የመንግስት መ/ቤቶችን ከኢህአዴግ ፅ/ቤቶች መለየት አዳጋች ነው
የመንግስት መ/ቤቶች ሰራተኞች በተለይም ደግሞ በትምህርት ቤቶች ፣ በወረዳና በክፍለ ከተማ ፅ/ቤቶች የሚሰሩ ባለሙያዎች መ/ቤታቸው የተቋቋመበትን አላማ ከማስፈፀም ይልቅ የኢህአዴግን አላማ እንዲያስፈፅሙ በመንግስት እየተገደዱ መሆናቸውን ለመረዳት ችሏል፡፡ በመ/ቤቶቹ በመንግስት የስራ ሰዓትና ገንዘብ እየተሰራ ያለው የኢህአዴግ ፓርቲ ስራ መሆኑ እንደሚያንገበግበው የገለፀልን አንድ መምህር “መንግስት በራሱ ሚዲያዎች አማካኝነት ዕለት ተዕለት በስራ ሀገርን ስለማበልፀግ ቢለፍፍም በተቃራኒው እየሰራ ያለው ግን የሀገርን ዕድገት የሚያቀጭጭ ነው፡፡
የየትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህራኖች እንደድሮው በውድድር ሳይሆን የኢህአዴግ አስፈላጊ አባል ተደርገው በመታሰባቸው ምክንያት የሚሾሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚፈለጉት በተሾሙበት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞችን በሙሉ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እንዲያጠምቁ ነው” ብሏል፡፡ ይኸው መምህር አምና ከተሾሙት ርዕሳነ መምህራን መሃከል ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የሚያስተዳድሩትን ት/ቤት ቤተ መፃሕፍትና ላብራቶሪዎችን የማበልፀግ፣ የመማር ማስተማሩን ስራ በሚገባ የመከታተልና ሌሎች ሙያዊ ስራዎች ላይ ያተኮሩ ርዕሰ መምህራን ዘንድሮ በተደረገው ግምገማ ከሀላፊነታቸው መነሳታቸውን ጨምሮ ገልጾአል፡፡
ከሀላፊነታቸው የተነሱት ርዕሳነ መምህራን እንደድክመት ተቆጥሮ የተገመገሙበት ጉዳይ “ሙያዊ የሆኑ ስራዎች ላይ አተኩሮ ለመሾም ምክንያት የሆናቸውን የፓርቲን ስራ ቸል ማለት” በሚል መሆኑንም ነግሮናል፡፡ አስተያየቱን የሰጠንን ወጣት ሀሳብ ያነጋገርናቸው መምህራን በሙሉ ይጋሩታል፡፡ ት/ቤቶች ከፖለቲካ ነፃ መሆናቸው በህገመንግስቱ ቢሰፍርም በተቃራኒው ወደ የኢህአዴግ ህዳሴ ጋዜጣና አዲስ ራዕይ መፅሔት መቸብቸቢያ የገበያ ስፍራነት መለወጣቸውን በምሬት የሚገልፁት መምህራን ከዚህ በተጨማሪ ኢህአዴግ ከ 1-20 ደረጃ የሚወጡ ጐበዝ ተማሪዎችን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የማጥመቁን ተግባር በሰፊው እየሰራበት እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ መንግስት የተጠቀሱትን አይነት ድርጊቶች በት/ቤቶች ላይ ይበልጡን አጠናክሮ ቢሰራበትም ሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ቢሆኑ የድርጊቱ ሰለባዎች ከመሆን አላመለጡም፡፡ ኢህአዴግ “የመንግስት ሰራተኞች እንደመሆናችሁ የመንግስትን ፖሊሲ ማስፈፀም አለባችሁ” በሚል ሽፋን በሳምንት ቢያንስ አንድ ጊዜ እየሰበሰበ የፓርቲውን ርዕዮተ አለም ሊግታቸው እንደሚሞክር ያነጋገርናቸው የመንግስት ሰራተኞች ሁኔታውን በደርግ ጊዜ ከነበረው “የውይይት ክበብ” ጋር በማመሳሰል ገልፀውልናል፡፡
እንደሰራተኞቹም ገለፃ በአሁኑ ወቅት በመንግስት መስሪያ ቤቶች ለመቀጠርም ሆነ በስራ ላይ ለመቆየት የኢህዴግ አባል መሆን ግድ ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አባል ያልሆኑ ሰራተኞች ላይ የሚደረገው ቁጥጥርም ከሌሎቹ ለየት ያለና የበዛ መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል፡፡
በየወረዳው በሚገኙ ጽ/ቤቶች የኢህአዴግ ፓርቲ ቢሮ ተሰጥቶት በመንግስት ሀብት እየተጠቀመ ይገኛሉ፡፡ ይህ ቢሮ “የወረዳ ስራ አስፈፃሚ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ” በሚል ሽፋን በወረዳው ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በውስጠ ታዋቂነት የሚሰራው ስራ ግን የገዢውን ፓርቲ ስራ ብቻ እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡