“ኢሳት ከሚገባ ቢላ በአንገቴ…” አቶ በረከት “የሚበጅዎትን እርሰዎ ያውቃሉ” እኔ

ይህንን ፎቶ ያገኘሁት ቢታንያ ከተባለች ወዳጃችን ነው። ርዕሱም ከፎቶው ላይ ተኮርጇል። ያኑርሽ እንላታለን!

ሰሞኑን አቶ በረከት ሰምዖን “ኢሳት ቴሌቪዥን ወደ ኢትዮጵያ ከሚገባ ቢላ በአንገቴ…” አይነት ንግግር መናገራቸውን ሰምተናል።

እንዴት አደሩ አቶ በረከት…! እኔ የምልዎት ከ “አረብ ሳት” ባለስልጣናት ጋር ያደረጋችሁትን ውይይት ኢሳት ቴሌቪዥን ዘግቦት ተመልክተነው እኮ! እውነት እርሶዎ አፍዎን ሞልተው፤ “የኤርትራ ቴሌቪዥን ከፈለገ ይግባ በኢሳት ጉዳይ ግን አንደራደርም!” ብለው ተናገሩ!?

ምነው አቶ በረከት ለራስዎ ስምዎ ጥሩ አይደለም። አንዳንድ ንግግሮች ላይ ጥንቃቄ ቢያደርጉ ምን አለበት!? እኔም ምን ጨነቀኝ ለራስዎ ብዬ ነው። ሰዉ፤ “እኒህ ሰውዬ ኤርትራዊ በመሆናቸው ከድሮም ጀምሮ የኤርትራ ጉዳይ እንጂ የኢትዮጵያ ነገር አያስጨንቃቸውም!” እያለ ስምዎን ሲያነሳና ሲጥል ተመልክቻለሁ።  ምን ጨነቀኝ እኔ፤  የፍርድ ቀን የደረሰ ጊዜ፤ “ምነው ምላስ ባልኖረኝ ኖሮ…! እኔን ብሎ ተናጋሪ… እኔን ብሎ ኮሚዩኒኬሽን ሚንስቴር… እኔን ብሎ መግለጫ ሰጪ…. እኔን ብሎ ተደራዳሪ…!”  ማለት ይመጣል።

ነገር  ግን መጪውን አላመላከትዎትምና  አልህ ጩቤ ያስውጣል እንዲል የሀገሬ ሰው ጭራሽ ብለው ብለው “የኤርትራ ቴሌቪዥን ላይ ተቃውሞ የለኝም ኢሳት ግን ወደ ኢትዮጵያ ከሚገባ ቢላ በአንገቴ!” ብለው ፎክረዋል አሉ። በርግጥ የሚበጅዎትን የመምረጥ መብትዎን መጋፋት ተገቢ አይደለም። ከኢሳት ቢላ ይሻለኛል። ካሉ እንግዲህ ወደ ጓዳዎ ገባ ብለው የሽንኩርት ወይም የስጋ አማርጠው መጠቀም ይችላሉ። ለምን ክፉ ያናግሩኛል አቶ በረከት!? እንደኔ እንደኔ ግን ከቢላ ኢሳት ይሻልዎታል!

የምር ግን እኛ ለአባይ መገደብያ ብለን በምናዋጣው ገንዘብ ራሳችንን እና እነ ኢሳትን መገደቡን ቀጥሎበታል። በዚህ አይነት ሁኔታ ነው… ለቀጣይ አርባ አመት ለመኖር ያቀድነው…? አረ ይደብራል!? እንዴት ነው ነገሩ ድርጅታችን ካለመገደብ ስራ የላትም እንዴ!? በኑሮ ውድነት ሳብያ አመጋገባችን ተገደበ ዝም አልን፣ በተለያዩ አዋጆች እና ህጎች ሳቢያ ከሰዎች ጋር ያለን ወዳጅነት ተገደበ ዝም አልን፣ ነጋ ጠባ ሀርድ እየተሰጠን ንግግራችን ተገደበ ዝም አልን፤ አሁን ደግሞ አትሰሙም አታዩም ተብለን እየተገደብን ነው! ተዉ ይሄ ነገር ጥሩ አይመጣም!

እውነቱን ንገረን ካሉኝ መካሪ እያጣችሁ ነው።

ተዉ… ብሶቲቱ ዛሬም ታረግዛለች።

ተዉ… ብሶቲቱ ዛሬም ትወልዳለች።

ተዉ… ዛሬም ጀግና ይፈጠራል

ተዉ… ዛሬም ንጉስ ይከሰሳል

ተዉ… ኋላ ማጣፊያው ይቸግራል

ተዉ… ምክር መስማት ይሻላል።

ተዉ… ተዉ… ተዉ… ዉዉዉ…!

ለማንኛውም ለጠቅላላ እውቀትዎ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተማ ያሉ ኮምፒውተር የሚጠቀሙ ወዳጆች የኢሳትን ዜናዎች እና ዝግጅቶች እንደምንም ብለው ለመከታተል እየቻሉ እንደሆነ ሰምቻለሁ። እናንተ በከለከላችሁ ቁጥር ሰዉ የተለያዩ መላዎችን መጠቀም ጀምሯል። ምናልባት ይሄ ክፉ ቀን ሲያልፍ ብልሀቶቹ በሙዚየም ይቀመጡ ይሆናል።

እኔ የምልዎ…

አብዮት አደባባይ የሚገኘው ሙዚየም እስቲ ዛሬ ጎራ ብለው ይጎብኙ። ደርግ በተቃወሙት ላይ ሲያደርግ የነበረውን የሚያሳይ ብዙ ነገር አለልዎት። እውነቱን ለመናገር አብዛኛውን ነገር ዛሬም ድረስ ያለ እንደሆነ ከጉብኝቱ ሲወጡ ራስዎ ይመሰክራሉ።

ለዛሬ ግን በደርግ ግዜ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ወጣቶች ሃሳባቸውን ለመግለፅ በድብቅ ሲጠቀሙባት የነበረች የማተሚያ ማሽንን ሄድ ብለው እንዲመለከቷት ልጋብዝዎ።

ልክ እርሱን ሲመለከቱ መከልከል መፍትሄ እንደማይሆን ትዝ ይሎታል። ዛሬም በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን ወጣቶች ምን እያደረጉ ይሆን? ብለው ራስዎን ይጠይቁ? እውነት እውነት እለዎታለሁ። የዘጋችሁትን በሙሉ የሚከፍቱ ብልሀተኛ ወጣቶች በሀገሪቱ ሞልተዋል።  እናም መገደብ መፍትሄ  አይሆንም!

Filed under: Uncategorized