ለኢትዮጵያ ሆቴሎች፣ የሸቀጣሸቀጥ መደብሮችና ለድርጅቶቹ ደንበኞች በሙሉ

[Click here to read in PDF]

በወያኔ/ህወሓት ላይ የሚካሄደዉን የኢኮኖሚ ማእቀብ ለማስተባበር የተቋቋመዉ ግብረ ሃይል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን (media) ያደረጉትን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ማእቀብ ጥሪ መሰረት በማድረግ ነዉ። የዚህ የኢኮኖሚ ማእቀብ ዓላማም የወያኔ አገዛዝን የገቢ ምንጭ ለማድረቅ ነው።

የወያኔ የንግድ ድርጅቶች ወደውጭ አገር የሚልኳቸው ሸቀጣሸቀጦች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙለት ነው። ስለዚህ ከኢትዮጵያ የሚመጡ እንጀራ፥ ቢራ፥ ወይን ጠጅና የመሳሰሉት ምርቶች ላይ የኢኮኖሚ ማእቀብ ተጥሏል። እነዚህ የገቢ ምንጮች ወያኔ በሕዝባችን ላይ የሚያደርሰዉን ግፍ እንደሚያጠናክሩ ሁላችንም ተረድተን ሕዝባችንን ለመታደግ ማእቀቡ ላይ እንድንተባበር በአክብሮት እንጠይቃለን።

ህወሓት/ወያኔ የመንግስት ስልጣን በጠመንጃ ሃይል ከጨበጠ ጀምሮ አንድነታችንን ሲሸረሽር፣ ሃገር ሲዘርፍና ሲያዘርፍ ኢትዮጵያውያን እንዳይጠይቁት በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ ሆዳሞቹን ደግሞ በፍርፋሪ እያታለለ ላለፉት 21 ዓመታት ቆይቷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ መብቱን በጠየቀ ቁጥር መልሱ ግድያ፣ ግርፋት፣ የረሃብ ቅጣትና እንዲሁም እንዲሰደድ ማድረግ ነው። ህወሓት/ወያኔ ዛሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎችን የእርሻ መሬቶቻቸዉን ለአረቦች፣ ለሕንዶች፣ ለቻይናና ዶላር ለሰጠዉ ሁሉ እየቸበቸበ የአገሪቱን ዜጎች የባርነት ቀንበር ስር እያስገባቸዉ ነዉ። ከወያኔዎችና ከቡችሎቻቸዉ በስተቀር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ ነዉ።

የዚህን የወያኔ አገር ዘረፋ በዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የሚተዳደሩ ሆቴሎች፥ ምግብ ቤቶችና የሸቀጣሰቀጥ መደብሮች አውቀውም ሆነ ባለማወቅ ተባባሪ በመሆን ሂደት ውስጥ ይገኛሉ። ለዚህም ዋናው ማስረጃ ግሎባል Global Financial Integrity የተባለዉ አለም አቀፍ ድርጅት ከኢትዮጵያ ዉስጥ ከ2000 እስከ 2009 (እአአ) ዓ.ም ድረስ ብቻ በተለያየ መንገድ ከአገር ዉስጥ የወጣዉ ገንዘብ 11.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ሪፖርት አድርጓል። በወያኔ ነጋዴዎች አማካኝነት ሸቀጣሸቀጦች ከአገር በወረቀት ብር ተሸምተዉ በዳያስፖራ ለኢትዮጵያዉያን የንግድ ድርጅቶች በማከፋፈል፥ የዳያስፖራ ኢትዮጵያዉያንም እነዚህን ሸቀጦች በመግዛት በአገር ዘረፋ ሂደት ዉስጥ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ መተባበራቸዉ ግልጽ ነዉ። ዜጎቻችን በዚህ ዘረፋ ምክንያት በሚፈጠረዉ የእቃ እጥረት የሲኦል ሕይወት ዉስጥ እየወደቁ፣ የወያኔ ወኪሎች ግን በዉጭ ባንኮቻቸዉ ሃብት እያካበቱና እየተጠናከሩ ነዉ።

ይህ የኢኮኖሚ ማእቀብ የትብብር ጥሪ ይፋ ከሆነበት ቀን ጀምሮ፣ ከኢትዮጵያ የሚመጡ የምግብና የመጠጥ ሸቀጦች፥ በተለይ እንጀራ፥ ቢራ፥ ወይን ጠጅና የመሳሰሉት ምርቶች እየተቀብላችሁ በየመደብራችሁና በየሆቴሎቻችሁ ለሽያጭ የምታቀርቡ ድርጅቶችና ባለቤቶቻቸዉ፣ እነዚህን ሸቀጦች ባለመግዛትና ባለማከፋፈል እንድትተባበሩ በትህትን እንጠይቃለን።

በዲያስፖራ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንም ይህ የማእቀብ ጥሪ የኢትዮጵያን ወገኖቻችን የመታደግ ጥሪ መሆኑን ተረድታችሁ፣ ጥሪው ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ባለመደብርና ባለሆቴል ባለቤት ወዳጆቻችሁ፥ ዘመዶቻችሁ ጥሪውን እንዲያከብሩ እንድትመክሩና፣ እናንተም እነዚህን ሸቀጦች መግዛት እንድታቆሙ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም በአክብሮት እንጠይቃለን።

በህወሓት ላይ ኢኮኖሚ ማዕቀብ ግብረሃይል| Email: [email protected] * Tel: 703 828 4821