ፈላጭ ቆራጩ የወያኔ አገዛዝ ውድቀቱ እየተፋጠነ ነው
በወያኔ አፋኝ አገዛዝ ላይ የሚደረገው ብሔራዊ የአርነት ትግል ወሳኝ ደርጃ ላይ ደርሷል
ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ለ20 ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ አስከፊ የሆነ አፋኝ አገዛዝ በመጫን፤ በአገሪቷ ላይ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ንጽሃን ዜጎችን በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በግፍ በመጨፍጨፍ፣ በእስር ቤት በማማቀቅ፣ ለስደት በመዳረግ፣ ንብረታቸውን በመዝረፍ፣ በማንገላታት፣ በማዋከብ እንዲሁም በርካታ ሰቆቃዎችን በመፈጸም ላይ የሚገኘው የወያኔ አገዛዝ ተገርስሶ የሚወድቅበት ጊዜ እውን እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሰሞኑን አምባገነን ገዥዋን ከሥልጣን መንግላ ካባረረችው ከቱኒዚያ ውስጥ ከነበረው ሁኔታ እንዲሁም ግብጽ ውስጥ ከሚገኘው ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ የከፋና የመረረ እንደሆነ በገሃድ የሚታይ ነው። በእነዚህና በሌሎችም በርካታ የአፍሪካና የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች ውስጥ የሚገኙት አገዛዞች የተለመዱ ወይም ተራ አምባገነኖች በመሆናቸው ማንኛውም አምባገነንና ፋላጭ ቆራጭ አገዛዞች የሚፈጽሙትን ግፍና በደል በህዝባቸው ላይ ይፈጽማሉ። ወያኔ ግን ተራ አምባገነን ሳይሆን በቅኝ ገዥነትና በጠላትነት የተቀመጠ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ህዝብ በጎሳ በመሸንሸን የጎሳ አፓርታይድ አገዛዝ በአገሪቷ ላይ በመጫን በአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች አንጋችነትና ቀላቢነት ለመንበረ ሥልጣን የበቃ በመሆኑም ጭምር ነው። ይህም ነው የኢትይጵያ ህዝብን ትግል ጣምራ ትግል እንዲሆን የሚያስገድደው። ቀዳሚው ትግል ቅኝ ገዥውን ወያኔን ከሥልጣን ሰገነት ላይ አውርዶ ማንኮታኮት ሲሆን ተከታዩ ደግሞ፣ ለሁሉም ዜጎች የሚሆን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማቋቋም ነው።
ወያኔ በዕለት ዕለት ተግባሩ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ እንዳስመሰከረው አምባገነንና ፈላጭ ቆራጭ ብቻ ሳይሆን የአገሪቷና የህዝቧ ጠላትም ጭምር ነው። በዚህም ምክንያት ነው ከወያኔ ጋር የሚደረገው ትንንቅ ከአንድ ተራ አምባገነን አገዛዝ ጋር የሚደረግ ዲሞክራሲ የማስፈን ትግል ሳይሆን የብሔራዊ የአርነትና የነጻነት ትግልና የተቀደሰ ዓላማ ያለው ታላቅ ተግባር ነው። ወያኔ የህይወት መስዋዕትነትን በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ለረዥም ዘመናት የከፈሉላትን አገር በወረራ በመያዝ የባርነትና የአፋኝ አገዛዙን በመጫን፤ እንዲሁም ለዘመናት በትደረጉ ጥረቶች የተገነቡትን በሕዝቦች መካከል የዳበሩትን መስተጋብሮች ገዝግዞ ለመበጠስ ያልፈነቀለው ድንጋይ አይገኝም። ወያኔ የገሪቱን ብሔራዊ ሰራዊት በመበተን፣ መንገዶችን ህንጻዎችንና ድልድዮችን በማውደም የአገሪቱን አንጡራ ሃብት የሆኑትን ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ባንኮች፣ የመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤቶችንና ሌሎችንም የአገር ንብረቶችንና ቅርሶችን በመዝረፍ በጠላትነት አገሪቷን ረግጦና አፍኖ በመግዛት ላይ ይገኛል። ይህ አፋኝ ሥርዓት የኢትዮጵያን ህዝብ ከዓለም በመጨረሻው ተርታ በማሰለፍ የመረጃ አቅርቦት እንዳይኖረው ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚተላለፉ የሬዲዮና የቴሌቬዝን አገልግሎቶችን በማፈን፣ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በመዝጋት ህዝቡን በኢኮኖሚ አድቅቆ፣ በሥነልቡና አደንዝዞና አሰቃይቶ በመግዛት ላይ ይገኛል።እንዲሁም የአገሪቱን ብርቅዬና ለም መሬቶችን ለባዕዳን በርካሽ በመቸብቸብ የማይጠረቃውን የገንዘብ አኮፋዳውን በመሙላት ላይ ይገኛል።
ሆኖም በተለያየ ጊዜ እደተዘገበው ወያኔ በሕዝብ የተጠላና የተወገዘ በመሆኑ በጣት ከሚቆጠሩት ጥቅም ተጋሪዎችና ፍርፋሬ ለቃሚዎች በስተቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ በ1997 ዓም ብሔራዊ ምርጫ ለዓለም እንዳሳየው ከጫንቃው ላይ አውርዶ ጥሎታል። ወያኔ በሥልጣን ኮርቻ ላይ ተንፈናጦ ለመቆየት የቻለው በባዕዳን እርጥባና አይዞህ ባይነት እንጅ በሌላ ምክንያት ባለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝህ ከዳር እስከ ዳር በመንቀሳቀስ ለአገሩ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም እርምጃ መውሰድ የሚገባው ታሪካዊ ወቅት ላይ ደርሷል። ከዛሬ 21 ዓመታት ገደማ በፊት የምሥራቅ አውሮፓ ሕዝቦች ለዘመናት ተንሰራፍቶባቸው የነበሩትን አምባገነንሥርዓቶች አንኮታኩተው በምትካቸው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቶችን ለመመስረት ችለዋል። ዘንድሮም ይህ የለውጥ ብርሃን በሰሜን አፍሪካ አገሮች ብቻ ሳይወሰን ወደ እኛይቱም ኢትዮጵያ እንደሚፈነጥቅ ሳይታለም የተፈታ ነው። ለሁሉም ጊዜ አለውና!