ዘፈንን ከማውገዝ የተሻለ ዝማሬ ማቅረብ!

ዘፈን በተነሳ ቁጥር “ዘፈንን” ለማውገዝ ከ “ሊቅ” እስከ ደቂቅ ስዋስዋዊ፡ ታሪካዊና፡ ስነ ጽሑፋዊ የመጽሐፍ ቅዱስ የአተረጓገም ስልት ወደ ጎን በመተው ቃሉ ከዓውደ ንባቡ ውጭ በዘፈቀደ በመተርጎም እንደ ማስረጃ ለማጣቀስ የሚያኮበክበው ማር. 6:25/ማቴ፡ 14፡6 ላይ ወደ ሰፈረው ቃል ነው:: ጥያቄው: ቃሉ እውነት ዘፈንን ስለ ማውገዝ ነው ወይ የሚያትተው ነው? ሙሉ ቃሉ እንደሚከተለው ይነበባል::

“ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤ የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት” ወጥታም ለእናትዋ ምን ልለምነው? አለች ርስዋም የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አለች ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ ብላ ለመነችው። ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም። ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥ ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች።”  

የሀገሬ ሰው “የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ” እንደሚለው ሌላው ቢቀር የሰው አንገት በሰይፍ ተቀልቶ በወጭት እንዲሰጣት የጠይቀች ልጅ የምትለምነው ነገር እንኳ አታውቅም:: እናትዋ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ” ስትላት “እንዴ! እንዴት? ሰው መግደገል ኃጢአት አይደለም ወይ” በማለት እንኳ እናትዋን ስትሞግት አንመለከትም እንደው ከመጽሐፉ በግልጽ እንደምናነበው  “ፈጥና” እንዲል በእንዲህ ያለ ሁኔታ ነው ንጉሡ ቃሉን አክብሮ ጥያቄዋን እንዲመልስ የጠየቀችው::

በመጀመሪያ ደረጃ ያም ይህም ለማለት ስለ ዘፈኑ ይዘት ምንም የምናውቀው ነገር የለም:: ባለ አመል ካልሆነ በስተቀር መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ምንም የሚለው ነገር የለም:: የልጅነት አንደበትዋ ይጣፍጠው እንቅስቃሴዋ ይማርከው የራስዋ ግጥምና ዜማ ሰርታ ትዝፈን የንጉሡ ጸሐፊዎች ሰርተው ይስጥዋት እናትዋ ትስጣት ምንም የምናውቀው ነገር የለም:: ከዓውዱ ለመረዳት እንደሚቻለው ግን ንጉሡን ያስደነቀው ልጅነትዋና ከልዩ ተሰጥዖትዋ ተዳምሮ ሊሆን ይችላል:: ይህም ቢሆን የታሪኩ ሙላት ሊሆን አይችልም በዋናነት ግን የታሪኩ አንኳር ሆኖ የምናገኘው ንጉሡ የፈጸመውን ማህላ/የገባውን ቃል ኪዳን ከመፈጸም ጋር የተያያዘ ነው:: ውሳኔውም በዘፈኑ ልቡ ከመቅለጡ (ዘፈኑን ከመውደዱ የተንሳ) ሳይሆን መጽሐፉ በግልጽ አንደኛ: “የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤ የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት ስለ መሐላው:: ሁለተኛ: “ከእርሱም
ጋር ስለ ተቀመጡት” እንዲል ስለ ምስክሮቹ: ቃል ከአፉ ሲያወጣ ስለሰሙትን ሲል ይህን አደረገ እንጅ የንጉሱ ውሳኔ ከዘፈኑ ጋር የሚያገናኝ ምንም ዓይነት ነጥብ የለውም:: እዚህ
ላይ በርግጠኝነት ለማለት የምወደው ነገር ቢኖር ንጉሡ ለገባው ቃል አይደለም የዮሐንስ አንገት ከጉልበቱ የተገኘ የልጁን አንገት
ብትጠይቀውም የለመነችውን ሁሉ እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋልና በ እርግጠኝነት ያደርገዋል::

ንጉሡ እንደሆነ “ጎሽ ገና አሁን ነው ያስደሰችን!” በማለት ቀድሞ በዘፈንዋ ደስ እንደተሰኘ ሁሉ አሁን ደግሞ በአሰቃቂ ልመናዋ የላቀ ደስታ ተሰምቶት የልብ ልብ እየተሰማው ጥያቄዋን በደስታ አልተቀበለውም:: በልመናዋ አልተደሰተም:: እንደው መጽሐፉ “ንጉሡም እጅግ አዝኖ…” ነው የሚለው::  ታድያ ይህ ማለት ምን ማለት ነው? የጻዲቁ የእግዚአብሔር
ሰው የዮሐንስ አንገት መቆረጥ ከተዘፈነ ዘፈን ጋር ምን ያገናኘዋል? ያስደሰተችው ያክል በሐዘን ቅስስ እንዲል አላደረገችውም ወይ? ከሆነ ደግሞ ለዚህ ሁሉ መሰባሰብ: ለፌሽታው ለዘፈኑ ንጉሱም ሆነ ብላቴናዋ እንዲገናኙ ያደረገ እለተ ልደቱ ነበር:: ከተወገዘ “በርዝ ደይ” Birthday ይወገዝ!!

ሌላው እንደ መከራከሪያ ነጥብ የሚቀርበው በገላትያ መጽሐፍ 5: 20 ላይ የስጋ ስራ ተብለው ከተዘረዘሩ መካከል አንዱ ሆኖ ተጠቅሰዋል ነው:: እንግዲህ እውነቱ ተጠቅሰዋል የሚባለው ቃል አይደለም በጥንታውያን ቅጅዎች በአማርኛ ከታተመ የቀድሞ  ቅጅ ቃሉ አናገኘውም ይልቁንስ በፈንታው “መንሰልሶል” የሚል ቃል ነው የምናገኘው ይህ ማለት ደግሞ ያለ ቅጥ/ከልክ በላይ መዝለል ማለት ነው (በስጋ)::

ታድያ መቼ ነው አንድ ዘፈን ኃጢአት ነው የሚባለው ያልን እንደሆነ ግን፥ አንደኛ:

  • በዜማው የተሰነጠሩ ቃላት ይዘት/መልእክት ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አንጻር
    የቆሙ እንደሆነ:
  • ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገባውን የእግዚአብሔር የሆነውን ለሰው  የሰጡ/ያጋሩ እንደሆነ:
  • የእግዚአብሔር መንፈስ ከመቅደስ የሚያባርር: መንፈስ ቅዱስን
    የሚያሳዝን:
  • ክህደትን የሚዘራ:
  • አመጻን የሚያበረታታ:
  • በአጠቃላይ ነገርን የሚቀላቅል ከእግዚአብሔር ህብረት የሚለይ
    ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ፍጹም ሃጢአት ነው::

አሁንም ቢሆን ግን የሆነውንና ያልሆነውን ሁሉ በጀምላ ኃጢአት ነው እያልን ራሳችንን ከማጨናነቅና በሄድንበት ሁሉ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማን ከማድረግ ለመላቀቅ መድሃኒቱ ቃሉን በአግባቡ ከማወቅ ውጭ ሌላ አማረጭ የለንም:: “ኃጢአት” የሚባለው ነገር በራሱ ጽንሰ ሃሳቡ ሊገባን ይገባል:: በተረፈ መጽሐፍትን አለ አግባብ መተርጎም ሌላ ማለትም ሳይሆን
የቃሉ ባለቤት ማሰደብ ነው የሚሆነው:: “በኢየሱስ ስም”/“እክህደከ ሰይጣን” ማለት ደግሞ  ሙዚቃው በጆሮህ ላይ ጥደህ ሳይሆን በዘሮረበት አለ መዞር ነው መፍትሄው!  እግዚአብሔርን መፈታተን ይሉትም እንዲህ ያለውን ነው::  ዘፈንን ከማውገዝ የተሻለ ዝማሬ ማቅረብ! ትውልድ እንዲተርፍ ከተፈለገም የተሻለ ስጠው:: በተረፈ ግን ከመሬት “ውግዝ ከመ አርዮስ” ብሎ ነገር የለም!!

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገርብኤል

[email protected]