ኤፍሬም እሸቴ: ብትስማማ ነው እንጅ የሚያስደምመው ባለመስማማትህ ምን ይደንቃል? ክፍል 2
ባለፍ የጽሑፉ ክፍል አንድ ንባብ ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ምእመናን “አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት: አንዲት ጥምቀት” ሲል በጻፈላቸው መልእክት በማንሳት አቶ ኤፍሬም ከግንዛቤ ማነስ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት እጥረት የተነሳ በደመነፍስ ያኮላሹትን የክርስትና አስተምህሮ የዓውዱ ታሪካዊ ስዋስዋዊና ስነ ጽሑፋዊ መልኩ ጠብቆ የመልእክቱን መንፈስ መጨበጣችንና ማግኘታችን የሚታወስ ነው::
ወደ ዋና ርእሰ ጉዳዬ ከማለፌ በፊት ግን በአንዳንዶች ዘንድ የተፈጠረውን የተሳሳተ ግምት ለማጥራት ያክል አንዳንድ ነጥቦች ለማለት እወዳለሁ በተለይ ኤፍሬም እሸቴ “አቶ” በማለቴ ‘የድቁና/ቅስና”ማዕረገ ክህነት በተመለከተ ይሆናል:: በመሰረቱ እኔ ኤፍሬም በዲቁናም ሆነ በቅስና ማዕረግ ስትጠራ ሰምቼ አላውቅም:: አባሪ ተደርጎ የተላከልኝና ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኘሁት “አደባባይ” የሚል ስያሜ ያለው ድረ ገጽም “ኤፍሬም እሸቴ” እንጅ ሌላ ተጨማሪም ሆነ ተደራቢ ቀሚስ አላየሁም አላነበኩምም:: በጻፍከው ጽሑፍም የተቀመጠው ስምህ ነው ስለዚህ “አቶ” ብዬ መጥራቴ የሀገሬን ባህልና ወግ መጠበቄ እንጂ በሌላ መልኩ መወሰድ የለበትም ስል በትህትና እጠይቃለሁ:: ላያገለጉልበት ብቻ ሳይሆን ከየት እንዳገኙት በግልጽ የማይታወቅ የቅስናም ሆነ የድቁና ማዕረግ ይዘው በቅስና: በድቁና በሌሎች የቤ/ያን መጠሪያ ቀሚሶች ስም የሚጠሩ እንደ’ነ ስንታየሁ አባተ: ዳንኤል ክብረት: ብርሃኑ ጎበና: ዶ/ር መስፍን ተገኝ: ሙሉጌታ ሃይለማርያም: ግርማ መታፈሪያ: ባያብል ሙላቱ: ሳምሶንና ሌሎች የማህበረ ቅዱሳን አባላት በቤ/ያን የክህነት ማዕርግ የሚጠሩ ዕጣን ሲሸተን ያፍነናል: አስሜ ትነሳብኛለች: የዕጣን አላርጅክ ነኝ: የአጥንት ካንሰር አለብኝ በማለት ላይቀድሱ ላያስቀድሱ የሚንቀሳቀሱ ዲቁናቸውናን ቅስናቸው በጋዜጣ ብቻ የምናነበው ግለሰቦች ግን እንደተጠበቀ ነው::
ኤፍሬም እሸቴ “በጠቅላላውም ካየነው የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ መታየት ያለበት “በቤተ ክህነቱ እና በቤተ ክህነቱ ብቻ” ነው ብዬ አምናለሁ።”
በመጀመሪያ ደረጃ “ማህበረ ቅዱሳን” ሲል ራሱን የሚጠራ ድርጅት አባቶችን በማጭበርበር ያስፈረመው ማህበሩ አለኝ በሚለው መተዳደሪያ ደንብ የማህበሩ ሙሉ ተጠሪነቱ ማህበሩ ለሚያቋቁመው የበላይ የስራ አስፈጻሚ አካል ይላል እንጅ የት ስፍራ ነው “ማህበረ ቅዱሳን” የቤ/ያን ለመሆኑ የሚያሳይ? የቤተ-ክርስቲያን ሲሆን አይደለም ወይ ጉዳዩ ቤተ-ክርስቲያን የሚታየው? ከመቼ ወዲህ ነው “ማህበረ ቅዱሳን” ተጠሪነቱ ለቤተ-ክርስቲያን የሆነው? የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን የአስራር መዋቅሮችን ጠብቆ የተገነባና የሚንቀሳቀስ ድርጅት መቼ ነው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ላቀረበችለት ጥያቄ ተገቤ የሆነ መልስ ሰጥቶ የሚያውቀውና ጉዳዩ ቤ/ያን የሚታየው? እንግዲህ እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች ለማድበስበስ አቶ ኤፍሬም እንዲህ ነበር
ያለው “በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት ማለት የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉዳይ ለራሷ መተው ነው።” በሌላ አገላለጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ነገር ላያደርጉ በፓርላማ በግላጭ አልተናገሩማና
መሞታችን አይቀር ገድለው ሳይቀብሩን በሚል ስሌት ጠቅላይ ሚኒስተሩ “ማህበረ ቅዱሳንና” የግንዛቤ እጥረት ሰለባ የሆኑ የማህበሩ አባላት ላይ ያነጣጠረ ያደረጉት ንግግር በቤተ-ክርስቲያን ላይ እንደዘመቱ በማስመሰል ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃይማኖታችን ጣልቃ መግባታቸው ነውና ምእመናን ሆይ! ምን እስከምንሆን ድረስ እየጠበቅን ነው? የሚል የተለመደውን የማህበሩ የዓመጽና የግርግር ማንሰራሪያ ዘዴ ደወል መደወሉ ነው::
በመሰረቱ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው መንግሥት ቤተ-ክርስቲያን ጉዳይ ቤተ-ክርስቲያን በመንግሥት አሰራር ላይ በሌላ አነጋገር አንዳቸው በአንዳቸው ጣልቃ አይገቡም ማለት ምን ማለት ነው? ውድ አንባቢ: በዋናነት ስለ እነዚህ ሁለት አካላት ማወቅ የሚገባን ነጥብ ቢኖርም ሁለቱም ተጠባብቀው የሚሔዱ የየራሳቸው ሥልጣንና ሃላፊነት ያላቸው አካላት እንጅ ቤተ-ክርስቲያን በመንግሥት መንግሥት በቤተ-ክርስቲያን ላይ አንዱ በሌላው አንዳችም ልዩ ሥልጣን የላቸውም:: ይህ ማለት ሁለቱም በየፊናቸው እንዳሻቸው ይሆናሉ ማለትም አይደለም:: ሁለቱም ባላቸው የማይበላለጥና በማይተናነስ ሥልጣን ድርሻቸውን ይወጣሉ ማለት እንጅ መንግሥትም ሆነ ባለሥልጣናቱ ሥልጣቸውን ተገን አድርገው
በሀገርና በሕዝብ ጥፋትና ውድመትን ሲያደርሱ ቤተ ክርስቲያን እጇንና እግርዋን አጣጥፋ ትቀመጣለች ማለት አይደለም:: ቤተ ክርስቲያን ያለሽንገላና አድልዎ ጽድቅንና እውነውትን የምታውጅ ቤት እንደ መሆንዋ መጠን በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ አመፀኞችን ትገስፃለች ክፋትን ትቃወማለች::
በተመሳሳይ መልኩ “መንፈሳዊያን” መሪዎች መንፈሳዊ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ከአንድ መንፈሳዊ ተቋምም ሆነ ግለሰብ የማይጠበቅ ሀገርንና ዜጋን የሚጎዳ ማንኛውም ዓይነት ተግባርና ድርጊት ሲፈጽሙ፣ ቤተ ክህነትም የሰላምና የፍትህ ቤት መሆኑ ቀርቶ የእሳት መከፋፈያ ጣቢያ ሆኖ ሲገኝ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ግለሰቡ እንደ አንድ ዜጋ በሕግ ፊት አቅርቦ የእጁን የማይሰጥበት ምንም ምክንያት የለም:: ይህም መንግሥት የሥልጣን ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር የተሰጠው (ያገኘው) ሥልጣን ነው:: (ለበለጠ “ምሥጢረኛዋ ሳንቲም” በሚል በጸሐፊው ከዚህ ቀደም በመንግስትና በቤተ-ክርስቲያን መካከል ሊኖር ስለሚገባ ግኑኝነት በማስመልከት የተዘጋጀውን ጥልቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ በጽሐፉ ግርጌ አባሪ ተደርጎ የቀረበውን ሊንክ ተጭነው ያንብቡ)[1]
ኤፍሬም እሸቴ “ከዚህ አንጻር ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ የወጣ እምነት ይዘው ቤተ ክርስቲያኒቱን እና ትምህርቷን በመለወጥ የራሳቸው ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች፣ ቡድኖች እና ድርጅቶች መኖራቸው እየታወቀ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ እና በዕውቀቱ ለቤተ ክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን ለአገሩም በቅንነት የሚያገለግለውን አንድ ትውልድ ጨፍልቆ በአክራሪነት ስም መፈረጅ በቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ላይ ትልቅ የሚዛን መናጋት ያስከትላል ብዬ በድፍረት መናገር እችላለኹ።”
ምላሳችን እስኪደማ ተናግረን ሰሚ ብናጣም ከአስር ወራት አከባቢ በፊት በአንድ የማህበሩ ነባርና የስራ አመራር አባል ነበር ዳንኤል ክብረት የተባለ አውሬ (እኔ አይደለሁም ራሱ ያለውን ነው) የማህበሩ ዋና ጸሐፊ ከአንድ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስለ ዳንኤል ክብረት የተባለው ግለሰብ ከማህበሩ ጋር ያለን ወቅታዊ ግኑኝነት ተጠይቀው “ዳንኤል ከቦታው የተነሳ ከድክመት የተነሳ ነው” ሲሉ ቃል በቃል የሰጡትን ሁለት አንድምታ ያለው ቃለ ምልልሳቸው የዳንኤል ክብረት ማንነት በአደባባይ አዝረክርከው በመናገራቸው ዳኔኤልም በበኩሉ
ከተዋረድኩ አይቀር ማህበሩን ጭምር በሚል መንፈስ “ምንም የማያውቀውን የተኛውን በሬ ነካክተው ነካክተው አደረጉት አውሬ” ሲል በጻፈው የማህበሩ ውስጣዊ አሰራርና ማንነት ካነሳቸው ነጥቦች መካከል “ማህበረ ቅዱሳን ተሃድሶ ተሃድሶ የሚለው ችግር ሲገጥመው ከገባበበት አዘቅት ለመውጣት የሚፈበርከው ማደናገሪያ ስልቱ ነው” በማለት ጽፎ እንደነበር ሁላችን የምናስታውሰው ነው:: ታድያ “ከዚህ አንጻር ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ የወጣ እምነት ይዘው ቤተ ክርስቲያኒቱን እና ትምህርቷን በመለወጥ የራሳቸው ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች፣ ቡድኖች እና ድርጅቶች መኖራቸው እየታወቀ” የሚለውን የአቶ ኤፍሬም ማደናገር ምን ይሉት ቅጥፈት ነው?
ደግሞስ “በገንዘቡ፣ በጉልበቱ እና በዕውቀቱ ለቤተ ክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን ለአገሩም በቅንነት የሚያገለግለውን” የሚባልልኝ ማንን ነው? ለመሆኑ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን “ከማህበረ ቅዱሳን”
አባላት ትምህርት ልጆችዋን ከማጣት: ከመለያየትና ከጸብ ያተረፈችው በጎ ነገር ምንድነው? ለዚህ የአቶ ኤፍሬም የዋዛ ንግግር “የማህበረ ቅዱሳን ዲግሪና የካንጋሮ እጅ አንድ ነው!”[2]
የሚል ከጽሐፉ ግርጌ አባሪ ተደርጎ የቀረበውን ሊንክ ተጭነው ያንብቡ::
ሌላው “ማህበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት ስም መፈረጅ በቤተክርስቲያኒቱህልውና ላይ ትልቅ የሚዛን መናጋት ያስከትላል ብዬ በድፍረት መናገር እችላለኹ።” ባቄላ ጠፋ ቢሉ ፈስ ቀለለ ብለን ጥርግ ይበል! እንዳንል የአቶ ኤፍሬም መልእክት ሌላ ነው:: ልብ ይበሉ! ይህ አነጋገር አንድ መሰረታዊ የክርስትና ትምህርት እያፋለሰ ነው ይኸውም: የቤተ-ክርስቲያን ህልውና በመንፈስ ቅዱስ እጅ መሆኑ ቀርቶ ለህልውናዋም ለመጥፋትዋም “በማህበረ ቅዱስን” እጅ ነው ተብሎ መታመኑ:: በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃላቸው ተግባራዊ ቢያደግሩ “ማህበረ ቅዱሳንን” ከምንጩ ለማድረቅ ቢንቀሳቀሱ ሊገጥማቸው ስለ የሚችለው ፖለቲካዊ ኪሳራም በእርግጠኝነት እየተነበየም ነው:: እንኳን ደህና መጣህ! ታሪክ ሳይሆን ራሱ የሚደግመው ፈጥረት የእግዚአብሔር ህልውናን ያያል:: የእግዚአብሔር ሰው “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፥ አንተንም፥ አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ አለው እሳትም
ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳውን ሰዎቹን በላች” እንዲል (መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 1: 10) እንዲል
ኤፍሬም እሸቴ: አንተንም መላ የማህበሩ አባላት ከሰማይ እሳት ወርዳ እንድትበላ ሳይሆን መንግስት በቁርጠኝነት
“ማህበረ ቅዱሳን” ከስሩ ነቅሎ ለመጣል ቢነሳና ቢጥለውም “ከማህበረ ቅዱሳን” ጋርም በተያያዘ መንግስት ይገጥመዋል ስትል የተነበከውን የትርምስ ትንቢታዊ ቃልህ እንዳለ ሆኖ
እኔ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ባሪያ በመንግስት ህልውና ላይ አንዳች ሊፈጥር የሚችል የጎላ ክፍተት ሊኖር እንደማይች ስገልጽ ይህችን ጦማር አግኝቶ
የማንበብ ዕድሉን የገጠማት ነፍስ ሁሉ ይህቺን ቀንና ቃሌን በማስታወሻው ያስፍር:: በድፍረት የተናገርከው
ያክል የማምነውን ብቻ ሳይሆን በእኔ የሚታመነውን እግዚአብሔር ይህን ባያደርግ ማላሴ ትታጠፍ! ባሳለፍኩትና በከፈልኩት ዋጋም ወደኋላ
ተመለሼ ሐዘን በላዬ ባልጠራም ቀሪውን ዘመኔን ጨለማ ያድግረው!! ደመና እያየህ ጉዞ እስከ መቼ!
ኤፍሬም እሸቴ “በርግጥ ገዳማትንና አብነት ት/ቤቶችን ከጥፋት መታደግ አክራሪነት ነውን? ወጣቱ ትውልድ ሃይማኖቱን አውቆ በሥነ ምግባር ታንጾ አገሩንና ቤተ ክርስቲያኑን በቅንነት እንዲያገለግል ማድረግ አክራሪነት ነውን? በገንዘቡ፣ በዕውቀቱና በጉልበቱ በነጻ የትውልድ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚሞክር ትውልድ መፍጠር አክራሪነት ነውን? በጭራሽ!!! ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ማኅበሩ ባሉት ሐሳብ አልስማማም።”
ማህበሩ በተለያዩ ያማሩ ስሞች ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆኖ የሚዘውራቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው ድረ ገጾች መካከል አንዱ “አንድ አድርገን” በመባል የሚታወቀውን ተጠቃሽ
ነው:: ይህ መካነ ድር እነዚህ በአቶ ኤፍሬም “እክራሪነት ነውን?” እየተባሉ የተነሱ ጥያቄዎችን በተመሳሳይ መንገድ በአንድ ስሜት ያየለበት የዋህ ጸሐፊ የተነሱ ጥያቄዎች ያዘለ ጽሑፍ አስነብቦ ነበር:: መጽሐፍ ቅዱስ በአንደኛው ክፍለ ዘመን ከዛም በፊት ስለ ነበሩ ፈሪሳውያን በመባል ስለሚታወቁ ሃይማኖተኞችና እክራሪዎች/ጽንፈኝች የሚለውን እንመልከት::
ፈሪሳውያን፥
ü የሙሴን ሕግ ጠንቅቀው የሚያውቁ:
ü ሰማይ የተዘገባቸው:
ü መንፈሳዊ መገለጥ የሌላቸው:
ü ጽድቅን በራሳቸው ሚዛን የሚለኩ:
ü ህይወት በሚሰጠው በሀዲስ ኪዳን ትምህርት “ኔፓ”:
ü ወግ አጥባቂዎች:
ü ሰው ለመግደል ጾም ጸሎት የሚይዙ ነፍሰ ገዳዮች:
ü አፈ ወርቆች ልበ ደንዳኖች:
ü ኃይማኖተኞች: ዳሩ ግን ፍቅር ርህራሄ የሌላቸው አውሬዎች:
ü ለማወቅም ሆነ ለመማር ፍቃድም ሆነ ፍላጎት የሌላቸው ትምክህተኞች:
ü የመልካም ነገር ጸበኞች ነበሩ::
እንግዲህ ይህን ማንነታቸው በሚገባ ያየና የተገነዘበ ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር ጌታ ደግሞ ምንም በነሱ ቤት ለእግዚአብሔር የቆሙ ቢመስላቸው: ሰው ሲያያቸውም የሚያስቀኑ ቢመስሉም ኢየሱስ ግን እውነተኛ ማንነታቸን ገልጾ ድርጊታቸው የሚያስከትልባቸውን ቅጣት አክሎ በማያሻማ ቋንቋ እንዲህ ነበር ያላቸው:- (በማቴዎስ 23፡ 1 – 36)
- መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ:
- በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ:
- አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት:
- ፍርድንና ምሕረትን፥ ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ:
- በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭስለምታጠሩ:
- በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጥ ግን የሙታን አጥንት ርኲሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ:
- የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ ፥ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና ወዮላችሁ! ሲል ካማረና ከተቀባ መቃብር [3] ጋር ዛሬ ክርስትናን ከጨለምተኝነት አስተስሰብ መለየት ያቃታቸው አቶ ኤፍሬምና ሌሎች የማህበሩ ከበሮ መቺዎች “ሰው ሀይማኖቱን ሲጠብቅ እንዴት አክራሪ ይባላል?” በማለት ቢጠይቁ ምን ይደንቃል? “ማህበረ ቅዱሳን” እንደሆነ ማሰብ ያቆመ ዜጋ የተከማቸበት መካን ለመሆኑ ማን ቢስተውስ ነውና ስለ መስማማትና አለ መስማማት የሚነገረው? አቶ ኤፍሬም: “ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ማኅበሩ ባሉት ሐሳብ አልስማማም።” የሚለውን አባባልህ ቀድሞውኑ መስማማት ያቃተህ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻም ሳይሆን ለዚህ ሁሉ ስህተት ራስህንም ጭምር እንዳታይ ያደረገህ ከመጽሐፍ ቅዱስን ጋር ያለህን ትውውቅ እጅግ አናሳ በመሆኑና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንዛቤም ስለሚያንስህ ነው:: እዚህ ላይ “ማህበረ ቅዱሳንና” አባላቱ ሲወሳ እውቀት ላይ ያልተመሰረተ ስሜት የወለዳቸው ጽንፈኞች/ነፍሰ ገዳዮች መሆናቸውን ልብ ይለዋል::
ኤፍሬም እሸቴ “አንድ አገር” ሲባልም ሥጋት የሚገባው ዜጋ ሊኖር አይገባም። … ኢትዮጵያውያንም እንደ አሜሪካኖቹ “ከፈጣሪ በታች ያለች አንዲት አገር/ one nation under God” አለችን ብንል የሚያሳፍር አይሆንም።
መልሱ ግልጽና አጭር ነው “አንድ አገር አንድ ሃይማኖት” ለሀገርም ለወገንም ጠንቅ ነው እንዲህ ያለ ዘመቻም በፖለቲካ አከባቢ የሚያስከትለው ጠንቅ እንደተጠበቀ
ሆኖ ክርስትናን የጥላሸት የሚቀባ: በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ስምና በምእመናን ትክሻላ ላይ ተንጠላጥሎ ሀገርን በማተረማመስና ሕዝብን በማወክ ምኞቱ የማስፈጸም ድብቅ ዓላማ ያለው ሃይል: የክርስትና ስም የሚያጠፋ የሀሳዌ መሲህ አጀንዳ ነው ተባለ እንጅ “አንድ ሀገር!” በጥሬው አትበሉ ያለ ማን ነው? አንድ አገር ማለትስ እንዴት ነው አሳፋሪ የሚሆነው? ማነውስ በዚህ ቃል የሚያፍር? እሳትና ጭድ ማጎራበት ዋ! [4] ተባለ እንጅ እሳት በእሳትነቱ ጭድም በጭድነቱ ላይ የተነሳ ማን ነው? ውድ አንባቢ: ከዚህ በላይ ግንዛቤ ማነስ ምን አለ? የሚያሳዝነው የአቶ ኤፍሬም ትንታኔ አንብቦ ደስታውን በመግለጽ ተባርከናልና እግዚአብሔር ይባርክህ የሚል ምእመን ነው::
ኤፍሬም እሸቴ “ማኅበረ ቅዱሳን “እግዚአብሔር ያከበራቸው የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት በአጠቃላይ የቅዱሳን ገድል፣ ትሩፋትና አማላጅነት የሚዘከበርበት” ማኅበር ሲሆን አገልግሎት መስጠት ከጀመረ እነሆ 20 ዓመት ሆነው። ማኅበሩም ያለውን ዓላማ፣ ግብና ርዕይ በመጽሔቶቹ፣ በጋዜጦቹ፣ በዐውደ ርእዮቹ፣ በኦዲዮ እና ቪዲዮ ውጤቶቹ ደጋግሞ ጽፏል፣ ተናግሯል፣ አስተምሯል። ከዚህ አንጻር ማኅበሩ አገርንም ሆነ ፖለቲካን፣ ሌሎች እምነቶችንም ሆነ ተቻችሎ መኖርን በተመለከተ ከማንም በላይ በሰፊው፣ በበሰለ እና ጤናማ በሆነ መንገድ ሐሳቡን አስተጋብቷል።”
አሁን አሁን እየቀለድ ሁላ ይመስለኛል ያለኸው:: የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት ስትል የዘረዘርካቸው ታሪካቸው እኮ የሌብነት የሽፍትነት ስራ በመስራታቸው ሳይሆን
የመስቃሉን ቃል ኑሮውበት ያለፉ ለመሆኑ ጭራሽ ዘንግተኸዋል:: እስቲ አሁን “ማህበረ ቅዱሳን” የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት ዝክር የሚዘክረው ቅዱሳንን በማሳደድ
በመግደልና በማሳጥት ነው? “ማህበረ ቅዱሳን” መጽሐፍ ቅዱስ የካቶሊክ: የጴንጤ ነው አያለ ከማውገዝና ከማንቋሸሽ አልፎ በ20 ዓመታት ውስጥ የቤተ-ክርስቲያን ጉልላትና መሰረት: የነገር ሁሉ ምንጭና የበላይ ባለስልጣን የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ አሰራጭቶ ያውቃል? የማህበሩ ልሳኖች እንደሆኑ ጸብን ከመዝራትና የቤተ-ክርስቲያን አገልጋዮች ስም ከማጥፋት አልፈው “ማህበረ ቅዱሳን” በዛሬው ዕለት በዚህ ስፍራ ላይ ይህን ያክል መጽሐፍ ቅዱስ ለተቃሚዎች አሰራጨ የሚል ዜና አስነብበው ያውቃሉ? እንደው ይህን የአቶ ኤፍሬም ጥብቅና ሳነብ ትዝ ያለኝ ታሪክ ልንገራችሁና ሐሳቤን ልቋጭ::
በአንድ ወቅት ነው ይህ ማህበር (“ማህበረ ቅዱሳን”) አንድ ለትርፍ ያልቆመ ዓለም ዓቀፍ ክርስቲያናዊ ድርጅት በሩ ድረስ በማንኳኳት ማህበሩ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ወሳኝ አካልና የጀርባ እጥንት: እንዲሁም ቤተ-ክርስቲያኑቱ ይህን ተልዕኮ ያከናውን ዘንድ አደራ እንደጣለበት በማስመሰል በእንግሊዝኛ ሰነድ አዘጋጅቶ መጽሐፍ ቅዱስ አሰራጫለሁ በማለት በመቶ ሺህ የሚቆጠር የተለያዩ የአማርኛ ትርጉሞችና መጠን ያላቸው ካገኘ በሃላ አጭበርብሮ በእርዳታ በነጻ ያሰራጨው ዘንድ ያገኘውን መጽሐፍ ቅዱስ በመላ አገሪትዋ ቱባ
ቱባ ደላላዎችን በማሰማራት ተመልሶ ለሌሎች የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያንና እንዲሁም ሱቅ ቤቶች በመቸብቸብ ከፍተኛ ገንዘብ ያግበሰበሰት አስታውሶኛል:: እውነት መንገድም
ህይወትም የሆነው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሰላምና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን!
ዛሬም እጄ በጠላቶቼ ደንደስ ላይ ነች!
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
28th April 2012
United States of America
[1] “ምሥጢረኛዋ ሳንቲም” http://www.ethiomedia.com/broad/secret_coin.pdf
[2] “የማህበረ ቅዱሳን ዲግሪና የካንጋሮ እጅ አንድ ነው! http://awdemihret.blogspot.com/2012/04/blog-post_6660.html
[3] መቃብር ምንም ውጩ ቢቀባ ቢያምርም በውስጡ የያዘው ግማቱ አገር የሚያስተው ብስባሽ አጥንት ነው!
[4] ጸሐፊው እሳትና ጭድ በምሳሌነት ሲጠቀሙ ሁለቱ በሚፈጥሩት ውህደት ላይ የሚያስከትለው አደጋ ላይ ለማሳየት እንጅ ሀገርና ሃይማኖት አንዱ እሳት ሌላኛው ጭድ የሚል አንድምታ የለውም::