አምላኬ ሰው ሥራ

 

ከብሥራት ደረሰ – አዲስ አበባ

ከጦቢያ መጽሔት ቅጽ 10፣ ቁጥር 11/1995 ከገጽ 25 የተወሰደ

 

አምላኬሰውሥራ

 ለወገኑ አሳቢ አገሩን የሚወድ፤

እባክህ አምላኬ ኢትዮጵያ ሰው ትውለድ፡፡

ቁጣህን አብርደው አንጀትህ ይራራ፤

ማህጸኗን ባርከህ እባክህ ሰው ሥራ፡፡

አርግዞ ለመውለድ ዘጠኝ ወር ይረዝማል፤

የዕድገቱም ሂደት በእጅጉ ይርቃል፡፡

ታምርህ ይገለጽ ኢትዮጵያ ሰው ትውለድ፤

ሳይማር ያወቀ ሳይድህ የሚራመድ፤

ስቃይ መከራዋን ፈጥኖ የሚያስወግድ፡፡

መስሚያ ጆሮ ያለው የሕዝቧን እሮሮ፤

አሽንቀጥሮ እሚጥል ጠላቷን ወርውሮ፡፡

አንገቱ የማይዞር መለስ ብሎ እማያይ፤

ማህጸኗን ባርከው ለዳግመኛ እንዳታይ፡፡

የጭቃ እሾህ ደምሳሽ ጀግና ባለፈረስ፤

ሰው ፍጠር አምላኬ ለዛሬ የሚደርስ፡፡

የጠባውን ጡቷን ጨክኖ በመንከስ፤

ድንበሯን በማጠር ከኤርትራ መለስ፤

በጎሣ ከፋፍሎ ዜጎቿን የሚያምስ፤

ማየት አትፈልግም ኢትዮጵያ መሯታል፤

ይህን እሚያውቅላት ሰው ያስፈልጋታል፡፡

ዐይኗ ሊጠፋ ነው ዘወትር በማልቀስ፤

አምላኬ ሰው ፍጠር ዕንባዋን የሚያብስ፡፡

አምላክ ወይ ጥበብህን እባክህ ግለጠው፤

ማለዳ ሰው ሠርተህ ለቀትር አድርሰው፡፡

“ጀግና የወጣበት ዘመኑ እኮ ርቋል፤

አርጅቶ ገርጅፎ ማህጸኗም ደርቋል፡፡”

ተብሎ ሲወራ በጅጉ ታዝናለች፤

ባርከው ማህጸኗን ቆራጥ ሰው ናፍቃለች፡፡

ዘጠኝ ወር ሩቅ ነው እንደዘጠና ዓመት፤

ጭራሽ ፋይዳም የለው “ወፌ ቆመች” ማለት፡፡

አምላኬ ሰው ሥራ ዛሬ እሚታደጋት፡፡