የዋልድባ ገዳምን በተመለክተ የሂዩስተን ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ምዕምናን የአቋም መግለጫ

ጥንታዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰው ልጆች ደኅንነትና ዘላለማዊ ሕይወት የምናገኝበትን ቅዱስ ወንጌል መሠረቱን ሳትለቅ በማስተማር ሁለት ሺህ ዓመታትን አስቆጥራለች። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ታማኝ ኣገልጋዮቿ በከፈሉት መስዋዕትነት ዕምነቷን፣ ሥርዓቷንና ትዉፊቷን ጠብቃ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ጽላት(ታቦተ ሕግ) አክብራና አስከብራ ለአኛ ትውልድ ለማድረስ በቅታለች። እኛም ይህን ከቀደምት አበው የደረሰንን የሃይማኖት አደራ ከማናቸውም በላይ አስበልጠንና አስቀድመን፤ ጠብቀንና አስጠብቀን ለቀጣዩ ትዉልድ የማስረከብ መንፈሳዊ ግዴታ እንዳለብን ለአፍታም አንዘነጋዉም።

ቤተ ክርስቲያናችን በረጅም ጊዜ ታሪኴ አያሌ ፈተናዎችንና ውጣ ውረዶች ቢገጥሟትም ሁሉንም አንደየአመጣጣቸው ተቌቁማ በፆምና ፀሎት ኃይል በመድኃኔዓለም ድጋፍ በድል አድራጊነት እንደተወጣችው የታሪክ መዛግብት ፍንትው አድርገው የሚያስነብቡን ሐቅ ነው።

በዘመናችን በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በያቅጣጫው የሚሰነዘሩትን ጥቃቶች እያስተዋልን በዝምታ ለመመልከት የሚያስችል ህሊና አይኖረንም። ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል በአሰቦት ገዳም በሚኖሩ መነኮሳት ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ፣ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ላይ የተካሄደው የመዝረፍና የማቃጠል ተግባር፣ በዓለ ጥምቀትን የመሳሰሉ ታላላቅ በዓላት በሰላም እና በድምቀት አንዳይከበሩ ማወክ፣የቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ ሌሎች ታላላቅ የመንፈሳዊ ጉባዔዎች እንዳይሰምሩ የመከፋፈልና የመበታተን ሤራዎች፣ አንደ ዝቌላን በመሳሰሉ ቅዱስ ገዳማት ላይ የአሣት ቌያ መልቀቅ ወዘተ..፣ ይጠቀሳሉ።

በተለየ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቤተ ክርስቲያናችን ታላላቅ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማት አንዱ በሆነው የዋልድባ ገዳም ላይ በልማት ሥራ ሽፋን አየተካሄደ ያለዉን አፍራሽና አሣፋሪ ተግባር በተመለከተ ሀገር ቤት ከሚገኙት ዘመዶቻችን በቀጥታ ከሚደርሱን መረጃና፤ በተለያዩ የዜና አውታሮችም ክሚቀርቡት ትንታኔዎች በጥሞና እንደተገነዘብነው በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተከፈተ ታላቅ ሤራና ጥቃት ነው።

የዋልድባ ገዳም ቅዱሳን አበው መነኮሳትና መነኮሳይያት ረሀቡንና ጥማቱን፣ ብርዱንና ሀሩሩን ታግሠው፣ የሀገርን ቅርስና ሀብት ጠብቀው፣ ለሀገር ሰላም ፣ ፍቅርና ዕድገት ያልተቌረጠ ፀሎት የሚያደርጉበት ቅዱስ ሥፍራ ነው።

የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱት ዋልድባ የአብረንታንት ገዳም በንጉስ አል አልዓሜዳ ዘመነ መንግሥት በ484 ዓ፡ም ተመሠረተ። ገዳሙን በማስፋፋትና በማደራጀት ረገድ በአፄ አምደ ፅዮን ዘመነ መንግሥት በ 1319 ዓ፡ም አቡነ ሣሙኤል ታላቅ አስተዋፆ ሲኖራቸው፣ ከዚያም ከደብረ ሊባኖስ የሄዱ አባቶች “ በገዳም እንኖራለን፣እህል አይገባንም” በማለት በመወሰናቸው የጣመ የላመ የማይቀመስበት የሞቀ የደመቀ የማይለበስበት ሲሆን ቌርፍ ወይም ሙዝ በጨው ተቀቅሎ በመመገብ ብቻ እንዲኖር የተወሰነበት ገዳም ነው።

የዋልድባ ገዳም ከአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት (1426-1460 ዓ፡ም) ጀምሮ በአራት ጅረቶች መካከል እንዲሆንና ገዥ እንዳይገባ አራሽ እንዳይሰማራበት የተወሰነ ሥፍራ ነው። በዚሁ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ ሽሬ እንዳሥላሴ እና በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ዓዲ አርቃይ ወረዳ ክልል በሚገኙ ሦስቱ የዋልድባ ገዳማት በአጠቃላይ ከ3000 ያላነሱ መነኮሳትና መነኮሳይያት የሚገኙበት ቅዱስ ሥፍራ ሲሆን አስከ 50 ዓመት ድረስ በአርምሞ ተወስነው/ከሰው ተነጋግረው የማያውቁ/ ቅዱሳን አባቶች በዘመናችን ሣይቀር የሚገኙበት ነው።

ይህን የመሰለ ለዘመናት የተከበረና የተቀደሰ ሥፍራ ነው እንግዲህ የወቅቱ መንግሥት የስኴር ፋብሪካ አቌቁማለሁ በሚል ገዳሙን አቌርጦ የሚፈሰውን የዛሬማን ወንዝ ለመገደብ በሚካሄደው ቁፋሮ የቅዱሣን አባቶች ዐፅም ያረፈበት በግሬደርና በሌሎችም መሣሪያዎች ኃይል እየታረሰና እየፈለሰ መሆኑን ስንሰማ ልባችን ይደማል። ሰላምና ፀጥታ ነግሶበት ተከብሮ የነበረ ሥፍራ ዛሬ ግን የዓለማውያን መናኸሪያ፣የነጋድያንና የሕዝብ መሥፈሪያ፣የመኪና መሽከርከሪያ መደረጉ ማኅበረ መነኮሳቱ ያዘኑበትና በፅኑ እየተቃወሙት መሆኑን በተለያዩ የዜና ማሠራጫዎች ካቀረቡት ዘገባዎች ተረድተናል።

ከላይ ከብዙ በጥቂቱ ለመግለጽ እንደተሞከረው ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት ላይ ከፍተኛ ጥቃት መድረሱን በወቅቱም መፍትሔ ሳይገኝላቸው እየተባበሱ መምጣታቸው የእምነቱ ተክታዮች የሆንነዉን እጅግ አሳስቦናል።በተለይም መንግሥት የሚለው መንግሥት የቤተ ክርስቲያንን ይዞታና መብት በመጠበቅ ለሌሎች ጭምር አርአያ መሆን ሲገባው ጉዳዩን ቸል በማለቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከታሪክ ተጠያቂነት አያመልጥም።የሕዝብን ድምፅ አለመስማት ፣የቤተ ክርስቲያንንም አቤቱታ አለመቀበል ትዕግሥትን የሚፈታተን፣ መፍትሔ ካልተሰጠውም ዉሎ አድሮ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ በመሄድ አገርን የሚጎዳ ፡ ታሪክንም የሚያበላሽ ክስተት ከመሆኑ በፊት አስቸኴይ ርምጃ ይወሰድ ዘንድ አበክረን እያሳሰብን የሚከተሉት ጥያቄዎች ባፋጣኝ ተገቢው ምላሽ እንዲሰጣቸው እንጠይቃለን።

የኢትዮጵያውያን ሁሉ መንፈሳዊ ሀብትና የተቀደሰ ሥፍራ የሆነው የዋልድባ ገዳም ክልል በማንም እንዳይደፈርና በልማት ሰበብ የተጀመረው እንቅስቃሴ እንዲቆምልን፣
በዋልድባ ገዳምና በዙሪያውም በሚገኙት አብያተ ቤት ክርስቲያናት የሚደርሰው ዝርፊያና ምዝበራ እንዲቆም መንግስት ለገዳማውያኑም ሆነ ለቅርሶቹ ተገቢዉን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግልን፣
የዋልድባ ገዳም መነኮሳት በዝርዝር ላቀረቡት አቤቱታ ተገቢና በጎ ምላሽ እንዲሰጣቸው፣
በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙት ገዳማትና አድባራት የሀገር ሀብትና ቅዱስ ቦታዎች ስለሆኑ በማንም እንዳይደፈሩ መንግሥት አስተማማኝ ማረጋገጫ እንዲሰጥ፣ጥበቃም አንዲያደርግላቸው።
የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስጠበቅ በሚንቀሳቀሱ አባቶችና ክርስቲያኖች ላይ በመንግሥት ኃይሎች የሚደረገው ዛቻና እንግልት አንዲቆም እንጠይቃለን።
የመንግሥት የዜና ማሰራጫዎች በኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት አንዲሁም ክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰዉን ጉዳት አንዳያፍኑና በግልፅ እንዲዘግቡ እንጠይቃለን።

እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያንና ጥንታዊ ገዳማችንን ይጠብቅልን። አሜን።