የአፍሪቃ ምርጫና የምዕራቡ የገቢያ ዋጋ የስሌት አንድነት (አ.ተሰማ)
መቸም ቢሆን እንደ ወያኔ ያለ ጠባብ ብሔርተኛ በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ውስጥ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ወያኔ ያፍናል፤ ይገድላል፤ ያስራል እንደ ልቡ የራሱን የስልጣኔ ዘመን ለማራዝም ያበላል፤ ያስርባል፤ ከሃገር ያባርራል፤ ይሾማል፤ ይሽራል። ህዝባችን በመዳፉ ስር ከወደቀ እንሆ ሃያ ዓመት ሆኖታል። በነዚህ ዓመታት ወያኔ እንካቹህ ብሎ መሬት በመቁረስ ለባዕድ ሃገር አስረክብዋል፤ ሃገሪቱን ባህር በር አልባ በማረግ አንገቷን አስገምድሎ፤ ባንድ ጎሳ ብቻ የተዋቀረ ወታደራዊ ሃይል መስርቶአል። የወያኔ በደል ስፍር ቁጥር የለውም።
የምጣጥፌ አላማ ግን ተገን ያረገው ምርጫን አስመልክቶ የሚቀርብልንን የሂሳብ ስሌት ነው። ልጅ ሁኜ እናቴ ጋ ገቢያ እሄድ ነበር። ታዲያ እህል ተሰፍሮ ስትገዛ የሚኒሊክ መስፈሪያ ካልሆነ አልገዛም ትል ነበር። ምነው እማዬ እይው ይህ ጣሳም እኮ ከሚኒልኩ ኩባያ ጋር እኩል ነው ስላት አይደለም ትልና የእህል ነጋዴውን በሁለቱም የመስፈሪያ መለኪያዎች ስፍሮ እንዲያሳያት ትጠይቀው ነበር። አይህ ልጄ የሚኒሊክ መስፈሪያ ይበልጣል በማለት ከፈቴ ያለውን እህል እየነካካች ታስረዳኝ ነበር። እውነትም ይበልጣል። ከዛም ጣሳውን በማንሳት ስሩን እየተመለከተች እየው ቂጡን ወደላይ መተውታል መስፈሪያው ያነሰ እህል እንዲይዝላቸው የፈጠሩት ብልሃት ነው በማለት አሳየችኝ።
በቅርቡ ከሥራ ወደ ሱፕር ማርኬት ገባሁና ፒነት በተር ሁለት አንስቼ ከሌሎች እቃዎች ጋር ከፍሎ ለመውጣት ተሰለፍኩ። በወረፋዬ እኔም ያለኝን አቅርቤ ዋጋውን ስካን ስታረገው ተመሳሳይ በመሰሉኝ ሁለት ፒነት በተር መያዣዎች ላይ የተለያየ ዋጋ ብልጭ አረገልኝ። እኔም ተመሳሳይ ዋጋ መሆን አለበት ለምን በማለት ጥያቄ አነሳሁ። ካሸርዋም እርስዎ ብቻ አይደሉም ሌሎችም ግራ ተጋብተዋል። ጉዳዪ እንደሚከተለው ነው። አንድ ቂጡ የተመታና ወደ ውስጥ ገባ ያለ ስለሆነ የሚይዘው አነስተኛ ነው። ሌላው ግን አካሉ የተጠበቀ ስለሆነ በውስጡ ያለው የፒነት በተር ክብደት ላቅ ያለ ነው ብላ ቁጭ። እኔም ደግሜ ሳየው ያለቸው ገባኝና የእናቴ ነገር ትዝ አለኝ። ዋጋውም 2..99 ለትንሹ 3.99 ቂጡን ላልተጎዳው ከፈልኩና እየሳቁ ወደ መኖሪያ ቤቴ አፈተለኩ። ወይ አሜሪካ!
ሻብያ ከጨቆነችው ኢትዮጵያ ነጻ ወጣሁ ብሎ ህዝባችንን ሲያምስ ባርነት ወይም ነጻነት የሚል የምርጫ ሳጥን አቁሞ 99% ህዝብ ነጻነትን መረጠ አለን። ትላንትን በዛሬ ዓይን ሲያዩት ኤርትራዊያን ምን እያሉ ይሆን? አዲስቱ ኤርትራ ሰው የማይናገርባት አንድ አምባገነን ሰው ፈላጭ ቆራጭ በመሆን ከጽልመት ጋር እያላተማት ነው። ዛሬም የቀበሮ ጉድጓድ ትላንትም ሞት። ለእናት ሃገር ሲባል መሞት። ማብቅያ የሌለው ዘበኝነት። ወንድምና እህትን ገድሎ መፎከር። ህልፈት የሌለው ህይወት። ዛሬም በበረሃ መንከራተት። ዛሬም ስደት ነገም ስደት።
ወያኔ ደግሞ ምርጫ ባደረገ ማግስት የሚያታልለን የቁጥር አሃዝ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ ድምፅ አገኘን ይሉናል። በማስፈራርት፤ በማፈን፤ በማታለል የተገኘውን የምርጫ ውጤት ያላዝኑበታል። ህዝባችን ግን ጠንቅቆ ያውቀዋል የወያኔን ውስልትና። በትግራይ ህዝብ ስም ነጋጅ፤ ቀሪውን የሃገሪቱን ክፍል በጎሳና በክልል ክፍሎ እሳት እየለኮሰ እንደሚያመሰው ህዝባችን ከገባው ውሎ አድሮኣል። በበረሃ እያለም ወያኔ ነጋዴ ነበር። ያው ባህሪው ዛሬ ደግሞ የከተማ ማጅራት መቺዎችን እስከመጠቀም አድርሶታል። ወያኔ ኢትዮጵያዊነት የማይሰማው አታላይ ድርጅት ነው። ምኑም አይታመንም። በዜናው ላይ ሁለት የፊደራል ፓሊሶች ሞተው ተገኙ ይላል። ገዳዩና መርማሪው የዜናው አቀባዪም ራሱ ነው። ቀብር ውሎ ለንፍሮ አብሮ ከሃዘንተኛው ጋር ይሰላፋል። በሃገራችን ውስጥ እንደዚህ ያለ መሰሪ ድርጅት ታይቶም ተስምቶም አይታወቅም።
እንደ ክፉ አንበጣ የህዝባችንን ነዋይ የግል መጠቀሚያ ያደረጉት የወያኔ አባላትና ተለጣፊ ድርጅቶች የእቅድን መሳካት የሚመዝኑት በራሳቸው ዝርፊያ ስኬት ነው። ቁሳቁስ የጫነ አውሮጵላን ያለምንም የመግቢያ ፈቃድ መቀሌ ላይ ያርፍና በህዝባችን ገንዘብ የተሸመተው የቻይና እቃ ሌሎች ክልሎች በመላክ መቸር ቸር ነው። ትርፉ ለወያኔ። ምን ያህል በምድሪቱ ላይ ግፍ እንደሚሰራ ያየ አንድ ሰው እንዳስቀመጠው “አሰራራቸው ልክ እንደ ጣሊያኑ የማፍያ ድርጅት ነው” ብሎታል።
በዩጋንዳ፤ በደቡብና በሰሜን ሱዳን የምርጫ ውጤቶች ሁሉ የሚገለጡት ዘጠኝ ቁጥርን አስታከው ነው። የሩዋንዳው መሪ ልክ እንደወያኔው አለቃ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ አምጭቼ አሽነፍኩ ብሎናል በጊዜው። እንደ አሜሪካው የቁሳቁስ ገቢያ የአፍሪቃው የምርጫ ሳጥን ማስላት የሚችለው በቁጥር ዘጠኝ ዙሪያ ብቻ ነው። መቼ ይሆን ተቀናቃኝ አርባ ዘጠኝ ከመቶ አሽናፊው ሃምሳ አንድ በመቶ ተብሎ የሚሰላውና የተቀራረበ ውጤት የምናየው። አወናባጅ የምዕራብ የፍጆታ ስሌት ሰውን በቁጥር ዘጠኝ ዙሪያ እንደሚያጭበረብረው ሁሉ የአፍሪቃውም ምርጫ እንዲሁ ሆኖአል።
በእውነቱ የአፍሪቃ መሪዎች የሚዳሰሰውን አለም ረስተው ራሳቸው በተለሙት የህልም ዓለም ውስጥ መቃዥትን እስካላቆሙ ድረስ ነገም ዘጠና ዘጠኝ በመቶ መረጠን እያሉን ጥርሳቸው አልቆ በድዳችው መገዛት ነው የሚጠብቀን። ሮበረት ሙጋቤ አፓርታይድን ለማስወገድ ጠበንጃ አንግቶ ዛሬ ራሱ ከኢያን ስሚዝ አገዛዝ የከፋ ነው የሆነው።
የዛሬው ይህን ይመስላል…. የነገን ጠብቀን እንይ!
አደፍርስ ተሰማ