ጅብ ከሚበላኝ ጅብ በልቼ ልቀደስ!

ከዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

በየትኛውም ዓለም ከፍርሃት የተነሣም ሆነ ከውርስ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንዲሁ ወደ ቤተ-እምነቶች ሲሄዱና ሲመላለሱ ማየት የተለምደ ያህል ነገር የለም። ከዚህ አልፎም ጎራ ለይተው “እኔ ከ እገሌ” (ቤተ-እገሌ) ነኝ አንተስ ከየት ነህ? እየተባባሉ በጎሪጥ ሲተያዩም ይስተዋላሉ። ከመላ ጎደል የእኛ የኢትዮጵያውያን የኑሮአችንም ሆነ ማንኛውም ዓይነት መገለጫችን ከምንም ይልቅ አሁን የምንታወቅበት ማንነትታችንን በመቅረጽ ረገድ “ቤተ-ክርስቲያን” ከፍተኛ የሆነ ሚና እንደተጫወተችና አሁንም ከዚህ አዙሪት ያልተላቀቅን/ነጻ ያልወጣን ዜጎች እንደ መሆናችን መጠን ይህን ማወቁ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ይህን በዛሬው ዕለት ለንባብ የበቃውን ጽሑፍ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆነ ሁሉ ቤተ-ክርስቲያን የሚለውን ጽንሰ ሃሳብም ሆነ የቤተ-ክርስቲያን በምድር ላይ የመኖር ዓላማና ተልዕኮ ምን ማለት እንደሆነና በቤተ-ክርስቲያን ስም ለሚፈጸሙ ማናጨውም ዓይነት ጥፋቶችና ወንጀሎችን በመከላከል ረገድም የአማኙ ድርሻ ምን ሊሆን እንደሚችል በጣም አጠር በለመኩ ለማቅረብ ተሞክረዋል ለጸብና ለአላስፈላጂ ክርክሮችና ንትርኮች ሳይሆን ለህይወት ይሆነን ዘንድ መልካም ምኞቴን እየገልጽኩ ወደ ሃሳቤ መግቢያ ልለፍ።

በሥልጣን ላይ ያለው “መንግሥት” በሰው ጫንቃ ላይ እንደ ተቀመጠ እንዲሁ ለ20 ዓመታት የመዝለቁ ምስጢር ብዙሐን የፖለቲካ ተንታኞች የሚያስቀምጧቸው ራሱ የቻለ የተለያዩ ምክንያትቶች እንደተጠበቁ ሆነው እንደ-ተደጎለ እሳት የኢትዮጵያ ምድርና ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ እያነደደና እየበላ ያለው ሌላው የመጡ መንግሥታት ተጨማሪ ብርታትና ጥንካሬ ከሚሰጡት መካከል አንዱና ዋነኛው ኃይማኖት/የቤተ-እምነት መሪዎች ነው/ናቸው። እንዴት? እንዴት ማለት ጥሩ። አሁን በመቀጠል የምትመስልና የሚመስሉ (ያይደሉ መልኩን ግን ከተላበሱ ማለቴ ነው) ጽድቅና እውነት መሠረትዋ ከሆነች እውነተኛ ቤተ-ክርስቲያን መልክ/መገለጫ ለይተን እንመለከታለን።

አስተዋይ ልቦና ሰሚ ጀሮ ያለው ልብ ይበል! ቤተ-ክርስቲያን፥

v  የመዳን ምክንያት፥

v  የማምለጫ ዓለት፥

v  የመማጸኛ ደጅ፥

v  የነጻነት አርማ፥

v  የፍትህ ድምጽና የክብር ሁሉ ጮራ ካልሆነችና ሆና ካልተገኘች የተጠለልከው የሰማያዊትዋ ኢየሩሳሌም ምሳሌ፣ በደም የተዋጀች የክርስቶስ ኢየሱስ ሙሽሪት በሆነችው ሳይሆን የወደቅከው በስውር አገዛዝ ሥር ነው።

ለመሆኑ ይህን ያውቁ ኖሯል?

  • ቤተ-ክርስቲያን ቋንቋ፣ ነገድ፣ ርቀትና ዘመን የማይለያያት መንግሥት መሆንዋን? ይህ ብቻም አይደለም መድረኩን በሚመጥንና በሚመስል ቋንቋ ተናገርኩ እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስ በደሙ የመሠረታት ቤተ-ክርስቲያን ከዚህም ሁሉ በላይ ናት።
  • “በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ” እንደሚባለው ቤተ-ክርስቲያን የድሆችና የሥራ-አጦች ማሰባሰቢያም ሳትሆን በጨርቅ፣ በወርቅና በሆዳቸው የማይደለሉ የጽኑአንና የኃያላን ቤት መሆንዋንስ?
  • መጽሐፍ “ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ-ክርስቲያን ሰጠው እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላት ናት።” እንዲል ቤተ-ክርስቲያን የክርስቶስ አካል እንጂ የምድራዊ መንግሥታት/የጥቂት ግለሰቦች መጫወቻ፣ መጠቀሚያና መፈንጫ ልትሆን እንደማትችልና እንዳይደለችስ?
  • ቤተ-ክርስቲያን እንደ የሰፈር/የቀበሌ እድር ከዚህም ከዚያም የተውጣጣ ሥጋዊ ማኅበርም ሳትሆን ሕያው የሆነና ዛሬም ለዘልአለም የሚሰራ በመንፈስ ቅዱስ የተገጣጠመ ሰማያዊ ማኅበር ለመሆንዋስ ጭላንጭሉ አለን? ወይስ ዛሬም ቤተ-ክርስቲያን (የቤተ-ክርስትያን ልጅ ነው) ሲባል ስንሰማ የሚታየን “ከሰው በታች”፣ “ኋላ ቀር” የሚሉትን ነው የሚታየን?
  • መጽሐፍ “እንደ ንጽህት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ላንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና።” እንዲል ክርስቶስ ሙሽራ ቤተ-ክርስቲያንን ደግሞ ሙሽሪት ሆና የመዳን ምክንያት ስትሆን ወያኔ ያገባት የኢትዮጵያ ኦርተዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሆነች ሌሎች የክርስትና እምነት ቤተ-እምነቶች ደግሞ በአንጻሩ ለትውልድ ምጥ ለሀገር እርግማን እንደሆንብንስ? እንግዲህ ከላይ ከፍ ብለው የተዘረዘሩ ጥቂት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የቤተ-ክርቲያን መገለጫዎች ለማይታይባቸው ማናቸውም በምድሪትዋ (በኢትዮጵያ) የሚገኙ የክርስትና ቤተ-እምነቶች ሁሉ ራስህን ማስገዛት ማለት  ወደውና ፈቅደው ራስዎትን በአዳኝ ወጥመድ ላይ እንደጣሉ ይቁጠሩት።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ሳይዘራ የበቀለና ያለ ሕዝብ ይሉኝታ በሕዝብ ጫንቃ ላይ የተቀመጠ “መንግሥት” ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ሳይሆኑ የእግዚአብሔር በሆነችውን ግዛት ሰርገው በገቡ ሰሮገቦችም (በቤተ-ክርስቲያን ከፍተኛ የአመራር ሥፍራ ላይ የተቀመጡ ስለ እግዚአብሔር ቤትና ስለመንጋው ግድ የማይላቸው ወረበሎች) ጭምር ናቸው። ውድ አንባቢ፥ ወደ ተነሳሁበት ርዕስ ዝርዝር ሐተታ ከመዝለቄ በፊት ለመግባባት ያክል በማስቀደም ጥቂትና ቀለል ያሉ ጥያቄዎችን በማንሳት እየተወያየን ሁላችን የመልዕክቱ ሙሉ ተካፋዮች እንድንሆን እወዳለሁ። ይኸውም ለመሆኑ ምን ለማግኘት? ምንስ አተርፋለሁ በማለት ነው ቀን – ሌሊት፣ ብርድ – ንዳድ፣ ቅርብ-ሩቅ ሳንል ያለችንን ይዘንና በአቅማችን አሸብርቀን ወደ አብያተ እምነቶችን የምንጋጋው? ምን አገኛለሁ ተብሎ ነው? እንደው ከልጅነት ዕድሜችን ጀምሮ መሄድና መምጣት በአጠቃላይ መመላለስ ልማድ ስለሆነብን ይሆን? ወይስ የገባን፣ ለጠያቂ አካል ያለመመንታት “አንተ! እንዴት ብታብድ ነው ዘንድሮ … ?” እያልን ቁና ቁና እየተነፈስን ቢሆንልንና ቢያጋጥመን በዘነዘና አናቱ ላይ ብለን በተገላገልን ሳይሆን “እንዴታ! ይሄውልህ …” በማለት ለሰሚ ጆሮ የሚሞላ የምንሰጠው ምላሽ አለን? ካልሆነ ይህ ሁሉ ሺሕ ዘመናት እምነት አለን ስንል ጸልየን ጥያቄአችን የማይመለስበት ሕዝብና ሀገር የማያርፉበት ምክንያት ምንድ ነው ይላሉ? ጥፋቱ የማን ነው ብለው ነው የሚያምኑ? “የእኔ/የእኛ” ወይስ የእግዚሄሩ?

ለመሆኑ ቤተ-ክርስቲያን ከታክሲና ከማኪያቶ የተራረፈውን ልቃቂ ሳንቲሞቻችን ለመጣል ብቻ ሳይሆን እንደ ቤተ-ክርስቲዋኒትዋ አባልና እንደ እምነቱ ተከታይ ሲወለዱ ክርስትና ከማንሳት፣ ሲሞቱም መጽሐፈ ግንዘት እያነበበች ገንዛ በወግ ቀብራና በሥርዓተ ፍትሃት ቤተ-ሰብን ከመጽናናት በተጨማሪ በአጸደ ሥጋም እያሉም እንደሆነ ከማንኛውም ረቂቅና ግዙፍ አደጋ ጣይ አካል ከጥቃት ለመከላልከልም ሆነ የሚገባዎትን ሁሉ የማግኘት ባለ ሙሉ መብት መሆንዎን ያውቃሉ?

እንግዲህ የመጀመሪያ የቤተ-ክርስቲያን ሥራ ደንበኛ ሙዳዬ ምጽዋት አሰርታ ጥላ እየዘረጋች እልል በሉ እየተባለ ገንዘብ ሰብስባ ማሰባሰብ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቤተ-ክርስቲያን የመጀመሪያ ሥራ ሰዎችን ከባርነት ከእስራት ከሰይጣናዊና አጋንንታዊ እንዲሁም ከሚታይና ከማይታይ ረቂቅ የሥልጣናት መጥመድና እስራቶችን መፍትት ነጻ ማውጣት አርነትን መስጠት ነው። በሥጋም በነፍስም!! በመንፈሱ የተፈታ/ነጻ የወጣ ግለሰብ ደግሞ በሥጋ እገዛዋለሁ፣ ባርነትን አከብድበታለሁ ማለት ህልም ነው። መጽሐፈ ክርስትና የሚለውም ይህንኑ ነው። ቀልል ባለ አማርኛ ዐረፍተ ነገሬን ልድገመው የሠራተኛውን ኪስ ለመቦርበር በተንኮልና በሴራ የተደራጀት ካልሆነች በስተቀር የቤተ-ክርስቲያን ቀዳሚ አጀንዳ የእግዚአብሔርን ሀሳብ ማገልገል ነው። ይህ ሃሳብ ደግሞ የሰውም ሆነ የሰይጣን ሀሳብ የሚያፈርስ የሰውን አእምሮ የሚያነቃ፣ ጅራት ሳይሆን ጫፍ የሚያደርግ፣ ለአመጻ ዕድል ፈንታ የማይሰጥ  የጽድቅ ሥራ ነው። አሜን!!

ጥቁር አሜሪካውያን ለመብታቸውና ለሰብአዊነታቸው መከበር ባደረጉት የሞት ሽረት ትግል አብያተ-ክርስቲያናትና የአብያተ-ክርስቲያናት መሪዎች በነጮች ዘንድ ከፍተኛ አድልዎና መገለል ይደርስባቸው ከነበሩ የጥቁር አሜሪካውያንን “እኛም እንደ አንተ ሰዎች ነንና ይገባናል” ሲሉ ላነሱት ጥያቄ በመደገፍና ከተገፊው ሕዝብ (ጥቁር አሜሪካውያን) ጎን በመቆም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አመራር በመስጠትም ሆነ በመንፈሳዊ ስልጣን (በድጋም ሳይሆን ኃይል ባለውና ኃይል በሚያወርድ ጸሎት) በሕዝቡ ድል ከፍተኛ ድርሻ ተጫውተዋል።

በአንጻሩ ደግሞ የዛሬትዋ የካቶሊክ “ቤተ-ክርስቲያን” ማበብና መግነት የብዙዎች ሊቃውንት ነፍስ በአሰቃቂና ዘግናኝ የአገዳደል ስልት እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ነፍስ በሰማዕትነት ማለፍና መገደል የክርስትና ታሪክ መዛባትና መበላሸትም እንዲሁ የቤተ-ክርስቲያን መሪዎች ተጠያቂዎ ናቸው። የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን መሪዎች ታሪክም እንደ ሆነ ከዚህ የተለየ ገጽታ የላቸውም። ዘመን አልፎ ዘመን በተተካ ቁጥር መንጋቸውን ከበላተኛ አውሬ ለመጠበቅ በሰማዕትነት በማለፍ ፈንታ “ጅብ ከሚበላኝ ጅብ በልቼ ልቀደስ” እየተባለ ከገዳዮች ጋር በማበር ሲቆርጡ፣ ሲያፈርጡ፣ ሲፈጩና የብዙሐን አንገት ከገመድ ጋር ሲያገናኙ ዛሬ ላይ ተደርሰዋል። በአፍዝ አደንግዝ አይበሉ አይጠጡ ሆነው ከሰው ተርታ ወጥተው ለሀገርና ለቤተ-ሰብ ሽክም ሆነው ተጥለው የቀሩ የቤተ-ክርስቲያኒትዋ ሊቃውንትማ ቤት ይቁጠራቸው። በተረፈ ግን “የሌላውን ስታማስል የራስዋን አረረባት” እንደሚባለው ካርታው የጠፋባትና የጠፋባቸው ለመሆናቸው ለራሳቸው ገደል ገብተው ገደል የከተቱትን ትውልድ መመልክት ነው።

ግን እስከ መቼ? እግዚአብሔር ስንል እግዚአብሔርን ሳናውቅ? ዕረፍትን ስንለምን ዕረፍትንን ሳናይ ከድጡ ወደ ማጡ እየተገለባበጥን ርሀብ፣ ችግር፣ ጦርነት … የሚቆሉን? ኧረ እስከመቼ ነው በእግዚአብሔር ስም ሕዝብ ተተረማምሶ ሀገር የሚታመሰው? ጦጣ ነው ሙዝ አልያም እንቁላል አሳይተህ ከወጣበት ዛፍ የምታወርደው እንጂ ሰውን የሚያክል ክቡር ፍጥረት ታጠምደው ዘንድ በእግዚአብሔር ስም አትደልለውም። እንግዲህ የነጻነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነትና የአንድነት ጥያቄ አንስተን ከፖለቲካው አቅጣጫ በምናገኘው ምላሽ ዕረፍታችን ፍጹም ይሆን ዘንድ በምድራችን ያለውን እንደ ሸረሪት ድር የተጠላለፈው/ን የኃይማኖት ጉዳይም እንዲሁ ዓቢይ ትኩረት የሚሻና ስር ነቀል ለውጥ የሚያስፈልገው ሌላ ራሱ የቻለ በሽታ/ምጥ መሆኑን ተረድተን መልካሙን ውጊያ ለመዋጋት ወገባችን እናጥብቅ። ካልበጀን ማንኛውም ዓይነት ክብር የማይታይበትና ኃይል የተለየው ቤተ-እምነትም ቢሆን መሪ ጥለን የማንሸሽበት ምክንያት የለንም። እምነት አለኝ በማለት ወደየ ቤተ-እምነታችን መመላልሳችን እግዚአብሔርን ለማምለክ እንጂ በገዛ እጃችን ወጥመድ ላይ ገብተን ዘንተ ዓለማችን እያለቀስንና እያቃሰትን እንድንኖር አይደለም።

ጥብቅ ማሳሰቢያ

“ቤተ-ክርስቲያን” ያሰፈርኩትን ቃል መሰሪዎች ክፉ ድርጊታቸውን በቤተ-ክርስቲያን ስም ስለሚያከናውኑና ለጊዜው ሌላ ስም መስጠት ስላልተቻለ ቃሉን ለመጠቀም ተገደድኩ እንጂ ቤተ-ክርስቲያን ስል ለጻፍኩት ቃል የክርስቶስን ኅብረት ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን መንደኛ መሪዎችን ላይ ብቻ የሚያመለክትና የሚመለከት እንደሆነ በመረዳት የጽሁፉን መልዕክት በመገባ ትረዱልኝ ዘንድ በአክብሮት ለመጠቆም እወድለሁ።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail [email protected]