የታሪክ ተጠያቂዎች ሁነናል (ክፍል 2)
ከአክሎግ ቢራራ (ዶር)
ህወሃት፤ ከጽንስ፡ ሃሳብ፡ ወደ፡ ተግባር፡
የህወሃት፡ ፍልስፍና፡ ከአጀማመሩ፡ በዘር፡ጥልና፡ ልዩነቶች፡ የተበከለ፡ መሆኑን ፡ መካድ፡ አይችልም። በቅርቡ፡ አቶ፡ ገብረመድህን፡ አራያ፤ እንደገለጹት፡ እ.አ.አ. 1974 መለስ ዜናዊ፡ “የአማራ፡ ሕዝብ፡ ዋና፡ ጠላታችን፡ ነው፤ ይህን፡ ጠላት፡ ማሽነፍ፡ ቀላል፡ ነው” ሲሉ፡ ያሰቡትን/ያቀዱትን፡ ያውቁ፡ ነበር፡ ለማለት፡ የሚያስችል፡ ብዙ፡ ማስረጃ፡ አለ። የህወሃት፡ ስም፡ ራሱ፡ እስከ አሁን፡ ያልተለወጠ፡ በትግራይነቱ የሚያምን፤ ለትግራይነቱ የቆመ፤ ለዚህ፡ የዘር ስራት፡ሆነ ብሎ ኢትዮጵያዊ፡ የሆኑ፡ ተቋዋሞችን፡ እየለወጠ፡ ወይንም፡ በሙሉ፡ እያጠፋ፡ በምትካቸው፡ በክልልና፡ በጠባብ፡ ዘረኝነት፡ የተቀረጹ፡ በስልት ያደራጀ፤ የትግራይን፡ ህብረተሰብ፡ ከሌላው፡ ለመለየት፡ “ትግራይ የራሳቺን፡ ኢትዮጵያ፡ የሁላቺን”፡ ብሎ፡ የተነሳ፤ አገር ከፈረሰ፡ “ታላቋን፡ ትግራይ” አገነባለሁ፡ ብሎ፡ ያሰበ፤ አሁንም፡ የሚከጂል፡ መሆኑን የሚያመለክቱ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ይህን፡ ስል፡ ግልጽ፡ ለማድረግ፡ የምፈልገው፡ በትግራይ፡ ሕዝብ፡ ስም፡ ለጠባብ፡ ቡድኑ፡ አገልጋይ፡ ሆነ፡ እንጂ፡ አብዛኛውን፡ የትግራይ፡ ህብረተሰብ፡ ከድህነትና፡ ከስደት፡ ነጻ፡ አወጣው፡ ማለት፡ አይደለም፡፡ ስለሆነም፡ አብዛኛው፡ የትግራይ፡ ሀብረተሰብ፡ ከሌላው፡ ሰፊ፡ የኢትዮጵያ፡ ህዝብ፡ ጋር፡ የሚጋራው፡ ያደላል። ለፊትህ፡ አብዛኛው፡ የትግራይ፡ ህብረተሰብ፡ አጋር፡ እንጂ፡ ጠላት፡ አይደለም።
ይህ፡ የህወሃት፡ ጠባብ፡ ቡድን፡ በኢትዮጵያና፡ በኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ላይ፡ ያደረሰውንና፡ የሚያደርሰውን፡ በደል፡ የትግራይ፡ ህብረተሰብ፡ ያውቃል። ብልሃቱን፡ ያላወቅነው፡ ግን፡ ይህ፡ ቡድን፡ እኛን፡ ያጠቃን፤ የሚያጠቃን፡ ሃይሉ፡ የማይበገር፡ ሆኖ፡ አይደለም። የእኛ፡ ድክመት፤ የእኛ፡ መከፋፈል፤ በኢሃደግ፡ የዘር፡ ፓርቲወች፡ ውስጥ፡ ያሉ፡ የአማራ፤ የኦሮሞ፤ የደቡብና፡ ሌሎች፡ ታዛዥና፡ አጎብዳጂ፡ የሆኑ፡ መሪወችና፡ የጥቅም፡ ደጋፊወች፡ ናቸው። ነው። አጎብዳጆች፡ ከፈረሱ፡ ወዪን፡ ወደ፡ ሕዝብ፡ ጎራ፡ ከገቡ፤ ይህ፡ ቡድን፡ እንደ፡ እምቧይ፡ ካብ፡ሊፈርስ፡ ይችላል።
ታሪክ፡ የመዘገበውን፡ እንይ። ኢሳይያስ አፈወርቂ፡ እና፡ ቡድኑ፡ ከኢትዮጵያ፡ ለመለየት፡ ያዘጋጁትን፡ እቅድ ከስራ፡ ያዋለው፡ ይህ፡ የመለስ፡ ዜናዊ፡ ጠባብ፡ ብሄርተኛ፡ ቡድን ነው። የዚህ፡ ቡድን፡ አድማ፡ ስራ፡ ላይ፡ መዋል፡ ኢትዮጵያን፡ ወደብ፡ አልባ፡ አድርጓታል፡፡ ደህንንቷንና፡ የረጂም፡ ጊዜ፡ ጥቅሟን፡ አደጋ፡ ላይ፡ ጥሏል። ኢትዮጵያ፡ ለመጀመሪያ፡ ጊዜ፡ በወደብ፡ አገልግሎት፡ ጥገኛ፡ በመሆኗ፡ የምትልከውም፡ ሆነ፡ የምትሸምተው፡ እቃ፡ ውድ፡ የሆነው፡ በዚህ፡ ችግር፡ ጭምር፡ ነው። ይህ፤ የወደብ፡ አልባ፡ ችግር፡ ለኢትዮጵያና፡ ለመላው፡ ህዝቧ፡ ከቆመ፡ መንግስት፡ የመጣ፡ አይደለም። ኢትዮጵያን፡ ወደብ፡ አልባ፡ ማድረግ፡ ጠባቡ፡ ብሄርተኛ፡ ቡድን፡ ለማን፡ አገልጋይ፡ እንደነበር፡ ያሳያል። በአሁኑ፡ ጊዜ፡ ያለውን፡ ሁኔታ፡ ስናይ፡ ደግሞ፤ የሳውዲ፡ አረቢያና፡ የገልፍ፡ ሃገሮች፡ ያልሙት/ያስቡት፡ የነበረውን፤ የኢትዮጵያን፡ የተፈጥሮ፡ ሃብት፡ የመቆጣጠር፡ አላማ፡ ያለምንም፡ ችግር፡ እያገኙ፡ ነው። ሸክ፡ አላሙዲ፡ በኢትዮጵያ፡ የዘረጉት፡ ታይቶ፡ የማያውቅ፡ የተፈጥሮ፡ ሃብትና፡ ቁልፍ፡ የሆኑ፡ የኢኮኖሚ፡ ክፍሎች፡ ቁጥጥር፡ ከዚህ፡ ጋር፡ የተያያዘ፡ ስልት፡ ውጤት፡ ነው። የስልምና፡ ተከታይና፡ አስፋፊ፡ የሆኑ፡ አገሮችና፡ ተቋሞችም፡ ስፋትና፡ ጥልቀት፡ ያለው፡ ስርጭት፡ ሊጎናጸፉ፡ የቻሉት፡ በዚሁ፡ በተቆላለፈ፡ አሰራር፡ ነው፡ ለማለት፡ የሚያስችሉ፡ ማስረጃወች፡ አሉ፡፡ ለዚህ፡ ሁሉ፡ የበላይነት፡ ዋና፡ ዳራጊው፡ የህወሃት፡ መንግስት፡ ነው።
በጠባብ፡ የዘር፡ ቡድን፡ ተቆጣጣሪነት፡ የተመሰረተ፡ ስራት፡ ሕዝብን፡ ከሕዝብ፤ ሃይማኖትን፡ ከሃይማኖት፡ መለያየት፡ መሳሪያው፡ ነው። ብዙ፡ ምሳሌወች፡ ለመስጠት፡ ይቻላል። ኩታገጠሙ፡ የትግራይ፤ የጎንደርና፤ የወሎ፡ ሕዝብ፤ በታሪኩ፡ የተቀራረበና፡ በሰላም፡ ተቻችሎ፡ የሚኖር፡ ነበር። ይህን፡ ጉርብትና፤ ይህን፡ ተሳሰቦና፡ ተከባብሮ፡መኖር፡ ህወሃት፡ ዋጋ፡ አልሰጠውም። የወልቃይት፡ ጠገዴን፡ አካባቢ፡ ቆርሶ፡ ወደ፡ ትግራይ፡ ያቀላቀለ፡ ህወሃት፡ በሰላም፡ ተቻችሎ፡ የሚኖረውን፡ ወንድማማች፡ ሕዝብ፡ ለማጣላት፡ እንጂ፡ ለሁሉም፡ ሰላም፤ ብልጽግና፤ እድገት፡ ፈልጎ፡ አይደለም። የኢትዮጵያን፡ ለም፡ መሬት፤ ደን፤ ወንዝና፡ ሌሎች፡ መተኪያ፡ የሌላቸው፡ የተፈጥሮ፡ ሃብቶች፡ በምስጢር፡ ለሱዳን፡ መንግስት፡ ያስረከበ፡ ሰላምን፡ በመፈለግ፡ ሳይሆን፡ ውለታ፡ ለመክፈል፡ ነው። ያጭር፡ ጊዜ፡ ጥቅሙ፡ የሚገዛው፡ የህወሃት፡ ቡድን፡ ብዙ፡ ሽህ፡ ኪሎሜትር፡ የሚሆን፡ ለም፡ መሬትና፡ ወንዞች፡ ለባእዳን፡ መንግስታትና፡ የግል፡ ሃብታሞች፡ ሲያስረክብ፡ ለነዋሪው፡ ህዝብ፡ የኑሮ፡ መሻሻል፤ ለኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ የምግብ፡ ዋስትና፤ ለወጣቱና፡ ተከታታይ፡ ትውልድ፡ እድገትና፡ ብልጽግና፡ አስቦ፡ ሳይሆን፡ የውጭ፡ ምንዝሬ፡ ለማካበት፤ ለውጭ፡ ድጋፍ፡ ማረጋገጫ፡ ወዘተ፡ ተብሎ፡ መሆኑ፡ አያከራክርም።
ሰላማዊ፡ ሕዝብ፡ ጥሮ፡ ግሮ፤ ራሱን፡ ችሎ፤ ዜግነቱ፡ ተከብሮ፤ በሃገሩ፡ ኮርቶ፡ እንዳይኖር፡ ካለበት፡ አስገድዶ፡ ያስወጣ፤ ለአካባቢው፡ ዘላቂነት፡ ደንታ፡ የሌለው፡ ወዘተ፡ ቡድን፡ ከራሱ፡ ስልጣንና፡ የኢኮኖሚ፡ ጥቅም፡ ባሻገር፡ ለኢትዮጵያና፡ ለ ፱፻ ሚሊዮን፡ ሕዝብ፡ ደንታ፡ አለው፡ ብሎ፡ ለመናገር፡ የሚያስችል፡ ብዙ፡ ማስረጃ፡ የለም። ለምሳሌ። በአሁኑ፡ ጊዜ፡ አብዛኛው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ የዋጋ፡ ግፍሸት፡ ስለመረረው፡ “ምን፡ ቀን፡ አመጣህብን፤ መቸ፡ ይሆን፡ ደህና፡ ኑሮ፡ የምንኖር” የሚለው፡የእድገቱ፡ ተካፋይና፡ ተጠቃሚ፡ ባለመሆኑ፡ ነው። አብዛኛው፡ ሃሁ፡ የቆጠረ፡ ሁሉ፡ ከአገር፡ መሰደድ፡ የሚመርጠው፡ እድልና፡ ሰላም፡ ስለሌለ፡ ነው። ይህ፡ አስቃቂ፡ ሁኔታ፡ ሊቀየር፡ የሚችለው፤ ለም፡ የእርሻ፡ መሬት፡ ለውጭ፡ መንግስታት፤ ሃብታሞችና፡ ለውስጥ፡ ምርጥ፡ ተጠቃሚወች፡ በመስጠት፡ ሳይሆን፡ ስራቱን፡ በመለወጥና፡ የአምራቹን፡ክፍል፡ አቅም፡ በማጎልመስ፤ ኢትዮጵያዊያን፡ የሃገራቸው፡ ባለቤት፡ ሲሆኑ፡ ብቻ፡ ነው። ባጭር፡ አነጋገር፡ ይህ፡ ጠባብ፡ የዘረኛ፡ ቡድን፡ ኢትዮጵያን፡ “ዘርፎ፡ ለዘራፊ፡ ዳርጓታል” ቢባል፡ ከእውነቱ፡ የራቀ፡ ሊሆን፡ አይችልም። የህንዱ፡ ካሩቱሪ፤ የሳውዲው፡ ሳውዲ፡ ስታር፡ የሚያዙባት፡ አገር፡ የሆንችው፡ በህወሃት፡ ግብዣ፡ ነው። ይህን፡ “farmland colonization by invitation” ብየ፡ ሰይሜዋለሁ። ይህ፡ ሁኔታ፡ ካልታረመ፡ ሃገር፡ አለን፡ ብሎ፡ ለመናገር፡ አጂግ፡ አስቸጋሪ፡ ነው።
ሕግ፡ የማይከበርበት፡ ሕገ፡ መንግስት።
ህወሃት፡ የፖለቲካ፡ ስልጣን፡ እንደያዘ፡ የቀረጰው፡ ሕገ፡ መንግስት፡ ኢላማ፡ የህዝብ፡ መብት፡ማጎልመስ ሳይሆን፡ ሕዝብን፡ ለመቆጣጠር፤ ህብረተሰቡን፡ እርስ፡ በእርሱ እንዲዋከብ፡ ለማድረግ፤ ዱሮ፡ በሰላም፡ የመኖር፡ ልምድና፡ ባህል፡ የነበረውን፡ ሕዝብ፡ አሁን፡ አንዱ፡ በወንድሙ/እህቱ/አባቱ/ዘመዱ/ወዳጁ፡ ወዘተ፡ ላይ፡ እንዲሰልል፡ ለማድረግ፡ በቅቷል። ጎጅ፤ ግልጽነት፡ የሌለው፤ በተቆጣጣሪነቱ፡ ዘመን፡ ያለፈለትን፡ የሶቪት፡ ህብረት፡ የቁጥጥር፡ ስራት፡ የሚመስል፤ ጎሳዊ፤ የኢኮኖሚ፡ አመራር፡ “በሌሊት፡ ጨለማ፡ እንደሚጓዝ” መንገደኛ፡ ይመስላል። ሂደትና፡ አቅጣጫው፡ አይታወቅም። ጥቅሙ፡ የማይታይ፤ ተሳትፎ፡ የሌለበት፡ የልማት፡ ስልት፡ እየተከተለ፡ ሰው፡ የሚበላው፡ አጥቶ፡ በርሃብ፡ አለንጋ፡ ሲገረፍ፡ ፩፩ በመቶ፡ እድገት፡ አለ፡ ብሎ፡ የፈጠራ፡ ማስረጃ፡ የሚያቀርብ፡ መንግስት፡ የት፡ ላይ፡ እንደሚታመን፡ ማስረጃ፡ ለማግኘት፡ ያዳግታል። አለም፡ ባንክ፤ ኦክስፎርድ፡ ዩንቨርስቲ፤ ሌጋተም፤ ሞ፡ ኢብራሂም፤ የተባበሩት፡ መንግስታት፡ የልማት፡ ድርጂት፡ ያወጡት፡ ዘገባወች፡ የነፍስ፡ ወከፍ፡ ገቢ፡ አሁንም፡ ከአሜሪካ፡ ዶላር፡ ፫፱፻ በላይ፡ እንዳልሆነ፤ የርሻ፡ ውጤት፡ ከህዝ፡ እድገት፡ ጋር፡ ሊራመድ፡ እንዳልቻለ፤ የዋጋ፡ ግፍሽት፡ መካከለኛ፡ መደብ፡ ውስጥ፡ ለሚገኙ፡ ወገኖቻችን፡ ኑሮ፡ አስቃቂ፡ እንደሆነ፡ ክ ፰ እስክ፡ ፩፫ ሚሊዮን፡ ኢትዮጵያዊያን፡ አሁንም፡ በውጭ፡ አገሮች፡ የምግብ፡ ድጎማ፡ እንደሚኖሩ፤ ፯፮ በመቶ፡ የሚገመቱ፡ ኢትዮጵያዊያን፡ አገር፡ ለቀው፡ ስደት፡ ለመውጣት፡ እንደሚፈልጉ፤ ቢያንስ፡ ፭ ሚልዮን፡ ኢትዮጵያዊያን፡ ከውጭ፡ በሚኖሩ፡ ወገኖቻቸው፡ ድጋፍ፡ እንደሚኖሩ፡ ያሳያሉ። ስለሆነም፡ እድገቱ፡ በሰው፡ የኑሮ፡ መለⷋያ፤ ደስታና፡ መሻሻል፡ ሲታይ፡ እንቆቅልሽ፡ ነው፡ ለማለት፡ ይቻላል።
እድገት፡ በፍትህ፤ ለፍትህ፡ እንዲስፋፋ፡ በማድረግ፡ ፋንታ፤ ህወሃት፡ ዝግና፡ ለጥቂት፡ ሰወች፡ የሚጠቅም፡ ኢኮኖሚ፡ ፈጥሯል። ስግብግብነት፤ ራስ፡ ወዳድነት፤ ለአገር፡ አለማሰብ፤ አድሎና፡ ሙስና፤ ለነገ፡ አለማሰብ፡ ባህል፡ ስር፡ እንዲሰድ፡ በማድረግ፡ላይ፡ ይገኛል። በሰላም፡ አብሮ፡ የመኖር፡ ባህል፡ እንዲጠፋ፡ ሆነ፡ ብሎ፡ ሲገፋበት፡ ይታያል። ህዝብ፡ ለህዝብ፡ እንዳያስብ፤ ፖለቲካና፡ የእድገት፡ መሰላሎች፡ ፍትሃዊ፤ ተሳትፊያዊ፡ እንዳይሆኑ–ልማት፡ በዘላቂነትና፡ በተሳትፎነት፤ እንዳይመሰረት፡ ህጉን፤ ደንቡን፡ በክፍፍል፡ አንጾትና፡ መርቶት፡ ይታያል። በታሪክና፡ በልምድ፡ የተገኘው፡ የህብረ-ብሄር፡ አገራዊ፡ ትሥሥር፡ በዘመናዊ፡ መልክ፡ ስር፡ እንዳይሰድ፡ ለዘር፡ ፖለቲካ፡ ቀደምትነት በመስጠት፤ ህብረተሰቡን፡ ዘርፎ፡ ለዘራፊ፡ ዳርጎት፡ ይገኛል። በአሁኑ፡ ወቅት፡ ኢትዮጵያዊያን፡ በሃገራቸው፡ የተፈጥሮ፡ ሃብት፡ ላይ፡ ለማዘዝ፡ አይችሉም። ስልጣን፡ ቀርቶ፡ መጠነኛ፡ ድምጽ፡ የላቸውም። አደጋው፡ ለአሁኑ፡ ትውልድ፡ ብቻ፡ሳይሆን፡ ለተከታታይ፡ ትውልዶች፡ ጭምር፡ ነው።
የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ የኢኮኖሚ፡ ባህል፡ ዘመናዊና፡ ሁለ-አቀፍ፡ እንዳይሆን፡ አዲሱ፡ ትውልድ፡ በምቀኝነት፤ በራስ፡ ወዳድነት፤ በፍርሃት፤ በጎጂ፡ ባህል፤ በውሸት፤ በስደት፡ ወዘተ፡ እንዲያምን፡ አስገድዶት፡ ይታያል። ለሃገርና፡ ለወገን፡ በማሰብ፡ ፋንታ፡ ለዘር፤ ለገዥው፡ ፓርቲ፡ ታማኝነት፤ ለራስ፡ ጥቅም፡ እንዲገዛ፡ አስገድዶታል። ዛሬ፡ ህወሃት፡ አንዱ፤ በአንዱ፡ ላይ፡ እንዲቀናና፡ እንዲሰልል፡ ከሩብ፡ ቢሊየን፡ ብር፡ በላይ፡ በአመት፡ ለማስታወቂያ፡ የሚያወጣው፤ ከዚህ፡ በላይ፡ የሚገመት፤ ለስለላ፡ የሚያፈሰው፡ ሕዝብን፡ ለማቅራረብ፤ አገርን፡ ለመላው፡ አለም፡ ለማስተዋወቅ፤ አዲስ፡ እውቀትን፡ ለመሸመት፤ ሰላምና፡ ርጋታን፡ ለማጠናከር፡ ሳይሆን፡ ቁጥጥርን፡ ለማስፋትና፡ ጥልቀት፡ ለመስጠት፡ ነው። በፍርሃት፡ የተበከለ፤ ለራሱ፡ ነጻነትና፡ ክብር፡ የማያስብ፤ ለታዛዥነት፡ ቅድሚያ፡ የሚሰጥ፤ በኢትዮጵያዊነቱ፡ የማያምን፤ ራሱን፡ ከድህነት፡ ነጻ፡ አውጥቶ፡ አገሩንና፡ ወገኑን፡ በኢትዮጵያ፡ ውስጥ፡ ሁኖ፡ ከድህነት፤ ከርሃብ፤ ከጥገኝነት፡ አዙሪት፡ ነጻ፡ ሊያወጣ፡ የሚችል፡ ትውልድ፡ እንዳይፈጠር፡ የትምህርት፡ ስራቱን፡ በጎሳ፤ በቋንቋ፤ በፓርቲ፡ ታማኝነትናት፡ በዘር፡ ልይነቶች፡ ላይ፡ መስርቷል፡፡ ይህን፡ በማድረግ፡ ኢትዮጵያ፡ አቀፍ፡ የሆኑ፡ ተቋሞች፤ አገራዊ፡ የህብረተሰብና፡ የኢኮኖሚ፡ እሥስር፤ መቆላለፍ፡ እንዳይኖር፡ አድርጓል። አገራዊ ወይንም፡ ኢትዮጵያዊ፡ ተቋሞች፡ ከሌሉ፡ ደግሞ፡ የፖለቲካ፡ ሆነ፡ የኢኮኖሚ፡ ጥቅሞች፡ ፍትሃዊና፡ ተሳትፏዊ፡ ሊሆኑ፡ አይችልም። አንዱ፡ የበላይ፤ ሌላው፡ ታዛዥ፤አንዱ፡ ድሃ፡ ሌላው፡ ሃብታም፤ አንዱ፡ በልቶ፡ አዳሪ፡ ሌላው፡ ጦም፡ አዳሪ፡ የሚሆን፡ ለዚህ፡ ነው።
የህወሃት፡ ባለስልጣኖች፡ ስለ፡ እድገት፡ የሚናገሩት፡ “በሬ፡ ወለደ፡” አይነት፡ ወሬ፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ የማይቀበለው፡ መሆኑን፡ እኔ፡ ላንባቢው፡ ማቅረብ፡ አያሥፈለገኝም። ለመካድ፡ ስለማይቻል። ለማንሳት፡ የምፈለገው፤የማንኛውም፡ ታዳጊ፡ አገር፡ ታሪክ፡ ጥሩ፡ የእድገት፡ ውጤት፡ የሚያሳየው፡ ገጽታ፡ አገራዊ፡ የሆኑ፡ ተቋሞችና፡ የህዝብ፡ ተሳትፎ፡ ቁልፍነትን፡ ነው። እድገት፡ በህዝብ፡ ጥቅም፡ ካልተዳኘ፤ የእድገት፡ ጥቅም፡ ለጥቂቶች፡ ብቻ፡ የሚሆነው፡ በዚህ፡ የተነሳ፡ ነው። እድገት፡ ከህዝብ፡ ጥቅምና፡ የኑሮ፡ መሻሻል፡ጋር፡ ካልተሳሰረ(ካልተገናኘ)፡ ዘመናዊነትና፡ ዘላቂነት፤ ፍትህና፡ ርትህ፡ እውን፡ አይሆኑም። ከጥግኝነት፡ ነጻ፡ የሆነና፡ ራሱን፡ የቻለ፡ ኢኮኖሚ፡ ለመገንባት፡ አይቻልም። ያሁኑ፡ ቅጡን፡ ያጣ፡ የፖለቲካና፡ የኢኮኖሚ፡ ስራት፡ እንደ፡ ነጻ፡ የገቢያ፡ ስራት፡ መሳሪያ፡ አድርጎ፡ ማቅረብ፡ ለጠባብ፡ ጥቅም፡ ያመቻል፡ እንጂ፡ ራሱን፡ የቻለ፤ ተወዳዳሪነቱ፡ የማይበገር፡ አገራዊ፡ ኢኮኖሚ፡ ለመገንባት፡ አያስችልም። ለዚህ፡ የቦትስዋናን፡ እድገት፡ ምሳሌ፡ ልጠቀም።
ይህችን፡ ራሷን፡ ያስመሰገነች፤ ህዝቧን፡ ያበለጸገች፡ አገር፡ ስናይ፡ እድገት፡ ምስጢር፡ ሳይሆን፡ የአገዛዝና፡ የብሔራዊ፡ አመራር፡ ጥሩነት፡ ገጽታ፡ ነው፡ ለማለት፡ ያስደፍራል። እ.አ.አ. በ 1966 ነጻነቷን፡ የተጎናጸፈችው፡ ቦትስዋና፡ በዚያ፡ ወቅት፡ 22 ብቻ፡ ዩንቨርስቲ፡ የጨረሱ፡ ዜጎች፡ ነበሯት። የድህነት፡ መጸብራቅ፡ ነበረች፡ ማለት፡ ነው። ከዚህ፡ ዝቅተኛ፡ ደረጃ፡ ተነስታ፡ እንዴት፡ የአፍሪካ፡ የእድገት፡ አራያ፡ (በአፍሪካ፡ ከፍተኛ፡ የነፍስ፡ ወከፍ፡ ገቢ) ያላት፡ ልትሆን፡ ቻለች፡ ብለን፤ እንጠይቅ። በመጀመሪያ፡ ደረጃ፡ ሁሉን፡ አቀፍ፡ የሆነ፡ አገራዊ፡ ህገ፡ መንግስት፤ ተቋሞችና፡ የመንግስት፡ አስተዳደር፤ ስራ፡ ላይ፡ አዋለች። ነጻና፡ ተሳትፏዊ፡ ምርጫወቺን፡ በግልጽነትና፡ በተደጋጋሚ፡ አካሄደች። የግል፡ ሃብት፡ በህግ፡ እንዲረጋገጥ፡ አደረገች። መአከላዊ፡ አስተዳደር፤ ከሚዛናዊ፡ የክፍለ፡ ሃገር፡ ተሳትፎና፡ የህዝብ፡ ድምጽ፡ ጋር፡ ጎን፤ ለጎን፡ እንዲሰሩ፡ አደረገች። እንቁ፡ (diamond) በብዛት፡ ሲገኝ፡ ሁሉም፡ የሃገሪቱ፡ ህዝብ፡ እንዲጠቀም፡ አደረገች። የሚገኘው፡ ትርፍ፡ የበላይ፡ ስልጣን፡ ለያዙ፡ ጥቂት፡ ሰወች፡ ጥቅም፡ ሳይሆን፡ ለሃገሪቱ፡ እድገት፤ ለመላው፡ ህዝብ፡ ኑሮ፡ መሻሻል፡ ስራ፡ ዋለ። ስግግብግብነት፤ ራስ፡ ወዳድነት፤ አድሏዊነት፤ ሙሰኝነት፡ ሳይሆን፡ ለህዝብ፡ ሃላፊነትና፡ ተጠሪነት፡ ያለው፡ አመራር፡ ተቋሞች፡ ሁሉ፡ ለህዝብ፡ አገልጋዮች፡ እንዲሆኑ፡ አስመሰከረ።
ቦትስዋና፤ አሁን፡ ደግሞ፤ ጋና፤ የሚያሳዩት፤ አገራዊ፡ ተቋሞች፤ አገራዊ፡ አመራር፤ የህዝብ፡ ተሳትፎ፤ ለህዝብ፡ ተጠሪነት፤ የህግ፡ የበላይነትና፡ ክቡርነት፤ ተክታታይ፡ ነጻ፡ ምርጫ፤ የግል፡ ንብረት፡ በህግ፡ መታወቅ፤ የተፈጥሮ፡ ሃብት፡ ለሃገርና፡ ለህዝብ፡ ጥቅም፡ መዋል፡ ወዘተ፡ ለልማት፡ ቁልፍ፡ መሆናቸውን፡፡ነው። እነዚህ፡ እውን፡ የሚሆኑት፡ ሁለ-አቀፍ፡ የመንግስት፡ ስራትና፡ ሁለ-አቀፍ፡ አገራዊ፡ ተቋሞች፡ ሲኖሩ፤ መሪወች፡ የህዝብ፡ አገልጋዮች፡ ሲሆኑ፡ ብቻ፡ ነው። ዘላቂነትና፡ ፍትሃዊ፡ እድገት፡ የሚመጣው፡ ወይንም፡ የሚገኘው፡ እንደዚህ፡ካለ፡ የአገዛዝና፡ የአመራር፡ ስራት፡ ነው። እድገት፡ የትም፡ አገር፡ ሊኖር፡ ይችላል፤ በተለይ፡ እንደ፡ ኢትዮጵያ፡ ባለ፤ ካርባ፡ ቢሊየን፡ የአሜሪካ፡ ዶላር፡ በላይ፡ በርዳታና፡ በድጎማ፡ ባገኘ፡ መንግስት፡ የምትመራ፡ አገር። ችግሩ፡ እድገት፡ ቢታይም፡ የአብዛኛው፡ ህዝብ፡ ኑሮ፡ ሊሻሻል፡ አልቻለም። አብዛኛው፡ በርዳታ፡ የሚገኝ፡ ገንዘብ፡ ለጥቂቶች፡ ሃብት፡ ማካበቻ፤ ታይቶ፡ የማያውቅ፡ የድሎት፡ ኑሮ፡ መኖሪያ፤ የገንዘብ፡ ማሸሻ፡ መንገድ፡ መሆኑ፡ ነው። ባንድ፡ አመት፡ የአሜሪካ፡ ሶስት፤ ነጥብ. ሁለት፡ ስድስት፡ ቢልየን፡ ብር፡ ከሃገር፡ ያለአግባብ፡ መውጣት፡ የሚያሳየው፡ በቦትስዋናና፡ በኢትዮጵያ፡ መካከል፡ ያለውን፡ ሰፊ፡ ልዩነት፡ ነው። በዚህ፡ አይነት፡ ቦትስዋና፡ ከደረሰችበት፤ ማለትም፡ በአመት፡ USD $16,300 (2011) vs. Ethiopia USD $1,100 (2012): የነፍስ፡ ወከፍ፡ የምርት፡ መለኪያ፡ ለመድረስ፡ምን፡ ማድረግ፡ እንዳለባት፡ ያመክታል። ቦትስዋና፡ ዛሬ፡ ከኮስታሪካ፡ ጋር፡ እንጂ፡ ከኢትዮጵያ፡ ጋር፡ አትነጻጸርም። ሁለቱም፡ መካከለኛ፡ ገቢ፡ የደረሱ፡ አገሮች፡ ናቸው።
ለሃገር፡ ሃላፊነት፡ የሌላቸው፡ ተቋሞች፤ ለሃገር፡ ተጠሪነት፡ የሌለው፡ መንግስት፤ ለመላው፡ ህብረተሰብ፡ ተጠሪነት፡ የሌለው፡ አመራር፡ ከጥቅሙ፡ ጉዳቱ፡ ይልቃል። ለዚህ፡ ማስረጃው፡ በቱኒዥያ፤ በግብጽ፤ በየመን፤ በሊቢያና፤ አሁን፡ በሶሪያ፡ የሚጦፈው፡ በህዝብ፡ የሚመራው፡ ለውጥ፡ ነው። እነዚህ፡ ለውጦች፡ ከጭቆና፤ ከኪራይተኛነት፡ ባህል (rent-seeking culture and system)፤ ከሙስና፤ ከአድሎ፤ ከህገ፡ ወጥነት፤ ከስባዊ፡ መብቶች፡ መዛባት፤ ከኑሮ፡ ውድነት፤ ከስራ፡ አጥነት፤ ከተስፋ፡ መቁረጥ፤ ወዘተ፡ የመነጩ፡ ናቸው። ነጻነቱንና፡ መብቱን፡ የተከለከለ፡ ህዝብ፡ ለማስብ፤ ለመፍጠር፤ ለማደግ፤ ራሱን፡ ረድቶ፡ አገሩን፡ ለመርዳት፡ አይችልም፤ ብልው፡ በመተባበር፡ የተነሱ፡ ናቸው። ለዚህ፡ ነው፡ የነዚህ፡ አገሮች፡ ህዝቦች፡ ለፍትህ፤ ለርትህ፡ የተሰውት፤ የሚሰውት። የሚፈልጉት፡ የቦትስዋና፡ የኮስታሪካ፡ አይነት፡ የኑሮ፡ ደረጃ፡ ለመድረስ፡ ነው። ከዚህ፡ ደረጃ፡ የሚያደርሳቸው፡ ስራት፤ ሁሉን፡ አቀፍ፤ ለሁሉ፡ እድል፡ ከፋች፤ በእኩልነት፤ በፍትህ፤ በህዝብ፡ የነጻ፡ ድምጽ፤ ለህዝብ፡ ተጠሪ፤ የሆነ፡ አማራጭና፡ ይህን፡ የሚመራ፡ ለህዝብ፡ ተገዥ፡ የሆነ፡ ችሎታ፡ ያለው፡ አገራዊ፡ አመራር፡ ነው።
የሃገራዊ፡ ተቋሞች፡ ቁልፍነት።
የመልካም፡ እድገት፡ ምርምርና፡ ልምድ፡ የሚያሳየው፡ የመንግስት፡ ስራት፡ ርስ፡ በርስ፡ የመጠራጠር፡ ባህል እንዲሆን፡ “ከፋፍለህ፡ ግዛው” የሚለውን፡ የቅኝ፡ አገዛዝ፡ አሰራር፡ ማንጸባረቁ፡ ለገዥው፡ ቡድንና፡ ስራት፡ አስፈላጊ፡ መስሎ፡ ይታይ፡ እንጂ፡ ለኢትዮጵያና፡ ለአብዛኛው፡ ሕዝቧ፡ በጣም፡ ጎጂ፡ ነው። ህወሃት፡ ይህን፡ ሁሉ፡ ያደረገው፡ ሚዛናዊ፡ የሆነ፡ ማእከልነትን፡ ከወካይ፡ የመንግስት፡ ስራትና፡ ስልት፡ ጋር፡ እንዳይጣመር፡ ለማጠንከር፡ ነው። የተከፋፈለና፤ ድሃ፡ ህዝብ፡ ለመግዛት፡ ቀላል፡ ነው። እንደዚህ፡ ባለ፡ የቁጥጥር፡ መንገድ፡ ዲሞክራሳዊ፡ ስራት፡ አይገነባም። ድህነት፡ አይፈታም። ስራ፡ አጥነት፡ አይወገድም። የዚህ፡ ሁሉ፡ ጨለማ፡ የሚመስል፡ የቁጥጥር፡ ኢኮኖሚ፡ ስልት፡ ዋናው፡ አላማ፡ የህወሃትን፡ ስልጣንና፡ ጥቅም፡ ለማጠናከር ነበር፡ ማለት፡ ነው፤ አሁንም ነው። ለዚህ ዋና፡ ዋና፡ የተቋም፡ መለኪያዎች፡ ማየት፡ ይበጃል። ሁለት ልጥቀስ።
የህወሃት፡ ተቋሞች፡ የኢትዮጵያን፡ ሕዝብ፡ አይመስሉም፡
የኢትዮጵያ የጦር፤ የፓሊስ፤ የስለላ ወዘተ፡ ተቋሞች፡ ማንን፡ ይመስላሉ፤ ማንን፡ ያገለግላሉ? የበላይ እዛዥቻቸው፡ ምን ይመስላሉ? አገራዊና፡ ኢትዮጵያዊ፡ ናችው፡ ወይንስ፡ ጎሳዊ/ ህወሃታዊ? የማይካደው፡ በማንኛውም፡ ቁልፍ፡ ቦታ፡ አብዛኛወቹ፡ የበላዮች/ወሳኞች/አዛዦች፡ የትግራይ፡ ስዎች፡ መሆናችው፡ ነው። ለይስሙላ፡ ትግራይ፡ ያልሆነ፡ ሃላፈ፡ ፊት፡ ለፊት፡ ተሹሞ፡ ቢቀመጥ፡ ከጀርባ፡ ወሳኙ፡ ታማኝ፡ የሆነ፡ የትግራይ፡ ሰው፡ ነው። ከዚሁም፡ ብሶ፡ “ከአንድ፡ መንደር”፡ የመጡ፡ ተብሎ፡ ይነገራል። እነዚህና፡ አገር፡ ያገለግላሉ፡ የተባሉ፡ ድርጂቶች፡ የኢትዮጵያን፡ ሕዝብ፡ ይመስላሉ፤ ኢትዮጵያን፡ ያገለግላሉ፡ ብሎ፡ ለመቀበል፡ ምንም፡ ማስረጃ፡ የለም። የቦትስዋና፡ ከኢትዮጵያ፡ የሚለየው፡ በዚህ፡ ነው። በንጕሱ፡ እና በደርግ ስራቶች፡ የኢትዮጵያ፡ የመክላክያ፤ የፖሊስ፡ እና፡ የስለላ ተቋሞች፡ አገራዊ፡ እንጂ፡ የአንድ፡ ጎሳ፡ ወይንም፡ ፓርቲ፡ የስልጣን፡ ምሰሶ፡ አልነበሩም። ይህ፡ የተቋሞች፡ ልዩነት፡ በደንብ መታወቅ፡ አለበት። የኢትዮጵያን፡ ሕዝብ፡ ካልመሰሉ፤ ህወሃት፡ ለራሱ፡ ቡድን፡ የበላይነት፡ ይጠቅምባቸዋል። ተቋሞች፡ የመላውን፡ ሕዝብ፡ ካልመሰሉ፤ መላዉን፡ ሕዝብ፡ ካላገለገሉ፡ ኢትዮጵያዊነታችው፡ የት ላይ፡ ሊሆን ይችላል፡ ብሎ፡ መጠየቅ፡ አግባብ፡ አለው። ስለሆነም፡ የአሁኑ፡ የወታድር/ፖሊስ/ስለላ፡ ስራት፡ ሆነ ሚናችው፡ ህወሃትን ፡ ለማገግል፡ እንጂ፡ የኢትዮጵያን፡ ሕዝብ፡ ያለ፡ አድሎ፡ ለመጠበቅ፤ አገሪቱን ክጥቃት ለማዳን፡ መሆኑ፡ ያክራክራል።
ሆኖም፡ ይህ፡ ስራዊት፡ ክሕዝብ፡ የተወጣጣ፡ እንደመሆኑ፡ መጠን፡ አንድ ቀን፡ ወደ፡ ሕዝብ፡ እና፡ ወደ ዋናው፡ አገርን፡ የመከላከል፡ ተግባሩ፡ መመለሱ፡ አይቀርም። ቢያንስ፡ ለማን፡ ለምን፡ እንደቆመ ፡ ራሱን መጠየቁ፡ አያጠራጥርም። አሁንም፡ እንደሚሰማው፡ ራሱን፡ እየጠየቀ፡ ነው። በኢሃደግ፡ ፓርቲ፡ ውስጥ፡ ያሉ፡ አባላትም፡ ቀስ፡ በቀስ፡ ራሳቸውን፡ መጠየቅ፡ ጀምረዋል። ኢትዮጵያዊያን፡ ለዚህ፡ የተደበቀ፤ ግን፡ ያልጠፋ፡ ባህል፤ የሚያኮራ፡ ታሪክና፡ የአስተዋይነት፡ ቅርስ፡ አለን። ምንም፡ አይነት፡ አገዛዝ፡ ሕዝቡን፡ ቢያማርረው፡ እርስ፡ በእርሱ፡ የመገዳደል፡ ባህል፤ ልምድ፤ ጸባይና፤ አዝማሚያ፡ የለውም። ጠቅላይ፡ ሚንስትር፡ መለስ፡ የተሳታቱት፡ እዚሕም፡ ላይ፡ ጭምር፡ ነው። በ፱፯ ምርጫ፡ ህዝቡ፡ ያለውን፡ ትግስት፤ መቻቻልና፡ ታላቅነት፡ ጠቅላይ፡ ሚንስትሩ፡ ሳያዙት፡ አስመስከሯል። እንደ፡ ሩዋንዳ፡ በትግራይ፡ ህብረተሰብ፡ ላይ፡ እልቂት፡ ይመጣል፡ ተብሎ፡ የተሰጠው፡ ፕሮፓጋንዳ፡ ሊሆን፡ አለመቻሉን፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ አሰምሮበታል። ስለሆነም፤ የበደለውን፡ ቡድን/ግለሰብ፡ ከስላማዊው፡ ህዝብ፡ መለየት፡ የሚችል፡ ህብረተሰብ፡ የጦር፡ ሃይሉን፡ ለሰላም፤ለመቻቻል፤ለእርቅ፡ ወዘተ፡ ይመራዋል፡ ብሎ፡ ለመገመት፡ ማስረጃ፡ አለ። በህዝብ፡ እምነት፡ ሊኖረን፡ የሚገባን፡ ለዚህ፡ ጭምር፡ ነው። ስለዚህ፡ ጦሩ፤ አገር፡ አቀፍ፡ በሆነ፡ ደረጃ፡ መላው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ቢነሳ፤ ድርጅትና፡ አመራር፡ ቢኖር፤ ወገኑ፡ ርስ፡ በርስ እንዲፋጅ፡ ያደርጋል፡ ብሎ፡ ለመገመት፡ አይቻልም። የሚፈልገው፡ ብሩህና፡ እርቅን፤ ሰላምን፤ እድገትን፤ አብሮ፡ መኖርን፡ የሚያቅፍ፡ አማራጭ፡ ነው።
የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ በዘር፡ የተመሰረተው፡ የህወሃት፡ ቡድናዊ፡ ስራት፡ ከደቡብ፡ አፍረካ፡ አፓርታይድ፡ ስራት አይለይም፡ ይላል። ስንመረምረው፤ ህወሃት፡ ራሱን፡ ያጋልጣል። በዘር፡ የተቀነባበረው፡ ክልል፡ የተባለ፡ የአገዛዝ፡ እና የአስተዳደር፡ ስራት፡ በኢትዮጵያና፡ በህዝቧ፡ ላይ፡ ሲተክልበት፡ አላማው፡ ምን፡ ነበር፤ ለማን፡ ሲባል? ማነን ለማድክም?፡ማነን፡ ለማሳደድ? ማንን፡ ለማክበር፤ ሲል፡ የቆየው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ› መልሱን፡ አግኝቷል። ህወሃት፡ ለአለም፡ ያቀረበው፡ ፕሮፓጋንዳ፡ የሕዝብን፡ መብት፡ ለማጠናከር፤ ለማጎልመስ፤ ኢትዮጵያን፡ ለመታደግ፤ ሕዝብ፡ ወሳኝ፡ እንዲሆን፡ ለማድረግ፤ ፍጥነት፡ ያለው፡ እድገት፡ እውን፡ ለማድረግ፡ ናቸው። የመወሰን፡ መብትን፡ ወስደን፡ ለህዝብ፡ አገልጋይነቱን፡ ብንመረምር፡ ክፍተቱን፡ ያሳየናል። የዲሞክራሲ፡ ዘመን፡ መጣልህ፡ የተባለው፡ ሕዝብ፡ ተጠቂና፡ ታዝዥ፡ ከሆነ፡ የዲሞክራሲ፡ ትርጉም፡ ባዶ፡ ነው፡ ማለት፡ ነው። በተለይ፡ ለአርሶ፡ አደሩ፡ ሕዝብ። አርሶ፡ አደሩ፡ በመወሰን፡ ደረጃ፡ ምንም፡ መብት፡ የለውም። የእርሻ፡ መሬቱን፡ ሆነ፡ የሚያርስውን፡ አያዝበትም። እንዲያውም፡ የነጠቃው፡ ችግር፡ ባለበት፡ ሁሉ፡ ከእርሻው፡ መሬት፡ እንዲፈናቀል፤ ያለ፡ መኖርያ፡ እንዲሰደድ፡ እየሆነ፡ ነው። ነጠቃው፡ በማን፡ ትእዛዝ፤ ለማን፡ ጥቅም፤ እንደሚደረግ፡ ብዙ፡ አለም፡ አቀፍ፡ ድርጂቶች፡ ዘግበውታል። ከቦትስዋና፡ ጋር፡ ስናወዳድር፡ የቁጥጥር፡ ስራት፡ ባለበት፡ እነደ፡ ኢትዮጵያ፡ ባለ፡ አገር፡ ሁሉ፡ የተፈጥሮ፡ ሃብትን፡ እንደተፈለገ፡ ለመስጠት፤ ለመሸጥ፤ ሃብት፡ ለማካበት፤ለአድሎና፡ ሙስና፤ ስራቱን፡ ለማራዘም፡ ይረዳል። የገጠሩ፡ ህብረተሰብ፡ ለቁጥጥር፡ የተዳረገው፡ ለዚህ፡ አመች፡ እንዲሆን፡ ነው። ስለሆነም፡ የከተማ፡ ሆነ፡ የገጠሩ፡ ህዝብ፡ ስልጣን፡ አለው፡ ብሎ፡ ለመናገር፡ በምንም፡ አይቻልም። አርሶ፡ አደሩ፡ የሚኖርበትን፡ ቀርቶ፡ የሚያመርተውን፡ ሊያዝበት፡ አይችልም።
የጋምብይላ፣ ያፋር፤ የኦጋደን፤ የደቡብ፤ የኦሮምያ፤ የአማራ፤ የቢን-ሻንጉል ጉሙዝ፡ ለም፡ መሬት፡ ከ 36 አገሮች፡ ለመጡ፡ እንደ፡ ህንድ፡ ኹባንያ፤ ካሩቱሪ፤ እንደ፤ አረብ-አገሮች፡ ጥቅል፡ ድርጅት፡ ሳውዲ-ስታር፤ እንደ፡ ግብጽ፡ ባንክ፤ እና፡ ክ 8 000 በላይ፡ ለሚሆኑ፡ የውጭ፡ ኮንትራት፡ አቅራቢዎች እና ሃብታሞች፤ ለምርጥ፡ የህወሃት፡ ደጋፊዎች፡ በጀምላ፡ እስክ፡ ፱፱ አመታት፡ ድረስ፡ በዝቅተኛ፡ ኪራይ፡ ያለምንም፡ ገደብ፡ ሲስጥ፡ የክልልን፡ አስተዳደር፡ ስራት፡ አጥፊነት፡ በሚገባ፡ ለማየት፡ ይቻላል። የሚነገረው፡ በኦሮምያ፡ ክልል፡ ብቻ፡ በብዙ፡ ቢሊየን፡ ብር፡ መዋእለ፡ ንዋይ፡ ሰፊ፡ የርሻ፡ ልማት፡ ይካሄዳል፡ የሚል፡ ነው። የመሬት፡ ነጠካና፡ ቅርሚት፡ ውጤታማ፡ ከሆነ፡ መራብ፡ የሌለባት፡ ሃገር፡ ለምን፡ ትራባልች፧ ርሃብ፡ በገጠር፡ ለምን፡ ይስፋፋል፤ የምግብ፡ ዋጋ፡ ግፍሸት፡ ለምን፡ እየባሰ፡ ይሄዳል፤ ማን፡ ተጠቃሚ፤ ማን፡ ተጎጂ፡ እየሆነ፡ ነው፡ ብሎ፡ መጠየቅ፡ ተገቢ፡ ነው። ባጭሩ፡ የክልል፡ ስራት፡ ለገጠሩ፡ ሆነ፡ ለከተማው፡ ሕብረተሰብ፡ ጥቅም፤ ለፍትህ፡ርእትእ፤ ለተሳትፎ፤ ዘላቂነት፡ ላለው፡ እድገት፤ እና፡ በእኩልነት፡ ለሚመራ፡ ማህበራዊ፡ ኑሮ፡ አመቻች፡ ነው፡ ማለት በምንም አይቻልም። የሕዝብ፡ ተሳትፎና፡ መብት፡ ያልተከበረበት፡ የኢኮኖሚ፡ ስራትና፡ እድገት፡ ደግሞ፡ ድህነትን እና ኋላ ቀርነትን፡ አያጠፋም። ይህ፡ አድሏዊ፡ ስራት፡ ከቀጠለ፡ ስደት፤ የኑሮ፡ ውድነት፤ስራ፡ አጥነት፤ ግጭት፤ ርሃብ፡ የሕዝብ፡ እጣ፡ ሁነው፡ ይቆያሉ። የባስ፡ ችግር፡ ይመጣል። ጥገኝነት ይቀጥላል።
ተከታታዩን፡ በመጭው፡ ሳምንት፡ ይመልከቱ፡