሰጡም እንደውም በንግግሩ የተደሰቱ ይመስሉ ነበረ::
፠ ከህወሃት ውጭ ያሉት የኢህአዲግ ድርጅቶች (ደህዴን ኦህዴድ ብአዴን) ድርጅታዊ ስብሰባዎች ያለ ህወሃት ወያኔ ተሳታፊነት አይካሄዱም በተቃራኒው ግን የህውሃት/ወያኔ ድርጅታዊ ስብስባ ላይ ምንም አይነት ከህወሃት ውጭ ያሉት የኢህአዲግ ድርጅቶች አይሳተፉም::
፠ እስካሁን በወያኔ የስልጣን ዘመን ከህወሃት ውጭ ያሉት የኢህአዲግ ድርጅቶችና አባላቶቻችው (ደህዴን ኦህዴድ ብአዴን) ብቻ ናቸው እንደ ጥፋተኛ ሙሰኛ ልማት አደናፋቂ……..ምናምን ተብለው በህወሃቶች/ወያኔዎች በአደባባይ የሚብጠለጠሉት:: በተቃራኒው ግን አንድም የወያኔ/የህወሃት ድርጅት አባል ከህወሃት ውጭ ባሉ የኢህአዲግ ድርጅቶች (ደህዴን ኦህዴድ ብአዴን) ጥፋተኛ ሙሰኛ ልማት አደናፋቂ ምናምን ተብሎ የተተቸ የለም:: አይደለም ጠመንጃና ስልጣን የያዘውን የወያኔን ድርጅት መተቸት ይቅርና አንድን የድርጅቱን አባል ቆጣ ብሎ መናገር በሀገር ውስጥ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ሁላችንም ያየነውና ያረጋገጥነው ነገር ነው::
፠ በወያኔ/ኢህአዴግ ድርጅታዊ መበስበስና የመልካም አስተዳደር ስርዐት መበላሸት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳስባቸው ኢህአዴግን ለማጭበርበሪያነት የፈጠሩት ህወሃቶች ብቻ ናቸው:: ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ካድሬዎች ስለድርጅቱ መበስበስም ሆነ መጠንከር የሚያውቁት ከህወሃት ሲነግራቸው ብቻ ነው:: ህወሃት/ወያኔ ድርጅታዊ መበስበስና የመልካም አስተዳደር ስርዐት መበላሸት የሚለካበት አንድና አንድ መመዘኛው መስፈርት የህወሃት/ወያኔ የስልጣንና የምጣኔ ሀብት ባለቤት የማያስደርገው አካሄድ ሲፈጠር ብቻ ነው::
፠ ከፍተኛ የደህዴን የኦህዴድ የብአዴን ብሎም ሌሎች አጋር ድርጅቶች ብሎ ወያኔ ስም ያወጣላችው ክልሎች ባለስልጣኖች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የተደረጉ ውሳኔዎችም ሆኑ ስምምነቶች ላይ ምንም አይነት የተሳትፎ ድምዕ የላቸውም:: የወሳኝነት ስልጣን ለወያኔና ለወያኔ ብቻ ነው:: ትላልቅ ሀገራዊ ውሳኔዎችን የሚሰሙት ልክ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በወያኔ የሚዲያ ማሰራጫ ነው:: በጣም የሚገርመው ደግሞ በክልሎቻቸው የተፈፅሙትን ድርጊቶች እንኩዋን የሚነገራቸው ወያኔ መረጃዎቹን በሚፈልገው መልኩ ከተጠቀመባችው በሁዋላ በነሱ ልክ እንዲሰፋ አድርጎ ነው::
፠ ከህወሃት ውጭ ያሉት የኢህአዲግና አጋር ድርጅቶች በሚያስተዳድሩዋችው ክልሎች በስተጀርባ ሆነው የሚመሩት የወያኔ ካድሬዎች ናቸው:: ከክልሎች ባለስልጣናት ይልቅ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጭነት ጉልበት ያላቸው በዝቅተኛ የስራ ደረጃ የተቀጠሩ የወያኔ/ህወሃት ካድሬዎች ናቸው::
ከላይ ያየናቸው ተጨባጭ ክስተቶች የሚያረጋግጡልን የህወሃት/ኢህአዴግ በተለያዩ ብሄረሰብ ስም እራሱን ደብቆ የአንድን ብሄር የስልጣንና የጥቅም አስከባሪ ድርጅት መሆኑን ብቻ ነው:: ከአንድ ብሄር ከተውጣጡ ካድሬዎች በስተቀር ምንም የሌሎች ብሄሮች የውሳኔ ተሳትፎ የሌለበት ዘመናዊ ቅኝ ግዛት በሚያስብል ደረጃ ሀገሪቱን እየዘረፍሩና እያስዘረፉ ይገኛሉ :: ከህወሃት/ከወያኔ ውጭ የሆኑት የኢህአዴግ አባላቶች የደህዴን የኦህዴድ የብአዴን ካድሬዎች ብሎም ሌሎች አጋር ድርጅቶች ብሎ ወያኔ ስም ያወጣላችው ክልሎችን የሚያስተዳድሩ የፓርቲ አባላቶች ለጊዜው የሚያገኙት ጥቅም ያስደሰታቸው ቢመስልም ያ ጥቅም ወያኔ ሆን ብሎ ለማባበልና አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ ለመፈዐም አዕምሮዋቸው የማይፈቅድላቸውን ግዳጅ የሚታዘዙበት እንደሆነ ዘግይተው የተረዱ ይመስላሉ:: በአሁኑ ሰዓት ከህወሃት/ወያኔ/ኢህአዴግ ጋር የሚሰሩ ድርጅቶችና አባላቶቻቸው ልክ እንደ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነታቸውን በመናፈቅ ላይ ይገኛሉ::