ወደ ክተት ትግላችን እንመለስ
የካቲት 19 ቀን፡ 2003 ዓ.ም. (2/26/2011)
ከኀዳፌ ክተት ቡድን የወጣ መግለጫ
የጥንቲቷ ኢትዮጵያ ሕዝብ በዘመናዊ የዲሞክራሲ ሥርዓት የራሱን መንግሥት አቋቁሞ፥ በነፃነት ለመኖር በአንድነት ተካትቶ፥ ደሙን እያፈሰሰ ብዙ ዓመታት ቢታገልም፥ ገና ከግቡ አልደረሰም። እንዲያውም፥ ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግምባር በሚል ስም የሚጠራው ጎሰኛ ቡድን በ1983 ዓ. ም. የኢትዮጵያን ሥልጣን ሲይዝ በሀገራችን ላይ ከደቡብ አፍሪካ ታሪክ ውጪ ታይቶ በማይታወቅ የጎሳ ክፍፍልና ጭቆና ዘረጋባት። የውጪውን ዓለም ለመደለል በጎሳ የከፋፈላትን ሀገር የክልል ፌዴራል መንግሥት ያቋቋመባት አስመስሎ አሳያቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፥ እያንዳንዱን ክልል የሚገዙት ራሳቸው ጎሰኞቹና በጥቅም የደለሏቸው ካድሬዎቻቸው ናቸው። ሀገሬው በነፃ የመረጣቸው አስተዳዳሪዎች ያለው አንድም ክልል እንደሌለ የየክልሉ ሕዝብ የሚያውቀው ነው።
ጎሰኛው ቡድን ልዩ ዓይነት ጭቆና ከማምጣቱም በላይ፥ ረጅሙን የሕዝብ ትግል ቀልብሶታል። ይህ ቡድን ሥልጣን እስከያዘበት ዘመን ድረስ በሀገራችን ታሪክ የነበረው የሕዝብ ትግል በክተት ደረጃ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሪቱን መንግሥት ከንጉሣዊ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ አስተዳደር ለመለወጥ የታገለው፥ በአንድነት ተካትቶ ነበር፤ ግን አብዮቱን መንግሥቱ ኀይለ ማርያምና ጓደኞቹ ነጥቀው፥ ሕዝቡን በደርግ ጭቆና ስር ጣሉት። ሕዝቡ ትግሉን መቀጠል ዕድሉ ሆኖበት ዓሥራ ሰባት ዓመት ሙሉ በዱር በገደል፥ በከተማ በመንደር ታገለ። የትግል ዕድሉ ሕዝቡን ታይቶ በማይታወቅ ሥቃይ ከሚያሠቃይ የጎሳ ቡድን ላይ ጣለው። ጎሰኛው ገዢ ሕዝቡ ትግሉን እንደሚቀጥል ስላወቀ፥ “የጎሳ ዲሞክራሲን ሰጥተናችኋልና በዲሞክራሲ መንገድ ታገሉኝ” ሲል ዐወጀ፤ ወዲያው ቢዘጋቸውም፥ ነፃ መሰል ጋዜጦችና መጽሔቶች እንዲታተሙ ፈቀደ፤ የፖለቲካ ታርቲዎች እንዲቋቋሙ አደረገ።
ባጭሩ፥ የክተት ትግሉን ስልት በከፋፍለህ ግዛው የይስሙላ ምርጫ አሰናከለው። ሕዝቡ የሚሆን መስሎት፥ በአንድነት ተካትቶ መታገሉን ትቶ፥ በፓርቲ ተከፋፍሎ፥ የዲሞክራሲን ጠላት ብቻ ሳይሆን፥ እርስ በርሱም ከአንዴም ሁለቴ፥ ከሁለቴም ሦስቴ ፥ ታገለ፤ የክተት ትግል ተጨናገፈ። በኢትዮጵያዊነት የተባበረው ቅንጅት በታዛቢዎች ፊት ቢያሸንፍም፥ ጎሰኛው ቡድን የአሸናፊውን መብት በኀይል ቀማው። አሁን ግን ሕዝቡ በዚያው በተቀለበሰው መንገድ መታገል ሲሞኙ መኖር መሆኑን ዐውቆ፥ ወደቀድሞው የክተት ትግል መመለስ እንዳለበት ቊርጥ ሐሳቡን አሰምቷል፤ በብዙ ቦታም ትግሉን ጀምሯል። የጎረቤት ሕዝቦች ጨቋኝ ገዢዎቻቸውን በክተት ትግል ማባረራቸው ለሕዝባችንም ተስፋና ጥንካሬ ይሰጣቸዋል፤ በሀገር ጠላት ላይ በክተት መነሣት አማራጭ የሌለው ትግል መሆኑንም አረጋግጦልናል።
በሀገር ውስጥ ያለው ሕዝብ በከተማ፥ በዱር በገደል በአካል ሲታገል፥ በውጪ ሀገር ያለው የድዮስጶራው ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ተደራጅቶ ትግሉን ባለው ትልቅ አቅም ሁሉ ለመደገፍ ፈጥኖ መነሣት አለበት። አቅሙ ለትግሉ በጥቂት ቀናት በሚሊዮን የሚቈጠር ዶላር የሚሰበስብና በምድር ከጽንፍ እስከ ጽንፍ፥ በሰማይ እስከ ራማ የሚደርስ ድምፅ ማሰማት የሚችል በሚሊዮን የሚቈጠር ሕዝብ አቅም ነው። አቅማችንን እናውቃለን፤ ከጓዳ ከትተን እንዲዝግ አናደርገውም፤ ተካትተን ለሕዝባችን ጥቅም እናውለዋለን። ትግሉ ወንድ፥ ሴት፣ ወጣት፥ ሺማግሌ ሳይል የኢትዮጵያውያን ሁሉ ቢሆንም፥ ፊት አውራሪው ዛሬም እንደቀድሞው ወጣቱ እንደሆነ ታሪክና በዚህ ሰሞን በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ትግል ሕያው ምስክር ናቸው። “ለእናት ኢትዮጵያ ያልሆነ ወጣትነት ለማን ሊሆን ነው? ጎሰኛው ቡድን እናት ሀገርን ታይቶ ከማይታወቅ ሥቃይ ላይ ሲጥላት ያልደረሰላት ወጣትነት ለመቼ ሊደርስላት ነው?” ብሎ እንደሚነሣ ታሪክን ጠቅሰን እናምናለን።
ተሰባስቦ በአንድነት መታገል ለሀገር የሚቆረቆረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ፍላጎት ሆኖ ሳለ፥ እንዴት እንደሚሰባሰብና እንደሚደራጅ የቸገረው መስሎ ስለታየን፣ ጥቂቶች ተጠራርተን፣ በራሱ፥ በፈቃዱ፥ በዲሞክራሲ ሥርዓት የሚካተትበትን መንገድ ነድፈናል፤ www.kitet.org ወይም ethiokitet.org የሚባል ድረ ገጽ ፈጥረናል። ለምን ወደጥንቱ ትግላችን መመለስ እንዳለብን የሚያስረዳ፥ መሆን አለባቸው የምንላቸውን ራእይ፥ ዓላማ፥ ተልእኮ የሚገልጹ ጽሑፎች አርቅቀን ለጥፈንበታል። “ሁሉንም ሞክረነዋል፤ የሚያዋጣው በሚያዋጣው በቀድሞው ትግል መቀጠል ነው” የሚል ጀግና ሁሉ በቀየስነው መንገድ ለመታገል እንዲመዘገብ እንጋብዘዋለን። እንዴት መመዝገብ እንደሚቻል በግልጽ ተጽፏል። እኛ የኀዳፌ ክተት ቡድን አባላት (Volunteer members of Kitet Steering Committee) መንገዱን የቀየስነው የሚቀይሰው ስላስፈለገው ብቻ ነው፤ ባለቤቱ ተመዝጋቢው ሕዝብ ነው። ሕዝቡ ተመዝግቦ፥ የራሱን ቦርድና ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ በመምረጥ የድርጅቱና የትግሉ ባለቤት ይሆናል።
ድርጅቱ እንዳይቋቋም፥ ትግሉም በአንድነት ተካትቶ እንዳይካሄድ፥ የጎሳው ቡድን የማያደርገው ነገር እንደሌለ አስቀድመን እናውቃለን። ሕዝቡ ግን ወንድ፥ ሴት፣ ልጅ፥ ሽማግሌ፣ እስላም፥ ክርስቲያን፥ ሃይማኖት አልባ ሳይል፥ የጭቆናው ቀምበር መሮታል፤ ከሃያ ዓመት በላይ መሸከም አልቻለም። የማይለወጥ አቋሙን በምርጫ 97 ተካቶ ባደረገው ድል አሳይቷል። ቅድስቷን ምድር ከጎሰኝነት ርኩስ አገዛዝ ሳያጸዳ ለዓይኑ እንቅልፍ አይሰጥም። ሊታገል የተነሣው፥ የጥንቷ ኢትዮጵያ እንድትታደስ፥ ከራሷ ተርፋ ለሌሎች አርአያና ተስፋ እንድትሆን ነው። በመካተት ሊታገል የተነሣው፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፈለገውን ዓይነት መንግሥት ለማቋቋም ዕድል እንዲያገኝ ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕይወት እንድትጥመው በነፃነት፥ በጤና ሠርቶ አትርፎ እንዲኖር ነው፤ ቊጥራቸው ከፍ ያለ አባላት ያላቸው ነገዶች ቊጥራቸው ዝቅ ያለ አባላት ያላቸውን ነገዶች የባህል ጭቆና ሳያመጡባቸው ባህላቸውን እያዳበሩ በሰላም እንዲኖሩ ለማድረግ ነው፤ ቊጥራቸው ዝቅ ያለ አባላት ያሉት ቡድን ቊጥሩ ከፍ ያለውን ሰፊ ሕዝብ በኢኮኖሚ የማይጨቁንበትን አዲስ ሥርዓት ሕዝቡ እንዲያቋቁም መብቱን ለማስከበር ነው።
የክተት ጥሪ ማንኛውንም ለዲሞክራሲና ለኢትዮጵያ አንድነት ሲል የጎሰኛው ቡድን የዘረጋውን የጎሳ ፖለቲካ ለማውደም የተዘጋጀውን ሁሉ የሚረዳ ድርጅት ለማቋቋም ነው። የክተት ጥሪ የሚያቋቁመው ድርጅት ለዲሞክራሲና ለኢትዮጵያ አንድነት ሲል የጎሰኛውን ቡድን ለመደምሰስ ከተቋቋመ ከማንኛውም ድርጅት ጋር ሁሉ ይተባበራል። ክተቱ አንድ ማእከል ቢኖረው ስለሚመረጥ፥ ያንን እውን ለማድረግ በሚወሰድ ጥሪ ሁሉ በቅድሚያ ይገኛል። ከድርድር የማይገቡ የኢትዮጵያ አንድነትና በብዙ ዘዴ የራስ ለማድረግ የሚስተካከል ዲሞክራሲ ብቻ ናቸው።
ሕዝቡ ወደቀድሞው ትግሉ እንዲመለስ በምናደርገው ጥሪ፥ “የኢትዮጵያ ሕዝብ በነፃነት፥ በእኩልነት፥ በአንድነት መኖር ጉዳዬ ነው፤ ወገኔ በጎሰኛ ቀምበር ተጠምዶ ለጎጠኛው ሲያርስ ማየቱን አልቻልኩም፤ የሞት የሽረት ትግል ሲያካሂድ መርዳት ግዴታዬ ነው” የምትሉ ሁሉ ተመዝግባችሁ የታሰበውን ድርጅት እንድታቋቁሙ እንጠይቃችኋለን። የውይይት ማኅበራት (Paltalks) ድረ ገጾች እና የሃይማኖት ድርጅቶች ለጥሪው ልዩ ትኲረት ልትሰጡት የሚገባ ነው። የሃይማኖት ድርጅቶች ትብብራችሁ ከብሔራዊ ግዴታችሁ ከመሆን አልፎ፥ ሥራችሁን የሚያቃና ውጤት የሚያተርፍላችሁ ነው። አማኞቻችሁን በነፃ ለማስተማር፥ አንዱ ሃይማኖት ሌላውን ሃይማኖት እንዳይቃወም ለማድረግ የሚቻለው ሕዝብ በክተት ታግሎ የሚያቋቁመው መንግሥት በሚያወጣው ሕግ ነው። ትብብራችሁን የምንጠይቀው ለጸሎት በምትሰበሰቡበት ቦታና ሰዓት ሁሉ ለትግሉ መሳካት ለነፃነት አምላክ እንድትጸልዩና ምእመናኑ ወደ ድረ ገጹ ሄደው እንዲመዘገቡ ጥሪውን በማስረዳት እንድታስታውሷቸው ነው።
ሕዝባችን ለነፃነቱ የሚያደርገው የትግል ዘመን ረዘመ፤ ትውልድ የሚፈራረቅበት ዘመን ሆነ። አሁን ግን ጎሰኛው ቡድን የኢትዮጵያን በሕዝብ የሚከፋፍልበትና የሚያሠቃይበት ዘመን ማብቂያው ነው። የበደሉ ክብደት ተቆጥተን በአንድነት እንድንነሣበትና ተሟሙተን ነፃነታችንን እንድንቀዳጅ ገፋፍቶናል። ታግሎ ድል መንሣት ለአባቶቻችን አዲስ ነገር እንዳይደለ፥ ለኛ ለልጆቻቸውም አዲስ ነገር አይሆንም። እንዲያውም ዘመናት የፈጀው የነፃነት ትግል በእኛ ዘመን በድል አድራጊነት ሲያከትም ይታየናል። የጎሰኛው ቡድን የሀገሪቱን የጦር፥ የፖሊስ፥ የጸጥታ ሠራዊት ምንም እንኳን ጎሳዊ መልክ ቢያሲዘው ሠራዊቱ ግዴታው የሕዝብን ሰላማዊ ኑሮና ነፃነት ማስከበር መሆኑን በልቡና በአእምሮው ተረድቶ ውገናውን ከጎሰኛው ቡድን ወደሕዝብ የሚያዞርበት ጊዜ ደርሷል።
እምነታችን በነፃነት አምላክና በአቅማችን ነው።
ጌታቸው ኃይሌ
ስለ ኀዳፌ ክተት ቡድን
(For the Steering Committee)