ትርፍራፊ ወሬ፤ “ሲዋረዱ” እንዲህ ከሆንን ሲወርዱ ምን ልንሆን ነው?
በዛ ሰሞን ከተፈጠሩ የኢንተርኔት ቀልዳ ቀልዶች መካከል የብዙ ሰዎችን ልብ በሳቅ ፍርስ ያደረገችው ይህቺ ናት፤ ባለቤቷ ማን እንደሆን እንጃ… ማለቴን የተመለከተው ወዳጃችን “አክሊል” የቀልዱ ባለቤት ተቦርነ እንሆነ ነግሮኛል። ቀልድህ ይበረክ እንበለው እንጂ…
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ልጃቸው ስመሃል እና ባለቤታቸው ወይዘሮ አዜብ ሆነው በአውሮፕላን እየሄዱ ሳለ አዲሳባን ቁልቁል እየተመለከቱ እጅግ ሩሁሩህ እና ደግ የሆኑት አቶ መለስ ከኪሳቸው አዲስ አንድ ብር አወጡና “ይቺን አንድ ብር ወደ አዲሳባ ልወርውራትና አንድ ነዋሪ ላስደስት” አሉ። ይሄን ግዜ ወ/ሮ አዜብ፤ “ከፀደቁ አይቀር ይንጋለሉ…” ብለው ከተረቱ በኋላ፤ “አምሰት ብር ጣልና አምስት ሰዎችን አስደስት!” አለቻቸው። ልጃቸው ስምሃልም የልጅ ነገር፤ “ከይት ያመጣዋል!?” ብላ ሳትጨነቅ፤ “ዳዲ ስሞትልህ አስር ብር ጣልና አስር ሰዎችን አስደስት…!” አለቻቸው።
በዚህ ግዜ የቤተሰቡን ውይይት በአንክሮ ሲሰማ የነበረው አውሮፕላን አብራሪው “ጌታዬ ለምን ራስዎን ጥለው ሰማኒያ ሚሊዮን ህዝብ አያስደስቱም?” ብሏቸው እርፍ አለ።
ዛሬም ከእርሳቸው ራስ ላይ አልወረድኩም። (“ራሳቸው እንዴት ቢመችህ ነው…?” ብሎ ማሽሟጠጥ ከርሳቸውም ከኔም ጋር አያቀያይምም እና አትስጉ… የማሽሟጠጥ መብት እስከ “ፑንት” ተፈቅዷል።) (በሌላ ቅንፍ “ፑንት” ምንድነው? በልጅነታችን ብዙ ለማለት እንጠቀምበት ነበር። ከምን የመጣ እንደሆነ ግን አላውቅም…!)
አቶ መለስ ዜናዊ የአሜሪካ ስብሰባቸውን (አበሳቸውን ማለት ይቀላል) ጨርሰው ትላንት ማምሻውን አዲሳባ ገብተዋል። አሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዘመድዎ ጋር ዛሬ እና ትላንት ስልክ ቢደውሉ “ሆያ ሆዬ” ሲጨፍር እንደነበር ጎረምሳ፤ በሁለቱ ቀናት የተቃውሞ ሰልፍ ድምፃቸው ዝግት ብሎ ታገኟቸዋላችሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትራችን አበበ ገላው ያከናነባቸው ካባ በበርካቶች ዘንድ የተለየ ስሜት ፈጥሯል። በየፓልቶክ ሩሞች ውስጥ ከአመት በዓል የበለጠ ድግስ ሲደገስ ነበር። እንደ ምሳሌ “የኢትዮጵያውያን ወቅታዊ ጉዳዮች መወያያ መድረክ” (ECADF) ቅዳሜና እሁድን በዝማሬ እና በመንዙማ ሳይቀር አምላካቸውን አመስግነዋል። አባላቶቹ በዚህ አላበቁም በመለው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ያስተባበረ “ዘመቻ አበበ ገላው” በሚል ለኢሳት ቴሌቪዥን እገዛ ለማድረግ ገቢ ማሰባሰቢያ ሁሉ አዘጋጅተዋል። (ስለ ECADF ካነሳን አይቀር አንዲት የስድስት አመት ህፃን ልጅ በፓልቶክ ላይ የሰጠችው አስተያየት በጣም አስገርሞኛል።
በፓልቶክ ሩም አበበ ገላውን ኢንተርቪው እያደረጉት ነበር። በመሃል ይቺ ህፃን ልጅ ገባች። እንደሚከተለውም ተናገረች፤ “አበበ ገላው እግዚአብሄር ይባርክህ… መለስ ዜናዊ ደግሞ ለንቦጩን ጥሎ ሲያስቅ…” ብላ በህፃን አንደበቷ ፍልቅልቅ ስትል አስገረመችኝ! “የሚያድ ልጅ አይጥላህ የሚሞት ሽማግሌ አይርገምህ” አለች ሙያዬ!
ለማንኛውም አበበ ገላው ጠቅላይ ሚኒስትሩን አስታጥቆ ሸኝቷቸዋል። በዚህም በርካታ ዌብሳይቶች ደግሰዋል ፌስ ቡክም በአርበኞቹ የግጥም አዚም ተሞልቷል።
መረጃዬን ሚዛናዊ ለማድረግ ብዬ አይጋ ፎረምን እና ዋልታን ኢንፎርሜሽንን ለማየት ሙከራ አድርጌ ነበር። ትንሽ ጭር ያሉ ይመስላሉ። ሁለቱም ጥቁር አለበሱም አንጂ ሀዘን ላይ ናቸው። ባለፈው ግዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደነገጡ ግዜ አብረው የደነገጡ እስከ አሁንም ክውታቸው የለቀቃቸው አይመስሉም! አይጋም ዋልታም በስሱ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋሽንግተን ዲሲ ህዝቡ አቀባበል አደረገላቸው” የሚል ዜና ይዘው ወጥተዋል። ነገሩን ለተከታተለ ሰው፤ እነ አይጋ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ሽሙጥ ጀመሩ እንዴ ያሰኛል!
የሆነ ሆኖ አበበ ገላው የሰራው ጀብድ እስካሁንም ተወርቶ አላለቀም። በአለም አደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አዋርዷቸዋል። ትዝ ይሎት እንደሆነ አዲሳባ በነበረው የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ቀጥታ ይመልሱልኝ!” ያላቸውን ሰውዬ አንስተን እንዴት ቢደፍራቸው ነው ብለን ቁጭታችንን ተናግረን ነበር። አሁን የባሰው መጣ! ወሬውም ደመቀ ለበርካቶችም የደስታ ቀን ሆነ።
አንዱ ወዳጄ፤ “ሲዋረዱ እንዲህ ከሆንን ቢወርዱ ምን ልንሆን ነው!?” ብሎ ጠይቆኝ ነበር፤ እኔም አልኩት “ውይ ተው ክፉ አትናገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳንስ ከስልጣን ሲወርዱ እና የኪሏቸው መውረድ እንኳ ያስከፋኛል!” አልኩት! (እሰይ የኛ አሳቢ አይሉኝም!?)
ውይ ረስቼው አንዳንድ እጅግ በጣም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅር የተለከፉ “ልክፍታሞች” (ይቺ ነገር ስድብ መሰለች ይቅርታ…) ለማንኛውም አበበ በለውንም ሆነ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የምንሰጥ ግለሰቦችን አብጠልጥለውናል። “እንዴት እርሳቸውን የሚያክሉ ሰው አታከብሩም…?” ሲሉ ጠይቀውናል። እኔ በበኩሌ ሂሴን ውጣለሁ። “አንቱ” እያልኩ “ክቡር ሆይ” እያልኩ “አላከበርክም” ከተባልኩ እድሌ ነው እንግዲህ ለወደፊቱ ጥንቃቄ አደርጋለሁ።
ታድያ ከእነርሱ ምክር በኋላ አንድ ወዳጄን በፌስ ቡክ ሳወጋው ጠቅላይ ሚኒስትሩን አለቅጥ ዝርጥጥ ሲያደርጋቸው። “ተው እንጂ ወዳጄ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማክበር አለብን እኮ!” ብዬ ብገስፀው “መቼ ነው ቀብሩ?” ብሎኝ እርፍ አለ። “መቅበር አለብንኮ” እንዳላልኩት ያውቃል ሆነ ብሎ ነው። አያችሁ አይደል፤ በየት በኩል እናክብራቸው ታድያ…!? ወይ ደግሞ አንድ ቀን በስማቸው እንሰይም… ያመቱ የወሩ እያልን እናንግሳቸው ይሆን!?
በመጨረሻም
በአሁኑ ጉዞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተከትሎ አሜሪካ የሄደው የኢቲቪው ጋዜጠኛ አሸብር ነበር። ከዚህ በፊት አሹ እንዳስለመደን ሲመጡ አውሮፕላን ውስጥ ኢንተርቪው ሲያደርጋቸው እስከ አሁን አላሳየንም! ምነው…? ብሎ የሚጠይቅልኝ ማነው!?
ቪዲዮውን ላላያችሁት ወይም መድገም ለምትፈልጉ ወዳጆች፤
Filed under: Uncategorized
![]()
