በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የመኖር ዋስትና ስለማጣት
ከየእግዜሩ ተሾመ ተፈሪ
የወያኔ/ኢህአዲግ መንግስት በአገሪቱ በዘረጋው ፍትህ የጎደለው የኢኮኖሚ ሥርዓትና የአስተዳደር በደል የተነሳ አፍቃሪ ወያኔ/ኢህአዲግ የሆኑ ግለሰቦች በአንድ ጀምበር ሚሊየነር ሲሆኑ አብዛኛው ህብረተሰብ ግን ወደ ድህነት አዘአቅት ተወርውሮ አይቶት የማያውቀው እጅግ አስከፊ ኑሮ እየገፋ ይገኛል፡፡
የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ጥረት ከማድረግ በስተቀር ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ደንታ የሌለው የገዢው መንግስት በማናለብኝነት እኔ አውቅልሃለው፣ እኔ የምልህን ብቻ ስማ፣ በምመራህ መንገድ ተከተል በማለት ሰብአዊ መብቱንና ዲሞክራሲያዊ ነፃነቱን ነፍጎታል፣ ለሰው ሰራሽ የከፋ የኑሮ ውድነትም ዳርጎታል፡፡ በዚህም የተነሳ የሀገሪቱ ዜጎች የሰው ሀገር እንዲናፍቁና ለስደት እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል፡፡ በኢሚግሬሽን መ/ቤት በየቀኑ የሚታየው ቁጥር ስፍር የሌለው ሰውም የዚህ ችግር ነፀብራቅ ነው፡፡ ከፊሉም በበረሃና በዱር ለመሰደድ ሲሞክር ለወንበዴና ለዱር አውሬ አደጋ እየተጋለጠ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እጅግ አስከፊና አሰቃቂ ነው፡፡ በገጠር የወያኔ/ኢህአዲግ ካድሬዎች የመሬት ሰጪና ነሺ ስለሆኑ ለሙ መሬት የሚሰጠው ለታታሪ ገበሬው ሳይሆን ለፓርቲ አባሎችና ለፖሊቲካ ደጋፊዎች ነው፡፡ ከዚህም በላይ ገዢው መንግስት በገጠር ገበሬውን እኔ የምልህን የማትሰማ፣ የምሰጥህን ትእዛዝ የማትቀበልና የማትፈጽም ከሆነ ከያዝከው የእርሻ መሬት ትለቃለህ እያለ ያስፈራራዋል፡፡ የከፊሉንም ገበሬ መሬት በመንጠቅ ለውጪ ባለሀብት እየሰጠበት ይገኛል፡፡ ይሄን መከራና ስቃይ አልቀበልም ያለ ገበሬ ሚስትና ልጆቹን በገጠር ያለአንዳች ረዳት በመተው ወደ ከተማ በስደት እየፈለሰ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሚስትና ልጆቹ ለችግርና ለረሃብ ተዳርገዋል፡፡ እሱም የከተማው ኑሮ ከምንግዜውም በላይ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥ የበዛበት ወቅት በመሆኑ ከእነሱ ያልተሸለ ኑሮ እየኖረ ነው፡፡
በከተማ የሚገኘው አብዛናው የመንግስት ሠራተኛ የBPR (Business processing and re-engineering) ፖሊሲ ተጠቂ ነው፡፡ በመሠረቱ የBPR አላማ ለፓርቲ አባል መመልመያና ለኢህአዲግ ለሚያጎበድዱ መሾሚያ ሲሆን የኢህአድግን የተሳሳተ ፖሊሲ ለሚቃወሙ ደግሞ የደረጃ እድገት መከልከያና ከሥራ ማፈናቀያ ዘዴ ነው፡፡ በመሆኑም የመንግስት ሠራተኛው በሰበብ አስባቡ እየተፈረጀ ያለ ምንም ምክንያት ከሥራ ገበታው እየተፈናቀለ ይገኛል፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በዚህ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ላይ ከሥራ ገበታው የተገለለ ሰው የኑሮ ውድነቱን እንዴት አድርጎ መቋቋም ይቻለዋል?
የሥራ አጡ ቁጥር እጅግ በጨመረበት በአሁኑ ወቅት የመንግስት መረጃ ወጣቱ ሥራ ይመርጣል እየተባለ በአዋጅ ይነገርለታል፡፡ የትኛው የሥራ መስክ ተከፍቶ ነው የሚመረጠው? ትንሽ አለ የሚባለውም የኮብል ድንጋይ ስራ ሲሆን ይህንንም የገዢው ፓርቲ ለፖለቲካ ድጋፍ ብሎ ያደራጃቸው ወጣቶች ናቸው እየተጠቀሙበት ያለው፡፡ በአንዳንድ የውጪ ኢንቨስተሮችና የእርዳታ ድርጅቶች የሚከፈቱ የሥራ እድሎችም በመንግስት በኩል ክልከላ ስለሌለ በአብዛኛው ከውጪ በሚገቡ የሌላ ሀገር ዜጎች ተይዞ ይገኛል፡፡
የኢህአዲግ የገዢው ፓርቲ የንግድ ድርጅቶችና ደጋፊዎች በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ተሰማርተው ቢሮክራሲያዊ እንቅፋት እንዳይገጥማቸው፣ የቀረጥና ግብር ውጣ ውረድ እንዳያስቸግራቸው፣ የካፒታል እንዲሁም የመረጃ እጥረት እንዳይኖርባቸው ሁሉ ነገር ተመቻችቶላቸዋል፡፡ በአንፃሩ የወያኔ/ኢህአዲግ ደጋፊ ያልሆነ የንግዱ ህብረተሰብ በነፃነት ተንቀሳቅሶና ተወዳድሮ እንዳይሰራ ፍታዊ ባልሆነ ግብርና ቀረጥ ጫና፣ ቢሮክራሲያውዊ ውጣ ውረድ፣ የፋይናንስ እጥረትና በጉቦ ወዘተ… ሁለገብ እንቅፋት እንዲገጥመው በማድረግና ተወዳዳሪነቱን በማዳከም ከሥሮ ከገበያው እንዲወጣ ይደረጋል፡፡
የተምሮ ማስተማር የትምህርት ዘርፍም አደጋ ላይ ነው፡፡ የገዢው መንግስት የተሻሉ መምህራንን በሰበብ አስባቡ እያባረረ እውቀት ችሎታና ብቃት የሌላቸውን አፍቃሪ ኢህአዲጎችን በመተካት የትምህርቱን ጥራት አዳክሞት ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ በወደፊቱ የሀገሪቱ እድገት ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅእኖ በጣም አደገኛ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በቅርቡ ደግሞ ለኑሮ ውድነት ማስታገሻ አስተማሪዎች ጥቂት ደሞዝ ጭማሪ ጠየቁ በማለት መንግስት በአንዳንድ መምህራኖች ላይ ከሥራ ገበታቸው የማፈቀናል ተግባር እያካሄደ ነው፡፡ በተማሪውና በአስተማሪው መካከል መልካም ግንኙነትም እንዳይኖር መንግስት አስተማሪውን በተማሪው እያሰለለ ይገኛል፡፡ በዚህም የተነሳ አስተማሪው በነፃነት ማስተማር፣ ተማሪውም ትምህርቱን በሥነ ሥርዓት መከታተል የማይችልበት ደረጃ በመድረሱ ት/ቤት ለስም ብቻ ገብቶ የሚወጣበት ሆኗል፡፡
በኢትዮጵያ ሀገራችን በአሁኑ ጊዜ የኑሮ ውድነትን፣ የትምህርት ጥራት ውድቀትን፣ የሥራ እጥረትንና በአጠቃላይ የአስተዳደር በደልን ተከትሎ ሀገሪቱ እጅግ የከፋ ችግር ላይ ነች፡፡ በዚሁ ላይ ህብረተሰቡ በነፃነት እንዳይንቀሳቀስና ሃሳቡን እንዳይገልፅ በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ጠንካራ የደህንነት/ስለላ ስርአት በመዘርጋትና እንዲሁም በህብረተሰቡ መካከል በገንዘብ በመደለል አንድ ለአምስት ሰዎች የሚል ስውር ሰላዮች በማሰማራት ህብረተሰቡ ከቤቱ በሰላም እንዳይወጣና እንዳይገባ እያወኩት ነው፡፡ ለመብታቸውና ለነፃነታቸው ለመታገል ቀና የሚሉትን ደግሞ አሸባሪዎች፣ የግንቦት 7 አባላት፣ የአርበኞች ግንባር አባላትና ደጋፊዎች በማለት በየፍርድ ቤቱና በየእስር ቤቱ ያለምንም መረጃ እንዲሰቃዩና እንዲታጎሩ እየተደረገ ነው፡፡
አቶ መለስ ዜናዊና መሰሎቻቸው በሀገር ያልታየ አሀዝ በውሸት በመጥቀስ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እንዳደገችና ወደፊትም እንዲሁ በፍጥነት እያደገች እንደምትሄድ በየጊዜው ይደሰኩሩልናል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ለሳቸውና ለመሰሎቻቸው ካልሆነ በስተቀር ለሌላው ህብረተሰብ የችግርና የመከራ ሀገር ሆናለች፡፡ በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ ከወያኔ ሹማምንቶችና መሰሎቻቸው በስተቀር ሌላው ህብረተሰብ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በሀገሪቱ የመኖር ዋስትናው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ይገኛል፡፡