ቤተ-ክርስቲያን የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ መድረክ አይደለችም!
የጽሑፉን ሙሉ ይዘት ለማንበብ ከመዝለቅዎ በፊት÷
የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ከለበትና ከሚገኝበት አስከፊ የአገዛዝ ስርዓት የተነሳ “በቃኝ!” በማለት በጋጠ ወጦችና በልበ ደንዳና የሀገር መሪዎች ላይ በሚያደርገው የህልውና ትግል “ተቋዋሚ” የፖለቲካ መሪዎች በብልጣ ብልጥነት ሳይሆን በቅንነትና በእውነት ላይ የተመሰረተ እርዳታ እሸው ለነፃነት ለፍትህና ዲሞክራሲ በሚደረገው ሰላማዊ ትግል ቤተ-ክርስቲያን የድርሻ ትወጣ ዘንድ በይፋ ጥሪ ካቀረቡ የቤተ-ክርስቲያንም የሆነ የሃይማኖት መሪዎች እርዳታ ውጤት ሊያስገኝ የሚችለው ቤተ-ክርስቲያንም ሆነች የእምነቱ ተከታዮች ምእመናን እርዳታ ፍሪያማነት በዋናነት እነዚህ ሁለት አካላት ይተዳደሩበትና ይመሩበት ዘንድ የተሰጠ ፍጹምና የበላይ ባለ ሰልጣን የሆነውን መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስ) ማዕከል ያላደረገ ማንኛውም ዓይነት “የቤተ-ክርስቲያንና” የሃይማኖት መሪዎች እርዳታና እንቅስቃሴ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዘን እንዲሁም ቤተ-ክርስቲያን እንደ ተቋም መሪዎችም እንደ መንፈሳዊያን እስከ ምን ድረስ መሄድ እንደሚችሉና እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀውን ጽሑፍ በተቀመጠውን የጽሑፉ ዓላማም አንፃር በመረዳት ያነቡት ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ። በተጓዳኝ የቤተ-ክርስቲያን ድርሻና ሃላፊነት የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት ከጽሑፉ ግርጌ የተቀመጠውን “ሊንክ” በመጨቆን ግንዛቤዎትን ያስፉ።[1]
“ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው።
ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።” ዕብራውያን 5÷ 11- 14።
መሰረት በሌለው የሐሰት ቃል በመጻፍ የሰዎችን ስሜት በማነቃቃትና በመኮርከር ተወዳጅነትን ማትረፍ፣ ክፉ ቀን ሲመጣም አላየሁም አልሰማሁም በማለት ጥሎ የሚሸሸ ዘለቄታ የሌለው ጊዜያዊ ወዳጅ ማፍራት፣ በተለይ በምዕራቡ ዓለም የከተመውን ወገን በሆነ ባልሆነ ርዕሰ ጉዳይ ገደል አፋፍ ላይ ደርሶም ሳለ ቁም ማለት ሲያስፈልግ ግድ የለም እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው ወደ ፊት ንካው! እያልኩ ምንም ዓይነት ነቀፌታና ውጣ ውረድ በሌለው አኳህን ወጎችን ባማረ ቃልና አገላለጽ እያጣፈጥኩ ሰውን ሁሉ ባስደስት ለእኔው በተሻለኝ። ምንም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ የሚገኘውን የዘልአለም ህይወት ውስጥ ለተጠቀለለ እንዲሁም ኩነኔና ፍርድ የሌለበትን ለሰው ልጅ ያልተገባ ከዘንዶ የአንደበት ፍሬ የሚወጣውን የስድ አደግና የልቅነት ቃላትም ሰለባ ባልሆንኩ ነበር። ዳሩ ግን የሚጻፈው ሁሉ ትውልድን ከስህተት የሚጠብቁ፣ ነገ የጽድቅ ጸሐይ የሚያወጡ ናቸውና ጸሐፊው ለጊዜው እንደማይጥምዎት እያወቀ እንሆይ እንዳለ ሁሉ እርስዎም በበኩልዎ እየመረርዎትም ቢሆን ያነቡት ዘንድ በአክብሮት በመጠየቅ ነው። መልካም ንባብ!
ከፍ ስል በጽሑፌ መግቢያ ያሰፈርኩትን ጥልቅ የልብ ስብራትና ሐዘን የሚታይበት መሪ ጥቅስ የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ ለዕብራውያን ሰዎች የጻፈው ቃል ነበር። መጽሐፉ በአጠቃላይ የተጻፈው ከአይሁድ እምነት በክርስቶስ ኢየሱስ ብቸኛ አዳኝነትና ጌትነትን በማመን ወደ ክርስትና እምነት የመጡትን የአብርሃም ልጆች የሆኑትን ዕብራውያን ሲሆን ከክፍሉ ለመረዳት እንደሚቻልም ተደራሲያኑ ወይም የመልዕክቱ ተቀባዮች ወጣንያን/አዳዲስ አማኖችም ሳይሆኑ በሚገባ የከራረሙ ነገር ግን ጆሮቻችው ከመስማት የደከሙ፣ በክርስትና ሕይወታቸውም እያደጉና እየጎለበቱ መሄድ ሲገባቸው ለመንፈሳዊ ነገር ልበ ሙትና ዳተኞች ለሆኑትን ነው። ታድያ ጸሐፊው ከቆይታቸው ብዛትና ቀደም ሲልም በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ሲያስተምራቸው እንደ መምጣቱም መጠን አሁን ደግሞ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ስላለው ስለ ክርስቶስ ዘላለማዊ ክህነት ሊያስተምራቸው ሲጀምር (በተጻፈው ደብዳቤ) የመቃብር አፈር እንደ ተነሰነሰባቸው መቁለጭለጫቸውን እጅግ ሲጨነቀው ነው የምናስተውለው።
እውነት ነው የሺህ ዘመናት ዕድሜ ያላት ጥንታዊትና ታሪካዊት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያናችንም ተመሳሳይ ችግር ተከስቶ ማየቱ እጅግ የሚያሳዝን ነው። የዚች ጥንታዊትና ታሪካዊት የሆነችውን ቤ/ያን እምነት ተከታዮች ለሆኑት ምእመናንም ቤተ-ክርስቲያን ማለት ምን ማለት ነው? ምንስ ማለት ነው? የማንስ ናት? ተብሎ ስለ ቤተ-ክርስቲያን ምንነት “ሀ” ተብሎ ለማስተማርና ለመጻፍ መነሳት በራሱ ያለንበትንና የምገኝበት ክፍተኛ የሆነ መንፈሳዊ ኪሳራና ዝቅተት የሚያሳይ ነው። ችግሩ የከፋ የሚያደርገውም የእውቀት ማጣቱ ነገር ከምእመናን በባሰ መልኩ በአንዳንድ ካባ ባጠለቁና መስቀል በጨበጡ የሃይማኖት መሪዎች መታየቱ ነው። ከዚህም የተነሳ የጽሑፉ ይዘት ከመላ ጎደል ያነጣጠረው መልካም በሚመስል ዳሩ ትክክል ባልሆነ ኢ- ክርስትያናዊና ኢ- መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልምምድ ለተዘፈቁ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን የሃይማኖት መሪዎችና ዋኖች ለሆኑት ተጻፈ። ጸሐፊው ይህን ጽሑፍ ሲያዘጋጁም በተሰበረ ልብ ሐዘን እየተሰማቸው ነው። የሚሰማኝ ሐዘንም ሌላ ሳይሆን ቃለ ወንጌል በሉቃስ መጽሐፍ ምዕ. 12÷ 35- 48 ላይ “ … ያ ባሪያ ግን ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ ሌሎዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል ከሁለትም ይሰነጥቀዋል ዕድሉም ከማያምኑ ጋር ያደርገዋል። የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደፈቅዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል።” እንዲል።
ወረደም ወጣም አንባቢ ሆይ! ቃል ሲነገር ለህይወትም ለፍርድም ነውና ምርጫው ለሰሚ ጆሮ ለአንባቢ ልቡና በመተው ወደ ነጥቤ እሄዳለሁ። በታላቅ ግፍና በጭቆና የሚገኘውን ሕዝብ ለነጻነቱ በሚያደርገው ትግልም ቢሆን የቤተ-ክርስቲያን ድርሻ ሚዛኑን በጠበቀና መጽሐፍ ቅዱስን ማዕከል ያደረገ ከመሆን ውጭ ለጥቂት ግለሰቦችና ለፖለቲካ መሪዎች ግላዊ ጥቅምና ስጋዊ አጀንዳ በሚያመች መልኩ/መንገድ በማመቻቸት አይደለም። በአሁኑ ሰዓት አንዳንድ ስም ያላቸው የሃይማኖት መሪዎች በቤተ-ክርስቲያን ስም እያደረጉት ያሉት መጽሐፍ ቅዱስ ያላማከለ እንዲሁም የክርስትና መሰርት የሌለው ያልተገባ እንቅስቃሴም ይህንን ሐቅ የሚያረጋግጥ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የበልዓም መንገድም ሕዝብን የሚያተርፍ አካሄድ ሳይሆን ውሎ አድሮ ሀገርንና ወገንን ወደ ከፋ አዘቅትና መንፈሳዊ ኪሳራ የሚጨምር ለመሆኑ የሰው ዘር (ኢትዮጵያዊ ዜጋ) ባይሰማም ምድር ሆይ! ስሚ በማለት እናገራለሁ!
በአጭሩ ወደድንም ጠላንም የቤተ-ክርስቲያን ዓውደ ምህረት÷
v ለሰው ልጆች ሃጢአት የፈሰሰውን የበጉ ደም የሚዘከርበት:
v የጽድቅና የወንጌል ቃል የሚነገርበት:
v ሰላምንና ምሕረትን የሚሰበክበት:
v ፍቅርንና መቀባበልን የሚታወጅበት ደጅ እንጅ:
የቤተ-ክርስቲያን ዓውደ ምህረት÷
- መንታ ምላስ የሚወጣወጥበት:
- ያልጠራ:
- ያለየለት:
- የተቀላቀለና የስጋ ለባሽ አጀንዳ የሚደሰኮርበት “የብሔራዊ ትያትር”[2] መድረክ አይደለም።
ቤተ-ክርስቲያን እንደ መንፈሳዊ ተቋም የእግዚአብሔር ናት! በዚች ቤትም በስልጣን የሚስተጋባው ድምጽ አንድ የጠራ ድምጽ የእግዚአብሔር ድምጽ ብቻ ነው። በቤተ-ክርስቲያንና በደሙ በተቀደሱ አማንያን መካከልም እግዚአብሔር ብቻውን ይነግሳል፣ ከፍ ከፍም ይላል። በተጨማሪም ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚሰበሰቡትና ከየአቅጣጫው የሚፈልሱትም የማንም መንፈሳዊነትን የተላበሰ እንጨት እንጨት የሚለውን ንግግር ለመስማት ሳይሆን የሚነቅልና የሚተክለውን፣ ህይወትን የሚሰጥ በህይወትም የሚያኖር፣ በባህር ዳርቻ እንደ ተተከለች ዛፍም የሚያለመልም የእግዚአብሔር ድምጽ ለመስማት መሆኑ መዘንጋት የለብንም። ይህን የአማኞች መሰባሰብ እንደ አጋጣሚ እንጠቀምበት በማለት ቤተ-ክርስቲያን እንደ መሰላል ለመጠቀም የቋመጠ ባለ ስልጣንም ሆነ ስልጣን ፈላጊ ቢኖር ቅድሳት መጻህፍት ለትምህርታችን ተጽፈዋልና እንደ ባቢሎን ግንብ በቤተ-ክርስቲያን ላይ የተዘረጋውን መሳልልም መሰበሩ አይቀርም።
ስለሆነም በዚህ አጋጣሚ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የምትገኙ ከምህረት ይልቅ ቁጣን ለማውረድ እየተጣደፋችሁ ያላችሁትን የሃይማኖት መሪዎች ለአፍታ ቆም ብላችሁ ዓይኖቻችሁንም ከፍታችሁ ስራዎቻችሁንና ድርጊቶቻችሁን ትመለከቱና ትመረምሩ ዘንድ ትጠየቃላችሁ። ከዚህ በተረፈ ግን ድርጊታችሁ ሁሉ በቅድሳት መፃህፍት ሲመዘን ሕዝብንና ሀገርን እየጠቀማችሁ ሳይሆን ሕዝብንና ሀገርን በቀላሉ ሊወጥው ወደ ማይችል ቁልቁል እየደፋችሁት መሆናችሁን ግልጽ ለማድረግ እወዳለሁ።
በጥቂቶች ዘንድ እንደ ጭራቅ መቆጠር ትውልድን ከማትረፍ አይበልጥብኝም!
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
United States of America
June 4, 2012
[2] እንደው የመድረኩን ልዩነት ለማሳየት እንጅ የብሔራዊ ትያትር መድረክ በደፈናው እንዲህና እንዲያ ነው በማለት ለማጣጣል አይደለም።